በንጉሱ ዘመን የሀገራችን ክፍሎች በጠቅላይ ግዛት፣ በአውራጃና በወረዳ የተከፈሉ ነበሩ፡፡ ወታደራዊው ደርግ ሲመጣ ደግሞ ክፍለ ሀገር፣ አውራጃ፣ ወረዳና ቀበሌ በሚል ተጠሩ። ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ሲቆናጠጥ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ በሚል ተሸነሸኑ፡፡ ቀስ በቀስም የቀበሌ አስተዳደር እንዲቀርና እንዲታጠፍ ተደረገ፡፡ ቀበሌዎች ደርግ መሠረቱን የጣለባቸው ስለነበሩ ኢሕአዴግ ቀበሌ ደርግን ያስታውሰኛል በሚል በፍርሃት ያጠፋቸው እንደሚሆኑ እገምታለሁ፡፡
በአዲስ አበባ ብቻ ቀበሌዎች ሲታጠፉ አራት አምስት ቀበሌዎች በአንድ ወረዳ ውስጥ እንዲጠቃለሉ የተደረገበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ አሁን የመንግሥት የታችኛው አስተዳደር ወረዳ ሆኗል፡፡ ቀበሌም ሆነ ወረዳ ከደርግ ጀምሮ በኅብረተሰቡ ጥሩ ሥም የላቸውም፡፡ የካድሬዎች መሰባሰቢያ ተደርገው ይታያሉ፤ አንዳንዶች ወረዳን፣ የወረደ፣ ወራዳ፣ በሚል እሳቤ የጎሪጥ ይመለከቱታል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን የመንግሥት ሥረ መሠረቱ ያለው ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ መንግሥትና ቀበሌ በእትብት ዓይነት ነገር የሚገናኙ ዓይነት ናቸው ብሎ መናገርም ይቻላል፡፡ እናም ወረዳዎች በመንግሥት አካላት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ብዙ ጊዜ የመንግሥት አመራሮች ወረዳን የሚያስታውሱት ምርጫ ሲደርስ ብቻ የሚመስልበት ሁኔታ አለ፡፡ ወረዳዎች ተገልጋዩን ሕዝብ እያገለገሉት ነው? ወይስ እየተገለገሉበት? የሚለውም መፈተሽ አለበት፡፡ እኔ አንዳንድ ወረዳዎች ሕዝቡን ከማገልገል ይልቅ ገለል ያደርጉታል፤ በሕዝቡ ሲገለገሉበት እና ሲያጉላሉት አያለሁ፡፡ የአገልግሎት አሠጣጡ ደካማ ነው፤ ቢሮክራሲው የተወሳሰበ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡
በወረዳ ወሣኝ ኩነት አገልግሎት አለ፡፡ የልደት፣ ሞትና ጋብቻ የመሳሰሉት ምዝገባ የሚካሄድበት፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ሰዎች ማሥረጃ ሲያስፈልጋቸው ወደ ወረዳ ይሄዳሉ፡፡ በተጨማሪም የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት አለ፡፡ ነዋሪዎች መታወቂያ ለማግኘት እንግልቱ የሚያማርር ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ ነዋሪውን ቀና ብለው ሣያዩ ዛሬ አገልግሎት የለም በሚቀጥለው ሣምንቱ ይምጡ የሚሉበት አጋጣሚ ሠፊ ነው፡፡ በቀድሞው አጠራር የዚህ ቀበሌ ነዋሪዎች ከሆናችሁ አገልግሎት የሚሰጣችሁ በዚህ ቀን ነው መባል ያለ ነው፡፡ በዚህ ቀን አገልግሎቱን ፍለጋ ሲሄዱ ደግሞ ስብሳባ ላይ ናቸው፤ ሥልጠና ላይ ናቸው ወዘተ…መባል አለ።