ሐምሌ ግም ሲል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ውሃ እሞላለሁ ስትል ቀጠሮ የያዘችው ኢትዮጵያ እነሆ የትኛውም ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይበግራት ብሎም ሳያንበረክካት የሙሌት ሂደቱን በስኬት አጠናቃለች። ኢትዮጵያ የሰኔ ወር ማገባደጃ ላይ ግድቤን የገነባሁት ውሃ በመሙላት የኤሌክትሪክ ኃይል ላመነጭበት እንጂ እንደሃውልት ቆሞ እንዲጎበኝ አይደለም በሚል መንፈስ እወቁልኝ ስትል ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሯን ይፋ ባደረገችበት ጊዜ መልዕክቱ ለኢትዮጵያውያን ብስራት፣ ለግብጽና ሱዳን ደግሞ የመርዶ ያህል የከበደ መሪር ሀዘን ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ የምታከናውነው ስራ ሁሉ ሚዛናዊና ፍትሃዊ ሆኖ የሚቀጥል እንደሆነ መጥቀሷ የሚታወስ ነው። ሶስቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የአባይን ወንዝ በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ድርድርን ለማካሄድም ኢትዮጵያ ያላት አቋም ጽኑ መሆኑን ያኔም ይሁን አሁን ደጋግማ ስታሳውቅ ቆይታለች። ይህንን መሰረት ያደረገ አካሄድ በመከተልም በመርህ ስምምነቱ መሰረት ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ተግባራዊ አድርጋለች። ይሁንና ግብጽና ሱዳን፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት በሦስቱ አገራት መካከል እነሱ የሚፈልጉት አሳሪ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ዓለምን ቢዞሩም ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ መቀልበስ አልተቻላቸውም።
ከዚሁ ሐሳብ ጋር በተያያዘና የህዳሴ ግድቡ የአስር ዓመት ጉዞ ስኬትና ፈተና እንዲሁም የዲፕሎማሲው ውጤት እንደምን ይገለጻል ሲል አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ከሆኑትና ከሁል ጊዜ ተባባሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ጋር ያካሄደውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ያለው የአስር ዓመቱ ፈተና እና ስኬት እንደምን ይገለጻል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት ከመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው ፈተና ቀላል የሚባል አይደለም። በእነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ እጅግ አታካች ወቅቶችም አልፈዋል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ግብጽና ሱዳን በአንድ ላይ ሆነው የግድቡን መጀመር አምርረው ተቃውመውት ነበር። አገራቱ ምን ሲደረግ ነው ኢትዮጵያ ግድብ የምትገነባው ሲሉም ከፕሮጀክቱ በተቃራኒ ቆመዋል፤ እኛ ሳናውቀውና ሳንፈቅድ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መስራት መፈለጓ አግባብነት የለውም ሲሉ የልባቸውን ተናግረዋል። ግድብ መስራት አይፈቀድላትም ከማለታቸውም በተጨማሪ የግድቡን መጀመር አናምንም ሁሉ ብለው ነበር።
በተለይ ከግብጽ ወገን አውሮፓ፣ አረብ አገራትንና ሌሎች ያግዙኛል ብለው ወደሚያስቧቸው አገሮችና ተቋማት ዘንድ እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ግድብ ጀምሬያለሁ የምትለውን ቀልድ ታቁም፤ ለአንድ ጠብታ የናይል ውሃ አንድ ጠብታ ደም እንከፍላለን እስከማለት ደርሰው ነበር። የሆነው ሆኖ የግድቡ ግንባታ ስራ ግን ከመነሻው ጊዜ ጀምሮ በቁርጠኝነት መቀጠሉ እርግጥ ሆነ።
