በዘመናችን የሚያደናግሩንና የሚያነታርኩን ጉዳዮች ብዙ ናቸው ። አንዱ የሚለውን አንዱ አይሰማም። አንዱ የሚያደርገው ለአንዱ ጭራሽ ሊታሰብ እንኳን እማይገባ ስህተት ነው፤ የአንደኛው አመራር ለሌላኛው አገዛዝ ነው፤ የአንዱ ቅን ሀሳብ ለሌላኛው ሴራ ነው ። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ በሁለቱ ወገኖች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን አገርና ሕዝብን ላልተፈለገ ስቃይና ኪሳራ፤ መከራም ጭምር ይዳርጋል ። እየተመለከትን፣ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው ።
“ፌዴራሊዝም” በሚለው ተስማምተን “ምን አይነት ይሁን?” በሚለው ግን የንፁሐን ቤት ድረስ ያንኳኳ ፀብ ውስጥ እንገባለን ። ደም ይፈሳል፤ ሕይወት ይጠፋል፤ ሀብትና ንብረት ይወድማል ። ዘንድሮ ትንሽ ተንፈስ አልን እንጂ በምርጫም መጋደል እንጂ በጉዳዩ ላይ መሟገት አይመቸንም ። የሥልጣን ነገር ሞታችን ይመስላል ። ድሮ የማናውቀው ሙስና ዛሬ እስከአንገታችን ውጦናል ። በፓርቲዎች ቁጥር ብዛት “አንደኛ” ነን (ከ137ቱ ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋሙ 18 ብቻ ነበሩ)። ለመመራት እንኳን ያልተዘጋጀው ሁሉ ካልመራሁ ሲል መስማት እንግዳ ያልሆነባት አገር እስክትመስል ድረስ የሥልጣን ሽኩቻው ጣራ ድረስ ነው ። የሴራው ነገር አይወራም ። ባንዳነት በግልፅ አለ ። የአንድ ወገን የፖለቲካ የበላይነትና ተረኝነት ይፋ ነው ። መጠላለፍ በሹክሹክታ የሚነገር ሳይሆን በገሀድ የሚታይ ነው ። “ለአገሬ ምን አደረኩላት” የሚለው ቁጥሩ እያነሰ፤ “አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ” የሚለው ቁጥሩ እያሻቀበ ነው ። ቆጥረን አንጨርሰውም ። ጥያቄው “ይህ ሁሉ ባለበት እንዴት ሆኖ፣ እንዴትስ ተብሎ ነው ስለ “ብሔራዊ መግባባት”፣ “አገር ግንባታ”፣ “አገረ መንግሥት ግንባታ”፣ “መደመር”፣ “ዲሞክራሲ” … እሚወራው፤ እንዴትስ ነው ተግባራዊ የሚደረገው?” የሚለው ሲሆን በዚህ ጽሑፍ በርዕሳችን ላይ ብቻ እናተኩራለን ።
(በአገራችን የዚህ ቅጥ ያጣ “ነገር” አቢይ ምንጭ፣ ምናልባትም ይህ ፀሐፊ ከዚህ በፊት ለዜና ግብአት ያነጋገራቸው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ተስፋዬ “ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚያይ ክፍል አለ፤ ኢትዮጵያን እንደ ፕሮጀክት የሚያይ አለ ….” እንዳሉት ቢሆን ነውና አይደለም ማለት በፍፁም አይቻልም ።)
እንደሚስተዋለው የበርካታ የማይጣጣሙ አካላት ግብ ግብ አገርን መልሶ መስራት ላይ ከሆነ ቆየ ። ልዩነታቸው አንዱ አፍርሰን እንስራት ሲል ሌላው ቆይ ቀስ እያልን፤ እያየን እያስተዋልን የሚል ነው ። ይህ የሚነግረን የአገር ግንባታ፣ አገረ መንግስት ግንባታ እና የ(መልሶ) ግንባታው፣ ምስረታው ጉዳይ የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞች አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ነው ። ሁሉም የሚሉት ያለፈው ልክ አይደለምና እንደገና እንደ አዲስ “አገር ግንባታ” (nation-building) እና “አገረ መንግስት ግንባታ” (State building) እናድርግ ነው። ጉዳዩን ትንሽ ወደ ኋላ ሄድ በማለት እንየው ። ከዛ በፊት ግን “ብሔረ-አገር ማለት አንድ አገርና ሕዝብ በጣምራ የሚገለፁበት ስያሜ ነው ፡፡ ብሔረ-አገር ግንባታ (Nation Building) በረጅም ጊዜ መስተጋብር ሕዝቡ ውስጥ የሚፈጠር ህብረትና አንድነት ነው ፡፡ ብሔር ግንባታ ከአገረ-መንግሥት (State Formation) ቀጥሎ የሚመጣ የተራዘመ አገራዊ ፕሮጀክት ነው ፡፡” የሚለውን የባለሙያዎች ብያኔ አጥብቆ መያዝ ይገባል ።
