በዚህ ክረምት ከቤት መውጣት የግድ ሆኖብኛል:: ጉዳዩ ትልቅ ነውናም ከመሥሪያ ቤትም ለዚሁ ብዬ ፈቃድ ወስጃለሁ:: ግብር መክፈል:: በቤተሠብ ከሚተዳደር ንግድ ጋር በተያያዘ ሁሌም በዚህ ወቅት ውክልናዬን ይዤ ግብር ሰብሰቢው መሥሪያ ቤት ከሆነው የአካባቢዬ ወረዳ ተገኝቻለሁ::
ወቅቱ የግብር ሠብሳቢ መሥሪያ ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብር የመክፈያ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ከሀምሌ 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ግብር ከፋዮችን ግብር እያስከፈለ ያለበት ነው:: እናም ሐምሌ ወር ይዞልን የመጣውን ብርድ፣ ጉም እና ዝናብ ሁሉ ተቀብዬ ግብር ወደሚሰበሰብበት ወረዳ ሄጃለሁ::
ከሩቅ መሥሪያ ቤቱን ተመለክትኩት፤ ግቢው ውስጥ ድንኳን ተጥሏል፤ ያየሁትን ማመን አቃተኝ:: ለምን ስል ራሴን ጠየቅሁ:: እንደሚታወቀው ድንኳን ለሐዘን፣ ለሠርግ ነው የሚጣለው:: ወረዳ ግቢ ውስጥ ድንኳንን ምን አመጣው ስል አሁንም ከራሴ ጋር ተሟገትኩ:: ወቅቱ የበጀት መዝጊያ ስለሆነ ከአፈጻፀም ጋር በተያያዘ ለሠራተኞች የተዘጋጀ መርህ ግብር ነበር ስልም ገመትኩ:: ከለውጡ በፊት በትንሹም በትልቁም ተሀድሶ በሚል የሚደረጉ መርሃ ግብሮችም ታሰቡኝ::
ይህን ሁሉ እያውጠነጠንኩ ቦታው ላይ ደረስኩ:: ድንኳኑ ግብር ለሚከፍሉ የወረዳው ነዋሪዎች ማስተናጋጃነት የተዘጋጀ ነው:: ግብር ለመክፈል ብዙ ሰዎች በአንዴ በሚሰበሰቡበትና ሠልፍ እንደሚኖር በሚጠበቅበት ሁኔታ፣ ለዚያውም በዚህ ክረምት በድንኳን ለማስተናገድ የተደረገው ጥረት ሊደነቅ ይገባል::
ትናንት የተጠናቀቀው ሐምሌ ወር እንዳለፉት ዓመታት ሐምሌዎች ብዙም ገራም ባልነበረበት፣ ከፍተኛ ቅዝቃዜ፣ ጉም እንዱሁም ዝናብ ባልተለየው በዚህ ወቅት በአግባቡ ግብር የመክፈል ግዴታን ለመወጣት እና ከቅጣትም ለመዳን በሚል ለብርዱም ለዝናቡም ሣልበገር ከግብር ተቀባዩ መሥሪያ ቤት ደርሻለሁ::
የድንኳኑን ውስጥ እና ደጃፉን በአጠቃላይ በአይኔ ገረፍ አደረኩት:: የተመለከትኩት ትዕይነት በእጅጉ ይገርማል:: በሥፍራው የደረስኩት ማለዳ ላይ ነው:: ማንም ይቀድመኛል ብዬ አልጠበኩም። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል። የወረዳው ግብር ሠብሳቢ መሥሪያ ቤት ግቢ በሰው ተሞልቷል። ቆፍጣና እናቶች እና አባቶች ቀድመውኛል:: በርካታ ወጣቶችም ተሠልፈዋል:: ሲሄዱ ነው እንዴ ያደሩት ስል አሰብኩ::
ግብር ሠብሳቢው መሥሪያ ቤት ድንኳን አዘጋጅቶ ግብር ከፋዩን እያስተናገደ ያለበት ሁኔታ ሊደነቅ የሚገባው ነው:: መሥሪያ ቤቱ አዝመራውን የሚሰብሰብበት ዋና ወቅት እንደመሀኑ እዚህ የደረሠ ዝግጅት ማድረጉ በርግጥም ሊደነቅ ይገባዋል:: ድንኳኑ ባይኖር ኖሮ በዚህ የዝናብ ወቅት ሰው ምን ያህል ሊቸገር ይችል እንደነበር መገመት አይከብድም::
