ሀገር ግንባታ ወይም ሀገር የመገንባት ተግባርና ሂደት እንዲህ በየመድረኩ እንደሚወራው፤ በየገፁ እንደሚፃፈው የዋዛ ሥራ አይደለም፤ ወይም ሰነፍ (ከመሪ እስከ ተመሪ ያለውም ቢሆን) እሚሞክረው አይሆንም፤ ወይም የነሸጠው ሁሉ ብድግ ብሎ ካላደረኩህ የሚለው የአቦ ሰጡኝ ሥራ አይደለም። በመንደር ጎረምሳም አይሆንም። በነውጠኞችም አይታሰብም። ባጭሩ ሀገር የመገንባት ሥራ ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ፤ ትጉሀንን የግድ የሚል፤ አገራዊና ህዝባዊ የሆነ የባለ ራእዮች ተግባር ነው።
ዘመን የራሱ ቋንቋ አለው እንደሚባለው በአሁኑ ዘመን ብርቅዬና ድንቅዬ፤ በቃላት ገበያ ላይ ከፍተኛ ከረንሲን እያስገኙ ካሉት ቃላት አንዱ “ሀገር ግንባታ” (በባህር ማዶ ስሙ Nation-building) ሲሆን፤ መሰረተ ልማት ግንባታ፤ ሰላም ግንባታ፣ ትውልድ ግንባታ ወዘተ የቅርብ ባልደረቦቹ ሲሆኑ፤ በተለይም “ሀገረ መንግሥት ግንባታ” (State Building) የሚለው የቤተሰብ አባሉና አገርን ወደ ፊት ከማስቀጠሉና ከመከራ ከማሻገሩ አኳያ የሥራ ባልደረባው ነው።
በመጀመሪያ የርእሰ ጉዳያችን አቢይ ጭብጥ ወደ ሆነው “ሀገር ግንባታ” ከመሄዳችን በፊት ከዚሁ ፅንሰ ሀሳብ ጋር ጎን ለጎን፤ ሲያስፈልገውም በአቻነት እየመጣ (ጥቅም ላይ እየዋለ) ለራሱም ለሌላውም ሳይሆን ሁሉንም የሚያደበዝዘውን፤ ልክ እንደ “ብሄር”፣ “ብሄረሰብ”፣” ህዝብ(ኦች)” ወዘተ ተገቢውን ብያኔና ስፍራ ያጣውን “መንግሥት ምስረታ”ን ከ”ሀገረ መንግሥት ግንባታ” ለጠቅላላ እውቀት ያህል በልዩነት እንመልከት።
አሁን የዘመናችን ትልቁ ችግርና ቁልፉ ጥያቄ “እንዴት እነዚህ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አገራት (በተለይ ባደጉቱ) ካልሆነ በስተቀር ዛሬ ላይ በጠቅላላ ምድራችን የመነጋገሪያ ቋንቋ ሊሆኑ ቻሉ?” የሚለው ሲሆን፤ መልሱም የገባው ለአላማው፣ ያልገባውም ለመምሰል ሲል እየተዋሰው ያለ ቦታና አውዱ (ልክ ማርክሲዝምን ሳይረዱት ወደ ተግባር ይዘውት እንደገቡት አይነቶቹ ማለት ነው።) በማስገባታቸው ነው ማለት እማይቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም። ባይሆንማ ለምን በአንድ የፓርቲ አባላት መካከል ሳይቀር መግባባት ላይ አይደረስባቸውም? ለምንስ በአንድ ፓርቲ ሰነድ(ኦች) ላይ እንኳን አንድ መሆኑ ይቅርና ተቀራራቢ ብያኔን እንኳን አግኝተው አልተሰደሩም? ሀሳቡን አፈለቅን ባሉት ወገኖች ሁሉ ሳይቀር ለምን የጋራ መግባባት ላይ አልተደረሰባቸውም? ብዙ ብዙ ጥያቄዎች አሉን።
“ሀገረ መንግሥት ግንባታ” ሲባል “state building”ን የሚለውን በአቻነት የሚወስድ፤ አለያም ለዚሁ እንግሊዝኛ ሀረግ በአቻነት የተሰጠ ሲሆን፤ “ሀገር ግንባታ” (የአማራ ብልፅግና ጽ/ቤት “ብሔረ-ሀገር ግንባታ” የሚለው ሲሆን፤ ትርጓሜውንም “ብሔረ-ሀገር ማለት አንድ አገርና ህዝብ በጣምራ የሚገለፁበት ስያሜ ነው።” ይለዋል።) በበኩሉ ለ”nation-building” በአቻነት የተቀመጠ ጽንሰ ሀሳብ ነው።
