ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው የዓለም ሀገራት ጫና በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል:: በሰበብ አስባቡ ምክንያቶችን በመደርደር፤ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሳይቀር በመግባት በየጊዜው የተለያዩ ጫናዎች ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሙከራ እየጨመረ መጥቷል:: በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጣዊ ሁኔታው አለመረጋጋቱን ተከትሎ፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉት አይነት የዓለም ሀገራት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ ለመግባት ያላቸውን ፍላጎት እያንጸባረቁ ነው፡፡
ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ የፈለጉትን አጀንዳ ቀርጸው ሊያተራመሱን እና ሊያፈራርሱን አልመው ነበር፡፡ ሆኖም በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከመፍረስ አምልጠን፤ እንደተመኙልን ምስቅልቅላችን ሳይወጣ እንደተመኙት ሳይሆን ቀርቷል።
ህዝቦቿን በመከፋፈል ለዓላማቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉ ፈልገው እንደነበር ተግባራቸው የሚጠቆም ሲሆን፤ ማሳያውም በመንግሥት አሻባሪ ተብሎ ከተፈረጀው የህወሓት የጥፋት ኃይል ጋር ወግነው በመደገፍ በመንግሥት ላይ ጫና ለማድረግ የተደረገው የአሜሪካ እርምጃ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡
ሆኖም ግን በዚህ ሂደት ሀገር እንዳትፈርስና እንድትቀጥል በመንግስት በኩል የተደረገው ጥረት ማንሳት አይፈልጉም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊና ነጻ ምርጫ መደረጉ ያስከፋቸው ይመስል፤ ስለምርጫው ምንም መናገር አይፈልጉም፡፡ ምርጫው በዘፈቀደ እንደቀልድ የተገኘ ድል የመጣ በማስመሰል፤ ስለእውነታው መናገር አይፈልጉም፤ የሚፈልጉት ጉዳይ ሆኖ ቢሆን ኖሮ የራሳቸው አጀንዳ አድገው ለያዥለገናዥ አስቸግረው ባወዳደሱ እና ባቆለጳጰሱ ነበር፡፡
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው ደግሞ ኢትዮጵያ ከድህነት እንዳትወጣ እና በነበረችበት የድህነት ጉድጓድ ውስጥ ተቀብራ እንድትቀር በመሻት የህዳሴ ግደብ ዋና አጀንዳ በማድረግ ግድቡ እንዳይሞላ መስራታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ህዝቦቿን ከድህነት ቀንበር ለማላቀቅ የሚያስችላትን ግድብ ግንባታ በራሷ አቅም ለመገንባት ቆርጣ መነሳቷ ያልጣማቸው በመሆኑ፤ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የምታደርገውን ጥረት ዋጋ ለማሳጣት እየሰሩ ነው፡፡ ለዚህም ነው ምክንያት እየፈለጉ በማ ያገባቸው ጉዳይ እየገቡ እኛ እናውቅላችኋለን እያሉ የሚያስቸግሩት::
እነኚህ ሀገራት ዓላማ ምንም ይሁን ምንም ከድህነት ለመላቀቅ በሩጫ ላይ ያላችን ሀገር መንገድ በማደናቀፍ ጋሬጣ እየሆኑ ይገኛሉ:: ታዳጊ ሀገራት ሁልጊዜ እጅ እጃቸውን እያዩ በልመና ደጅ እንዲጠኑ እንጂ በልጽገው ማየት በፍፁም አይሹም:: ለዚህ ነው፤ የተግባራቸው ደጋፊና ተባባሪ እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩት መንግሥት መፈለጋቸው:: ከጎናቸው ሳይሆን፤ በተቃራኒው ወገን ቆሞ የሀገር ህልውና ጥቅም ለማስቀደም የሚሮጥ ላይ ማዕቀብ በመጣል የሚሳድሩት ጫና አይጣል፤ አያድርስ ያሰኛል:: አሁን ላይ በዓለም አደባባይ በጉልህ እየታየ ያለው ይሄው ነው::
ይህቺ ሀገር ህዝቦቿን ከድህነት ጫንቃ ለማውጣት እያደረገችው ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባ እንጂ የሚያስኮንን አልነበረም፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በውስጥ ጉዳይ ዘልቆ ገብቶ መፈትፈት ግን የጤና አይደለም:: ሆኖም ግን ሃያላኑ እጃቸውን ረጅም በመሆኑ ያሻቸውን ለማድረግ ሞክረዋል:: አሁን ላይ ደግሞ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ለማደናቀፍ ጋሬጣ እየሆኑ ይገኛሉ ::
ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን ሀገራቸው በብዙ ውጥረት ውስጥ ብትሆንም ለሀሳባቸው አልተንበረከኩም:: ስለግድቡም ሆነ ስለሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ያለውን እውነታ በየጊዜው ለማስረዳት ሞክረዋል:: በተለይ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የግድቡ ግንባታ በማስተጓጎል በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። የግድቡ ተደራዳሪ በሆኑት ተፋሰስ ሀገራት ድርድሩን እንደፈለጋቸው በማድረግ ሲያጓትቱ በርካታ ጊዜያት ወስደዋል :: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያኑ አቋም ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ቆይተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት ግድቡ ሲጓተት፤ በፈለጉት መልኩ ሊያስኬዱት ባለመቻላቸው በነበረው ሁኔታ እጅግ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ ትናንት ግን ዛሬ አይደለምና ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚሹ የቁርጥ ቀን ልጆች የኢትዮጵያን አቋም ተጠናክረው አጉልተው አሳይተዋል፡፡ ያላቸውን አቋም በዓለም አደባባይ በተለያየ መልኩ በማስረዳት የዜግነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያውያኑ በአንድነት ያስተሳሰረው የህልውና መሠረት የሆነው የህዳሴ ግድብ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የእድገት መሠረት የሆነው ይህ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያን በእጅጉ ያስተሳሳረ ሆኗል። ግድቡ የአንድነትን መሠረት አጽንቶ ውጭ ያሉትም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከምንም ጊዜ በላይ ተስፋቸውን የጣሉበት ሆኗል፡፡ ለግድቡ ግንባታ ከትንሽ እስከ ትልቁ፤ ከህጻናት እስከ አዛውንቱ ያለው በሙሉ ያለውን እየሰጠ ለግድቡ እውን መሆኑ እየተጋ ይገኛል፡፡
ይህ ኢትዮጵያውያኑ እንደ አይን ብሌን የሚያዩትን ግድብ ግንባታው ሲጠናቀቅ አብዛኛው የሀገራችን ክፍሎች ጨለማ ተገፎ መብራት የሚያገኝበት ሲሆን፤ ሀገራቸውን ከድህነት ተላቅቃ ህዝቦቿም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ለአፍሪካዊያን ጥቅሙ የጋራ ነው፡፡ ከዚያ በላይ በርካታ ጥቅሞች ያሉት ነው። ለግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በመነሳት የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር ለሀገራችን ድምፅ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩት የዲያስፖራው ማህበረስብ ደግሞ ባሉበት ሆኖ የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር ከምንም ጊዜ በላይ በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ። በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውን በሀገራቸው ጉዳይ ቀልድ ብሎ ነገር አያውቁምና ሀገራቸው ጎን ቆመው የሀገራቸው ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሞገቱ እና ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በርካታ ሥራዎች በመስራት ላይ ይገኛሉ::
‹‹እጃችሁንን ከሀገራችን ላይ አንሱ›› ሲሉ በአደባባይ ሰልፍ በማድረግ እና በተለያዩ መንገድ ጥያቄ አቅርበዋል። የዓለም አቀፋ ማህበረሰብ ግብጽና ሱዳን በግደቡ ላይ የሚያቀርቡትን ውትወታ ለማዳመጥ የአፍሪካ ጉዳይ ለአፍሪካውያን እንዲታይ ከማድረግ ይልቅ ዓለም አቀፍ ጉዳይ አድርጎ በመቀበል በተባበሩት በመንግሥታት ድርጅት እንዲታይ መደረጉ ጭምር ተቃውመዋል። ተቃውሞውም ፍሬ አፍርቶ የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የዲያስፖራው ማህበረሰብ በግድቡ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ለመቋቋም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ይገልጻሉ። እንደዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ዲያስፖራውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግድቡ ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመቀልበስ የሚያደርገው ጥረት እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን መብት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግና በሌሎችም መንገዶች እየተጋ ይገኛል። የዲያስፖራው ዓለም አቀፉን ጫና ለመቀነስና ለመቋቋም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን የዜግነት ድርሻውን እየተወጠ መሆኑ ሊበረታታ የሚገባ ነው፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013