ግብር ከፋዩ በዚህ ልክ በሥፍራው መገኘቱም የሚያስመሰግነው ነው:: ሁኔታው ግብር የመክፈል ግዴታውን የሚወጣ ዜጋ እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል:: ግብር ለመክፈል በዚህ ልክ ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት መገኘት ግን በግብር ከፋይነት ላይ ጥሩ መነቃቃት እንዳለ ይጠቁማል::
እነዚህ ብዙሃን በጥቂት አጭበርባሪዎች ተውጠው ነጋዴውና ግብር የመክፈል ሃላፊነት ያለበት ዜጋ ሃላፊነት የጎደለው ተደርጎ አንዲታይ ያደርጉታል። ለነገሩ በሥፍራው ተገኝቶም ገቢውን የሚሸሽግና ከሚገባው በታች ለመክፈል የሚጣጣር አይጠፋም፤ ምን አይጠፋም ብቻ፤ ሞልቷል እንጂ፤ የመንግሥትስ አንዱ ትልቅ ራስ ምታት እነዚህ አይደሉ አንዴ::
ብርዱ እንዳየለ ነው። አካባቢው በጉም ተሸፍኗል። ብርዱና ጉሙ ገና ሰዓቱ ያልደረሰ ቢያስመስሉትም ሰዓቱ ግን ጊዜውን ጠብቆ መሄዱ አይቀርምና ሠራተኞች የሚገቡበት ሰዓት ደረሰ። ወዲያው የሥፍራው ድባብ መቀየር ጀመረ። ጭብጥ ብሎ የተቀመጠው፣ ወረፋ ይዞ የተሠለፈው ሁሉ መንቀሳቀስ ውስጥ ገባ:: ጫጫታ እዚህም እዚያም ድምጽ በዛ:: ቅድሚያ ለማግኘትና ፎርም ሞልቶ ክፍያ ለመፈፀም ግርግሩ ተጧጧፈ።
በወረዳው ሁለት ሦስት ቀን የተመላለሱ ሰዎች መኖራቸውን መታዘብ ችያለሁ። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ አግባብነት የሌለው እጅግ ኋላ ቀር አሠራር የተመለከትኩት። ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ የተሥፋፋበት ከመሆኑ አንፃር ደንበኞችም ሆኑ የወረዳው ሠራተኞች ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ሲያደርጉ አልተመለከትኩም። መገፋት እዚህም እዚያም መሯሯጥ መሹለክለክ ብቻ ሆነ። እነዚህ ሁኔታዎች ምቾት የሚነሣቸው ሰዎች በአካባቢው ለሰከንድ ለመቆየት እንደሚቸገሩ ግልፅ ነው።
የተመለከትኩት አንድ ጉዳይ ግን ይበልጥ አሳሰበኝ። በወረዳው ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሠራተኞቹ ውጪ ግርግሩ እንዲፈጠር የሚሰሩ፣ ፎርም በቀላሉ እንዳይገኝ የሚያደርጉና ባልተለመደ ቅርርብ ከወረፋቸው ውጪ የሆኑ ሰዎችን እያሳለፉ ጉዳይ የሚያስጨርሱ ሰዎችን ተመለከትኩ።
የሚገርመው ደግሞ ትላልቅ ሰዎች ተሠልፈው ተራ እየጠበቁ ሣለ ወጣቶች ናቸው በዚህ የጓሮ በር ለማለፍ ሲሞክሩ የሚታዩት፤ ሁለት ጥፋት:: እነዚህ ሕገ ወጦች ተራቸውን ጠብቀው መስተናገድ ሲገባቸው ተራ የሚጠብቁትን አባቶችና እናቶች ቀድመው ይስተናገዳሉ:: ይኼ ሕገ ወጥነት ብቻ ሣይሆን የሥነ ምግባር መበላሸትም ነው::
