ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ ተስማሚ አየር ንብረት፤ ክረምትና በጋ ሲያቆራርጥ የሚፈስ ወንዝ፤ ታላላቅ የተፈጥሮ ደንና ተራሮች፤ ማዕድናት፤ የእንስሳት ሀብት ልማት፤ ሰርቶ የማይታክት ታታሪና ጠንካራ አርሶ አደር የተቸረች አገር ናት፡፡
ግብርና ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ባለ ውለታ ፣ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ዋልታና መከታ፤ ለገጽታ ግንባታ መታያና መመልከቻ ነው፡፡ የአገሪቱ አርሶ አደር በትግበራ ያካበተውንና በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ በመጠቀም በዘመናዊና ቴክኖሎጂ ወለድ በሆኑ መሳሪያዎች ሳይታገዝ፣ በአንድ በኩል በየጊዜው የአፈሩ ለምነት እየቀነሰ በሌላ በኩል ቁጥሩ እየናረ የሚሄደውን ህብረተሰብ የመመገብ ግዴታውን በመወጣት ላይ በርካታ አመታት አሳልፏል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የግብርናው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ ብሎ ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ዕድገቱ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ሐቅ ነው፡፡ ዘርፉ ዘምኖና ተትረፍርፎ የህብረተሰቡን ህይወት በሚፈልገው ደረጃ ለውጦታል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡
ሮማኒያ አሜሪካዊው የምጣኔ ሃብት ምሁር እና በካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተመራማሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ኢርማ ግሊክማን አደልማን በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ድህነትን ለመቀነስ ሊተገብሯቸው ስለሚገባቸው የፖሊሲ አቅጣጫ ለመጠቆም ‹‹Beyond export-led growth›› በሚል ርዕስ አንድ የምርምር ፅሁፋቸው አሳትመው ነበር፡፡
ፕሮፌሰሩ በዚህ የምርምር ስራቸው እንዳተቱትም፣ ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ እጅግ ሁነኛው የእድገት አማራጭ ነው። የግብርና ምርት እና ምርታማነት መጎልበት ለኢንዱስትሪው ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ስለመሆኑ ሃሳባቸውን አስፍረዋል።
ሪቻርድ ግራቦስኪ እና ሻር ሰልፍ የተባሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፣ እኤአ በ2007‹‹Economic development and the role of agricultural technology›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ የምርምር ስራቸውን በጋራ አሳትመው ነበር፡፡
በዚህ ጥናታዊ ፅሁፋቸው፣ በድሃ አገራት አብዛኛው ህዝብ በግብርናው ዘርፍ ላይ ጥገኛ በሆነበት ሁኔታ የኢንዱስትሪ ልማት በማፋጠን መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ በቅድሚያ የግብርናው ዘርፍ እድገት የግድ እንደሆነና ግብርናው ባላደገበት ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ማድረግ በፍፁም አዳጋች መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ስንቃኝም፣ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲና ፕሮግራም ማሻሻያዎችን በመውሰድ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት እርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም የሚፈለገውን ያሕል ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡ አገሪቱ ለግብርና እጅግ በጣም ተስማሚ ብትሆንም በዚያው ልክ ከሚፈለገው የምርትና ምርታማነት ዕድገት ደረጃ መድረስ አልተቻለም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ በገጠር የሚኖር እና መተዳደሪያውም ግብርና መሆኑ፣ የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ጥገኛ የሆነው ከግብርናው ዘርፍ በሚገኙ ምርቶች ላይ እንዲሁም የግብርናው ዘርፍ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ቀዳሚ የነበረ ከመሆኑ አኳያ የተለየ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የተለያዩ ባለሙያዎች ሲገልፁ ይሰማል፡፡
ይሁንና የመንግስት ተሳትፎ የግሉን ዘርፍ ሚና መተካቱ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አለመስፋፋትና ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አለመቻል፣ ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋማዊ ድጋፍ ማነስ፣ የግብርናና ገጠር ልማት ተኮር የሆነ የፋይናንስና ብድር አቅርቦት አለመኖር፣ እንዲሁም የአካባቢና ሰነ ምህዳር መሸርሸር ለአገሪቱ ግብርና እድገት ማነቆ ሆነው ከቆዩ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
የዘርፉ ምሁራን እንደሚያስገዝቡት፣ ለአንድ አገር የግብርና እድገት የመስኖ መሰረተ ልማት፣ የተሻሻለ ግብአት፥ ምርጥ ዘር፥ ማዳበሪያ፥ አረም ማጥፊያ፣ የምርት ገበያ፣ መሬት፣ ጉልበት፣ እውቀት፣ የገጠር መንገድ፣ የአርብቶ እና አርሶ አደሮች ትምህርት፣ የሃይል አቅርቦት፣ ሰላምና ደህንነት የግድ ይላል፡፡ በተለይም የመንግስት ከኢንቨስትመንቶች ባሻገር የግሉም ዘርፉ ተሳትፎ ለዘርፉ ምርት እና ምርታማነት መጎልበት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርናው የኢኮኖሚው ዋልታ ሆኖ እንዲቀጥል የልማት ቀጠናዎችን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት መከተል እና ሌሎች በግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ እንደሆነ ሙያተኞች ይመክራሉ። በተመሳሳይ የግል ባለሀብቱ በግብርና ልማት ላይ የሚኖረው ድርሻ ከፍ እንዲል በማድረግ አገሪቱ ለያዘችው ልማትና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ የሚናገሩት አፅእኖት ሰጥተው ነው፡፡
ኢትዮጵያን በግብርና ዘርፍ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጓት ምቹ ዕድሎች አላት፡፡ በሰሊጥ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ በእንስሳት መኖ እና በዶሮ እርባታ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም አላት፡፡ በአሁን ወቅት በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ አገራት ባለሃብቶች እየተሳተፉ ናቸው፡፡ ይሑን ሃገሪቱ መልማት ከሚችለው መሬት አንድ ስድስተኛውን ብቻ እየተጠቀመች በመሆኑ ምርታማነትን ለመጨመር የግሉን ዘርፍ በስፋት ማካተት የግድ ይላል ፡፡
በተለይ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተዳምሮ በምግብ ራስን ከመቻል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት የሚገባት ወቅት ላይ እንደምትገኝ የሚያስገነዝቡም በርካቶች ናቸው፡፡ በአሁን ወቅት በመንግስት የተጀመሩ የበቃ መስኖ ልማቶችም ይሕን ስጋት የማቃለል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ይበልጥ ሊሰፉ እንደሚገባቸው ይጠቁማሉል፡፡ በግብርናው ምርት እና ምርታማነት ለማጎልበትም ከሌሎች የማሻሻያ ተግባራት በተጓዳኝ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባም ያሰምሩበታል፡፡
የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክቡር ገና እንደሚያስረዱት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ግብርናው የኢኮኖሚ መሰረት መሆን አለበት፡፡ ማንኛውም ኢንዱስትሪም የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ ያደረገ ነው፡፡ ይሕ እንደመሆኑም ከሁሉ በፊት ግብርናው ላይ የሚተገበሩ ኢንቨስትመንቶች ከሁሉ በላይ ለአገሪቱ ጠቃሚ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ክቡር ገለፃ፣ የግብርና ኢንቨስትመንት ምእራባውያንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የተለየ የስትራቴጂ ትኩረት የሚሰጠው እና የመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ የሚቀርብለት ዘርፍ ነው፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራው በራሱ ቀላል አይደለም፡፡ ትልቅ ኢንቨስትመንት እና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ኢንቨስትመንት ተገቢው ትኩረት የተሰጠው ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የተሰሩ ስራዎች እጅግ ደካማ ናቸው፡፡ በእርግጥ የመንግስት እርሻ ልማት ተብለው በከፍተኛ መጠነ ሰፊ መሬት ላይ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ይሁንና ባለፉት አስራ አምስት እና ሃያ አመታት እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የሚፈለገው ያህል አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፡፡ ብዙውን ጊዜ ትርፍ አላመጡም እየተባለ እንዲቀነስ ወይንም ወደ ግል እንዲዘዋወሩ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
የግሉ ዘርፍ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሳትፎም ቢሆን አለ ከሚባል ይልቅ የለም ለመባል የፈጠነ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ክቡር፣ የግሉ ዘርፍ በዘርፉ እንዲሳተፍ የማይከለከል ቢሆንም የሚፈለገው ያሕል ተሳትፎ ማድረግ ግን እንዳልቻለ እና መግባት ያልቻለውም ከአቅም ውስንነት ብሎም በመንግስት በኩል የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
የአገሪቱ የኢንዱስትሪ አሰራር የተመሰረተው በተናጥል፣ ተያያዥነት በሌላቸው ስራዎች ላይ ነው፡፡ እዚህ ጋር ጠርሙስ ፋብሪካ ከተስተዋለ ከፍ ሲል ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አለ፡፡ እርሻ ላይ መሰረት አድርጎ መስራት ቢቻል እነዚህን እርስ በእርስ ማያያዝ ያስችላል፡፡
