የአሸባሪው ህወሓት ነገር እያደር አስገራሚ እና አሳፋሪ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ አዳዲስ ነውር በመፈጸም በራሳቸው የተያዘውን ሪከርድ ተግተው በማሻሻል ላይ የሚገኙት ህወሓቶች አሁን ደግሞ እዚያው መዝገብ ላይ አዲስ የነውር ታሪክ ጨምረዋል፡፡ ጨካኙ ጁንታ እንኳን ጦር ሜዳ ወርዶ ለመዋጋት የጦርነት ፊልም ለማየት እንኳን ያልደረሱ ህጻናትን ሰብስቦ ወደ ጦር ሜዳ ልኳል፡፡ የጁንታው አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳም ይህን ወደ ራያ የላኩትን የህጻናት ስብስብ‹‹ በትግራይ እናቶች ስም የሰየምነውን ዘመቻ የሚፈጽም “ጦር” ነው›› ብሎታል፡፡ የትግራይ እናቶችን በዚህ መልኩ ያሞገሱት የትግራይ እናቶች በውድም ሆነ በግድ እነዚህን አፍላ ህጻናት ለመስዋእትነት አሳልፈው ስለሰጧቸው እንደሆነ በይፋ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግሯል፡፡ ደግነቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሁን ላይ በትግራይ ክልል የሚያካሂደውን ዘመቻ ማቆሙ በጀው እንጂ ድርጊቱስ ብዙ ሀጢያት የሚያስከትል ተግባር ነበር፡፡
ነገሩ አስገራሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ የሚደረገው በእድሜያቸው መባቻ ላይ የሚገኙ ሽማግሌዎችን በስልጣን ለማቆየት መሆኑ ነው፡፡ ጁንታው ለዶሮ በሽታ በሬ ማረድን መርጧል፡፡ ለዶሮው ጤና ብሎ የሚያርስበትን እና የሚያበራይበትን በሬ የሚያርድ ገበሬ ሞኝ ወይም እብድ ነው፡፡ ህወሓት እንደዚያ ነው። በእድሜያቸው መገባደጃ ላይ የሚገኙ እና መቃብራቸው በቅርበት የሚታያቸው የህወሓት ሰዎች ግን ነገ በጉንፋን ወይም ራስ ምታት ለሚጠናቀቅ ህይወታቸው የነገ የትግራይ እና የኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑ ህጻናትን ለመሰዋት ቆርጠዋል። አሳዛኝ ነው፡፡
ለህወሓት ትውልድ እየገበሩ ሥልጣንን ማስቀጠል የተለመደ ነው፡፡ የመጀመሪያው ትውልድ የተገበረው በትግል ወቅት ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት ከሆነ 60ሺ ሰው በዚያ የትግል ወቅት መስዋእት ሆኗል፡፡ ያ ሁሉ ትግል ግን በመጨረሻ ያስገኘው ነገር ቢኖር ጥቂት የህወሓት ባለሥልጣናትን ወደ ሚሊየነርነት ማሻገር ነበር፡፡ የቀረው ታጋይ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር በዊልቸር እየተገፋ አደባባይ እንዲወጣ እና የበዓል ማድመቂያ እንዲሆን ነበር የተፈረደበት፡፡ ሊያውም ከተረፈ፡፡ ሌላው የት እንደሞተ እንኳን የማይታወቅ ወጣት ግን የቀረው ለእናት አባቱ ማልቀሻ የሚሆነው ፎቶው ብቻ ነው፡፡
አንድ ትውልድ ያስበላው ህወሓት ሁለተኛ ለመድገም አላመነታም፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ዛሬ ላይ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የትግራይ ወጣቶችን ሰለባ አድርጓል፡፡ የብዙዎቹ መርዶ ገና አልተነገረም፡፡ የትግራይ እናቶች ገና የማዘኛ እረፍት አላገኙም፡፡ በዚህ ግን ብዙም መደነቅ የለብንም። ምክንያቱም ጁንታው ከዚህም በላይ ሊያስገርመን የቆረጠ ሆኗልና አሁን ደግሞ በአዲስ መንገድ ብቅ ብሏል፡፡ አዲሱ የነውር መንገድም ከቀጣዩ ትውልድ ተበድሮ ውጊያን የማስቀጠል ስልት ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ የህወሓት ሰዎች ከመጪው ትውልድ የተበደሩት ገንዘብ አይደለም፡፡ ሀሳብም አይደለም፡፡ ህይወት ነው፡፡ ተስፋ ነው፡፡ አላማ ነው፡፡