“ባደጉት አገራት የአስተዳደር ሕግ ዕድገት ጥርት ባለ መልኩ ወጥነትና ሥርዓት እየያዘ ራሱን የቻለ የሕግ ክፍል ሆኖ ብቅ ማለት የጀመረው ዘመና[ዊ] የአስተዳደር (Administrative State) ወይም የማህበራዊ ዋስትና መንግሥት (Welfare State) መከሰት[ን] ተከትሎ” መሆኑን የሚነግረን የአብረሃም ዮሀንስ ጥናት (“አጼ ቴዎድሮስ እና የአስተዳደር ሕግ”) የአጼ ቴዎድሮስ ውጥን እና ጥረት እንዳለ ሆኖ “በርካታ የአገራችን ሆኑ የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በአገራችን ዘመናዊ አስተዳደር የተተከለው የኃይለስላሴን ዙፋን ላይ መውጣት ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይስማሙበታል ፡፡ በተለይም ከኢጣሊያ ወረራ ማብቃትና የንጉሱ ዙፋ[ኑ]ን መልሶ መረከብ አንስቶ ዘመናዊ አስተዳደር ፈጣን ለውጦች አሳይቷል ፡፡” ሲልም የአገራችንን የዘመናዊ አስተዳደር እድሜና ታሪካዊ ዳራ ይነግረናል ። ይህንን ሲል በአገራችን የዘመናዊ የአስተዳደር እድሜ አንድ ምእትን እንኳን በአግባቡ አልደፈነም እያለን ነውና ገና ለጋ ነው ። ዛሬስ?
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንደሚሉት በአሁኒቱ ኢትዮጵያ “አምክህኖን (reason/rational) ከፖለቲካ እያራቅን በስሜት ብቻ የምንነዳበት ሁኔታ ውስጥ ስንወድቅ፣ እንዴት መደማመጥ እንደሚጠፋ፣ እንዴት ሊያቀራርቡን ከሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ይበልጥ የሚያለያዩን ጉዳዮች እየሰፉ የሚመጡ መሆኑን ለማሳየት ጥረት የማደርግበት ይሆናል።” ባሉበት ጥናታቸው (ኖቬምበር 12፣ 2011 ዓ.ም በሲያትል ከተማ “የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ፎረም“ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የቀረበ::) ላይ እንደገለፁት በአምክህኖ ድርቅም ተመተናል ።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአንድ ወቅት ከ”ሰንደቅ” ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ያላለፉት የታሪክ ፈተና፣ ማሸነፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና በተለይም ተባብሮ የመስራት፣ አቅም ገንብቶ የመስራት፣ ልዩነቶችን አቻችሎ አብሮ የመስራት፣ ተባብሮ ገዢውን ፓርቲ የመግፋት ፖለቲካው አሁንም ድረስ ያላለፉት [የ]ታሪክ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ። አሁንም አላለፍነውም ። እንደውም ከ97 ጋር ሲተያይ ደከም ብለን የምንታይበት ሁኔታ ነው ያለው ።” በማለት የገለፁትም እዚህ ከገለፅናቸው ሀሳቦች ጋር ስምም ሲሆን አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ “በእንደዚህ አይነት የፖለቲካ አውድ፣ አረዳድና ተግባራዊ ሂደት ውስጥ እንዴት አድርጎ አገርም ሆነ አገረ መንግሥት መገንባት ይቻላል?” የሚል ጥያቄን እንድናነሳ ማድረጋቸው ነው ።
ሰሞኑን ጠ/ሚ/ር ዐብይ አሕመድ “ኢትዮጵያን የመሰለ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲን እንገነባለን” በማለት መግለፃቸው እስከዛሬ የተገነባው በሙሉ ልክ እንዳልሆነ ሲነግሩን ነው ። ባለመሆኑም አዲስ የአገር ግንባታን እናካሂዳለን ማለታቸው መሆኑ ግልፅ ነው ። ከዚህ አኳያ እስከ ዛሬ የመጣው ሁሉ “አዲሲቷን ኢትዮጵያ …” (ከበፊቶቹም ጀምሮ) ሲል የነበረው ሁሉ ከአፋዊነት የዘለለ አልነበረም ማለት ነው ። ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ዐብይ አሕመድ ያለው ይህንን ይመስላል ። ወደ ዋናው ርዕሰ-ጉዳያችን እንለፍ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትና ከሶቪየት ህብረት (ኮሚኒዝም) መፈራረስ በኋላ እየጨመረ የመጣው የአገራት መገነጣጠልና የዓለም አገራት ቁጥር መብዛት ምክንያት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጡትን “Nation-building” እና “State building”ን የተለያዩ ጥናቶች በተለያዩ መንገዶች ሲተረጉሟቸው ቆይተዋል፤ በንድፈ ሀሳቡም በኩል እንደዛው ። (እኛ አገር ገፋ አድርጎ የሄደባቸው ሀብታሙ አለባቸው በ”ታላቁ ተቃርኖ” ሲሆን፤ በአብዛኛው በእንጠልጥሎና ለውይይት አመቺ አድርጎ ነው የዳሰሳቸው።)
“ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ታሪኮቻቸውን ተቀብለው የአሁኗን እና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእኩልነት እና በመከባበር ላይ እንዲመሰርቱ ለማገዝ” ታስቦ የተመሰረተው “የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ፕሮጀክት” በ2019፣ ኔዘርላንድ (ደናህግ ከተማ) ባካሄደው ኮንፈረንስ ላይ እንደተገለፀው “ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የቀደመ የአገረ መንግስት ታሪክ ያላት ብትሆንም እስካሁን ግን ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ መሆን አልቻለችም ። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ጥንታዊ የሥነጽሁፍ እና የሥነጥበብ ባለቤት፣ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድህነት የሰፈነባት፣ ግጭት እና ጦርነት የሚካሄድባት እና አምባገነናዊ አስተዳደር የሰፈነባት ሀገር በመሆን ታውቃ” ቆይታለች ። በመሆኑም ይህ መለወጥ አለበት ። ለዚህም “የስዊድን፣ የኔዘርላንድስ እና የቤልጂየም የአገር ግንባታ ታሪኮች እና ልምዶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ። ከጀርመን፣ ቤልጄየም እና ከስካንዲኒቪያ አገራት የመጡ የልዩ ልዩ ስብስቦች ተወካዮች እና አባላት ስብሰባውን ተሳትፈዋል ። ” የዚህ አይነቱን ልምድ ሁሌ ማዞተርና ከሌሎች ተምሮ የራስን የተሻለ ማድረግ ይገባል ።
Conor O’Dwyer (2007) እንደሚሉት አገረ መንግስት ግንባታ በተለያዩ ዘመናትና ተግባራት የሚገለፅ ቢሆንም ተግባሩ ያለማቋረጥ የሚጠና ዘርፍ ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹ ቋሚ ሰራዊት፣ የዲፕሎማሲ ልኡካን፣ የተማከለ መንግሥታዊ/ተቋማዊ አሰራር፣ ጠንካራ ተቋማት – በተለይ ከግብር መሰብሰብ ጋር በተያያዘ፣ የሕግ የበላይነትንና ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ የሕግ ሥርዓት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ የራሱ ገቢ ያለው መሆን፣ እንዲሁም የአገሩን ሰዎች እንደ ዜጋ እንጂ በአገሪቱ አጠቃላይ (የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና መንፈሳዊ) ሀብት የመጠቀም መብት እንደሌላቸው አድርጎ አለማየት (as citizens rather than status groups) እና የመሳሰሉት የሁሉንም ማለት በሚቻል ደረጃ ስምምነትን ያገኙ የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ክንውኖች ናቸው ። እነዚህንን መሰል ተቋማትን በመገንባት ላይ ያለ መንግሥት ከወደቀ መንግሥትነት (ፌልድ ስቴት) ወደ ጠንካራ መንግሥትነት (ኢፌክቲቭ/ፈንክሽናል ስቴት) እየተሸጋገረ ነው ማለት ነው ። እነዚህ ላይ አተኩሮ የማይሰራ ከሆነ ያ መንግሥት በአገረ መንግስት ግንባታ ላይ እየሰራ አይደለምና አገርም እየተገነባ አይደለም ማለት በመሆኑ የዛች አገር የወደፊት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ማለት ነው።
