አባቶቻችን “መልካምነት መልሶ ይከፍላል” ይላሉ በጎ ማድረግ፣ ለተቸገረ መርዳት ለሚታገዘው ሳይሆን ለራስ ብድር ማቆየት መሆኑን ሲያስረዱ። ጥሩ በመዋል ውስጥ በምላሹ ቁሳዊ ምላሽን እንኳን ባናገኝበት የሚሰጠው የህሊና እረፍትና እርካታ ልዩ መሆኑን ከሳይንስ ሳይሆን ከነዚሁ አያት ቅድመ አያቶቻችን ተምረናል።
አርሶ አደሩ የራሱን እርሻ ብቻ አይከውንም፤ እርሻቸውን መከወን የማይችሉ አቅመ ደካሞችን፣ ችግረኞችን ያግዛል፡፡ ይህ በመሆኑም የአቅመ ደካሞች፣ ረዳት የሌላቸው አርሶ አደሮች ማሳ ጦም አያድርም፤ አዝመራቸው የሚያርመው የሚኮተኩተው የሚሰበስበው አያጣም፡፡ ህብረተሰቡ ሆ ብሎ ሁሉኑም ያደርጋል፡፡ ቤታቸው ሲያዘነብል ቀና ያደርጋል፤ ሲያፈስ ይደፍናል፡፡ እንዴት አደራችሁ እንዴት ዋላችሁ ይላቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ ማድረግ ሃላፊነቱ መሆኑን በሚገባ ይገነዛባል፡፡
በዚህ ተግባር ውስጥ ማንም ረጂ ማንም ደግሞ ተረጂ አይደለም። ይሄ ባህል፣ የመተባበር እና መደጋገፍ ባህል ነው። በመደጋገፍ ውስጥ ከሚገኝ ደስታ ሁሉም በጋራ ይቋደሳል። ትናንት በጎ የተዋለለት ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ ለሌላኛው ዋልታና ማገር ይሆናል። ይሄ በመስጠት ውስጥ የሚገኝ መቀበል የኢትዮጵያውያን ባህል ነው!
በዛሬው የጋዜጠኛው ቅኝት የቅዳሜ አምዳችን ላይ መልካም ስለማድረግ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። ዛሬ መልካም ያደረጉ እጆችን እያመሰገንን በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ቢደረግ ለማለት ስለወደድን እንጂ። እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “በበጎ ፍቃደኝነት” ያላቸውን ሳይሰስቱ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እጆቻቸው የሚፈታ እየበረከቱ መምጣቸውን እየተመለክትን ነው። በተለይ በዚህ ረገድ መንግስት ወጣቱን፣ ባለሀብቱን ለማነቃቃት፣ አገራቸውንና ወገናቸውን በነፃ ያለማቅማማት “የማገልገል” ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር ይበል ያሰኛል። መንግስትን ለማድነቅ የወደድኩት ተነሳሽነቱ በመንግስት በኩል የሆነ የበጎ ተግባር እያየሁ ስለሆነ ነው፡፡ ያው የሚመሰገን ሲገኝ በርቱ ማለት ህጸፅ ሲስተዋል ደግሞ ገንቢ ትችት መስጠትም ባህላችን ሊሆን ይገባል።
ለመሆኑ በጎ ፍቃደኛ ማን ነው?
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፅንሰ ሃሳብ ትርጓሜው እንደ ማህበረሰቡ የዕድገት ደረጃና ከባቢያዊ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ መረጃዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን “በዋነኛነት ሰዎች/ ግለሰቦች ከሰብዓዊነት አመለካከት ተነስተው ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት በነጻ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና በጐ አመለካከታቸውን የሚያውሉበት በምላሹም ትምህርትና የህይወት ልምድ እንዲቀስሙ የሚያስችላቸው ተግባር ነው” በማለት ይገልጹታል፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚሁ መከራው/ ችግሩ ሞልቶ በተረፈባት ምድር ላይ የምትገኝ ይልቁንም የችግር መዓት በተከማቸባት አህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ያለች በመሆኗ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጥብቅ ከሚሹ ሀገራት አንዷ ነች።
ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል ያላትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ የሚፈቱባት ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የሀገሪቱ ባህል ነው። ይህ ሲፈጸምበት የኖረ ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም አለ። ሲወልዱ “የግምዶ” ፣መከራ ሲደርስ “የዝን” ብሎ ከመስጠት ጀምሮ፣ ሲዘምቱ “የስንቅ”፣ ሲመለሱ “የደስታ” ፣ሲሾም “የምስራች”፣ ሲሻር “የሹመት አይደንግጥ”፣ወዘተ ብሎ እስከ መስጠትም የሚደርስ የመተባባር ባህል አለ።
ከምንም በላይ ግን ወርቃማ የነበረው ሲታመሙ የመጠየቂያ ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲወረስ፣ ሲቃጠልበት፣ ሲቀማ… እርጥባን ብሎ መስጠት የተለመደ ነበር። /ፍኖተ አእምሮ፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፤ 1953 ዓ.ም/ ለችግረኞች፣ ለአረጋውያን፣ ለእጓለ ማውታ ተሰብስቦ በደቦ ማረስ፣ መውቃት፣ ሰብስቦ ከጎተራ መክተቱ በግብርና ኖሮ እዚህ ዘመን ድረስ ለዘለቀው ማኅብረሰብ እንግዳ ነገር አልነበረም።
በበጎ ፍቃድ በጎ ጅማሮ