ለግብጽና ለሱዳን እንዲሁም ለሌሎች ወዳጆችም ሆነ ጠላቶች ኢትዮጵያ ግድብ መጀመሯም በ2003 ዓ.ም ወርሃ መጋቢት እርግጥ ሆነ። በኢትዮጵያ በግልጽ የተነገረው፣ ስለግድቡ መጠየቅ፣ ማወቅ፣ መነጋገርና መምከር የሚፈልግ የትኛውም ወገን ማወቅ ያለበት በመስራት ላይ ስላለው ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንጂ ገና ሊሰራ ስለታሰበ ግድብ አለመሆኑ በግልጽ ተነገረ። ሁሉም ወገን ቁርጡን ስላወቀ ስለግድቡ ተጽዕኖ፣ ጉዳት ወይም ጥቅም፤ ውይይት፣ ድርድር ወዘተ የቀጠለው የኢትዮጵያን ሐሳብና የግድብ ስራ ሊያደናቅፍ በማይችል መንገድ ነው።
ከዚያ በኋላ የነበሩ የድርድር ሂደቶችም ውጣ ውረድ የበዛባቸው እንደነበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ወገን ማለትም የመንግስት አመራር፣ ተደራዳሪዎች፣ መላ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ፤ በሐሳብም በተግባርም በብሄራዊ ጥቅምም በአገር ፍቅር ላይ የተመሰረተ ስራ ስላከናወኑ ድርድሩ ስኬታማ ሆኗል።
የግድቡ ግንባታ ቴክኒካዊ ተግዳሮት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በመንግስት ቁርጠኛ አመራር እርምት ስለተደረገበት በግንባታ በኩል ተከስቶ የነበረውም ቀዳዳ ሊወገድ ችሏል። በድርድሩም በግንባታውም የተተገበረ ስራ ስለተከናወነ ስኬቱ አሁን የምናየው አይነት ሆኗል። ለወደፊትም ቢሆን በዚሁ ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ የግብጽ፣ የአሜሪካ እና የምዕራባውያኑ ተጽዕኖ በኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች ላይ ያሳደረው ጫና ምን ይመስላል? በወቅቱስ እንዴት ታለፈ?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- በግብጽ በኩል የነበረው ጫና አሰልቺ ፣ አታካች፣ የተምታታ እንዲሁም ውል የሌለው ነበር። እውቀትንና ጥበብን በራስ ወዳድነት በማዛባት እና ስህተትን መልሶ መላልሶ በመድገም ጊዜ የሚያባክን ነበር። የሆነ ሆኖ የግብጽ ወገን ሊረዳ ያልቻለው ግድቡ እየተሰራ መሆኑን፤ በየቀኑ 24 ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀናት፣ ግንባታው እየተቀላጠፈ መሆኑን ነው። እንዲሁም ግድቡ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አንጡራ ጥሪት የሚሰራ መሆኑን፤ የግድቡ ስራ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወሳኝ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን እንዲሁም መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን በቁጭት እና በአርበኝነት ስሜት የያዘው ስለመሆኑ አለመረዳታቸው ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡን ጉዳይ የያዘው በአርበኝነት ስሜት ብቻ ሳይሆን ዋጋ ለመክፈልም ተዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።
የግድቡ ስራ ከውጭ የፋይናንስ ተጽዕኖ ነጻ መሆኑን፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማት ፍላጎቷ ሊሰናከል እንደማይገባ ቁርጠኛ እምነቷ መሆኑን የታችኞቹን አገሮች በከፋ ሁኔታ እስካልጎዳ ድረስ ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቷ የመጠቀም መብቷ የማይገሰስ መሆኑን ነው።
ከዚህ በኋላ የግድቡ ልማት ትሩፋት እንደሚጠቅመው የሱዳን መንግስት ተገንዝቦ ወደ ኢትዮጵያ ወገን ቢለጠፍም የግብጽ ወገን አደናቃፊ አጀንዳዎች በጥምረት ማስቸገሩን ቀጥላበት ነበር። እነርሱ ሊረዱት ያልቻሉት የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴ ግድብን መጀመሩና በአገሪቱ በሁሉም ስፍራ የሚንዠቀዠቁ ወንዞቿን ኢትዮጵያ ማልማት መጀመሯ ብሎም በዚሁ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗ ትልቅ አጀንዳ መሆኑን ነው።