እንደ ሚሎናስ፣ ሀሪስ (2012) አስተያየት ከሆነ በሁለቱም (አገር ግንባታና አገረ-መንግሥት ግንባታ) ፅንሰ ሀሳቦች መካከል ምንም ልዩነት የለም ። ልዩነት ያላቸው እንዲመስሉ ሆነው ተበየኑ እንጂ የሁለቱም ዓላማ አንድና የውጪ ኃይሎችን፣ ቅኝ ገዥዎችን እንዲያገለግሉ ሆነው የተፈጠሩ፣ በእነሱ ፍላጎትና የእነሱን ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ተቋማትን፣ መሪዎችን ወዘተ በማስቀመጥ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ እንዲያስችላቸው አድርገው የፈጠሯቸው ናቸው ። አሻንጉሊት መንግስት፣ አገልጋይ ተቋማት፣ በግጭት የተሞላችና ሰላሟ የተናጋ ፀጥታ አልባ አገር መፍጠሪያ ቃላት ናቸው፤ አገር እስከማናጋት ድረስ የሚዘልቁ ።
በአገረ መንግሥት ግንባታ የሚያምነው የጄምስ ዴቢንስና ሌሎች (2003) ጥናት በበኩሉ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ጦርነት እራሱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ያስቀምጣል ። በጉዳዩ ላይ ያሚያተኩረው ንድፈ ሀሳብ (Predatory Theory)ም የውጪ ጦርነት መከሰት ከጦርነቱ በኋላ ለሚፈጠረው የተሻለ አገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብሎ ያምናል ።
የአገረ መንግስት ግንባታ ቀዳሚ አስፈላጊነት የሕዝቦችን አንድነት በመፍጠር፣ ወይም የእኛው ሕገ መንግሥት በወረቀቱ ላይ እንደሚለው “አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር” ሲሆን ለዚህ መሳካት ዋና ዋና እንቅፋቶች ናቸው ከሚባሉት መካከል አንዱ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ፤ እሱንም የመረዳትና አለመረዳት ጉዳይ ነው ።
እንደ የዓለም የኢኮኖሚ መድረክ (WEF) ጥናት የአሁኑና የሚቀጥሉት ዓመታት የአለማችን ቁልፍ ችግሮች በጣም በርካቶች ሲሆኑ አንዱም እየተራቀቀ የመጣው የኢንተርኔት አገልግሎት (“አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት” ብለውታል) ነው ። መሰረተ ልማቶች እየወደሙ ነው ። ታዲያ እንዴት ተደርጎ ነው የአገረ መንግሥት ግንባታ የሚካሄደው? በተለይ ችግሮች ተቆጥረው በማያልቁበት አፍሪካስ [አጀንዳ 2063 ይፈታዋል/አይፈታውም የሚለው እንዳለ ሆኖ] እንዴት ነው ይህ እውን ሊሆን የሚችለው? የሚሉት የመድረኩ ጥያቄዎች ሲሆኑ የየአገራት መሪዎችም እንዲያስቡበት መክሯል።
አልቤርቶ አሌሲና (Harvard and IGIER Bocconi) እና ብሪዮኒ ሬች (University College London) በ”Nation-building” (2012) ጥናታቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ አገራት የሚኖሩት ዜጎች የዛን አገር ሀብት እኩል መጠቀምና በሀሳብም ተነጋግረው መግባባት ሲችሉ ነው ። በሕዝብ መካከል አንድነት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችንም (“Homogeneity” ለመፍጠር) ትምህርት፣ አንድ የጋራ ቋንቋን በማስተማር ቀለል ቀለል ያሉ መሰረተ ልማቶችን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፤ አንዳንዴም ኃይልን በመጠቀምና አገርና ሕዝብን ከሚጎዱ ጎጂ ድርጊቶችና ጥፋቶች እንዲቆጠቡ ማድረግ ወዘተ በማለት የዘረዘሩ ሲሆን፤ በአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ዲሞክራትነትና አምባገነንነት እኩል እንደሚያስፈልጉም በጥናታቸው አመላክተዋል ።
