
በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እጅግ ፈጣን ዕድገት ከሚያሳዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በአሁኑ ወቅትም ዘርፉን የተቀላቀሉ እና ለመቀላቀል እተንደረደሩ የሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች አሉ። እነዚህ ኩባንያዎችም ያለቁ እና ያላለቁ የተለያዩ የቆዳ ምርቶችን ለውጭ ንግድ እና ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ዘርፉም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ባላት የቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ ብትይዝም ከቆዳ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም። አገሪቱ ከኢንዱስትሪው በዓመት እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ትልቅ አቅም ቢኖራትም በዚህ መጠን ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። ከ100 ሚሊዮን ዶላር የተሻገረ ገቢን ማግኘትም አልሆነላትም።
በርግጥ ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን ወደተለያዩ አገራት የምታቀርባቸው የቆዳ ምርቶች ከቁጥር አንፃር ዕድገትን ቢያመለክቱም ኢንዱስትሪው የተበተቡ ችግሮች በአንፃሩ ተዋናዮችም ሆነ አገሪቱ ማግኘት የሚገባቸውን እንዳያገኙ ከፍተኛ ማነቆ ሲሆን ይስተዋላል።
በዘርፉ የተሠማሩ አምራቾች እና ባለሃብቶች የማምረቻ ቦታ እጥረት፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ ኬሚካል አቅርቦት ችግር፣ ከጉምሩክ አሠራር ጋር በተያያዘ እና የሃይል አቅርቦት ተግዳሮቶች በእጅጉ እንደሚፈተኑ ሲገልጽ ቆይቷል።
የሞደርን ዘጌ የቆዳ ውጤቶች ድርጅት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አሥኪያጅ አቶ በቀለ ገብረሕይወት እንደሚገልፁት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቆዳ ኢንዱስትሪ የገበያ ችግር የሌለበት እና በውጭ ንግዱ ተሣትፎም በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝ ይገለፃል። የቆዳው ዘርፍ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ችግር ገበያ ሣይሆን የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ በመሆኑ ምርት እና ምርታማነትን በመቀነስ እንደ አገር የዘርፉን ሕልውና ክፉኛ እየተገዳደሩት ነው። ከቆዳ ኢንዱትሪ አብዛኞቹ ጥሬ ዕቃዎች በአገር ውስጥ አይመረቱም። በተለይ የኬሚካል እጥረት የቆዳ ምርት እንዲጠፋ ያደርጋል። እጥረት ሲከሰት ደግሞ አምራቾች ለማምረት የሚቸገሩ መሆናቸውን አቶ በቀለ ይናገራሉ።
ጥሬ ቆዳ ከአርብቶ አደሩም ሆነ ከቄራዎች ድርጅት ይሰበሰባል። ይሁንና የሚሰበሰው ቆዳ ወደ ምርት የሚሸጋገረው በኬሚካል ቢሆንም የኬሚካል ችግር አለ። ኬሚካሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሚመጡት ከውጭ አገራት ነው። ኬሚካሎቹን ለመግዛት ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ይጠይቃል። ይሁንና የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሉ፣ ጥሬ ቆዳ ወደ ምርት ተቀይሮ ከገበያ እንዳይቀርብ ያደርገዋል።
ማጣበቂያ (ማስቲሽን) እና የሦል ኬሚካሎችን ጨምሮ ሌሎችም ግብዓቶች አገር ውስጥ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ በቀለ ለምርቱ ግብዓት የሚሆኑ የዕቃ አቅርቦቶች ገበያ ወጥተው ለመግዛት ሣይቀር መቸገራቸውን ድርጅታቸው ለተማሪዎች የሚያቀርበው ጫማ ላይ ከባድ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበርም ነው ያስታወሱት። ችግሩን መንግሥት ትልቅ ሀላፊነት ወስዶ የሚሰራቸው መሠል ትልቅ ፕሮጀክት ሣይቀር እየፈታ መሆኑን ሣይጠቅሱ አላለፉም።
የውጭ ንግድ በሁሉ ነገር ተዘጋጅቶ መጠበቅን የግድ እንደሚልና ይህ ካልሆነ ምርትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያዳግት የሚያስገነዝቡት አቶ በቀለ ዘርፉ ላይ የተደቀኑ ችግሮች በአንፃሩ የውጭ ትዕዛዞችን በታቀደው የጊዜ ሠሌዳ ተደራሽ እንዳይሆኑ ሁነኛ ማነቆ የሚፈጥር መሆናቸው ነው ያመላከቱት። ‹‹ችግሩም በቆዳው ኢንዱስትሪ እንደ አገር ማግኘት የሚቻለውን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚያሣጣ እንደሆኑ በልክ እና መጠኑ ሊታሰብ ይገባል›› ብለዋል።