አሁን የመጪው የትግራይ ትውልድ በጁንታው ምክንያት ወደጦርነት ገብቷል፡፡ ሊዋጋም እየሞከረ ነው። በህይወት ከተረፈ ከፊቱ ሊኖር የሚችለው ነገር አስደሳች አይደለም፡፡ ያኔ በ60ዎቹ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ በረሃ የወረዱት የጁንታው መሪዎች ከዚያ ሲመለሱ ሥልጣንን እና ሀብትን አግኝተዋል፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ የደቀቀች ትግራይን በዊልቸር ሆነው ተረክበዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ጦር ሜዳ ሄዷል። እድለኛ ሆኖ ከጦርነቱ በህይወት ከተመለሰ የሚያገኘው በድጋሚ የደቀቀች ትግራይን እንጂ ሥልጣንን አይደለም። እድሜው ባክኗል፡፡ አላማውን ተነጥቋል፡፡
በነጌታቸው ረዳ መሪነት ወደ ጦር ሜዳ እየተጋዘ ያለው የትግራይ አፍላ ወጣት አሁን ላይ መማር ፤ መመረቅ ፤ ሥራ መያዝ ፤ ማግባት ፤ መውለድ፤ ቤት መስራት አላማው አይደለም፡፡ ምክንያቱም አላማውን በጁንታው አመራሮች ተነጥቋል፡፡ እስኪርቢቶህን አስቀምጥ ጠመንጃህን አንሳ ተብሏል፡፡ ከአሁን በኋላ ትልቁ ተስፋው ከዚህ ጦርነት በህይወት መውጣት ነው፡፡ አለመሞት የህይወትህ ትልቁ አላማ ከሆነ ደግሞ ትልቅ ችግር ውስጥ ነህ ማለት ነው፡፡ ጁንታው የትግራይን ወጣት የከተተው እዚህ ስሜት ውስጥ ነው፡፡
እስኪ ወደፊት ጥቂት በሀሳብ እንጓዝና የሚሆነውን እንገምት፡፡ ከ10 አመት በኋላ ይህ በጦርነት የህይወት አላማውን ያጣ ወጣት በ30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ በመቀሌ ጎዳናዎች ያለ አላማ እንዲሁ ሲንገላወድ እናስበው። ተቀጥሮ እንዳይሰራ የትምህርት ጊዜውን በጦር ሜዳ አሳልፎታል፡፡ ትዳር እንዳይዝ ስራ የለውም። ያለው ብቸኛ አማራጭ በግድ በገባበት ውትድርና መግፋት ነው። አንድ ክልል አንድ ሙሉ ትውልዱን ወታደር ሊያደርግ ይችላል? ከባድ ነው፡፡ እየተኬደበት ያለው መንገድ ግን ይሄ ነው፡፡
ውትድርናው ቀርቶ ወደመደበኛ ህይወቱ እንዲሁ ቢመለስስ? ይሄም ከባድ ነው፡፡ ይሄን የሚለው ደግሞ ሳይንስ ነው፡፡ አይደለም እነዚህ ያለ እድሜያቸው ወደጦርነት የገቡ ህጻናት ቀርቶ በትክክለኛ እድሜያቸው ተገቢ ስልጠና ሰልጥነው የሚሊተሪው አባል የነበሩ ወታደሮች እንኳን ከሚሊተሪ ህይወት ወደ ሲቪል ህይወት ሲመለሱ ከፍተኛ የመዋሃድ ችግር ያጋጥማቸዋል። በሰለጠነው ዓለም ይህ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ ለዘመቻ ሄደው ከተመለሱ ወታደሮች ቢያንስ ሩቡ ከማህበረሰቡ ጋር ለመዋሃድ እንደሚቸግራቸው ጥናት አመላክቷል፡፡ ልብ አርጉ ይህ የሚሆነው በባለጸጋዋ እና ለወታደሮቿ ከፍተኛ እንክብካቤ በምታደርገው አሜሪካ ነው፡፡ የፒው ሪሰርች ማእከል የ2011 እ.ኤ.አ ጥናት እንደሚያመለክተው በቂ የቀለም ትምህርት የሌላቸው እና በጦር ሜዳ ብዙ ዘግናኝ ነገር ያዩ ወታደሮች በተለይ ድህረ ጦርነት ከማህበረሰብ ጋር ለመዋሃድ እጅጉን እንደሚቸግራቸው አረጋግጧል። በጥናቱ ውስጥ ከማህበረሰብ ጋር ለመዋሃድ ቸገረን ካሉት ወታደሮች መሀከል አብዛኞቹ ደግሞ እነዚሁ ብዙ የቀለም ትምህርት የሌላቸው እና በጦር ሜዳ ብዙ ሰቆቃ ያዩቱ ናቸው። እንግዲህ አሁን በትግራይ ወደ ጦርነት እየተማገዱ ያሉ ህጻናት ነገ እድል ቀንቷቸው በህይወት ከተመለሱም ዛሬ በውድም ይሁን በግድ ወደ ጦርሜዳ ከላካቸው ህዝብ ጋር ለመዋሃድ የሚገጥማቸው ችግር እጅግ የበዛ እንደሚሆን ይህ አመላካች ነው፡፡ ብዙዎቹ በአካል ቢመለሱ እንኳ በስነ ልቡና ግን ከጥቅም ውጭ ሆነው ነው የሚመለሱት፡፡ በአጭሩ የህወሓት አሉታዊ ሌጋሲ ወደፊትም ገና ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
