መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል። የመንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ትግራይን ለቆ እስከ መውጣት የዘለቀ መሆኑን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ጨምሮ በብዙ አገሮች ተደግፏል። አሸባሪው ሕወሓት በእርሱ ሃይል የተገኘ ድል እንደሆነ በማስመሰል ፈንድቆ ህጻናትን ወደ ጦርነቱ ለመሳብ ጥረት አድርጓል። አሸባሪው ህወሃት በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ ሆኖ ህጻናትን፤ አረጋውያንና የኃይማኖት አባቶችን ለጦርነት እያሰለፈ ይገኛል።
ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው አቶ ቶፊቅ አብደላ የተባሉ አንባቢ ወደ ዝግጅት ክፍላችን በመደወል በህወሃት የሚከናወነው ህጻናትን ለጦርነት የማሰለፍ ተግባር ተጠያቂነት የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ በማንሳት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ እንድንሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል። እኛም በጉዳዩ ዙርያ ባለሙያ አነጋግረን የሚከተለውን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።
ህፃናት ለግጭትም ሆነ ለጦርነት መመልመል ክልክል መሆኑን የሚያመላክቱ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው እና ያፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ህግጋቶች አሉ። ከእነዚህ ህግጋቶች መካከል በህፃናት መብት ላይ ያተኮሩ ስምምነትን (convention on the rihgts of the child (CRC) የሚባለው ተጠቃሽ ነው። ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት አካል ነች። ይህንን ስምምነት በዓለም ከ190 ያላነሱ አገራት ፈርመዋል። እንደውም በጊዜው ሶማሌያ እንደ አገር ባለመቆጠሯ አሜሪካን ደግሞ ከዚህ የተሻለ የህፃናት መብት ህግ አለኝ በማለቷ ካለመፈረማቸው ውጪ ሁሉም የዓለም አገራት ሰነዱን ፈርመዋል። በዚህ ስምምነት ላይ ህፃናትን 15 ዓመት ሳይሞላቸው ለጦርነት መመልመል እና ማሰለፍ ይከለክላል የሚሉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ሙሉጌታ አካሉ ናቸው።
እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለፃ፤ ከዚህ ስምምነት በተጨማሪ በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እ.አ.አ በ1949 የተደረገው ስምምነትም፤ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ቡድኖች 15 ዓመት ያልሞላቸውን ህፃናት መመልመል እንደማይቻል ይከለክላል። ይህ የጄኔቫ ፕሮቶኮል ሲሆን፤ አገራቱ ለስምምነት ከፈረሙ በኋላ የሚገቡት ግዴታ ነው።
የጣሊያኗ ሮም ላይም እ.አ.አ በ1998 የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነት (ICC) የኢንተርናሽናል ክሪሚናል ኮርትም በተመሳሳይ ሁኔታ 15 ዓመት ያልሞላቸውን ህፃናት ለጦርነት ማሰለፍ፤ የጦር ወንጀል ነው ይላል። ህፃናትን ለጦርነት መልምሎ ያሰለፈ ቡድን በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀው መሆኑን ያስቀምጣል ያሉት የህግ መምህሩ፤ ይህ የጦር ወንጀለኝነትን ለመቆጣጠር የወጣ ስምምነት መሆኑን ያብራራሉ።
በተጨማሪ እንደገና ተሻሽሎ የህፃናቱን ዕድሜ ከ15 ወደ 18 የሚያድግበት ሁኔታም ተፈጥሯል ያሉት የህግ ምሁሩ በህፃናት መብት ላይ ያተኮረ ስምምነትን (convention on the rihgts of the child (CRC) ተከትሎ የመጣ ፕሮቶኮልም መኖሩን ይገልፃሉ። አንድ ስምምነት ከወጣ በኋላ የሚቀርብ ሰነድ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ስምምነት የተቀበሉ አገራት እንደአስፈላጊነቱ ሊቀበሉትም ላይቀበሉትም የሚችሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ፕሮቶኮል ምናልባት ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፤ የፈለጉ አገራት ያንን ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉታል ያልፈለጉትም ይተውታል ማለት መሆኑን ያስረዳሉ። በዛ መሰረት በ2ኛነት የመጣውን ፕሮቶኮል 15 ዓመት የነበረውን ለጦርነት የመመልመል ዕድሜን ወደ 18 ዓመት አሳድጎታል ይላሉ።
እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለፃ፤ በህፃናት መብት ላይ ያተኮሩ ስምምነት አስገድዶም ሆነ በፍቃደኝነት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለጦርነት መመልመል እና መጠቀም ክልክል መሆኑን ያስቀምጣል። የመጀመሪያውን ስምምነት የተቀበሉ የተወሰኑ አገራት ባይቀበሉትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ተቀብለው ፈርመዋል። መንግስታዊ ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ሃይላት ህፃናትን ማሰለፍ አይችሉም፤ ከማለት አልፎ መንግስት ላይ ግዴታ የሚጥል መሆኑን ያብራራሉ።
የህግ መምህሩ እንዳሉት፤ መንግስት ራሱ ህፃናትን ለጦርነት እና ለግጭት ካለመመልመል ባለፈ፤ ይህንን በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ያስቀምጣሉ። መንግስት የቻለውን ያህል እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በመጥቀስ፤ ህግን ማውጣት፣ በወንጀል መቅጣት እና መከልከል እና ጥፋተኛ የሆኑትን ተጠያቂ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበትም ያመለክታሉ።
ሌላው ኢትዮጵያ የፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተጠቃሹ አፍሪካ አቀፍ ስምምነት ነው። በአፍሪካ ህብረት አባል አገራት መካከል የተካሄደው ይህ ስምምነት በህፃናት ደህንነት እና መብት ላይ የሚያተኩር ስምምነት ነው። በዚህ ስምምነት ላይ መንግስታት ማናቸውንም አይነት ህፃናትን ለጦርነት መልምሎ በግጭት እና በጦርነት ላይ ማሳተፍን ይከለክላል። ይህንን የፈረሙ መንግስታት ህፃናትን ላለመመልመልና በግጭት እና በጦርነት ውስጥ ላለማሳተፍ ቃል ገብተዋል። በአገር ውስጥ ያሉ ቡድኖች ህፃናትን ሲመለምሉ ተጠያቂ ለማድረግም መንግስታት ፈርመው ቃል ገብተዋል። በአፍሪካ ቻርተር አንቀፅ 2 ‹‹ህፃን ማለት ማንኛውም 18 ዓመት ያልሞላው ሰው ነው›› የሚል መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የጦርነት ህግ ላይም በጦርነት ጊዜ መከተል ስለሚገባው ህግ የሚጠቀሰው የ1949 የጄኔቫ ስምምነትም ሁሉም ያንን የፈረሙ የመንግስት አካላት፤ ህፃናትን በአግባቡ መንከባከብ እንዳለባቸው እና የህፃናትን መብት በሚገፋ መልኩ አስገድዶ ለጦርነት ካለመመልመል በተጨማሪ በፈቃደኝነትም ቢሆን ህፃናት መመልመል እንደሌለባቸው ያስቀምጣል።
አለም አቀፉ የአሰሪ እና ሰራተኛ ድርጅትም (ILO) ይህንን የህጻናት ስምምነት እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ለአባል አገራቱ አስፈርሟል። ይህ ስምምነት ማናቸውም አገራት አሰቃቂ የሆኑ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛን የሚከለክል ሲሆን፤ በሥሩ ከ18 ዓመት በታች የሆኑትን ህፃናት በባርነት ውስጥ መክተት እንደማይቻል ያስቀምጣል። ህፃናትን መሸጥ፣ በዕዳ ማስያዝ፣ ያለፍላጎታቸው አስገድዶ ሥራ ማሰራት በማለት በዚህ ውስጥ መልምሎ በጦርነት ማሳተፍን ይከለክላል ብለዋል።
ይህንን ስምምነት የፈረሙ አገራት መንግስታት ይህንን ስምምነት በሚጥሱ አካላት (ቡድኖች) ላይ እርምጃ መውሰድ አለባቸውም ይላል። ህጻናትን በመመልመል ወደ ጦርነት የሚያሰማሩ ቡድኖችን መንግስታት እየተከታተሉ እርምጃ እንዲወስዱ የሚበረታታ ሲሆን፤ ይህንን በሚያደርጉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስገድድ መሆኑን አመልክተዋል። እነዚህን ስምምነቶች ኢትዮጵያ ያፀደቀች መሆኑን በማስታወስ፤ በኢትዮጵያ ህገመንግስት ደግሞ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው እና ያፀደቀቻቸው ስምምነቶች የአገሪቱ የህግ አካል ናቸው የሚል መሆኑን አብራርተዋል።
ስለሆነም አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን በማስገደድ በጦርነት እንዲሳተፉ እያደረገ ያለው ኢሰብአዊ ድርጊት በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በህግ የሚያስጠይቀው ነው።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013