አሁን አሁን መፅሐፍትን የሚያነብም ሆነ በአካባቢያቸው ያላለፈ ሁሉ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለውን አባባል በንግግሩ መሀል ጠቀስ አድርጎ ማለፉ እየተለመደ መጥቷል። ምንም እንኳን ይህ አባባል ስለተደጋገመና በየጨዋታው መሀል ስለተነሳ “ሙሉ ሰው” የሚለውን ማእረግ ባያጎናፅፈንም የነገሩን እውነታነት ግን አይቀይረውም። ምክንያቱ ደግሞ እጅግ በጣም ግልፅ ነው። ጥቂት ሰዓት ቆጠብ አድርገን የማንበብ “ሀሞት” ካለን ውጤቱን ሳይውል ሳያድር ስለምናገኘው ነው። ስለዚህ በማንበብ የሚገኝ ሙሉ ሰውነት በተግባር ሲገለጥ እንጂ እንዲያው በደፈናው “በፉከራና ቀረርቶ” እንደማይመጣ ሁላችንም ልንገነዘው ይገባል።
ዛሬ መግቢያችን ላይ ጠንከር አድርገን እንደገለጽነው ስለ “ንባብ” እናወጋለን። ይህን ወቅት የመረጥነው ደግሞ በግርድፉ አይደለም። ጊዜው ክረምት ከመሆኑ አንፃርና ተማሪዎች እፎይታን አግኝተው “ትምህርት ነክ ከሆኑ” ንባቦች በተለየ “ጥቅል ገንዛቤ የሚያስጨብጡ” መፅሐፍት ላይ ትኩረታቸውን ቢያደርጉ መልካም ነው ብለን በመገመታችን እንጂ።
በዋናነት ግን የዛሬ ርእሰ ጉዳያችን “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፤ መፅሐፍት ጋር ጓደኝነት ፍጠሩ” ማለት ላይ ብቻ የሚያተኩር አይደለም። በተለይ አገር የመረከብ ኃላፊነት የተደቀነበት ትውልድ “ንባብን ባህሉ” እንዲያደርግ “ምን መቹ ሁኔታ አለ?” “ምንስ እየተሰራ ነው?” የሚለውን ጉዳይ በስፋት ለመዳሰስ በማሰብ ነው። ለዚህ ደግሞ የብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመፃህፍት ኤጀንሲን እንደማሳያ ወስደን አንዳንድ ጉዳዮችን ከጋበዝነው እንግዳ ጋር እንጨዋወታለን።
አቢያተ መፅሐፍት
አቶ ያሬድ ተፈራ ይባላል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ የአብያተ መፅሐፍት አገልግሎት ዳይሬክተር ነው። እንደ ርእሱ ገለፃ ኤጀንሲው በመላው ኢትዮጵያ “የማንበብ ባህል” እንዲሰርፅ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ሰፊ ሥራ ይሰራል። በዚህ ዓመት ብቻ በባሌ፣በአዴት፣ በአርባምንጭ፣ድሬዳዋ፣ሀረር፣ ጅግጅጋ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ንባብን የተመለከቱ ሥራዎች እንዳከናወኑ ይናገራል። በተለየ መልኩ “ለምድር እፅዋት ለአእምሮ ደሞ መፅሐፍት” በሚል መሪ ሃሳብ ቤተመፅሐፍቶችን የማደራጀት፣ የንባብ ቀን በማድረግ ንፅናቄ በመፍጠር፣ ደራሲዎች በዘመቻዎቹ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ወጣቶችን በማነቃቃት፣ መፅሐፍትን በመስጠት ብሎም የማንበብ ጠቀሜታዎችን የሚያጎሉ ስትራቴጂክ ሥራዎችን መስራት ተችሏል።
“ቤተ መፅሐፍት መመስረት ብቻ ሳይሆን በደረስንባው ቦታዎች ሁሉ እንዴት የማንበብ ባህልን ማዳበር እንደሚቻል በማስተማርና ክበቦችን በማቋቋም ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን” የሚለው ዳይሬክተሩ አቶ ያሬድ፤ ጥቅል ሃሳቡን በግንዛቤ መልክ በማስጨበጥ መልካም መሰረት እየጣሉ እንደሚያልፉ ነው የሚገልፀው።
ከከተማ በራቁ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ይሰሩ እንጂ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞችም የማንበብን ልዩ ጥቅም ለማስረፅ እንደሚሰራ ይገልጻል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየሞች) ጎፋ፣ጎተራ፣ጀሞ መኖሪያ አካባቢ ህፃናትልጆች በንባብ አእምሯቸውን እንዲያበለፅጉ የሚረዱ ልዩ ልዩ መንገዶችና ማበረታቻዎችን በመቀየስ ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም አበረታች ለውጥ እየታየ መምጣቱንና ቤተሰብም ልጆቹ ለንባብ ቅርብ እንዲሆኑ ፍላጎት እያሳየ መምጣቱን ይገልፃሉ።
የያዝነው ክረምት
ኤጀንሲው ክረምትን እንደ አንድ አጋጣሚ ለመጠቀም አስቧል። ይህ ወቅት በርካታ ተማሪዎች በቤታቸው ውስጥ የሚቆዩበት ነው። ስለዚህ የመፅሐፍት አውደ ርእይ እንዲበረታታ በማድረግ፣ በኮንዶሚኒየም አካባቢ ባሉ የጋራ መጠቀሚያዎች /ኮሚናሎች/፣ በተለያዩ ቤተ መፅሐፍት የኢትዮጵያውያን ደራሲያን ሥራዎች በስፋት የሚደርሱበትን አጋጣሚ ለመፍጠር እየተጉ መሆኑን ያነሳል። ከዚህ በተለየ ደራሲዎቹ ለህፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች የማንበብ ጠቀሜታንና ልምዳቸውን በቀጥታ ተገኝተው የሚያጋሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር መድረኮች እንደሚያዘጋጁ ነው የአብያተ መፅሐፍት አገልግሎት ዳይሬክተሩ ለዝግጅት ክፍላችን የገለፀልን።
ሌላውና ዋንኛው ጉዳይ አንጋፋና ወጣት ደራሲያንን እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሳው ዳይሬክተሩ “የንባብ ባህል የሚያድገው የሚፅፉ ደራሲዎችን ማበረታታት ስንችል ነው” በማለት ኤጀንሲው እውቅና የመስጠት ዝግጅቶችን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት መወሰኑን ነግረውናል።
ምን ምጤት መጣ?