ህወሓት አሁን የሽብር ቡድን ነው፡፡ በዚህ ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ ደግሞ አምሳያው የሚሆኑ ብዙ የሽብር ቡድኖች አሉ፡፡ ከነዚህ መሀከል አንዱ የዩጋንዳው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ ነው፡፡ ይህ ቡድን ልክ እንደ ጁንታው ሁሉ በሰሜናዊ ዩጋንዳ የሚገኝ ሲሆን የዩጋንዳን ማእከላዊ መንግሥት ለመጣል በሚያደርገው ጥረት እስከ 25ሺ የሚደርሱ ህጻናትን በውትድርና ተጠቅሟል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጠቀሳቸው አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ይህ ከዩጋንዳም አልፎ በደቡብ ሱዳን ፤ በዴሞከራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተስፋፍቶ የነበረ ሀይል ከነበረው ወታደር 90 በመቶው በህጻናት ነበሩ፡፡ ይህ ቡድን ዛሬ ላይ የሽብር ቡድንነቱ ታውቆ መሪዎቹም በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት የሚፈለጉ ናቸው፡፡
ወደ ህወሓት ስንመጣ ግን ነገሩ ተቃራኒ ነው፡፡ የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚን ሽብርተኛ ያለው እና መሪዎችን ለክስ የሚፈልገው ዓለም ጁንታውን ግን የሚያበረታታ ሆኗል። ለዚህም ጥሩ ማሳያው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ነው። ጋዜጣው ጠመንጃ የታጠቁ ህጻናትን ፎቶ በተጠቀመበት ዘገባው ላይ ህጻናቱን “highly motivated young recruits” (ለውጊያ የተነሳሱ ወጣት ምልምሎች…) በማለት ነውሩን አንቆለጳጵሶለታል፡፡ ለወትሮው እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ያሉ ጽንፈኛ የሊበራል ሚዲያዎች ለቤተሰቦቻቸው ውሀ የሚቀዱ ወይም ከብት የሚጠብቁ ህጻናትን እንኳ “ጉልበታቸው ተበዘበዘ” ብለው የሚጮሁ ሲሆን መሳሪያ የታጠቁ ህጻናትን ግን “ተነሳሽነት ያላቸው” ብለው ያሞገሱበት ምክንያት ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለምን? አላማቸው ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ምዕራባውያኑ የሰብዓዊነትን ጉዳይም ሆነ የህጻናት መብትን ጉዳይ የሚያነሱት ለነሱ ጥቅም በሚበጅ መልኩ ሲጠቅም ብቻ እንደሆነ ነው፡፡
ምዕራባውያኑ አሁን የጁንታው ዋና ደጋፊ ናቸው። ጦርነቱን አሸነፈም ተሸነፈ፤ የትግራይ ወጣት ሞተም አልሞተ፤ መጪው ትውልድ ከሰመም አልከሰመ ጦርነቱን አራዝሞ ኢትዮጵያን እስካዳከመላቸው ድረስ ማንኛውንም አይነት ቴክኒክ ቢጠቀም ግድ የላቸውም። አሁን እየተደረገ እንዳለው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በዝምታ ቦታውን ቢለቅ” በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ባልሥልጣኑ ጎሬላ ተዋጊዎች ተሸነፈ” ብለው ዘገባ ይሰራሉ። ሠራዊቱ መልስ ቢሰጥና ቢደመስስ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሠራዊት ንጹኃንን እየገደለ ነው” ብለው ይከስሳሉ። ስልታቸው ሟችም ሲባል አቤት ገዳይም ሲባል አቤት የማለት ነው፡፡