ኢንዱስትሪውን ከውድቀት ለመታደግም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ በማህበርም ሆነ በተናጥል ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የሚገልጹት ሥራ አሥኪያጁ፣ ችግሩን ከመቀበል ባለፈ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ረጅም ጊዜ መውሰዱን ነው ያሣወቁት።
የአገርን ሁኔታ ታሣቢ በማድረግ ዋጋ እየተከፈለ በትግሥት መቆየት ቢቻልም መፍትሄዎች እየዘገዩ በሄዱ ቁጥር የሚያስከትሉት ጉዳት የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እና ኢንዱስትሪውን ወደ ሞት አፋፍ የሚወስዱ በመሆናቸውን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ፈጣን መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ሣይጠቁሙ አላለፉም።
መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ እስካልቻለ እንደ አገር ከባድ ኪሣራ የሚያስከትል መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ በቀለ የውጭ ድርጅቶች ካልተመቻቸው ጥለው የሚሄዱ በመሆኑ ሁሌም ከአገር ጎን የሚቆመውን የአገር ውስጥ ባለሃብትን ደግፎ ለማቆም ተገቢው ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።
በተለይ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ሥምምነት ወደ እንቅስቃሴ በሚገባበት ወቅት መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሃብቱን ደግፎ ማቆም ካልቻለ ገበያው በውጭ ባለሃብቶች የበላይነት ሥር እንዲወድቅ መልካም ዕድል ይፈጥራለ። ‹‹የአገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ ከወዲሁ እስካልተጀመረ ኢትዮጵያውያን አምራቾች መዝለቅ ያልቻሉትን ገበያ ሌሎች እንዲቆጣጠሩ ያደርጋልም›› ነው ያሉት።
በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ከ80 በመቶ በላይ የምርት ግብዓት ከውጭ የሚገባ መሆኑን የሚጠቁሙት የካንጋሮ ጫማ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ አቶ እዮብ አርጋው ይህን ያህል ግብዓት ከውጭ ለማስገባት መሥራት አለመቻል ደግሞ በተለይ በርካታ ቁጥር ያለው ሠራተኛ በሥራቸው ለሚያስተዳድሩ ፋብሪካዎች ከባድ ራስ ምታት መሆኑን ይገልፃሉ።
ቀደም ሲል ግብዓትን ከውጭ በማስገባት ሂደት ከታክስ ነፃ አሠራር ይተገበር ነበር፣ ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት እንዲቆም ሆኗል የሚሉት አቶ እዮብ በርካታ ባለሃብቶች ኢንዱስትሪውን ከመቀላቀል እንዲሸሹ የሚያደርጉት መሠል ችግሮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
መንግሥት ለውጭ ምንዛሬ እጥረትና የታክስ ጉዳዮች መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባው የሚገልፁት ምክትል ሥራ አስኪያጁ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ በሥራቸው የሚገኙ ፋብሪካዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ያስረዳሉ።
በቀጣይ 10 ዓመታትም ያሉትን ኢንዱስትሪዎች አቅም በማሣደግና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በወጪ ንግዱ አሣታፊ በማድረግ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን እስከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በዕቅዱ የመጨረሻ ዘመን ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል።
ባለሙያዎችም ሆነ በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች በቆዳው ኢንዱስትሪ እንደ አገር የተቀመጠው ዕቅድ እና ግብ እንዲሣካ ከሁሉ በላይ ዘርፉ ከሥራ ዕድል ፈጠራና የወጪ ንግድ ገቢን በማሣደግ ካለው አጠቃላይ አበርክቶት አንጻር ከወዲሁ የመንግሥትንም ሆነ የሌሎችን ባለድርሻ አካላትን ትኩረት እንደሚሻ ጥርጥር የላቸውም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013