
ከውጭ የሚገባውን የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ፍላጎትን ለመሸፈን ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ጥረቱ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ እና በዋጋም ሆነ በአቅርቦት የሚታየውን ቅሬታ መቅረፍ አልተቻለም፡፡
ያም ቢሆን ግን የዘይት ምርት ፍላጎት ጥያቄን ለመመለስ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች የተለያዩ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ረገድም የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ፌቤላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ግዙፍ የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በማቋቋም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ፌቤላ የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በምግብ ዘይት ፋብሪካ በአገሪቱ የሚታየውን እጥረት በመቅረፍ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፋብሪካው የዘይት ምርቶቹን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ሲሆን በርካቶችም የምርቱ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥና በፈሳሽ የምግብ ዘይት ንግድ ሥራ የተሰማሩት ቄስ ልሳኑ በላይ፤ እንዳሉት በሚኖሩበት አካባቢ ፋብሪካው ከመቋቋሙ በፊትም በአነስተኛ አምራቾች አቅርቦት በመኖሩ እንደሌሎች አካባቢዎች የጎላ ችግር አልነበረም። ሆኖም ግን በቅርቡ ይታይ የነበረውን እጥረት የፌቤላ ምርት ክፍተቱን በመጠኑም ቢሆን አርግቦታል፡፡
አዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ውስጥ ያገኘናቸው ወይዘሮ መሪማ አደም የፋብሪካው የዘይት ምርት በመርካቶ ገበያ ውስጥና በሌሎች አካባቢዎች በየመደብሩ ተደራሽ መሆኑን መመልከታቸውን ይገልፃሉ ። ወይዘሮ መሪማ ምርቱ ተደራሽ መሆን ደስተኛ ቢሆኑም በዋጋው ላይ ግን ቅሬታ አላቸው፡፡
ከፋብሪካ የሚወጣበት ዋጋ እና ገበያ ላይ የሚሸጥበት ዋጋ ተመጣጣኝ እንዳልሆነና የሚገልጹት ወይዘሮ መሪማ፣ መርካቶም ሆነ በየሰፈሩ ባሉ መደብሮች የምግብ ዘይቱ በችርቻሮ ተቀድቶ የሚሸጥበት ዋጋ በአንድ ሊትር ከውጪ ከሚገባው እኩል እስከ 130 ብር ሆኗል ነው ያሉት፡፡
የፋብሪካው ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ፋብሪካውን 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርገው ሲገነቡ ዋና ዓላማው የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎትን ለማሟላት እንደሆነ በማስታወስ ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ፣የምግብ ዘይት ምርቱ ከምርት ሂደት ማሟሻ ሙከራ ጊዜው ጀምሮ ከፋብሪካው እየወጣ የሚገኘው በአንድ ሊትር ስሌት በተተመነለት 42 ብር ሂሳብ ነው ። ምርቱ ከተመረተ በኋላ በጅምላ የሚቀርበውም ለመንግሥት የዘይት አከፋፋዮች ሲሆን ስርጭቱ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆነው የዋጋ ትመና በሚመለከተው የመንግስት አካል አማካኝነት ነው ።
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ማምረት በሚያስችለው አቅሙ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ ባይኖርም በሙከራ ጊዜው እያመረተ እንደሚገኝ የሚጠቁሙት አቶ በላይነህ፣ ይሕም ሆኖ የምግብ ዘይት አቅርቦት ላይ የተከሰቱ ችግር በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽ እያበረከተ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም አሁን ላይ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ማምረት የሚያስችለውን አቅም ተጠቅሞ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ የለም ። ወደ ፊት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ግን 22 ሚሊዮን 500 ሺህ የምግብ ዘይት ምርት በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብበት ሰፊ ዕድል ይኖረዋል።
እንዲሁም የሀገሪቱን ከውጪ የሚገባ የምግብ ዘይት ፍላጎት 60 በመቶ ያህል በመተካት የሚሸፍንበት ሁኔታ ይኖራል። በዚህም በአንድ በኩል እጥረቱን መፍታት በሌላ በኩል ዋጋውን ማረጋጋትና የተሻለ የምግብ ዘይት ምርት ተጠቃሚነትን ማጎልበት ይቻላል ።
ፋብሪካው የሰሊጥ ምርትን በተለያዩ ደረጃዎች አምርቶ ወደ ውጪ የሚልክ መሆኑና ከዚሁ ጎን ለጎንም ድፍድፍ ዘይት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑን መረጃው ያመለክታል ።
መንግሥት የምግብ ዘይት እጥረት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለይ ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካቱ ሥራ እንዲሰሩና ባለሀብቶችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ፍላጎት መኖሩ ይታወቃል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013