ግብጽ ያለ እረፍት የአሜሪካን መንግስት በመወትወት ድጋፍ እንዲሰጣት ባደረገችው ጥረት የአሜሪካ መንግስት በህዳሴ ግድብ ውይይት /ድርድር/ በታዛቢነት ደረጃ ብቻ ለመገኘት ፈቃድ በመጠየቁ አግኝቶ ነበር። እንዲያም ሆኖ ለታዛቢነት የተፈቀደለትን ውለታ እና መስመር በማለፍ ‹‹ ላሞኛችሁ አይናችሁን ጨፍኑ› እንደሚባለው አይነት ለግብጽ የወገነ አቋም በመያዝ ራሱን ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት በማሳደግ ያልተገባና ለግብጽ ብቻ አመቺ የሆነ፣ የኢትዮጵያን መብት እና ጥቅም የሚጎዳ ረቂቅ ስምምነት ማቅረብ ጀመረ። ይሁንና ይህን አይን ያወጣ አካሄድን የኢትዮጵያ ወገን አልተቀበለውም።
በድምሩ የግብጽን የተምታታ እና አታካች የድርድር አካሄድን የኢትዮጵያ ወገን በትዕግስት፣ በአስተውሎት፣ በእውቀት፣ በአገር ፍቅር እና በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ እና ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ለስኬት አብቅቷል። የአሜሪካን ‹‹ላሞኛችሁ›› በሚል ግምት የግብጽን ወገን ጠቅሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለዘመናት ሊጎዳ ይችል የነበረውን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ ተችሏል።
የሱዳን የሚዋዥቅ አቋምና በአብዛኛው ከብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የተላላኪነት አካሄድ በትዕግስትና በትዝብት ጭምር በመከታተል እዚህ ስኬት ላይ ተደርሷል። እስካሁን የነበረው ድርድር ያለፈው በእንዲህ አይነት ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ስራ ገና በጅምር ላይ ስለሆነ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ ስለሆኑ ገና ብዙ የልማት ስራ ይጠብቀናል። እስካሁን በተገኘው ልምድ እና ስኬት ወደፊት ለሚያጋጥሙ ድርድሮች ተዘጋጅቶ መጠበቅ ተገቢ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግስት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያሳካቸው ዲፕሎማሲያዊ ሂደቶች ምን ያህል ስኬታማ ናቸው? ገጥሟቸው የነበረውስ ፈተና እንዴት ይገለጻል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡– ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተጀመረ በመጀመሪያዎች ወራት በግብጽ ወገን የነበረውን ሮሮ እና ግብጽን በሆነ ባልሆነው በሚደግፉ ወገኖች የሚሰራጨውን ስሞታ ለማምከን የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡ በጥንቃቄና በተሟላ ጥናት እንዲሁም ዲዛይን ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያጣራ አንድ የዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል እንዲቋቋም ሐሳብ አቀረበ።
በኢትዮጵያ በኩል የግድቡ አሰራር በተገቢ ጥናት እና ዲዛይን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማረጋገጥና የግብጽን ጫጫታ እና የደጋፊዎቿን ስሞታ ለማምከን የታሰበ ነበር። ግብጽና ሱዳን በበኩላቸው ግድቡ እንደነገሩ እየተሰራ ያለ በመሆኑ እነሱን የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ ጥፋተኛ የሚያስብል ህጸጽ እናገኝበታለን ብለው በማሰብ የፓናሉን መቋቋም በወቅቱ ተቀብለውታል።