ሦስት አራት ቀበሌዎች ታጥፈው በአንድ ጠባብ የወረዳ ጽህፈት ቤት ግቢ ታጉረው ተገልጋይ የሚበዛበት ጊዜ እንዳለ እሙን ነው፡፡ በቀጣዩ ሣምንት ስትሄዱ ደግሞ መታወቂያ የሚፈርሙት ስብሰባ ሄደዋል ይባላሉ፡፡ በወረዳ መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጡ የተዝረከረከ ነው፤ መታወቂያ በአሻራ ይሁን ከተባለ ቆየ፤ ነገር ግን መታወቂያ ለማግኘት ስትሄዱ ሲስተም የለም/ ሲስተምማ ሁሌም የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሥራቸውን ሥፋት ታሣቢ ያደረገ የአይሲቲ መሠረተ ልማት ያላቸው አይመስልም፡፡ በኔት ወርክ አለመኖር ወይም ፈጣን አለመሆን የተነሳ አገልግሎት ፈላጊዎች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡
መብራት የለም የሚሉ «የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ» ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለነዋሪው ባለጉዳይና ተገልጋይ መታወቂያ መስጠትን እንደ ግዴታ ሣይሆን እንደ ስጦታ ያዩታል፡፡
በዚህ ዘመንም ፋይል ይሠወራል፡፡ የለም ይባላሉ። በቅርቡ ለልጆች ትምህርት ቤት ምዝገባ የልደት ምሥክር ወረቀት ፍለጋ አንድ ቀበሌ የሄደ ሰው ፋይልህ የለም ብለውት ጉዱ ፈጦ እንደነበር ነገረኝ። የሚሻለው በደብዳቤ እንድትስተናገዱ እናደርጋለን ብለውት ደብዳቤ እንደተጻፈለት ነግሮኛል፡፡
በወረዳ አገልግሎት ዙሪያ ከአንድ ግለሰብ ስንጨዋወት ኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ሕንፃ ዕጣ እንደደረሣቸው ነገሩኝ፤ ለመፈራረም የነዋሪነት መታወቂያ ይጠየቃሉ፤ መታወቂያ ለማግኘት ለሚኖሩበት ወረዳ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከሣምንት በኋላ ይመለሱ ይባላሉ፡፡ መታወቂያ ማቅረብ የነበረባቸው በሦስት ቀናት ውስጥ ነበርና ግራ ይጋባሉ፡፡ ጉዳዩን ሊያስረዱ ቢሞክሩም ከቁብ የሚቆጥር አስተናጋጅ ያጣሉ፡፡ ግራ ሲገባቸው ወደ አመራሮቹ ሄደው ችግራቸውን አስረዱ፤ በፍጥነት መታወቂያ እንዲሰጣቸው ተደረገ፡፡
የባንክ አክሲዮን ለመግዛት የፈለጉ ግለሰብም የታደሠ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ተጠየቁ፡፡ ከወረዳ መታወቂያ ለማውጣት ሄደው የአንድ ሣምንት ቀጠሮ ተሰጣቸው፤ ሆኖም አክሲዮን የመግዛት ፍላጎታቸው፤ ቀኑ በማለፉና መታወቂያ በቶሎ ማግኘት ባለመቻላቸው ተገታ፡፡ ስለ መታወቂያ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ዘርዝረን አንጨርሰውም፡፡ ወደ ውጪ ሀገር ለሥራ፣ ለሕክምና፣ ለትምህርትና ለሃይማኖታዊ ለመሣሠሉት ጉዞዎች መሄድ የሚፈልጉ ሰዎች በሚፈለገው ፍጥነት መታወቂያ አያገኙም፡፡ በዚህም ጉዟቸው የሚስተጓጎልና የሚቀር አለ፡፡
በወረዳ ሥር ትምህርት፣ መሬት፣ ቤቶች አስተዳደር የሚከታተሉ (የቀበሌ የግል ቤቶችንና የጋራ ሕንፃዎችን የሚመራውና ግንባታዎችንና ዕድሣቶችን የሚቆጣጠሩ) አካላት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎችን የሚያደራጀው ንግድ ፈቃድ የሚሰጠው ሸማቾችን የሚመራው ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤትም አለ፡፡ እንዲሁም አሁን ከወረዳው አስተዳደር ተነጥለው በወረዳ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት የሚሰጡት ገቢዎች እና ጤና አገልግሎት (በጤና ጣቢያዎች) በየወረዳው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ እንኳን በአንጻራዊነት ከወረዳ አስተዳደሮቹ ቀልጠፍ ያለ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እናም ወረዳዎች ቀርፈፍ ያለውን አገልግሎት አሰጣጣቸውን ቅርጥፍ አድርገው ጥለው ቀልጠፍ ያለ አገልግሎት ለመስጠት ይዘጋጁ፡፡