ጎበዝ ይህን ድርጊት በትውውቅና በዝምድና የሚፈፀም ብቻ አድርጋችሁ እንዳትመለከቱት:: ጉዳዩ በእጅጉ የተለየ ነው:: ሃላፊውን ቀረብ ብዬ ፎርም ማግኘት ችግር ስለመሆኑ ነገርኩት:: አከታትዬም ይህ ለምን ሆነ ስል ጠየቀኩት:: እርሱም ደንገጥ ብሎ ችግር እንደሌለ ነገሮኝ በፍጥነት አምጥቶ ሰጠኝ። ይሁን አንጂ ለብቻዬ ፎርም የሰጠኝ አጠያየቄን አይቶ መሠለኝ:: በዚህ የአሠራር ሥርዓት እጅጉን ተበሣጨሁ።
ተገልጋዩ ያለምንም ችግር ፈጣን መስተንግዶ ማግኘት ሲገባው “የዜግነት ግዴታውን” ለመወጣትና ግብር ለመክፈል ሲል “ሙስና” መክፈሉና ለኪራይ ሠብሳቢዎች ተጋላጭ መሆኑ የሕሊና እረፍት ነሣኝ። እነዚህ ሌቦች በውጪ የፎቶ ኮፒ ማሽን ሥራ ከሚሰሩ ጀምሮ ውስጥ ግብር ሠብሳቢ ባለሙያ ድረስ በኔትወርክ የተሳሰሩና በተጠና መንገድ ተገልጋዩን ያልተገባ ክፍያ ወይም ሙስና እየተቀበሉ ለመሆናቸው ከአንዳንድ ግብር ከፋዮች ጋር መረጃ አገኘሁ። ግብር ክፍያን በሙስና ማለት ነው::
እኔ የማውቀው በዚህች ሀገር ግብር አለመከፍል ትልቅ ችግር ስለመሆኑ ነው:: ግብር በወቅቱ አለመክፈል፣ መክፈል የሚጠበቅበትን ያህል አለመክፈልም ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን አውቃለሁ:: እነዚህን ሁሌም የሚጠቀሱ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት እየሰራ መሆኑን ሲገለጽ፣ የተለያዩ አሠራሮችንም እየቀየሰ ሥራ ላይ ሲያውል ቆይቷል:: ይህን ትከትሎም በየዓመቱ የሚሰበሰበው ግብር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል::
አሁን ደግሞ ግብር ለመክፈል ያለ ጣጣ አያድርስ ሆኖ አየሁት:: ግብር መክፈል በሙስና እንዲፈፀም እየተደረገ ነው:: ህብረተሰቡ ግብር ለመክፈል ሲመጣ ተዘጋጅቶ ቶሎ መቀበል ሲገባ እንዲንገላታ፣ ለኪራይ ሠብሳቢዎች እንዲጋለጥ ማድረግ ምን ይሉታል::
የሀገር ዋንኛው የገቢ ምንጩ ግብር መሆኑን ጠንቅቆ የሚያውቀው መንግሥት በእነዚህ ኪራይ ሠብሳቢዎች / የምን ኪራይ ሠብሳቢ ሌቦች ናቸው/ ላይ ለምን ርምጃ አይወስድም ስል አሰብኩ:: ይህን ኪራይ ሠብሳቢነት የተሞላበት አሠራር በቴክኖሎጂ እንዴት መፍታት እንዳልቻለ ይገርማል።
ይኼ አካሄድ ቶሎ መታረም አለበት:: ሥር የሠደደ ችግር ከሆነም እንደሌሎች የግብር ዘርፉ ችግሮች ከሥር መነቀል ይኖርበታል:: መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ግብር ከፋዩን ግብር ሠብሳቢው መሥሪያ ቤት ውስጥና አካባቢ ከሚገኙ ከኪራይ ሠብሳቢዎች መታደግ ያስፈልጋል:: ግብር ለመክፈል መሥሪያ ቤቱ ድረስ የመጣ ህብረተሰብ በሚገባ ተስተናግዶና ተመሥግኖ ወደመጣበት መመለስ ይኖርበታል:: ግብር ሊከፍል ደጁ የመጣን ማህበረሰብ ምንም ዓይነት እንግልትም ሆነ ያልተገባ ክፍያ እንዲፈጽም መደረግ የለበትም:: ይህን ማህበረሰብ መጠበቅ ሌሎችም ሰዓቱን ጠብቀው ግብር እንዲከፍሉ ያደርጋል::
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013