በሃይድሮሎጂ፣ በኢንቫይሮንሜንት፣ በግድብ ስራ ጥብቀትና በማህበራዊ መስኮች በዓለም የታወቁ ኤክስፐርቶች በውድድር ተመርጠው በሶስቱም አገሮች (በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን) ይሁንታ እና ወጪ ተቀጠሩ። ሶስቱም አገሮች ሁለት ሁለት ኤክስፐርቶች ሰይመው አስር የፓነል ቡድን ተቋቋመ። ከየአገራቸው በውሃ ጥናት እውቀትና ልምድ ያላቸው አማካሪዎችም ከፓነሉ ጋር ተሰየሙ።
እኤአ ከ2012 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፉ የኤክስፐርቶች ፓነል የመስክ ጥናትን ጨምሮ ሰፊና ሙያዊ ጥናት በማካሄድ የግድቡ አሰራር ዓለም አቀፍ ከፍተኛውን ደረጃ የሚያረጋግጥ መሆኑን፤ ለወደፊት ግድቡ በስራ ላይ በሚውልበት ወቅት በታችኛዎቹ መዳረሻዎች ላይ ሊያስከትል የሚችል ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ከተጠረጠረ ሶስቱም አገሮች በጋራ በማስጠናት ሊኖር የሚችለውን ተጽዕኖ በጋራ በማስጠናት ማስተካከል እንደሚችሉ ምክረ ሐሳብ አቀረበ። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።
ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና አሞላል ኦፕሬሽን የግብጽ እና የሱዳን ወገን አስቀድመን ማወቅ አለብን በማለት የሚያቀርቡትን ጭቅጭቅ መስመር ለማስያዝ ተብሎ እኤአ በ2015 እጅግ ፈታኝ ድርድር ተካሂዶ የመርህ መግለጫ ስምምነት (Declaration of principles) እኤአ በመጋቢት 2015 በሱዳን ካርቱም ላይ በሶስቱም አገር መሪዎች ደረጃ ተፈረመ።
በዚህ ስምምነት መሰረት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሞላል ከግድቡ ግንባታ ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ ስለመሆኑ ውል ተገብቷል። ይህን የስምምነት መርህ ተከትሎ ነው ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ እርከን የግድብ ሙሌት የተካሄደው። የሁለተኛው እርከን ሙሌትም የተካሄደው ይህንኑ የስምምነት መርህ በተከተለ መንገድ ነው። በቀጣይ ዓመታት የሚከናወነው የሙሌት ስራም የሚካሄደው በዚሁ መንገድ ነው።
ይህንን የዲፕሎማሲ ውጤት የግብጽም ሆነ የሱዳን ወገን ሊቀበለው አልቻለም። በዚህ ረገድ ያደረጉት የተምታታ ጥረት መክኖባቸዋል። ነገር ግን የግድቡ ቁመት እንዲሁ ይቀጥላል። ግድቡም እየተሞላ እስከ መጨረሻው ይሄዳል። የግብጽ ወገን የአሜሪካን አስተዳደር ከጎናቸው በመያዝ የኢትዮጵያን ብሄራዊና ዘላቂ ጥቅም በሚጎዳ መንገድ አጨናብረው ሊያስሩት የነበረው የዋሽግተን ድርድር በኢትዮጵያ ወገን ተቀባይነት አለማግኘቱ እና በኋላም ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ተቀባይነት እያገኘ መሄዱ አንድ ሌላ የኢትዮጵያ መንግስት የዲፕሎማሲ ስኬት ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የዲፕሎማሲ ስኬቶች እየተደማመሩ ብዙ ናቸው ለማለት ይቻላል። ከሁሉ በላይ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው የዲፕሎማሲ ስኬት የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች፣ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የተለያዩ ከግድቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አዳዲስና ነባር ተቋሞች እኛ የግድቡ የተለያዩ የድጋፍ አደረጃጀቶች እና ስብስቦች በትብብርና በመናበብ በአንድ ላይ መስራት መቻላቸው ትልቁ የዲፕሎማሲው ስኬት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይገባል።
ዲፕሎማሲ ሁል ጊዜም ቢሆን ማዶ ካለው ወገን ጋር የሚደረግ የብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መድረክ ስለሆነ አልጋ በአልጋ የሆነ ሂደት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ድርድር በተመለከተ እልህ አስጨራሽ እና መልካም ፈቃድና መተማመን ከራቃቸው ባላንጣዎች ጋር የተደረገ ስለሆነ የማያልቅ ትዕግስትና የሰከነ አስተውሎትን ይጠቀሙ ነበር። በየደረጃው ከገጠሙ ፈተናዎች ይልቅ የተገኙ ልምዶችና የድርድር ክህሎቶች የሚያረኩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በየትኛውም አይነት አዎንታዊ ድጋፍ የህዝቡ ተሳትፎ ለኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች እንዴት ይታያል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ ህዝብ አዎንታዊ ድጋፍ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በአንድ ቃል ለመግለጽ ያህል ‹‹አስገራሚ›› ማለቱ ይቀላል። ወንዱና ሴቱ፣ ህጻንና አዋቂው፣ አርሶ አደሩና ከተሜው ፣ ወታደሩና ሲቪሉ፣ ተማሪውና ሰራተኛው፣ ሁሉም በየፊናው የችሎታውን ያህል ገንዘብ ለግሷል። ተስፋውንም ሰንቋል። የጋለ ትብብሩን አሳይቷል። በዚህ ሁሉ የአገር ፍቅሩን እና አለኝታነቱን የመበልጸግ ተስፋውንና ዘላቂ ጥቅሙን አረጋግጧል።
አርቲስቱ በግጥሙና በዜማው፣ ምሁሩ በስነ ጽሑፉና በድርድሩ፣ ሽማግሌው በምክሩና በምርቃቱ፣ የኃይማኖት አባቶች በጸሎታቸውና በሱባዔያቸው፣ ወታደሩ በጥበቃውና በጸጥታ አስከባሪነቱ፣ ምን ያልተደረገ ድጋፍ አለ? አንድ የኃይማኖት አባት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉባኤ ላይ ‹‹ከሞቱትና ገና ካልተወለዱት በቀር ግድቡን የማይደገፍ ሊኖር አይችልም›› ብለው ነበር። ከዚህ ባልተናነሰ በመላ ዓለም የሚኖረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በእጅጉ የሚያኮራ ተግባር መፈጸሙ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ለህዳሴ ግድቡ በገንዘብ፣ በድጋፍ ሰልፍ፣ ስለግድቡ ትክክለኛ ሁኔታ የዓለም ህዝብ እንዲያውቀው በማስተማር፣ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የሚገኙ ምሁራን እና ባለሙያች የሚተጋገዙበትን ሁኔታ ለማቻቸት በድረ ገጽና በሌሎች ተመሳሳይ መገናኛዎች ግንኙነት በመፍጠር የማይተካ ተሳትፎና አስተዋጽኦ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ያለውን ድጋፍና ለአፈጻጸሙ የሚያሳየውን ጉጉት፣ ስለ ግድቡ የድጋፍ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቼ ትምህርታዊ መግለጫዎችን እንድሰጥ ተጋብዤ በሎንዶን፣ በኒዮርክ፣ በሎስአንጀለስ፣
በሳንዲያጎ፣ በሲያትል፣ በላስቬጋስ፣ በኦክላንድ እና በሳንሆሴ ከተሞች በተገኘሁባቸው አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ለአገሩ ልማትና ክብር እጅጉን ቀናኢ እና የአርበኝነት ስሜት ያለው መሆኑን ለማየት ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማስኬድ የነበረውን ፈተና እና ምቹ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ሁለተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጉዳይ ኢትዮጵያውያን እና የዓለምን ፖለቲከኞች ቀልብ በእጅጉ የሳበ ክስተት ነበር። በተለይ ግብጽና ወደ ግብጽ ተለጥፋ ያልተገባ ጭቅጭቅ ውስጥ የምትገኘው ሱዳን በነዙት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እና አሳሳች መግለጫዎች የተነሳ የሕዳሴ ግድባችን የሁለተኛው እርከን ሙሌት ጉዳይ ከመጠን በላይ በተጋነነ ወሬ ውስጥ ነበር የቆየው። መታወቅ የነበረበት አሁንም ያለበት ጉዳይ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የምትገነባው ሙሌት አካሂዳ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው።