በወረዳ ሥር ከሚሰጡት አገልግሎቶች አንዱ ቤቶች ግንባታና ዕድሣት ፈቃድ ነው፤ በያዝነው ክረምት ወር ቤታችሁ ጣራ ዝናብ እያፈሰሰ ዕድሣት ፈቃድ ለመጠየቅ ብትሄዱ በጥቂቱ አንድ ሣምንት መጉላላት የማይቀር ነው፡፡ ሰዎች አማራጭ ሲያጡ በምሽት ወይም በሠንበት ጣራ ነቅለው የሚያድሱበት ሁኔታ አይቻለሁ፡፡ ግፋ ቢል ተቆጣጣሪ አካላት ቢመጡ በኪሳቸው ጣል ማድረግ ያለ አማራጭ ነው፡፡ በወረዳ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙት «ጣል» የሚያደርጉ ናቸው። የወረዳዎች አገልግሎት ሲታይ በዚህ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን ውስጥ ናቸው ወይ ብሎ መጠየቅ ውስጥም ያስገባል፡፡ በጋርዮሽ ሥርዓት ውስጥ ነን እንዴ ያለነው ትላላችሁ፡፡ መፍትሔው ምርጥ ተሞክሮ መቀመር የሚባለውን መተግበር ነው፡፡ የተገልጋይ እርካታ የሚዳስስና የአገልግሎት አሰጣጥ ግብረ መልስ የሚሰበስብና የሚፈትሽ አሠራር ይኑር፡፡ የባለሙያ እጥረት ላለባቸው መፍትሄ ይሰጣቸው፡፡ ሥልጠናና ግብዓት ማሟላት ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማካሄድ አመራሩን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡
ክፍለ ከተሞች ወረዳዎችን ይመልከቱ፤ በወረዳዎች መካከል የውድድር እና የፉክክር መንፈስ ይኑር፡፡ (ጤና ጣቢያዎች የውድድር መንፈስ እንዳላቸው ሁሉ) ወረዳዎች ልምዶቻቸውን ይለዋወጡ፤ ሞዴል ወረዳም ተብሎ የሚወደስና የሚሞገስ ይኑረን፣ የመዲናዋ ወረዳዎችን የሚያወዳድር ይኑር፡፡
የወረዳዎች የነዋሪዎች መረጃ አያያዝ የይስሙላ ሣይሆን የምር ዘመናዊና በኮምፒውተር ሥርዓት የተደገፈ መሆን ይኖርበታል፡፡ የኔትወርክ አቅማቸውም ማደግ የለበትም፡፡ ሁሌም ኮኔክሽን የለም ማለት ያሣፍራል፡፡ አሊያም በቀድሞው መንገድ መሥራት ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደጠቅስነው ከወረዳ አይቀርም፤ የእያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ መረጃ ያለው ወረዳ ላይ ነው። ይህን አለማዘመን አገልግሎት ፈላጊውን ብቻ ሣይሆን አገልግሎት ሰጪውንም ይጎዳልና ለማዘመኑ አቅምን ለማጎልበቱ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት ሌላው ችግር ነው፡፡ ነዋሪዎች ተሰልፈው እያለ ያልተሰለፈ ሰው ጉዳይ ፈጽሞ ይወጣል። ይህ ከምን ይመነጫል? ከኪራይ ሰብሳቢነት ነው መልሱ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ መፈተሽና አሠራሩን ማዘመን ያለበት በቢሮክራሲ አሠራር የታጠረውን የወረዳ አስተዳደር ነው። ሕዝቡን ብልጽግናን የመረጠው ወደ ጉስቅልና የሚወስዱ ቢሮክራሲያዊ ሠንሰለቶችን እንዲበጣጥስለት ነውና፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013