በመሰረቱ “ዩኒቨርሲቲ” እና “ችግር” (problem) የማይነጣጠሉ፤ አንዱ አንዱን ሲሸሽ፣ አንዱ አንዱን ሲያባርር፤ አንዱ አንዱን ሲፈልግ፤ አንዱ ከአንዱ ሲደበቅ ነው አጠቃላይ ህልውናቸው። ይህን ስንል ተፈላላጊዎች ናቸው እያልን ሳይሆን ፈላጊና ተፈላጊዎች ናቸው ማለታችን ነው።
በመሰረቱ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚው አላማው ባለሙያ ማፍራት፤ ተከታዩ ደግሞ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ በየደረጃው (ከአካባቢው ጀምሮ) ያለውን ማህበረሰብ ማገልገል ነው።
የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ሰነድ (2006 ዓ/ም) የከፍተኛ ትምህርት ተልእኮ “[…] የሚመጥኑ ብቁ ዜጎችን” ማፍራት መሆኑን ያስረዳል። በ”አላማዎች” ስር ከዘረዝራቸው ዘጠኝ ነጥቦች መካከል 2ኛው “በአገሪቱ ፍላጎት ላይ የተመሰረተና ትኩረቱ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሆነ ምርምርን ማራመድና ማጎልበት” ሲል፤ 4ኛው ደግሞ “በአገሪቱ የዕድገት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የማሕበረሰብና የማማከር አገልግሎትን ማበርከት” ይላል። ከዚህ አኳያ ከላይ “… ማህበረሰብ ማገልገል” ያልነው ትክክል ይሆናል ማለት ነው። ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም የተቋቋመበትን ምክንያት የሚያስረዳ ሰነድን ብንመለከተ “የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች …” የሚሉ ዝርዝሮች አለመታጣታቸውንም ልብ ይሏል።
ይህ ከሆነ “መሬት ያለው እውነትስ ምን ይመስላል?” የሚለውን እንመለከት፣ በተለይም “ከመወቀስ ወደ መወደስ” እየተሸጋገሩ ያሉ የሚያስመስሏቸው ተግባራት ላይ በማተኮር “ይበል” የሚያሰኘውን ይበል ለማለት፤ በተለይም ከራሳችን ጓዳ አንፃር ካሉን ዩኒቨርሲቲዎችና ከሚያበረክቱት የማህበረሰብ አገልግሎት አኳያ ከሚሏቸው፣ ከሚያደርጓቸው፣ ከሚያከናውኗቸው፣ ከሚያራምዷቸው (ረብ ያለውም ይሁን የሌለው) አይዶሎጂዎች እና ከመሳሰሉት አኳያ ሀሳብ መለዋወጡ ጠቃሚ ነው።
በተለይም በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገፅታ ምንድን ነው? ይዞታውስ? ዩኒቨርሲቲና ማህበረሰቡ፣ ተማሪውና አስተማሪው፣ ተማሪውና ተማሪው፣ አስተማሪውና አስተማሪው፣ ወንዱና ሴቱ፣ አስተዳዳሪውና ተዳዳሪው . . . ባጠቃላይም የዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ አባላት ያላቸው የእርስ በእርስም ሆነ የተናጠል ግንኙነት ምን ይመስላል? ወዘተርፈ ለሚሉት ጥያቄዎች በራሳቸው ሊጠኑና መፍትሄ ሊያገኙ የሚገባቸው ችግሮች ለሚመለከታቸው አስተላልፈን እንለፍ።
እንደ አጠቃላይ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ እናንሳ። ማንሳታችንንም “ለመሆኑ የአሁኑ ዘመን ዩኒቨርሲቲዎቻችን ይዞታ ምን ይመስላል?” በሚል ጥያቄ እንጀምር። መልሱንም የሚከተሉትን፣ ከተለያዩ ምንጮች (በተለይም ከሚዲያ) ያገኘናቸውን ዋቢ አድርገን እንጥቀስ።
“ዩኒቨርሲቲ ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ ‘ዩኒቨርሲቲዎች’”፣ “በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረው ምንድነው?”፣ “የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ ቤታቸው ለመላክ ለምን ወሰነ?”፣ “በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ጊዜያዊ ገደብ ተጣለ”፣ “ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑ ተገለፀ” (በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለቢቢሲ ገልጿል።)