እርግጥ ነው፤ “ሀገር ግንባታ” እና “ሀገረ መንግሥት ግንባታ” ቢዛመዱ አይገርምም። የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ቢባልም ያንን ያህል የጎላ ክፍተትን አይፈጥርም። ጠቅለል አድርጎ ለመግለፅ ከተፈለገ ግን በአሁኑ፣ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ፣ በዚህ የሰዎች ፍላጎት ከዘመኑ ቀድሞ በሄደበት ዘመን፣ ለአንድ አገር ወደ ፊት መራመድ ሁለቱም የግድ አስፈላጊዎች ሲሆኑ ከነቢብነትም ባለፈ በተግባር ወደ መሬት ሊወርዱና እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ሊቀርፉ ይገባል። ይህ ደግሞ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ ግዴታ ነው።
ይህ የ”ሀገር ግንባታ” (nation-building) ጉዳይ ሲነሳ የመነሻ ዘመኑ ወደ ኋላ የሚሄድ ሲሆን ባልደራሱም “ሀገረ መንግሥት ግንባታ” (“ምስረታ”ም የሚሉት አሉ) ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው።
በ1928፣ እጅግ ዘመናዊውና ኒው ዮርክ የሚገኘው ዋልዶርፍ ኦስቶሪያ ሆቴል (Waldorf Astoria Hotel) በ20 ሚሊዮን ፓውንድ ለቤተልሄም ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (Bethlehem Engineering Corporation) ተሸጠ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላም የዓለማችን እጅግ የተጋነነ ህንፃ ተባለና እንዲፈርስና ተመልሶ እንዲገነባ ተወሰነ፤ ግንባታውም መጋቢት 17 ተጀመረ። መልሶ ግንባታውም “ዘ ኢምፓዬር ስቴት ቢውልዲንግ” (the Empire State Building) የሚል ስያሜ ተሰጠው። ህንፃውም ባለ 102 ፎቅ (102-story building) ዓለምን ጉድ ባሰኘ ሁኔታ በ1 ዓመት ከ42 ቀኑ ተጠናቀቀ። ግንቦት 1፣ ፕሬዚዳንት ሁቨር በዋሽንግተን ተገኝተው መረቁት። ይህም በታሪክ “ፕሬዚዳንት ሁቨር በዋሺንግተን የተገነባውን የመንግሥትን ህንፃ ከፍተው የህንፃውንም መብራቶች ለመጀመሪያ ጊዜ አብርተው መርቀዋል” (President Hoover presses a button in Washington, D.C., officially opening the building and turning on the Empire State Building’s lights for the very first time.) ተብሎ የተመዘገበላቸው ሲሆን “ዘ ኢምፓዬር ስቴት ቢውልዲንግ”ም አንዱ የ”ሀገረ መንግሥት ግንባታ” አይነት ሆኖ በሥራ ላይ ይገኛል። (ስያሜውን “ኪነ ህንፃ ለፖለቲካ ፍልስፍና የዋለው ውለታ” ልንለው እንችላለን።) “City State” እና ሌሎች የState Building አይነቶችንም በዚሁ አይነት መመርመርና ለይቶ መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የአብዮቱ መሪዎች ህዝቡን አንድ (homogenization) ለማድረግ እየጣሩ ባሉበት ወቅት የተጠቀሙበት አገላለፅ “to form French citizens” የሚል የነበረ ሲሆን በሂደትም “ሀገረ መንግሥት ግንባታ” ገፅታንና ትርጉምን እየተላበሰ መጥቶ ዛሬ “nation-building” በሚል ዓለም አውቆት ለተግባራዊነቱም እየጣረ ይገኛል። እዚህም እየሆነ ያለው ይሄው ነው።
የጄምስ ዴቢንስና ሌሎች (2003) ጥናት በበኩሉ ከጦርነት በኋላ እንዴት ወደ ሀገር ግንባታ ተግባር መግባት እንደሚቻልና ውጤታማም ለመሆን እንደሚበቃ “the use of armed force in the aftermath of a conflict to underpin (ለመገንባት) an enduring (ዘላቂ) transition to democracy.” በማለት “nation-building”ን ከበየነ በኋላ በማስረጃነትም ሰባት ታሪካዊ ክስተቶችን (cases) ያስቀምጣል። ኬዞቹም በጀርመን፣ ጃፓን፣ ሶማሊያ፣ ሀይቲ፣ ቦስኒያ፣ ኮሶቮ እና አፍጋኒስታን የተከሰቱ ሲሆኑ፤ የአሜሪካ ጦር ኃይል በእነዚህ አገራት ላይ በወሰደችው ርምጃ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነች “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዴሞክራሲን ለመገንባት የአሜሪካ ወታደር ጥቅም ላይ ውሏል” በማለት ጥናቱ ያስቀምጣል።
