
አበው ሲናገሩ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይላሉ፡፡ ይህ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወሬ ፊት ለፊት ከሚደረግ ጦርነት የበለጠ ተሸናፊነትን ወይም አሸናፊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሣሪያ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የወሬ ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ዘመኑም የኢንፎርሜሽን /የመረጃ ዘመን/ ነውና መረጃ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እየሆነ ነው፡፡
በዚህ ዘመን መረጃ ከአንድ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ በቀላሉ ለመዘዋወር የሰከንዶች ሽርፍራፊ ብቻ በቂ ነው፡፡ ይህ የመረጃ ፍጥነት ባልከፋ፤ ነገር ግን የሚዛመተው ወሬ ደግሞ ትክክለኛ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በዚህ ዘመን ወሬ ልክ እንደጦር መሣሪያ በአንድ ቤት ውስጥ የሚመረትበት እና የሚሠራጭበት ጊዜ በመሆኑ ይህንን መረጃ ሣያጣሩ መውሰድና መጠቀም ከጉዳቱ ይልቅ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደምም በዚህ ዓይነት መንገድ በቤት ውስጥ በተፈበረኩ የሐሰት ወሬዎች በርካቶች ለጉዳት ተዳርገዋል፤ አገርም እስከመፍረስ ደርሷል፤ አብነት እናንሣ፡፡
ኢራቅ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያየ ሁሉ ከዚህ ቀደም የነበረችበትን ደረጃ በማስታወስ ሊያዝን ይችላል፡፡ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ብዙዎቹ ኢራቃውያን ከራሣቸው አልፎ ለሌሎች የሚተርፉ ባለፀጎች ነበሩ፡፡ የሃገሪቷም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሲታይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ የነፍሰ ወከፍ ገቢ እና አጠቃላይ ምርት ካላቸው የዓለም ሃገራት አንዷ ነበረች፡፡
ነገር ግን ይህች ሃገር በቅድሚያ ጎረቤቷን ኩዌትን ወረረች በሚል ሠበብ በአሜሪካና ወዳጆቿ የጥፋት ሠለባ ለመሆን በቃች፡፡ በዚህ ሂደት አሜሪካ በኢራቅ ላይ ጦሯን ለማዝመት ስትፈልግ በቅድሚያ ያደረገችው ታዲያ የውሸት ወሬ መፈብረክ ነበር፡፡ ምክንያቱም የራሷን ባለሥልጣናት እና ዓለምን ለማሣመን በኩዌት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ማሣየት ነበረባትና፡፡ በዚህም አንዲት በኢራቅ የኩዌት አምባሣደር ልጅ ለድራማው ተመርጣ የውሸት ዜናው ገፀ ባህርይን ተወነች፡፡ ይህች ሕፃን ታዲያ በተሰጣት ሥልጠና መሠረት ከመገናኛ ብዙሃን ፊት ለፊት ተቀምጣ እያነባች የኢራቅ ጦር ያደረሠባትን በደል ዘረዘረች፡፡ ጦሩ በአስቸኳይ ከሃገሪቱ ካልወጣ ሕፃናትና እናቶች እየተጎዱ እንደሆነ ተረከች፡፡ አልቅሣ ዓለምን አስለቀሰች፡፡ ይህ ድርት ታዲያ ለአሜሪካና ሸሪኮቿ ጦር ወደኢራቅ መዝመት ትልቁ መነሻ ሆነ፡፡
እነሆ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የምናያቸው በርካታ ተመሣሣይ ታሪኮች አሉ፡፡ ለአብነትም ከወራት በፊት በአክሱም ቤተክርስቲያን ቄስ እንደሆኑ ሲናገሩ የነበሩት ሰው የኤርትራ ጦር በቤተክርስቲያኗ እና በምዕመኑ ላይ ያደረሱትን በደል በመዘርዘር ያለእፍረት ሲናገሩ ሠምተናል፡፡ ይህንንም የዓለም አቀፉ ሚዲያ ከሚዲያ ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ያለምንም ማጣራት ተቀብሎ አሠራጭቷል፡፡
ከዚህም አልፎ ምዕራባውያኑ ሚዲያዎች ለዓለም ማህበረሰብ በተለይ ለአፍሪካ ሃገራት ስለዴሞክራሲና ስለ ሚዲያ ነፃነትና ሐቀኝነት ሲያስተምሩ የሚውሉትና ራሣቸው የሚሰሩት ማዶ ለማዶ ሆኖ በገሃድ ተመልክተናል፡፡ በትግራይ ከተከሰተው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ጀርባ ያለውን እውነታ ከመፈለግ ይልቅ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሚሰጣቸውን የአንድ ወገን መረጃ በመያዝ ሲያባዙ ይታያሉ፡፡
እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን እውነትን ለማጣራት ቦታ የላቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ የነሱ ፍላጎት የሚናገሩትን እንድንቀበል ብቻ ማስገደድ ነው፡፡ ለነሱ እውነት ማለት እነሱ የሚናገሩት እና የነሱ ወዳጆች የሚያቀርቡት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሌላው መረጃ የውሸት አሊያም ቦታ የሌለው ነው፡፡
