በአንድ የአዲስ አበባ ከተማ ውድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አናት ላይ ቆሜያለሁ። የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር ይፋ የተደረጉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሚገነባው መንገድ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፤ ከእዚህ ርቀት ውስጥ 320 ሜትሩ ዋሻ ተደርጎ ነው የሚገነባው።
ዋሻ፣ ድልድይ እና የተለያዩ መንገዶች ለሚገነቡበት ለእዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ የሚወጣው ሀብትም አንድ ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ነው። አንዱ ኪሎ ሜትሩ መንገድ የሚገነባው ደግሞ በ395 ሚሊየን ብር ነው። ይህም ሊሆን ይችላል ውዱ የመንገድ ፕሮጀክት ያሰኘው። ግንባታው ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር የሚካሄድ ሲሆን፣ ግንባታው የሚካሄደውም ቻይናው ፈረስት ሀይዌይ ኢንጂነሪግ ኩባንያ ነው። ግንባታው የተጀመረው በፈረንጆቹ ጥቅምት አንድ ቀን 2019 ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ። የጎተራ ሳር ቤት ፑሽኪን አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት።
ወደ ሰፈሬ ላፍቶ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚካሄድ ግንባታ መሆኑ ትኩረቴን ስቦታል። መንገዱ ለግንባታው ሲባል እስከሚቆረጥ ድረስ መውጫ መግቢያዬ በቄራ በኩል ነበር፣ ግንባታው መውጫ መግቢያዬን ዙሪያ ጥምጥም አርጎታል፤ ሁሌም በሳር ቤት፣መከኒሳ ጀርመን አደባባይ ጎፋ ካፕም ጎፋ ገብርኤል ጎፋ መብራት በኩል ሆኗል። በታክሲ የአምስት ብሩን መንገድ በአስር ብር መሄድ ከጀመርኩ ዓመት አልፎኛል። ከሜክሲኮ ላፍቶ የሚኬድበት አንዱ መንገድ ይሄ ነው። ሌላው በለቡ መብራት አርጎ፣ የፈለገም በስታዲየም አጎና ጎተራ ግርጌ አርጎም በመሄድ ላፍቶ መድረስ ይችላል።
ግንባታው ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ስል ሁሌም ራሴን እና ሰዎችን እጠይቅ ነበርና ለምን መልሱን ራሴ አልመልሰውም በሚል ያለፈውን ቅድሜ የተወሰነ ሰዓት ለእሱ ቅኝት አዋልኩት። የዚያን እለቱ የጉዞ አቅጣጫዬም በሳር ቤት ጀርመን አደባባይ መሆኑ ቀርቶ በሜክሲኮ ቄራ በኩል አድርጌያለሁ። 10 ሰዓት ሜክሲኮ አካባቢ ደርሻለሁ። ቀኑም ብራ መሆኑ ሀሳቤ እንደሚሳካ ታሰበኝ። መንገዱ ምቾት ሊሰጥ እንደማይችል አውቄ ነው የገባሁበት።
በሀይገር አውቶብስ የሁለት ብሩን መንገድ ሦስት ብር ከፍዬ ጉዞ ወደ ቄራ ሆነ። ያ የተሽከርካሪ ትርምስ የሚታይበት የሜክሲኮ ቄራ ጎዳና የተወረረ መስሏል። ውር ውር የሚሉ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው የሚታዩበት። እነሱም ቄራን የማይሻገሩ ናቸው። አቤት የዚህ አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ ምንኛ ይዳከም ስል አሰብኩ። የማህበረሰቡም የትራንስፖርት ፈተናም ታሰበኝ።
ከሜክሲኮ ቄራ ቅርብ ስለሆነ ወዲያው ደርሰናል። ቄራዎች ድርጅት ፊት ለፊት ወርጄ ወደ ጎፋ ማዞሪያ መጓዝ ጀምሬያለሁ። መሄድ የሚቻለው በእግር ብቻ ነው። ሰዎች ተከትዬ ግንባታው በሚካሄድበት በኩል ወደ ውስጥ ዘለቅሁ። ትንሽ ቆም ብዬ ተመለከትኩ፤ ለዋሻነት ሲቆፈርና በኮንክሪት ሲሞላ የነበረው ቁልቁል ይታይ የነበረው የመንገዱ ግንባታ ክፍል አሁን ጨርሶ አይታይም። የዋሻው ሥራ አልቋል። የዋሻው መንገድ ከጎተራ ወደ ሳር ቤት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ መጀመሩን በመንገዱ ከተጠቀሙ ወገኖች መስማቴም ታወሰኝ።
መንገዱን ማቋረጥ አለብኝ። ከቆምኩበት አፋፍ ስፍራ ቁልቁል መውረድ ይኖርብኛል።አንዳንድ ወጣቶች እየተንደረደሩ ጢብ ጢብ እያሉ ሲወርዱ ተመለክትኩ፤ ይቺ ለእኔ አትሆንም አልኩና እንዴት አድርጌ መውረድ እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ። በአካባቢው የሚያዝ ነገር የለም። ፊት ለፊት መሄድም አይቻልም። በስላች ቁልቁል በዘዴ እንደ ምንም ወርጄ ታች ከተደለደለው ስፍራ ደርስኩ። ይህ ስፍራ ከስሩ ከጎተራ ሳር ቤት የሚያገናኘው ዋሻ የተገነባበት ነው። እናም ዋሻው አናት ላይ ነው የቆምኩት ስል አሰብኩ።