ሀገር ግንባታ ወይም ሀገር መገንባት ይህንን ያህል አስፈላጊ ከሆነ እንዴት ይደረግ፣ ምንስ ይደረግ የሚሉት ጥያቄዎች መሰረታዊ ሆነው ይመጣሉ። ለዚህ ፈጣን ምላሽ ለማግኘት ወደ ኪነጥበቡና ሥነፅሁፉ ዘርፍና ባለሙያዎቹ (ለሀገር ግንባታና ገፅታ ግንባታ፤ ህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ሚና ልብ ይሏል) ጎራ ማለት ተገቢ ነው።
ወደ ሥነፅሁፉ ዘርፍ ስንመጣ አዳም ረታን ሲሆን በ”ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሀገር ግንባታ” ጥናታዊ ፅሁፉ፤ “የባህል ጭቆና (Cultural Dominance) ጣጣ ሆኖባቸው አይደለም። ወይንም ሰፊ የሆነ አንባቢ ፍለጋ አይደለም። እነዚህ ከያኒያን በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ጥሩ አድርገው ይጽፋሉ። በነዚያ ቋንቋዎች ቢጽፉ ሰፊ የሆነ አንባቢ ማግኘት ይችሉ ነበር። ግን አላደረጉትም። በነዚህ ሰዎች አማካኝነት የአማርኛ ስነ ፅሁፍ የኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ መሆን አይችልም ወይ? የብሔርተኝነት ጉዳይ የቋንቋ ጉዳይ ነው ካልን፤ እዛ ውስጥ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት የለም ወይ? እሱን ሳናነብ ሀገር መገንባት እንችላለን? ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (Ethiopian Nationalism)ን ለመገንባት ፖፕ ካልቸር፣ ስነፅሁፋዊ ጥበብ (pop culture, literary art) እና ሌላውም የጥበብ ሥራ መስራት አለበት። በፖለቲካ ዲስኩር መስራት አይቻልም። ፖለቲካ ሊሰራ የሚችለው ሀሳብን በሃሳብ ማስረዳት ነው። ጥበብ ግን ሃሳብን ፈርክሶ፣ ቀለም እና ቅርጽ ኖሮት ሰው እንዲኖርበት አድርጎ ነው የሚሰራው።” በማለት አስነብቦ አናገኘዋለን።
በእርግጥ “ሀገር ግንባታ”ን በቀዳሚና አቢይ አጀንዳነት መያዝ ለሁሉም፤ በአጠቃላይ ለዓለማችን ወሳኝና ተገቢ ነው። በተለይ ወደ አፍሪካ ስንመጣ የበለጠ አንገብጋቢ ሆኖ ነው የምናገኘው። ሁሉም ተከፍቻለሁ፤ ሁሉም ተበድያለሁ፤ ሁሉም ተጨቁኛለሁ ወዘተ በሚልበትና እየዞረ እየተዟዟረ ወደ ጦርነት በሚገባበት አፍሪካ (ደቡብ ሱዳን በተገነጠለ በሁለት ዓመቱ ተመልሶ ወደ ከፋ ጦርነት ከገባ 10ኛ ዓመቱን መያዙን ልብ ይሏል) ለሀገር ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ቅድሚያ የሥራ እንኳን መሆኑ ቢያቅት የውይይት አጀንዳ ማድረጉ ምንም ስህተት የለውም።