ዳይሬክተሩ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ማንበብ ባህል እንዲሆን በተሰራው ሥራ ላይ በርካታ ውጤቶች ማምጣት መቻላቸውን ይናገራሉ። ከዚህ መካከል ርቀት የገደባቸውና ምቹ ሁኔታዎች ያልነበሯቸው አካባቢዎች ላይ መድረስ መቻላቸው፣ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ የእነርሱን አርአያ ተከትለው የሚሰሩ ሌሎች አካላት መፈጠራቸው ፣በከተሞች አካባቢ በርካታ የመፅሐፍት አውደርእይ መዘጋጀት መጀመራቸውና ህብረተሰቡም መፅሐፍትን ገዝቶ ለማንበብ ፍላጎት ማሳየቱን እንደ ውጤት መለኪያ ወስደዋቸዋል። በቀጣይም እነዚህን ልምዶች የማሳደግና አዳዲስ ስልቶችን ነድፎ የመንቀሳቀስ ግብ መኖሩን ጠቅሰውልናል።
የኤጀንሲው ፈተናዎች
አቶ ያሬድ የንባብ ባህል እንዲሰርፅ፣ በምክንያት የሚያስብ ትውልድ እንዲፈጠር በተገኘው ምቹ አጋጣሚ ሁሉ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል ይላል። ይህ ደግሞ የተለያዩ የሚያገባቸው አካላት ትብብርንና ቅንጅትን የሚጠይቅ ነው። አሁን ላይ ኤጀንሲው በዚህ መንገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስን መሆኑን ይናገራል። በዚህ በኩል ኤጀንሲው በሚሄድበት ፍጥነት ሌሎች አካላት እኩል የመራመድ፣ እኩል ግንዛቤ የመኖር ችግር ይታያል። ይህ አንዱ የሚገለፅ እንቅፋት ነው።
ሌላኛው ችግር ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው “የንባብ ጠቀሜታ” ግንዛቤው ማነስ ነው። ለዚህም አቶ ያሬድ ምክንያት ሲያስቀምጡ ኤጀንሲያቸው በተለያዩ ስፍራዎች እየተዘዋወረ “ባህሉን” ለማስረፅና መሰረት ለመጣል ጥረት ሲያደርግ በድጋሚ ወደኋላ የማፈግፈግ ምልክት ማየታቸው ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ቤተ መፅሐፍት ፣ ክበባትንና መሰል የማንበብ ልምድን ለማዳበር የሚያግዙ አደረጃጀቶች ቢፈጠሩም ተመልሰው የሚዳከሙበት አጋጣሚ በመታየቱ ነው።
እንደ መውጫ
በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው “ማንበብ ሙሉ ሰው የሚያደርገው” ስናነብ እንጂ እንዲያው በደፈና ስለማንበብ ደጋግመን “ስለዘመርን” አይደለም። ለማንበብ የሚሻ አካል ምቹ ሁኔታ ይፈልጋል። በእርግጥ በአገራችን የተሟላ ነገር እንደሌለ ብናምንም ለዛሬ በምሳሌነት እንዳነሳናቸው “ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ” አይነት ንባብን ባህል ለማድረግ የሚሰሩ አካላት አሉ።
ከዚህ ባለፈ በከተማዎች ውስጥ (ምንም እንኳን በየቀኑ እንደሚከፈቱት ግሮሰሪ ቤቶች ባይሆኑም) “መፅሐፍትን” የምናገኝባቸው ሥፍራዎች እየተፈጠሩ ነው። ለዚህ ምሳሌ በከተማችን ጎዳናዎች ከሚዘዋወሩት ነጋዴዎች ባሻገር በሰፋፊ ሥፍራዎች ላይ የሚዘጋጁ የመፅሐፍት አውደ ርእዮችን ማየት ይቻላል። ስለዚህ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ከሚለው መዝሙር ወጥተን ማንበብ እንጀምር” የሚለው የማጠቃለያ መልዕክታችን ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013