ለምሣሌ ከሰሞኑ ሕወሃት የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታዎች አሻሻለ ብለው ሲናገሩ ይሠማል። ይሁንና ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሣኔን በተመለከተ ግን ምንም መናገር አይፈልጉም፡፡ አሁን አሸባሪው ቡድን መውጫ ሲጠፋው የተኩስ አቁሙን ይዘው ይጮሃሉ፡፡ ስለሰብዓዊ መብት ጥሰትም በተመለከተ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በማይካድራ ስለፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለመናገር የሞራል ልዕልና የላቸውም። ከዚያ ይልቅ የነሱን ቀልብ የሚገዛው እነሱ የሚፈበርኩት የሐሰት ዜና ነው፡፡
በአጠቃላይ አሁን መንግሥት በትግራይ እያደረገ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ፊት ለፊት ከሚደረገው የጠላት ግጥሚያ ይልቅ በህቡዕ የሚደረገው የአሸባሪው ቡድን የደፈጣ የተሣሣተ መረጃ አደገኛ እየሆነ ይገኛል፡፡ አሸባሪው ሕወሃት ውጭ ካለው ደጋፊው ጋር በመሆን በቤት ውስጥ የሚፈበርካቸው የውሸት መረጃዎች በህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት ሕዝቡሠላማዊ ኑሮውን እንዳይኖር ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች አማካይነት የሚረጩት መረጃዎች ሕዝቡ አንድ እንዳይሆን ለማድረግና የአሸናፊነት ሥነ ልቦናውን ለማራቅ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የራሱ አሉታዊ ጫና አለው። በአንድ በኩል እነዚህ የውሽት መረጃዎች የግለሰቦችን ውስጣዊ መንፈስ ይጎዳሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ሃገርን ይረብሻሉ፡፡ ሰዎች ተረጋግተው እንዳይሠሩና እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ በተለይ ከሕግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ ያሉ ማናቸውንም መረጃዎች ከትክክለኛ የመረጃ ምንጮች ብቻ በመውሰድ ራሱንም ሆነ ሃገሩን ከጉዳት ሊታደግ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የሃገር መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መረጃ መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ መረጃዎችን ሲወስድ የመረጃ ምንጫቸው ያልታወቁ፣ ነገር ግን ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን ሼር ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል፤ ሠራዊታችን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ የሚጓጓዙ የጦር መሣሪያዎች ዓይነትና ብዛት፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችን ፎቶ በማንሣት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከመለጠፍ መቆጠብ አለበት፤ የጠላትን የትንኮሣ ሥራም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከመለጠፍ ሊቆጠብ ይገባል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አሁን…አሁን በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደፋሽን የተያዘው “ሠበር” በሚል በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚለጠፉ ዜናዎች አሣሣችና የህብረተሰቡን ቀልብ በመሣብ የተዛባ መረጃ የሚሰጡ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት መረጃዎች ከላይ ሲታዩ ሣቢ ቢመስሉም ውስጣቸው ባዶ፣ በብዛትም አሣሣች በመሆናቸው እንዲህ የሚያደርጉ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
የሃገር መከላከያ ሠራዊት በማህበራዊ ትሥሥር ገፁ እንዳስታወቀው ማንኛውም ሃገር ወዳድ ዜጋ በሠራዊታችን ግዳጅ አፈጻፀምና በሕዝባችን ሞራልና ሥነ-ልቦና የበላይነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩና ጠላት ሆን ብሎ የሚለቃቸውን መረጃዎች ባለማሠራጨት ትብብር ሊያደርግ ይገባል፡፡
የሃገር መከላከያ ሠራዊትን የምንደግፈው በማህበራዊ ትሥሥር ድረ ገፆች ላይ ጊዜያችንን በማባከን ሣይሆን ትክክለኛ መረጃዎችን በመቀበልና በመተግበር እንዲሁም ከመከላከያ ጎን በመቆም በሞራል፣ በገንዘብና በሐሳብ ስንደግፍ ነውና ለዚህ ሁላችንም የየራሣችንን አስተዋፅኦ ልናደርግ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም