የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ̋ትናንት ሀምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም መግለጫ ሲሰጡ የሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት ተጠናቆ ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰሱን እና ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆችም እንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ማስተላለፉቸውን ስሰማ ልቤ በደስታ ተሞላ።
የግድቡ ሙሌት ሁለት ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ያስገኘ ሲሆን ይህም ውጤት በዘንድሮው አመት እየዘነበ ያለው ውሃ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ይህም ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና እንዴት እያገዘን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ለዚህም ምስጋና ይግባውና እዚህ ደረጃ ለመድረስ በዘንድሮው አመት መጠነ ሰፊ ስራ እንደተሰራ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ሁለቱ ተርባይኖች እንዲያመነጩ ብርቱ ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ በቅርብ ወራት በማጠናቀቅ ልፋታችን ውጤት ላይ እንደሚደርስም አብስረውናል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ደስታ ለማን ይኖረው ይሆን እያልኩ፤ ልክ እንደ እኔ የሌሎች እናቶች ደስታ ምን እንደሚመስል ለመቃኘት አዲስ አበባን አካልያለሁ።
ማልደው የእንጦጦን ዳገት ከሚያቋርጡት ጠያይም ሴቶች ፊት ላይ ድካምና ተስፋ ይነበባል። እለት ከእለት ዳገቱን ወጥቶ እንጨት ለቅሞ ከክብደታቸው በላይ የሆነን ሸክም ተሸክሞ ደግሞ ቁልቁለቱን መውረድ አስቸጋሪም አሰልችም ቢሆንም የእለት ጉርስ ማግኛ ነውና ይሄንን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም።
ወይዘሮ ፀሐይነሽ ጎልጃም ኑሮ እንደሚወጡት ዳገት አልገፋ ካላቸው ከእንጨት ተሸካሚዎቹ ሴቶች አንዷ ናቸው። ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል ቢሆንም ሠርተው ለመለወጥ በማሰብ አዲስ አበባ ከተሙ ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ወይዘሮዋ የአዲስ አበባ ኑሮ እንዳሰቡት አልሆን ቢላቸው ኑሮን ተደጋግፎ ለማሸነፍ በማሰብ በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቋቸው ሰው ጋር ትዳር መስርተው አራት ልጆችን አፍርተዋል።
ትዳር ከተባለ ልጅ መከተሉ አይቀርምና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ላይ ልጅ የማሳደግ ሀላፊነት ተጨምሮ ድህነት ቤት አላስቀመጥ ቢላቸው የእንጨት ለቅሞ የመሸጥ ስራውን መልመድ ግድ ሆነባቸው። ከጀርባቸው እንጨት ከፊታቸው ደግሞ ሕፃን ልጅ እያዘሉ መጠነኛ ገንዘብ በማግኘት ኑሮን ለማሸነፍ መጣራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮዋ በየጊዜው እየተባባሰ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት ጋር ችግር ቢገፉት የማይገፋ ታላቅ መከራ እንደሆነባቸው በምሬት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፀሐይነሽ ቀን በቀን ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ኑሮን ለማሸነፍ ቢጥሩም ደኑም አልቆ የሚለቀም እንጨት ከመጥፋቱ በስተቀር ኑሯቸው ላይ ምንም ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩን ነው የሚናገሩት።
ታዲያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቢጠናቀቅ ለእርሶ ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ እኚህ እናት ሲመልሱ ሁሉም በኤሌክትሪክ ሃይል ሲጠቀም የተሻለ ይሆናል፣ እኛም የሚገዛን ስለማይኖር እናርፋለን ብለዋል። ይህን ስል መንግስት ለኛም የምንተዳደርበት ነገር ማሰቡ ስለማይቀር ድካማችን ተቃሎ በእፎይታ ኑሯችንን መምራት እንችላለን ብለዋል።
ሀገር ስታድግ ለድሃውም ለሀብታሙም እድገት ይመጣል የሚሉት ወይዘሮ ፀሀይነሽ ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በተስፋ ከሚጠብቁት መካከል መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት።
ሌላዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ በላይነሽ አበበ ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት የመጠናቀቁ ዜና የድል ብስራት መሆኑን ነው የሚናገሩት። ወይዘሮዋ ተወለደው ያደጉበትን ሸዋ ሮቢት አካባቢ ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ በእረኝነት ከመሳለፋቸውም በላይ ቤታቸው ሲመለሱ ለቤት ውስጥ ማብሰያ የሚሆን እንጨት ከህፃናቱ አቅም በላይ ተሸክመው መግባት ይጠበቅባቸው እንደነበር ይናገራሉ።
በየእለቱ ህፃናቱ እንጨት በመሸከም ከመሰለፋቸውም በላይ በዚህ የስራ ጫና ውስጥ በበቂ ሁኔታ ለትምህርት ጊዜ አለማግኘታቸው ከባድ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
“የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ሙሌት መከናወኑ ለእናቶች በጣም ብዙ ደስታና ብዙ ጥቅም አለው። በገጠሩ ክፍል ያሉ እናቶቻችን በጭስ እየተጨናበሱ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ ለእነሱ የተተወ ስራ ከመሆኑም በሻገር፤ እንጨት ለቅሞ ለማምጣትም ረጅም ርቀት በእግር መጓዝ ሊያስቀርላቸው የሚችል ተስፋ ነው።” ብለዋል።