ብዙዎች እንደሚሉት በአፍሪካ የሀገር ግንባታም ሆነ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በፖለቲካዊ ስህተቶች የተሞላ ሲሆን፤ እሱም አካሄዱ፣ አተገባበሩ፣ ዘዴና ብልሀቱ የተለያየ መሆኑ ሲሆን፤ አንዱ “አፍርሰን እንደ አዲስ” ሲል ሌላው “የተሻለውን ይዘን የማያስኬደውን ትተን “ሀገር መገንባት”፤ ከዛም “ሀገረ መንግሥት መመስረት” እንችላለን ይላል። በመሀላቸው ያለው ልዩነት ከገደል የሰፋ ነው። እንኳን ለመቀራረብ ለመተያየት እንኳን የሚፈልጉ አይደሉም። ምርጫቸው ከመወያየት መዋጋት ነው። ለዚህ ደግሞ ከላይ እንዳልነው ቅርባችን ካለችው ደቡብ ሱዳን በላይ ማሳያ የለም። ሪክ ማቻርንና ሳልቫ ኪርን የመሰለ ምሳሌ ደግሞ ከየትም ማምጣት አይቻልም። ሁለቱም ለህዝባችን ባይ መሆናቸው ደግሞ የ”ህዝብ” ትርጉም እስኪጠፋ ድረስ ያደናግረናልና የአሁኗ ዓለማችን የእንደነዚህ አይነቶቹ ቅጥ ያጡ ትያትሮች መድረክ ነች። “የዚህ ሁሉ ችግር ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ፤ ወይም ብናነሳ ትክክል ይሆናል። ሰላም ግንባታ (ፒስ ቢውልዲንግ)፣ ሀገር ግንባታ፣ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወዘተረፈ እዚህ ጋር ቢመጡ ምንም የሚገርም ነገር የለውምና “መደመር”ን በቀዳሚ መፍትሄነት መውሰድ አይጎዳም።
እንደ የዓለም የኢኮኖሚ መድረክ (WEF) የአሁንና የሚቀጥሉት ዓመታት የዓለማችን ቁልፍ ችግሮች፤ ወይም የተጋረጡባት አደጋዎች በማለት በ2016 በራሱ ልክ ኢኮኖሚን ማዕከል ያደረገ (economy-centered view) በሆነ አተያይ የዘረዘራቸው ነጥቦች በርካቶች ሲሆኑ አስሩ መሳጭ ነጥቦች ያላቸው በማለት የገለፃቸው የምግብ ዋስትና፤ ሁሉን አካታች ልማት አለመኖር፤ ከፍተኛ የስራ አጥነት፤ የአየር ንብረት ለውጥ፤ የፋይናንስ ቀውስ፤ እየተራቀቀ የመጣው የኢንተርኔት አገልግሎት (“አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት” (Fourth Industrial Revolution) ብለውታል)፤ የስርአተ ፆታ እኩልነት፤ አለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት እና የቁጥጥር ማእቀፍ፤ የረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት እቅድ ስትራቴጂ ሲሆኑ በ10ኛ ደረጃም የማህበረሰብ የጤና አገልግሎትን ያስቀምጣል። የዚህ ጽሑፍ ጥያቄ አፍሪካም (በተራዛሚው እኛም) የዓለም አካል ናትና እነዚህ ችግሮች ባሉበት (ጭራሽም የተሰሩት ሁሉ እየወደሙ ባሉበት) እንዴት አድርጎ ሀገረ መንግሥትን መገንባት ይቻላል? የሚል ሲሆን፤ ፎረሙንም አብዝቶ ያሳሰበው ይሄው ከመሆኑ አኳያ መንግሥታት እንዲያስቡበት አሳስቧል፤ ምክረ ሀሳቡንም ሳይሰስት አካፍሏል።
በተለይ ፎረሙ የአፍሪካን ችግሮች ድህነት፣ በሽታ፣ በረሀማነት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የአካባቢ ግጭቶች እና ሌሎችን ለይቶ ያመልከተ ሲሆን አህጉሪቱ ከእነዚህ አዘቅቶች ውስጥ ለመውጣት ምን ያህል እየሰራች፤ እየተሳካላት ነው? የሚለው በራሱ ግዙፍ ጥያቄ ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠው አጀንዳ 2063 ይፈታዋል/አትይፈታውም የሚለው ጥያቄ እንደላይኛው ሁሉ የባለሙያን ትንታኔ የሚሻ ነውና ወደ እነሱው ገፍተነው እናልፋለን።
በህንድ ሀገር ሀገረ መንግሥትን ለመመስረት በርካታ ውጣ ውረዶች የታለፉ ሲሆን የሰላም፣ አንድነት ሀይሎች፣ ባለ ራእይ መሪዎች በከፈሉት ከፍተኛ መስዋእትነት የዛሬዋ ህንድ ልትኖር ችላለች። ፓሪስም ትምህርትን የሀገር ምስረታ/ግንባታ ከማስረፅም ባለፈ የተግባሩ ማስፈፀሚያ በማድረጓ ውጤታማ ሆናለች። ሌሎችም ብዙ አሉ። እኛስ? ጥያቄው ይሄ ነው!!!