ይህ እንደሚሆን በኢትዮጵያ መንግስት ጥናትና ዲዛይን፣ በድርድሩ ሂደት፣ በግድቡ ግንባታ ስራና በየጊዜው በሚወጡ በኢትዮጵያ መንግስት መግለጫዎች የተሰመረበት መሆኑን ነበር። በኢትዮጵያችን በኩል በተከናወኑት እጅግ በርካታ እና እልህ አስጨራሽ ውጥረቶች በተገኘ ውጤት ላይ ተመስርቶ እነሆ የግድቡ ሙሌት እየተካሄደ መሆኑን ዓለም ከተገነዘበው ውሎ አድሯል። የኢትዮጵያ መንግስትም ለግብጽና ለሱዳን መንግስት ይህንኑ በጽሁፍ አሳውቋል።
ኢትዮጵያ ፈተናውን በሚያስፈልገው ሁሉ ተቋቁማ ሙሉ ዝግጅት በማድረግ አሳውቃለች። ቀጥሎ ሊከሰቱ የሚችሉትንና በየጎንዮሽ የሚጋረጡትን ፈተናዎች ለማስተናገድና ለመሻገር ለአንድ አፍታም መስነፍና መዛነፍ የለባትም። እስካሁን የተገኘው ስኬትና ልምድ ለነገው ስንቅ መሆኑን በጥንቃቄ መቀመርና ለመጪዎቹ ፈተናዎች በብቃት መዘጋጀት አማራጭ የሌለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በቀጣይ ለማልማት እንዴት ልትሄድበት ትችላለች ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ልማት የመጀመሪያ አይደለም፤ የመጨረሻም አይሆንም። ከአሁን ቀደም አባይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ በርካታ ልማቶች ተካሂደዋል። የፊንጫ ግድብ እና የስኳር ፋብሪካ፣ የተከዜ ግድብ እና የኃይል ማመንጫው፣ የጣና በለስ የኃይል ማመንጫውና የልማት ፕሮጀክቶች፣ የአቦቦ ግድብ እና የልማት ዝርጋታ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ኢትዮጵያ በሌሎች ተፋሰሶች ለምሳሌ በአዋሽ፣ በዋቤ ሸበሌ፣ በገናሌ ዳዋ፣ በኦሞ-ግቤና በመሳሰሉት በርካታ ልማቶችን አካሂዳለች።
በአባይ ተፋሰስ ብቻ ከሰላሳ በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ከንጉሰ-ነገስቱ ዘመን ጀምሮ ተጠንተው ለልማት አቅምና ወረፋ የሚጠብቁ ናቸው። ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በታችኛዎቹ መዳረሻ ለሚገኙ አገሮች እና ማህበረሰቦች የጎላ ጉዳት በማያስከትል መንገድ የመልማት መብት አላት። ህብረተሰቡ ከድህነት ለመላቀቅና ብልጽግናን ለማምጣት መንግስት የአገሪቱን የውሃ ሀብት የማልማት ግዴታም አለበት።
የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መዳረሻ አገሮች ለራሳቸው ህብረተሰብ ጥቅም ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር፣ በመተማመን እና በመተጋገዝ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህን የትብብር አግባብ የናይል ተፋሰስ አገሮች እስካሁን የፈረሟቸው ስምምነቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኮንቬንሽን እና የሌሎች አገሮች የትብብር ሰነዶች እንዲሁም ልምዶች ያረጋግጣሉ።
በተለይ ግብጾች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የሚደርሷቸውን ወንዞች ለብቻ በመቆጣጠር በሞኖፖል አንቀው ይዘው ለመጠቀም መፈለጋቸው የማያዋጣቸው ስለሆነ ወደ ትብብር ብሎም በመተማመን ላይ ወደተመሰረተ ጉርብትና ይመጣሉ ብዬ አምናለሁ። ሌላ አማራጭም የላቸውም።
ከዚህ በተጨማሪ አባካኝ እና በካይ የውሃ የአጠቃቀም ልምዳቸውን በማሻሻል ለውሃው ለራሱ አዘኔታ እና ክብር መስጠት መጀመር ይኖርባቸዋል። ከኢትዮጵያ የሚያገኙትን ውሃ እያባከኑና እየበከሉ አልፈው ተርፈው የጋራ ሀብት ነው በሚል መንፈስ የተፈቀደላቸውን በተገቢው መንገድ መጠቀም ትተው ለተጨማሪ ብክነትና ብክለት ከመዳረግ ደንታ ሊሰጡ ይገደዳሉ። የወደፊት ውሃ አመንጪ ኢትዮጵያ፤ የውሃ ተቀባይ ግብጽ የውሃ ትብብር የጋራ የሆነውን የውሃ በረከት ባከበረ አግባብ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮፌሰር ለሁልጊዜ ቀና ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013