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቀድሞውኑም የነበረውን በነፃ “የማገልገል” ባህል ዛሬ ላይ ለማጠናከርና ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረጉ ስራዎች እየተመለከትን ነው። ወጣቱ መነቃቃት እየታየበት ነው። ጉልበቱን ገንዘቡን ሳይሰስት ድጋፍ ለሚሹት እየሰጠ ነው። መንግስትም በተለይ አገር ተረካቢው ትውልድ ይህን የቆየ መልካም ባህል አጠናክሮ እንዲቀጥል በርካታ ስራዎችን እየተሰራ ነው።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተግባር “በጎ የማድረግ” ትርጉም እየተመለከትን እንደሆነ ይሰማኛል። ለዚህ ደግሞ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በርካታ አቅመ ደካሞችን የሚደግፉ ማህበራትና ግለሰቦች እየተበራከቱ ናቸው። በተለያዩ ተቋማት እየተደገፉና በግል እየተሰባሰቡ እውቀትና ሃብታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡ እዚህም እዚያም እያየን ነው።
በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ ብንዘዋወር የትራፊክ እንቅስቃሴውን የሚያሳልጡ፣ ሰዎች አደጋ እንዳይደርስባቸው የሚጠብቁ በርካታ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሲያገለግሉ እንመለከታለን። አቅመ ደካሞችን በመንገድ ማቋረጫ /ዜብራዎች/ ላይ ከመኪና አደጋ እየጠበቁ የሚያሻግሩ፣ ፍሰቱን የሚቆጣጠሩና እግረኞችና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህጎችን እንዲያከብሩ የሚያደርጉት እነሱ ናቸው። ጉልበትና ጊዜያቸውን በነፃ መስጠታቸው እጅግ በርካታ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ያስችላል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ማህበራት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ አቅመ ደካሞችን እየጦሩ የሚገኙ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ መተባበርን በተግባር እያሳዩ ናቸው። አረጋዊያንን ከጎዳና እያነሱ ልብሳቸውን እያጠቡ፣ ምግባቸውን እያበሰሉ የመልካም ምግባር ምሳሌ ሆነዋል። ለዚህ ጠንከር ያለ ምሳሌ የሚሆነን የሜቄዶኒያ የአረጋዊያን መጦሪያ ነው። በዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በርካታ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተረድተናል።
ከሀገራዊው ለውጥ ወዲህ ደግሞ አንድ ሌላ ተጨማሪ መልካም የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴን መመልከት እየቻልን ነው። ይሄም “የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ” ነው። በዋናነት በመንግስት ተቋማት (በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር) እየተመራ በተለይ በክረምት ወቅት የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ እየተለመደ መጥቷል።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በክረምቱ ዝናብ ጣሪያ የሚያፈስባቸውን እናቶች ቤት በማደስ ዜጎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ በተለምዶ ‘አቧሬ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስጀመራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በወቅቱም ዜጎች ይህን ፈለግ በመከተል በየአካባቢያቸው ያሉ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ተጋግዘው እንዲያድሱም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የተነቃቁ ወጣቶችም በተለያየ አካባቢ መሰል የበጎ አድራጎት ተግባር ሲሰሩ ቆይተዋል። ባለፉት ሁለት አመታት የዘለቀው ይህ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮ መንግስታዊ ተቋማት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን የቤት እድሳቱን ተያይዘውታል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር፣የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣የባህል ሚኒስቴር ለእዚህ በአብነት የሚጠቀሱ ተቋማት ናቸው፡፡
ስራው ለሶስት አመታት በተከታታይ መካሄዱ ደግሞ በመንግስትና በህብረተሰቡ ዘንድ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ ጥሩ እየተሰራ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ መጥቀም ይቻላል። ሁሉም ዜጋ ችግኝ ከመተከል ጎን ለጎን በሚያፈሰው፣ እንደነገሩ በቆመው መኖሪያ ቤታቸው ሳቢያ ክረምት መጣ አልመጣ እያሉ የሚሳቀቁ እናቶችን ችግር መፍታት ከምንም በላይ የህሊና እርካታ የሚሰጥ ተግባር ነው። እናቶችም ልጆች ያገኙበት ተግባር ነው ለዚያውም የተባረኩ፡፡
ዛሬ እኛ ከቃኘናቸው የበጎ ስራ ተግባራት ውጪ እጅግ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ እናምናለን። የቆየውን በጎ ምግባር ማስቀጠል ታሪካዊ የትውልዱ ሃላፊነት ነው፡፡ ስራው የትውልዱ ሃላፊነት ቢሆንም ማስተባበርን ይጠይቃል፡፡ ከችግሩ ስፋት አኳያ የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ አሁንም በስፋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል መንግስት ክረምት በመጣ ቁጥር የችግረኞችን ቤት ለማደስ እያካሄደ ያለውን የማስተባበር ስራ እያደንቀን ህብረተሰቡ የመንግስትን ጥረት እንዲቀላቀል እንጠይቃለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2013