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የተስማማባቸውና ለአገርም ይሁን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚጠቅሙ ምን ምን ጉዳዮች እንዳሉ በብዙዎች ይታወቃል። በተፈጥሮ፣ በባህል፣ በመንፈስ፣ በሰው ሰራሽ፣ በታሪካችን፣ በጥንታዊ አገርነታችን . . . ሁሉም ያውቀናል። እናስ??
125ኛውን የአድዋ የድል በዓል ለመዘከር በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ባዘጋጀው የዙም የኢንተርኔት የውይይት መርሀ ግብር ላይ የክብር እንግዳ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል አቶ ፈቃዱ በየነ “ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ጉልህ ድርሻ ያለውና የአንድነታችን ስኬት የሆነው ይህ ዓለም ሁሉ የሚዘክረው ታሪካዊ ድል ላለፉት 84 ዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል” ማለታቸውን እዚህ ላይ መጥቀስና በእግረ መንገድም “ሌሎቹስ ውለዋል?” የሚል ጥያቄን (ለእሳቸው አይደለም) አንስቶ ማለፍ ተገቢ ነው።
አዳም ረታም ከላይ በጠቀስንለት ሥራው “የኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ቀኖና (Literary Canon) ብንሰራ” ተገቢ መሆኑን በጥቅስ መልክ ብንጠቅስለት ተገቢ ቦታው ይሆናል ብለን እናስባለን። “እንደ አደጉት አገራት ሁሉ እዚህም የአንድ ወገን የፖለቲካ የበላይነት፣ ተረኝነት … ሊቀር ይገባዋል። እሱ ካልቀረ እንዲሁ ሲባሉ መኖር ነው” የሚሉትም ድምፅ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፤ ከነማስደንገጡም ቢሆን ሊታሰብበት ይገባል።
“ሀገር ግንባታ” ማለት የመንግሥትን ኃይል (ስልጣን፣ መዋቅር፣ ተቋማት፣ በጀት ወዘተ) በመጠቀም በአንድ አገር ውስጥ አንድ አይነት አገራዊ ስሜትና ማንነት ያለው ህዝብ ለመፍጠር የሚደረግ ተግባር ሲሆን፤ አላማውም በዛ አገር የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ፤ ግን ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ የተለያዩ የባህል እሴት ያላቸውን ወዘተ ዜጎች ወደ አንድ አገር ዜግነት በማሰባሰብ በአንዲት ሉአላዊት አገር ጥላ ስር በማሰባሰብ፤ የጋራ ማንነትን በመፍጠር፤ ከሁከትና ብጥብጥ የፀዳ፣ የተረጋጋ (ያልሰከረ፣ አቅሉን ያልሳተ …) ፖለቲካ ድባብ፣ በሂደትም የተዋሀደ ህብረተሰብ (ዜጋ)ና የተዋሃደ ማንነት መፍጠር ነው።
አንድ ሰሞን “በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በአዋጅ መታገድ አለበት።” የሚል አስተያየት ጎልቶ መውጣቱና በሚዲያ ሳይቀር አጀንዳ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። አስተያየት ሰጪዎቹ ወደው አይደለም፤ ወይም ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠልተው አይደለም። ለዚህ አስተያየት ያበቃቸው የሚያዩት፣ የሚሰሙትና በዕለት ዕለት የሚኖሩት ህይወታቸው ሲሆን ይህም ለሚባለው ሀገር ግንባታም ይሁን ሀገር መንግሥት ግንባታ እንዲሁም ሰላም ግንባታ ከማደናቀፍ ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳን ስለማያመጣ ነው።
ባጭሩ፣ ከክፍለ ዘመኑ ፍላጎት አንፃር፣ ከብዝሀነታችን አኳያ ወዘተ … ሀገር የመገንባቱ ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለምና ሁሉም ታጥቆ ሊነሳ ይገባል።
ዛሬ ሀገር ግንባታን (Nation Building) በዚህ መልኩ ካየን፤ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ስለ ሀገር መንግሥት ግንባታ (State Building) በሰፊው ለማየትና ለመተንተን እንሞክራለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013