በህንድ አገረ መንግሥትን ለመመስረት በርካታ ውጣ ውረዶች የታለፉ ሲሆን “የህንድ ወላጅ አባት” Sardar Vallabhbhai Pateን በመሳሰሉ የአንድነት ኃይሎች በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት የዛሬዋ ህንድ ልትኖር ችላለች ። በ1840 እና 50ዎቹ አለቀላት ከተባለ በኋላ ብድግ ያደረጓት የአሜሪካ “መስራች አባቶች”ንም እዚሁ ጋር ማንሳት ተገቢ ነው ። አፍሪካ ለሁለት ተሰንጥቃ (የሞኖሮቢያ እና ካዛብላንካ ቡድን) ተሰነጣጣቂዎቹ ቻው ቻው ሊባባሉ ጥቂት ሲቀራቸው የገለልተኝነት አቋምን በመያዝ ለዛሬዋ አፍሪካ ቤዛ የሆኑትና “የአፍሪካ አባት” ማህበራዊ ማዕረግን ያተረፉትን ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም የሚዘለሉ አይደሉም ።
መግቢያ አንቀፆቻችን ላይ ያልነው እንዳለ ሆኖ፣ 125ኛውን የአድዋ የድል በዓል ለመዘከር በጀርመን ከተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን “ለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምስረታ ጉልህ ድርሻ ያለውና የአንድነታችን ስኬት የሆነው ይህ ዓለም ሁሉ የሚዘክረው ታሪካዊ ድል ላለፉት 84 ዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል” የሚል አስተያየት መደመጡን፤ የጋራ ጀግና መፍጠርና አርአያነቱንም መከተል እንደሚገባን በብዙዎች መወትወቱን፤ እንደጥላሁን ገሠሠ አይነት በቁሙም (በዜማው)፣ በሞቱም (የቀብር ሥነሥርአቱ) ለአገር ግንባታ የሚሰራው ቁጥር በፍጥነት እየወረደ መምጣቱን፤ በተለይ የፖለቲካ ልሂቃን እየተባባሉ የሚጠራሩት እንደ መጠራሪያቸው ሲሆኑ አለመታየታቸውን ደምረን ጉዳዩን ስንመዝነው የሚታየን የጉዳዩ አሳሳቢነት ነው ። ቢሆንም “ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ነች” እንደተባለው ነውና እዳው ገብስ ነው ።
የተለያየ ቋንቋ፣ ብሄር፣ ኃይማኖት፣ ፍላጎት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ባህል ወዘተ ባሏቸው አገራት፣ ከላይ በጠቀስናቸው የተለያዩ ምክንያቶች “አገር ግንባታ” እና “አገረ መንግስት ግንባታ” የዘመኑ ቋንቋና ወቅታዊ ጥያቄ ሆነዋል። አሁን፣ ጥያቄው መሆን ያለበት “እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት ነው ማስተናገድ የሚገባው?” የሚለው ነው ። የሩዋንዳው ካጋሜ አገራቸውን ወደ ሰላም የማምጣቱን ስራ የጀመሩት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ላም በመስጠት ነው (ዶ/ር ዐቢይንም እዚህ መጥተው ሲጎበኙ ስጦታ ያመጡላቸው ላም እንደ ነበር ያስታውሷል) ። ጠንካራ ተቋማናትን መገንባት ምንም አይነት ጊዜ የሚሰጠው ሳይሆን ዛሬውኑ መጀመር ያለበት ጉዳይ ነው ።
ባጭሩ፣ እዚህ ዘርዝረን የማንጨርሳቸውን የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ፣ መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን በሙሉ እስከሚባል ድረስ ለአገርና ለአገረ መንግሥት ግንባታ አለመጠቀማችን ከበቂ በላይ የተረጋገጠ ነው ። በመሆኑም ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።
(ይህን ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ በተለይ ዋና ዋና (The basic theories of nations) በሚባሉት የመስኩ ንድፈ ሀሳቦች – primordialism፣ perennialism፣ ethno-symbolism፣ modernism እና Constitutionalism – ለፈተሸ ብዙ የሚያስተምረን ጉዳይ ይኖራልና እናበረታታለን። ለመመረቂያ ፅሑፍ ርዕስ በመፈለግ ላይ ያሉ እችን ላፍ ቢያደርጓት እንደሚያዋጣቸው መግለፅ ተገቢ ነው ።)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013