ባለፈው ሳምንት መኮንኖች ክበብ ውስጥ አርቲስቶች በሙያቸው ለመከላከያ ሰራዊቱ ስለሚያደርጉት ድጋፍ ለመወያየት ተሰባስበው ነበር። በዚህ መርሀ ግብር ላይ ንግግር ካደረጉት መካከል አንዱ የመከላከያ ሰራዊቱ የህዝቡ ግንኙነት ክፍል ሀላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ናቸው። እሳቸውም ንግግር ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያዊነት አፈር ልሶ ተነስቷል ሲሉ ገልፀው ነበር። ይህ ንግግራቸው ከወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ አንጻር አንዳች ስሜት ፈጠረብኝ።
በርግጥም ሰሞኑን በመላው አገሪቱ የታየውን ወቅታዊ ሁኔታ ላስተዋለ ኬሎኔሉ እንዳሉት ኢትዮጵያዊነት ከወደቀበት እየተነሳ ነው። ርግጥ አሁን ኢትዮጵያዊነት ተነሳ ስል አንዳንድ ሰዎች የተለመደውን ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? ወደሚል ሌላ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ውስጥ እንደሚገቡ እገምታለሁ። እኔ በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት ተነሳ ስል ከአንድ ነጠላ ነገር ግን በጣም ግዙፍ ምክንያት አንጻር ነው። እሱም በሀገር ጉዳይ ምንም የሚለየን አለመሆኑ ነው። አንድ ነን። ለዚህ አንድነታችን መመለስ ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ ዋነኛ ምክንያት ነው።
አሁን በሚገርም ሁኔታ መከላከያ ሰራዊቱ የኔ ነው የሚል ህዝብ ተነስቷል። ወጣቱ ሰራዊቱን እየተቀላቀለ ነው። ህዝቡ ለሰራዊቱ ከገንዘብ አንስቶ ህይወቱን እስከ መስጠት ለመድረስ ወስኖ ተግባራዊ እያደረገ ነው። ይህም የቆረጠ የኢትዮጵያዊነት ወኔ ፈንቅሎ መውጣቱን ያመለክታል። አሁን ላይ ከጁንታው እና ጥቂት ደጋፊዎቹ በስተቀር መከላከያ ሰራዊቱ የኔ ነው የማይል የለም።
ህዝብ መከላከያ ሰራዊቱ የኔ ነው ማለት ከጀመረ በኋላ ሰራዊቱ ሲዋደቅለት የነበረውን ሠንደቅ ዓላማም ይዞ አደባባይ እየወጣ ነው። ይህንንም በቅርቡ በመላ ኢትዮጵያ ለሀገር መከላከያ ስራዊት ድጋፍ ለማድረግ ከተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች መረዳት ይቻላል። ህዝቡ ሠንደቅ አላማችንን በኩራት ሲያውለብልብ ተመልክተናል። ይህ በእጅጉ ያስደስታል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት በህዝቡ ዘንድ የታየው የአቋም አንድነት ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ያመለካተ ነበር፤ ኢትዮጵያውያን በፀጥታው ምክር ቤት የሆነውን ከመገናኛ ብዙሃን እሰማዋለሁ ብለው አልተቀመጡም። በዚያ ሌሊት ቁጭ ብለው ንግግሩን ተከታትለዋል። ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት። በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫም ኢትዮጵያዊነት በሚገባ ተገልጧል። ይህ በመሆኑም ምርጫው አይሳካም ብለው ያሟረቱ አንዲያፍሩ ተደርጓል።
ሀገራችን አሁንም አንድ ሆኖ መንቀሳቀስን የሚጠይቁ በርካታ ፈተናዎች አሉባት። የውክልና ጦርነት እየተካሄደባት ነው። አንዳንድ ምእራባውያን መንግስታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ካልገባን ሲሉ መቆየታቸው አንሶ የውክልና ጦርነት ከፍተውብናል። ተወካዩ ደግሞ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወደ መቃብር አፋፍ ተወርውሮ የነበረው አሸባሪው ህወሃት ነው።