‹‹ዛሬም ላይ ቢሆን ወተት ከውጭ የሚመጣበት ሁኔታ ይስተዋላል›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ይሑንና ለግብርና በምትመች አገር መሰል ታሪክ መለወጥ የግድ ያስፈልጋል። በአሁን ወቅት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ መጠናከር ብሎም የግሉን ዘርፍ አቅም መገንባት እና በሁሉ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባና ኢንዱስትሪዎቹም በማበረታታት አብረው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
‹‹የአገሪቱን የወደፊት የግብርና ኢንዱስትሪ ብሎም ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የሚያስችል በተለይ ጥራትና እውቀት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ የገበያ ስራ መስራት ከተቻለ ዘርፉ መልካም ውጤት ለማስመልከት የሚቸገር አይደለም›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ዘርፉም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኢንቨስተሮች እንዲሁም በመንግስት ድጋፍ እና ቅንጅት ሊሰራበት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት፡፡
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር የሆኑት ፍሬዘር ጥላሁን፣ ለየትኛው አገር ልማት እና ብልፅግና የግብርና ኢኮኖሚ እጅግ ወሳኝ መሰረት መሆኑን በመጠቆም፣‹‹ግብርናው ትኩረት የሚነፈገው እና ከዚህ በኋላ ስለ ግብርናው ማንሳት የለብንም የሚባልበት ደረጃም የለም››ይላሉ፡፡
የትኛውም አይነት ኢንዱስትሪም ሆነ አገልግሎት ከግብርናው ውጪ ሊንቀሳቀስ እንደማይችልና ግብርናው ከሌለ ኢንዱስትሪውም ሆነ አገልግሎት ዘርፉ ውጤታማ የሚሆንበት መንገድ እንደሌለ የሚያስገነዝቡት አቶ ፍሬዘር፣‹‹ ግብርናን የዘነጋ እና ግብርና አያስፈልግም የሚል መንግስት በአለም ደረጃም የለም፤ ሊኖርም አይችልም›› ይላሉ፡፡
አሁን ባለንበት የኢኮኖሚ ደረጃ ለግብርናው ምን ያክል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚለው ሁሉም ሊያስብበት የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ፍሬዘር፣ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን ይምራው የሚለው የማያከራክር ቢሆንም ግብርናው የኢንዱስትሪው ደጀን መሆኑ ሊዘነጋ የሚገባው እንዳልሆነ አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለፃ፣ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን ይምራ ማለት ከፍተኛው ድርሻ ይውሰድ ማለት እንጂ ግብርናውን አያስፈልግም፤ ግብርናን ዜሮ እናድርገው ማለት አይደለም፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚሆን ኢኮኖሚ መኖር
የለብትም፡፡ ለአብነትም የዩናይትድ እስቴትስ ዜጋ ሁለት በመቶ በግብርና ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ይሑንና 70 በመቶውን የአገሪቱን ኢንዱስትሪ የሚደግፈው የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡
‹‹በጣም የተበጣጠሰን እና ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ አሁን ባለበት ሁኔታ መቀጠል የለበትም። ምርት እና ምርታማነቱ ማደግ አለበት፣ በዘመናዊነትም አብሮ መራመድ አለበት›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፣ የግብርናው ዘርፍ ላይ የግሉ ዘርፍ ደካማ ተሳትፎ መለወጥ እንዳለበት እና በተለይም ገበያን ትኩረት ያደረገ እና ለኢንዱስትሪው ግብአት የሚውል ኢንቨስትመንት ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው
ያስገነዝባሉ፡፡ መንግስት ለግሉ ዘርፍ የሚገባውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ መግባት የሚኖርበትን ዘርፎች እየመረጠ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አገር በሁሉም ረገድ ለመበልፀግ ከተፈለገ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ተሳትፎ እና ኢንቨስመንት እምርታ ቢያሳይ እንኳን ብቻውን ብዙ ርቀት መጓዝ የማይችል መሆኑን ያመላከቱት አቶ ፍሬዘር፣ ለግብርና ዘርፍ የሚሰጠው ትኩረት ከኢንዱስትሪ ጋር አብሮ የሚሮጥ እና መከታተል ያለበት ሊሆን እንደሚገባና በዚህ ሂደት ውስጥም ግብርናው መታደስ እና መዘመን ይገባዋል›› ነው ያሉት፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚጠቁሙት ከሆነም በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ከማበረታታት ባሻገር ዘርፉ ውስጥ ላሉትም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ በተለይ የሰላምን ደህንነት ጥበቃ ስራዎች ንብረታቸውን እንዳይወድም ዋስትና እና አስፈላጊው የቴክኖሊጂ ብሎም የፋይናንስ ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም