የሠፈራችን ጋሽ ሳህሉ ቆዳቸው ነጣ ነጣ፣ ገርጣ ገርጣ ካለ አሊያም ጥፍራቸው ወይም ጣታቸው የመሰብሰብ ምልክት ካሳየ ሳይውሉ ሳያድሩ ነው ወደ ህክምና የሚሄዱት። እጅግ በጣም ሲበዛ የሐኪም ቤት ደንበኛ ናቸው፤ ለትንታ ሁሉ ወደ ሕክምና ይሄዳሉ።
በቅርቡ እንኳን ለምርጫ ቀን ጥፍራቸው ላይ የተቀቡት ቀለም ቢፈትጉት ቢፈትጉት አልጠፋ ብሏቸው ጤና ጣቢያ ሄደዋል። አስባችሁታል፤ ቀለም ከጥፍር ላይ ለማስለቀቅ ካርድ አውጥቶ ለምርመራ ወረፋ ጥበቃ መቀመጥን። ብቻ ይኼ ለጋሽ ሳህሉ ወሳኙ ጉዳይ ነው። አንዲት ነጥብ ቆዳቸው ላይ እንድትታይ አይፈልጉም።
ጋሽ ሳህሉ ደጋግመው ሐኪም ቤት ከመመላለሳቸው የተነሳ እርሳቸው የሚሄዱበት ጤና ጣቢያ በዓመት ይህን ያህል ታካሚ አክመናል በሚለው ሪፖርት ውስጥ እርሳቸውን እንደ 10 ሰው ሳይጠቀም ይቀራሉ ብላችሁ ነው። ምክንያቱም ጋሽ ሳህሉ ህመመቻው የከፋም ሆነ መጠነኛ ከሐኪም ቤት አይጠፉም። እኔን የሚገርመኝ ግን የእርሳቸው ደጋግሞ ሐኪም ቤት መሄድ አይደለም። ለጤና ሲባል እንኳንስ ሐኪም ቤት ሌላስ ቦታ ቢኬድ ምን ችግር አለው። ነገር ግን የሕመማቸው አንድ ዓይነትነት ያስገርማል። በዚህ ዓመት ብቻ ሐኪም ቤት በሄዱ ቁጥር አምስት ጊዜ ታይፎይድ ተብለዋል።
ልብ በሉልኝ አምስቱንም ጊዜ ታይፎይድ ሲባሉ አምስት የተለያየ የምልክት ዓይነት ነበር የታየባቸው። ይኼ ታይፎይድ ግን መጥፎ ነው ለካ እናንተዬ። ሊያም ከፈለገ አይን ሁላ ሊያሳክክ ይችላል። እኔ አይደለሁም ያልኩት። ያው ጋሽ ሳህሉ ከታየባቸው ምልክቶች አንዱ አይን ማሳከከ እንደነበር ነግረውን ነው። ነገሩ “በሕክምና ባለሙያዎች” ሲጣራ ነው አሉ ታይፎይድ ሆኖ የተገኘው።
እኔ የምለው የኢትዮጵያውያን በሽታ ታይፎይድ ብቻ ነው እንዴ? እኔም እንደ ጋሽ ሳህሉ በዚህ ዓመት ሁለት ጊዜ ሐኪም ቤት ስሄድ፤ ታይፎይድ ነው ተብዬ ነበር። በእርግጥ ስለተጠራጠርኩ ሌላ ሕክምና ቦታ ስሄድ ደግሞ የጨጓራ ባክቴሪያ ነው አሉኝ። ሦስተኛ ቦታ ደግሜ ሌላ በሽታ ከሚሰጡኝ አልኩና በዚሁ ፀንቼ ከፈጣሪ ዕርዳታ ጋር ተሻለኝ። ከዚያ በኋላ ግን ሐኪም ቤት መሄዱን እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ። እና ሕመም ቢሰማኝም የሥቃዩ መጠን በተሳሳተ ሕክምና ከሚሰጠኝ መርፌ ይሻለኛል። ብሄድም ከታይፎይድ ውጭ አይሆንማ። ወይ ታይፎይድ በሽታው ራሱ በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጥ እኮ ነው የሚመስለው።
እንዲያውም አሁን…አሁን አብረው ሰው የሚይዙት መንትያ ይመስል ታይፈስና ታይፎይድ ተባልኩ ይላል ብዙ ታማሚ ሰው። የሥማቸው የመጀመሪያ ሁለት ፊደሎች መመሳሰላቸው ምናልባት ወንድማማች ወይም አብሮ አደግ ባልንጀራ አስብሏቸው ይሆን? በዚያ ላይ ሰው የተባለውን መቀበል እንጂ የመጠየቅ ባህል የለውም። ምናልባት የሌላውን በሽታ ምንነት ስለማንረዳ ይሆን እንዴ ከመጨቃጨቅ ብለው ታይፎይድ ነው የሚሉን?
አገራዊውን ሪፖርት ስላላደመጥን ይሆናል እንጂ በየዓመቱ ታይፎይድ “የሚያዙ” ሰዎች ቁጥር የት የየለሌ ሊሆን ይችላል። የሚያዙ የሚለውን አላልታችሁም አጥብቃችሁም ማንበብ በዚህ ዐረፍተ ነገር አውድ ውስጥ የተፈቀደ ነው። ምን ላድርግ ሕክምናው ነው እኮ የሚያስወራኝ። አንዳንድ ጊዜ ተፈንክተህ ወደ ሕክምና ስትሄድ ታይፎይድ ነው ሊሉህ ይችላሉ።
እንግዲህ እንዲህ የመሰለው የሕክምና ጉዳይ ለብዙዎች ትምህርት የሚሰጥ ነው። በሥጋችን በጽኑ በሽታ ክፉኛ ስንታመም በቅጡ ሳይመረምሩን ታይፎይድ ነው የሚሉን ለምን ይሆን? መቼም ሥራ ለማቅለል በጤና አይቀለድም። ቢቀለድ እንኳን የትኛው የምርመራ ውስብስብነት ነው ጊዜያችንን የሚወስደው። ሕዝቡ እንደሆነ በቀጠሮም የሚታከም ምስኪን ነው።
አንድ ሰው በበሽታ እንደተጠቃ ተገንዝቦ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት ይሄዳል። ሐኪሙም እነዚህን በሽታውን ለማወቅና የተቃወሰውን ጤንነት ለመመለስ ከልብ ይሰራል። ይኼን የሚያደርጉና የሙያ ሥነ ምግባርን የተላበሱ የሕክምና ተቋማትም ባለሙያዎችም እንዳሉ እገነዘባለሁ። ነገር ግን ለፍልጠትም፣ ለቁርጥማትም፣ ለውጋትም፣ ለመሸቅሸቅም…ለእነዚህና የመሳሰሉት እንዲሁም እነዚህን ላልመሳሰሉት ምልክቶች ታይፎይድ ነው የሚሉ ደግሞ ብዙዎች ናቸው።
በእርግጥ የሕክምና ባለሙያ አይደለሁም። ችግሩ ግን በደንብ ይገለጽልኛል። የጤና ሙያተኞቻችንን ልፋት እያየሁ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት ማለፍ እችል ነበር። ነገር ግን ታይፎይድን በሌለበት መጥራት አንዲያቆሙ ማሳሰብ ስለምፈልግ ነው። የኔ ፍላጎት ሐኪም ተረኛውን በቅደም ተከተል ጠርቶ እያስገባ በትንሽ ደቂቃ ቃላዊ ምርመራ ታይፎይድ ነው የሚል ሳይሆን ከታማሚው በፊት የታመመውን የህክምና ሥርዓት እንዲያክምልኝ ነው። ለሁሉም በሽታ ታይፎይድን የሚያስጠራ ተሕዋሲያንን ከአገራችን እንዲያስወጣልኝ ነው።
ብዙ ጊዜ ሐኪሞች በተለይ ከጥቅም ጋር በተያያዘ ሰልፍ ወጥተው መፈክርም ሲያሰሙ እናያለን፤ እንሰማለን። በርግጥ እነርሱ ሰልፍ ሲወጡ ታካሚውም በእነርሱ ምክንያት ለሚደርስ የሙያ ሥነ ምግባር ሰልፍ መውጣት ያምረው ነበር። ደግሞ በኛ ላይ አመፃችሁ ተብለው ወለል ላይ ተኝተው ለመታከም ቢገደዱስ። ጎመን በጤና። ይልቅ ሠልፍ ከመውጣት ወደ አስተዳደር ቢሮ መግባት አይሻልም ወይ። ጤነኛ ዓሣ ለመብላት የፈለገ ዓሣ አጥማጅ አስቀድሞ የባሕሩን ጤንነት መጠበቅ ይኖርበታልና። ምን ይታወቃል አንዳንድ ልበ ብርሃን ሐኪሞቻችን እንዲሰለቹና በማን አለብኝነት እንዲሰሩ የሆነው በተቋሞቻቸው ብልሹነት ሊሆን ይችላል። በርግጥም የታመመን ከማከም በፊት መከላከልን መሠረት ያደረገ ሰፊ ሥራ መሥራት ከሁሉ በላይ ይመከራል።
የሙያ ሥነ ምግባርን የሚጥሱ ራሣቸው ከደዌያቸው በቶሎ ታክመው ይድኑ ዘንድ ሁላችንም የማናግዛቸው ከሆነ በሕይወታቸው ተስፋ ይቆርጡና ነገረ ሥራቸው ሁሉ የጥፋት ይሆናል። ተሥፋ የቆረጡት ደግሞ በሽታቸውን ወደ ጤነኞች ማስራጨት እነርሱን የሚያድናቸው ይመስላቸዋል። የዚያኔ በሽታህ ቀለል ተደርጎ በታይፎይድ ብቻ የሚታለፍ አይሆንም። ታይቶ የማይታወቅ በሽታ ሰጥተውህ ያልሆነ መድሃኒት ቅመህ ታርፈዋለህ።
በሉ ለዛሬ በዚሁ ላብቃ አውራ ጣቴን አመመኝ። ታይፎይድ ነው መሰለኝ። ከተረፍኩ ቀጣይ እንገናኛለን። ቸር ሠንብቱ።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013