ብዙዎች መሳሪያ የያዘ ህጻን እስካላዩ ድረስ ህጻናት ለውትድርና ጥቅም ላይ የዋሉ አይመስላቸውም፡፡ ነገር ግን የዩኒሴፍ ብያኔ እንደሚያመለክተው ከሆነ ህጻናት ለውትድርና የሚውሉት በተዋጊነት ብቻ አይደለም። በጥበቃ፤ በመል እክተኝነት ፤ በሰላይነት ወዘተ…ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ ሴት ህጻናት ከሆኑ ደግሞ ከውጊያ እና መልእክተኝነት ባለፈ በምግብ አብሳይነት ፤ በጽዳት እንዲሁም በወሲብ ባርነት ሊያገለግሉም ይችላሉ፡፡ በዚህ አንጻር ካየነው ህወሓት ህጻናቱን በብዙ መልኩ ለውትድርና እንደተጠቀመ ማሳያዎች አሉ፡፡
ከትግራይ የሚወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት የጁንታው መሪዎች ህጻናትን ጨምሮ ንጹሃንን በጦር ጋሻነት ሲጠቀሙ ከርመዋል፡፡ ይህም ህጻናትን በዘወርዋራው በውትድርና መጠቀም ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንደኒውዮርክ ታይምስ ያሉ የጁንታው አጀንዳ አሻሻጮች የሚለቋቸው ፎቶዎች የሚያሳዩት ነገር ከሰለጠነው እና ከተደራጀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጋር እንዲዋጉ በጁንታው መሪዎች እየተመለመሉ ያሉት እድሜያቸው በዓለም አቀፉ ህግ መሰረት 18 ያልደረሰ አፍላ ወጣቶቸ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ መሀከል የሰብአዊ መብት ጠበቃ ነን ከሚሉት አንዳቸውም ጁንታውን ወንጀል ሰራህ ብለው ማንኛቸውም ሊወቅሱት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እየፈጸመ ያለው የእነሱን ምኞት በመሆኑ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ ማህበረሰቡን ዝምታ በሀፍረት እንደተመለከተችው አስታውቃለች፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በትናትናው እለት ባወጡት መግለጫም ይህን አሳፋሪ ክስተት በይፋ ገልጸውታል፡፡ ”ጁንታው ህጻናት እና ወጣቶችን በአደንዛዥ እጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ህጻናት ወታደሮች የመታደግ ግዴታ ወድቆበታል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በዚህ ዙሪያ ያሳየውን አሳፋሪ ዝምታ አስመልከተው ሲናገሩም “ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ስለ እርዳታና ረሀብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ ጁንታው ህጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል” ብለዋል። መንግሥት እነዚህን ሁሉ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ሁሉ በተገቢው መንገድ እንደሚያደርግም አሳውቀዋል፡፡
እርግጥ ለጁንታው መሪዎች ወቀሳ ቢመጣም ብዙም አያሳስባቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድም የተለመደ ታሪካዊ የጁንታው ባህል ስለሆነ ነው፡፡ ሁለትም የጁንታው መሪዎች ልጆች እዚህ ውስጥ ስለሌሉ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ሟች የሚሆነው የድሀ ልጅ ነው፡፡ ይህ የድሀ ልጅ ወደ ጦርሜዳው እንዲገባ ደግሞ በተቻለ አቅም ተስፋ የሚያስቆርጥ እና ጥላቻን የሚፈጥር ፕሮፓጋንዳ የተሰራበት ሲሆን አንድም በዚህ ፕሮፓጋንዳ አልያም በግዳጅ ወደዚህ መውጫ ወደሌለው ዘመቻ ገብቷል። ጁንታው አሁን ላይ ትናንቱን እና ዛሬውን አስበልጦ ቀጣዩን የትግራይ ትውልድ ለጊዜያዊ አላማው መጠቀሙን ገፍቶበታል፡፡ ነገዬን አላስበላም ብሎ መታገል የትግራይ ህዝብ ፋንታ ነው። ከዚያ ባለፈ የሀገር ህልውናን ማስቀጠል ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013