ይህ ተስፋ የቆረጠ አሸባሪ የአጥፍቶ ጠፊነት መንፈስ የተጠናወተው ነው። ሀገራችን ከዚህ አሸባሪ ሀይል ጋር አሁንም ፍልሚያ ገጥማለች። ይህን አሸባሪ ቡድን ኮርኩሞ ማስተካክል ደግሞ ግዴታ ነው። ስለዚህ መተጋገዝ ያስፈልጋል።
ርግጥ ይህን ሀይል ለማንበረክክ መላ ኢትዮጵያውያን ፊትም ብዙ ተጋድለዋል፤ አሁንም ዝግጁነታቸውን በአደባባይ ወጥተው አረጋግጠዋል። ሀገራችን ሉአላዊነቷን የሚጠብቁ ጀግኖችን አሁንም ወልዳለች። በምእራባውያኑ ሴራና በአሸባራ የጥፋት ድርጊት የተቆጡ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መከላከያ ሰራዊቱን እየተቀላቀሉ ናቸው። ይህን ለማድረግ ምንም ጊዜ ሳይወስድባቸው ወደ ማሰልጠኛ ማእከላት ገብተዋል።
ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወጣቱ መከላከያን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ በመገረም በተደጋጋሚ ሲናገሩ ስምተን ነበር። በስንት ቅስቀሳ የተመዘገበልን ሰው አምስት ሺህ ብቻ ነው ብለው ማለታቸውን አስታውሳለሁ። አሁን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች መከላከያን እየተቀላቀሉ ናቸው። ይህ አንድ ነገር ነው።
ወገኔ፤ ጦርነት በዋነኝነት የሰው ነፍስ ይበላል፤ ብዙ ሀብት ይፈልጋል። ከዚያ ደግሞ ኢኮኖሚን ይጨረግዳል። ሁለቱንም ላለመበላት ሁነኛው መፍትሄ ወደ ጦርነት አለመግባት ነው። ከገተባ በኋላ ግን ቶሎ መጨረስ ነው። ቶሎ እንዲያልቅ ደግሞ ትክክለኛው መንገድ ህዝብን ደጀን ማድረግ ነው። ህዝብ ደጀን ከሆነህ ከማንም ጋር ብትዋጋ አሸናፊ ነህ፤ ካልሆነ ግን ጦርነት ራስን እንደ ማጥፋት ይቆጠራል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጣም ጠንካራ ደጀን አለው፤ ይህ ደጀን በተደጋጋሚ አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጧል፤ አሁንም ጠንካራ ደጀንነቱን ማስመስከር ጀምሯል። ለዚህም ሰሞኑን ለሰራዊቱ ደጋፍ እየተደረገ ያለበትን ሁኔታ በአብነት መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን ከዚህም በላይ ማድረግ ይችላል።
እስካሁን ለመከላከያ ሰራዊታችን የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። ክልሎች፤ የከተማ አስተዳደሮችና ህዝቡ ሀብት እያሰባሰቡ እየለገሱ ናቸው። ሰንጋዎች፣ በጎችና ፍየሎች በስጦታ እየተበረከቱ ናቸው።
የመንግስት ሰራተኞች ወርሀዊ ደመወዛቸውን እየሰጡ ነው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ እናቶች የበሶ እህልን የመሳሰሉ ደረቅ ምግቦችን ሲያዘጋጁ አይተናል። ግን ገና ምን ተነካና….ይኼ ማለት ከባህሩ በጭልፋ ነው። እየተሰበሰበ ያለው ሀብት ሰራዊቱን መመገብ እና ማስታጠቅ አይችልም? በፍጹም።
ህዝብ ለሰራዊቱ አለኝታነቱን ከዚህ በፊት አረጋግጧል። ለዚህም አድዋን ማስታወስ ይበቃል። የአድዋን ዘመቻ እናስታውስ እስኪ..ያ ሁሉ ወታደር ከየቦታው በመቶዎች እና በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር በእግሩ ሲኳትን በየቦታው እየተቀበለ ያበላው ህዝብ ነው። ምን ተቀብሎ ያበላው ብቻ ያን ሁሉ ኪሎ ሜትር መንገድ በሌለባት ሀገር በፈረስ በአህያ በበቅሎ በጋሪ በአጋሰስ ወዘተ…ጭኖ በየሜዳው ግብር እየጣለ ደግሶ ሲያበላ የኖረው ይኼ ህዝብ ነው። በተለይም ደግሞ እናቶች። ያለ እነዚያ ጀግና ሴቶች የአድዋ ድል ይታሰብ ነበር። በፍጹም!