የህዳሴው ግድብ መሞላቱ በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ እናቶች ታላቅ እፎይታን የሚያመጣ ነው። በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች የኤሌክትሪክ ሀይል ባለማዳረሱ ለምግብ የሚሆኑ እህሎችን በእጅ ከመፍጨት አንስቶ አዘጋጅቶ ለገበታ እስከማቅረብ ድረስ ያለው ሂደት ሀይልን የሚፈለግ በመሆኑ ሴቶች ተገቢውን ጊዜ አግኝተው የሚማሩበት የሚለወጡበት ጊዜ የሚያቀርበ መሆኑ እንደማይቀር በተስፋ ተናግረዋል።
የማማከርና የስልጠና ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ፍፁም አጠናፍ ወርቅ ኪዳነማርያም በበኩላቸው በሰው ልጅ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የኤሌክትሪክ ሀይል እጅግ መሰረታዊ ነገር ነው ይላሉ። ይህ ሲባል ለጤና አገልግሎቱም ይሁን ለተለያዩ ስራዎች ሀይል ዋናው ሞተር ነው። ከሁሉም በላይ ግን የሰው ልጅ ቆሞ እንዲሄድ መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች አንዱና ዋንኛው ምግብ በመሆኑ ይሄንን መሰረታዊ ነገር ለማዘጋጀት ደግሞ የሀይል አቅርቦት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሀገራችን ባህል ሆኑ እያንዳንዱ የማጀት ስራ የሚተወው ለሴቶች በመሆኑ ምግብን ለማዘጋጀት በሚደረገው ሂደት በጭስ ምክንያት የአይን ታማሚ የሆኑ እናቶችን ለማሳረፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ይህ ፕሮጀከት ከኢትዮጵያዊያን ሴቶች በላይ ደስታ ለማንም የማይኖረው መሆኑን ነው የተናገሩት።
“አንዲት እናት ከጭስ ተገላገለች ማለት፤ እንጨት ከመሸከም ወጣች ማለት፤ የሀይል አቅርቦት ደጃፏ ድረስ ደረሰ ማለት፤ ጊዜዋ ተቆጥቦ የማንበብ የመማር ጊዜ ይኖራታል፤ የተማረች እናት ደግሞ የተማረውን ትውልድ ከማስቀጠል አንፃር ታላቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖራት የሰለጠነ ትውልድን በማፍራት ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል።
በሀገራችን በአይን ህመም የሚሰቃዩ በርካታ እናቶች የሚድኑበት ከመሆኑም ባለፈ በእንጨት ሸክም ምክንያት ያለእድሜያቸው የሚጎብጡ እናቶች የማይታይበት ጊዜው ቅርብ ስለሚሆን ደስታው እጥፍ ድርብ ነው፤ ብለዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪያችን ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት መአዛ መንክር ይባላሉ። ወይዘሮ መአዛ የልጅነት ጊዜያቸውን በኮረም አካባቢ ማሳለፋቸውን አስታውሰው በዛች ትንሽ ከተማ ውስጥ በአብዛኛው በእሳት የሚጋግሩ በከሰል የሚያበስሉ እናቶች መኖራቸው በሴቶች ላይ የጤና ችግር ከማስከተሉም በላይ የአካባቢ መራቆት ላይ ትልቅ ጫና እንደነበረው ያስታውሳሉ።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ መሞላት ለሴቶች ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያዊያን ጉጉት የነበረ መሆኑ እጅግ በጣም ታላቅ ደስታን የሚፈጥር መሆኑን ነው የሚናገሩት። ይህ ሲባል ከአለም እኩል ቀና ብለን እንድንናገር ያለ ማንም እርዳታ ከራሳችን ኪስ በወጣ ገንዘብ በራሳችን ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሁኔታ ግድቡ ተገንብቶ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት መያዙ ታላቅ ስሜትን የፈጠረ እንደሆነ ገልፀዋል።
“ከዚህም በላይ የቀደምት አባቶቻችንን ታሪክ መልሰን ስማችንን በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቅ ቀለም የምናስፍርበት ጊዜ ላይ መድረሱ እጅግ በጣም የሚያስደስት ለህዝቡም ተስፋ የሚፈጥር በኩራት አንገትን ቀና የሚያደርግ በመሆኑ ለህዝብ ስነ ልቦና ግንባታ ታላቅ ፋይዳ አለው።” ያሉት ወይዘሮ መአዛ፣ሴቶች ሁልጊዜም በኢኮኖሚ ወደ ኋላ ያሉ በመሆናቸው የእያንዳንዱ ችግር ገፈት ቀማሽ የሚሆኑትም እነሱ ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አሁን በሀገራችን ያለውን የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት መቀረፍና ሀይል ለሌሎች ሀገራት በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ፤ ከተለያዩ ልማቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እናቶችን የሚጠቅም መሆኑን ተናግረዋል።
ሴቶች እያንዳንዱን የቤት ውስጥ ስራ ለማከናወን ሀይል በማስፈለጉ ያንን ሀይል ከሚያገኙበት የማገዶ እንጨት ሊያመጡ ሲሄዱ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል፤ ያንን ተከትሎ ስነ ልብናዊ ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑ ይሄንን ችግር ከመቅረፉ በላይ ሴቶች ከድካማቸው ወጥተው ራሳቸውን የሚያሻሽል እድል የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስረዱት።
በሀገራችን ደግሞ ስነ ምህዳሩን የጠበቀ የውሃ ሀይል ለመጠቀም መታሰቡ ተፈጥሮ ሳይጎዳ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ታላቅ ድል ነው ያሉት ወይዘሮ መአዛ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ሙሌት ላይ መድረሱ እናቶች ከሁሉ በበለጠ እልል ብለው የሚቀበሉት መሆኑን ነው የተናገሩት።
ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ ትናንት ተጠናቋል። ይህ ሙሌት በተገቢው ከተጠናቀቀ በኋላ በኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ላላገኙ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተስፋ ከመሆኑም በላይ በጭስ የተጨናበሰውን የእናቶችን አይን በደስታ የሚያበራ ፕሮጀክት እንደሆነ በችግሩ ውስጥ ያለፉት እናቶች የመሰከሩት ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013