የዋሻውን አናት ይዤ ትንሽ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ መጓዝ ጀመርኩ። እየተጓዝኩ ያለሁበት ስፍራ ጎድጓዳ ነው። ፊት ለፊት ስመለከት መንደሮቹ እላይ የተሰቀሉ መሰለኝ። ከዋሻው አናትም በጣም ከፍ ብለው ነው የሚታዩት። መንገዱ ከሱቆቹ ከተቆራረጠ ከዓመት በላይ ሆኖታል። ናዳ ለመከላከል እንዲያስችል የተደረገ ግንባታ አለ። ከመሬት ቁልቁል ያለበትን ስፍራ ሳስብም እዚህ ውስጥም ሌላ መንገድ እንደሚኖር ታሰበኝ።
ከጎድጓዳው ስፍራ መውጣት ያለብኝ ቦታ ደርሻለሁ። ስፍራው ከቂርቆስ ወደ ጎፋ ማዞሪያ የሚገነባው ድልድይ ምሰሶዎች የቆሙበት ነው። አንዳንዶች ከጎድጓዳው ስፍራ አንዴት መሬት እየያዙ እንደሚወጡና እንደሚወርዱ ሲታሰብ ያስፈራል። እኔም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ቀኙን ሳማትር ሰዎች የሚመላለሱበት ሌላ መንገድ ታየኝ። በዚያ በኩል ወጣሁ። ዋናውን ፈተና ጨርሻለሁ ስል አሰብኩ።
መስቀለኛውን ስፍራ ቆም ብዬ መመልከት ጀመርኩ። ዋሻውን አሰብኩት። ከቂርቆስ ወደ ጎፋ ማዞሪያ የሚዘልቀው ድልድይ ምሰሶዎች ከቆሙ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ምሰሶዎቹን ለማገናኘት ታሰቦ ነው መሰለኝ ሌሎች ግንባታዎች ከስር ይታያሉ። ከጎፋ ማዞሪያ ድልድዩ አካባቢ እስከ ሶፊያ ሞል እንዲሁም ከድልድዩ ወደ ቆርቆስ ወጋጋን ባንክ አቅጣጫ ያሉት የመንገድ ግንባታዎችም እየተካሄዱ ናቸው።
የጎፋ ማዞሪያ አካባቢ ግርግር ታወሰኝ። አሁን እንደነገሩ ሆኗል። ሱቆች ፈዘዋል። የሚያልፍ የሚያገድመው ጥቂት ሰው ነው። ትራንስፖርት ለማግኘት ሶፊያ ሞል ድረስ መጓዝ የግድ ነው። ግራ ቀኝ የነበሩ ሱቆች የሉም፤ በአዲስ መልክ የተገነቡ ሱቆች ይታያሉ። እስከ ሶፊያ ሞል ያለው አካባቢ ተቆፋፍሮ በግንባታ ግብዓት እየተሞላ ነው፤ አንዳንዱ ቦታ ባህር ይመስል በውሃ ተሞልቷል፤ ሰው ሊወጡ የተዘጋጁ የሚመስሉ ክፍት የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስኮቶች በብዛት ይታያሉ።
ዝናብ ቢኖር እንዴት ጉዞው ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል። ልጆች ፣ አዛውንቶችና እናቶች እንዴት ሊሻገሩት እንደሚችሉም ታሰበኝ። የመንገድ መብራት እንደማይኖር ገመትኩ። መንገዱ ለዓይን ከያዘ በኋላ እንደማይሆን ተረዳሁና ቶሎ ቶሎ መጓዝ ጀመርኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ እውን የሚሆነው ዘመናዊ መንገድ ይህን ሁሉ እንደሚሽረው ታሰበኝ። ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው እንደሚባለው ማለት ነው።
ስለግንባታው የያዙኩት መረጃና የተመለከትኩት ግንባታ በጣም ውስብስብ መሆኑን ገለጹልኝ ። በግንባታው ላይ ለውጥ ያላየሁ የመሰለኝን ያህል በሆነው ሁሉ መደነቅ ጀመርኩ። 320 ሜትር የሚረዝም ዋሻ በመሬት ውስጥ መገንባት፣ ድልድይ እና ሌሎች ተደራራቢ መንገዶች መገንባት፣ የፍጥነት መንገድ ሲታሰቡ ፕሮጀክቱ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደመሆኑ በሌሎች የመንገድ ግንባታዎች ዓይን መታየት የለበትም አልኩ። ዋሻው አልቆ ስራ ጀምሯል፤ ይህ ትልቅ ዜና ነው። ከቄርቆስ ወደ ጎፋ ማዞሪያ የሚያሻግረው ድልድይ ምሰሶዎች ከተገነቡ ቆይተዋል። አሁን መሸጋገሪያውን ለመገንባት እየተሰራ ነው። በጎተራ እና በሳር ቤት በኩል ያሉት መንገዶች ግንባታም አልቋል።
ይህ ግንባታ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ሲና መግቢያ አናቱ ላይ ካለው የጣርማ በር ዋሻ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል። ያንን ረጅም ዋሻ ማየት ያልታደለ ግን ጣርማ በርን በአዲስ አበባ ማየት ይችላል። ይሄኛውም ያኛውም የኛው ናቸው።
ለግንባታ የተያዘው ሁለት ዓመት ከመሆኑ አኳያም ጥሩ እየሄደ የሚባል ፕሮጀክት ነው። የተጀመረው በፈረንጆቹ ጥቅምት 2019 መሆኑ ሲታሰብም በትክክለኛ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መገኘቱን መረዳት ይቻላል። አብዛኛው ስራ እየተጠናቀቀ ከመሆኑ አኳያ በአዲስ ዓመት ብዙ ለውጦች እንደሚታዩ ታሰበኝ። ሀገራችን በፕሮጀክት መጓተት ምን ያህል እንደምትቸገር ሲታሰብ ይህ ፕሮጀክት ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013