አሁንም የገጠመንን ጠላት ድል አድርገን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እስከምንመለስ ድረስ የህዝቡ አጋርነት ወሳኝ ነው። ከተጀመረው መንገድም በላቀ መልኩ መፈጸም ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ መሰራት ያለበት ነገር አለ። ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ቴሌ ቶኖች እየታዩ አይደለም፤ የሞባይል የአጭር መልዕክት ቁጥር በቅርቡ ይፋ መደረጉ አንድ ነገር ቢሆንም፤ ህዝቡ ድጋፍ ሊያደርግ የሚችልባቸው መድረኮች መፈጠር አለባቸው። እየተሰበሰበ ያለው ሀብት በየጊዜው ለህዝቡ ይፋ መደረግ አለበት።
የሙዚቃ ድግሱስ የታለ? ርግጥ ነው ከትናንት በስቲያ በብሄራዊ ትያትር የተዘጋጀ መድረክ ነበር። ይህ ዝግጅት በእነ መስቀል አደባባይ ወዳጅነት አደባባይ ወዘተ…መቀጠል ይኖርበታል። ኪነ ጥበብ በዚህ ወቅት ፋይዳዋ ብዙ ነው። ጦር ሜዳ ማሰልጠኛ ካምፕ ሂዶ ጦሩን ማነቃነቅ እንዳለ ሆኖ ገቢ መሰብሰብ ላይ ጥሩ መሳሪያ እንደመሆኑ በሚገባ ለመጠቀም መስራት መጀመር አለበት።
ሌላው ሌላው?…ገንዘብ ማዋጣት ያለበት ባለሀብቱ ብቻ ነው እንዴ? የአንድ ወር ደመወዙን ሊሰጥ የሚገባውስ የመንግስት ሰራተኛው ብቻ ነው እንዴ? ሌላውስ? ወገኖቼ ሠላም የጋራችን ነው። ወጪውም የጋራ መሆን አለበት።
የሀገር ህልውና የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሁሉም ድርሻውን መወጣት አለበት። ግድቡ የኔ ነው ስንል እንዲሁ በባዶ ሜዳ አንዳልሆነ ይታወቃል፤ ሁላችንም የአቅማችንን አዋጥተን ነው። መከላከያው የኔ ነው ስንልም ይኼው መቀጠል አለበት። እኔም ለሀገሬ እዘምታለሁ ስንልም በተግባር ነው መሆን ያለበት። ደጀን ሆነን አንድም የምንዘምተው እጃችንን ወደኪሳችን በመስደድ ነው። ድጋፍ አሰባሳቢ አካል በሁሉም እርከን ከላይ እስከ ታች ሊዘጋጅ ይገባል። መከላከያን መደገፍ የማይፈልግ አይኖርም። ድጋፉን ለማሰባሰብ ግን ታችኛው ህብረተሰብ ክፍል ድረስ መሰራትን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታ ግን ብዙም አይታይም። መከላከያ ሰራዊታችንን በመደገፍ ረገድማ ገና ነን።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013