፣ “የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል መልቀቁን ተከትሎ በራያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ከ200 በላይ ተማሪዎች መንገድ አቆራርጠው ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ መግባታቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ገለጹ፡፡”፣ “ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በተካሄደው ውይይት […] ሰሞኑን በማንነታቸው ምክኒያት በንጹሃን የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በደረሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ህይወታቸው ያለፉና ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን በማሰብ የህሊና ጸሎት በማድረግ” ነው የተጀመረው ወዘተረፈ ወዘተረፈ (በ”የትምህርት ጥራት” በኩል ያለውን ችግርና የተሰጡ አስተያየቶች ሳናካትት በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሰላምና ፀጥታው ወቅታዊ ይዞታ ብቻ ይህንን ይመስላል – “ለጠቅላላ እውቀት ነው” የሚባለው የዚህ አይነቱ ወሽመጥ ከሆነ ነው ማለት ይቻላል)።
እዚህ ጋር “ይህ ሁሉ ሲሆን የምሁራኑ ሚና ምን ነበር?” የሚል ገራገር ጥያቄ ቢነሳ ትክክል ነው። “የት ነበሩ?”፣ “ከዚህ በላይስ ችግር (problem) አለ ወይ?” ቢባልም የሚያስወቅስ አይደለም። ብቻ ጥላሁን “ያለፈው ሁሉ አልፏልና / ዳግም ላይመለስ ሆኗልና …” እንዳለው ያድርግልን፣ እንዳይመልስ ሆኖ ይሄድልን ዘንድ እየተመኘን ወደ አሁናችን፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እያሳዩት ስላለው እመርታና እየሰጡት ስላለው ማህበራዊ አገልግሎት፤ እንዲሁም እያከናወኗቸው ስላሉት መጠነ ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎች አንዳንድ ሀሳቦችን እንሰንዝር። ይህን ስናደርግ ግን አላማችን ማመስገን ሳይሆን ማበረታታትና ሌሎች የዘገዩ ዩኒቨርሲቲዎችም ከቀደሙት ትምህርት እንዲወስዱ፤ ልምድ በመቅሰም እንዲከተሏቸው ለማድረግ በማሰብ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል።
ከላይ ጨረፍ ጨረፍ ያደረግናቸው እጅግ አስቸጋሪና አስጨናቂ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ይዞታዎች ጠቅላላ የመገናኛ አውታሮችን እንዳላጨናነቁ ሁሉ፤ ዛሬ ደግሞ ያ ተቀይሮ በሌላ፣ በሚያጓጉ ዜናዎች ተተክቶ በየእለቱ ቀንና ምሽት የሚያጠግቡና ተስፋም የሚሰጡ ወሬዎችን እየኮመኮምን እንገኛለን። ድምፃዊው “ዋናው ነገር ጤና / እናያለን ገና” እንዳለው የወደፊቱ ይበልጣልና ጅምሩ ሊበረታታ የሚገባው ነው።
እነዚህ አበረታች፣ ተስፋ ሰጪ እጅጉንም አጓጊና የአገራችንን እውነተኛ ታሪክ፣ እምቅ (ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽ፣ መንፈሳዊ ወዘተ) ሀብቶች፣ ያለንበትን የድህነት መጠን፣ ለማደግና ለመበልፀግ ማድረግ ያለብንን ጥረት፤ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ወዘተርፈ እያመላከቱ ያሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች፤ ከእነሱም ተነስተው እየተሰነዘሩ ያሉ የመፍትሄ (እና ምክረ) ሀሳቦች በእውነት አሁን ቢያስደስቱም እስከዛሬ አለመደረጋቸው ደግሞ እጅጉን ይቆጫል። በተለይ አገሪቱ ያሳለፈችውን መከራ (“መከራ” የሚለው በሚገባ የሚገልፀው ከሆነ) ዞር ብሎ ለተመለከተ፣ ምን ያህል ሀይ ባይ ሁሉ ጠፍቶ እንደነበር ላስታወሰ፤ በመፍትሄና ምክረ ሀሳብ ማጣት ድርቅ ምን ያህል ተመትታ እንደ ነበር ለተገነዘበ፤ በአዋቂና አላዋቂ መካከል ያለው ድንበር ሁሉ ተደበላልቆ፤ ገጣሚው “መለየት አቃተኝ ዳንሱን ከዳንሰኛ” እንዳለው አይነት ችግር ሁሉ ገጥሞን እንደ ነበር ላስታወሰ … እውነትም የእስከ ዛሬው ጥናት አልባ ዘመን፣ ምክረ ሀሳብ አልባ ዘመን፣ የምሁራን ፀጥ-ርጭታ ዘመን፣ የግጭትና ደም መፋሰስ ዘመን፣ የግብፅ አካኪ ዘራፍ ዘመን፣ የኢምፔሪያሊዝምና እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (እጅ ጥምዘዛ) ዘመን ወዘተርፈ ይቆጫል። ቢቆጭም አሁን ብልጭ ያለው ደግሞ ተስፋን ያጭራልና ይበል ያስብላል።
ለመሆኑ ይህንን የተጋነነ የመሰለ አስተያየት ስንሰጥ ማስረጃችን፣ መረጃችን፣ ማሳያችን፣ መግለጫችን ምንድን ነው? ስንል ምንም ሳይሆን የራሳቸው የዩኒቨርሲቲዎቹ ስራዎች ናቸውና እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን።
ክንውኖቹን ከ”እናት ዩኒቨርሲቲ”ው (አአዩ፣ ከቀዳሚነቱም ባለፈ በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንን ያሰለጠነው እሱ በመሆኑ የተሰጠው አክብሮት (ማህበራዊ ማዕረግ) ሳይሆን አይቀርም) እንጀምር። (ከዚህ በፊት አአዩ በተለይም በ1950ቹና 60ዎቹ ለአፍሪካ አገራት ወጣቶች ስኮላርሺፕ ይስጥ እንደነበር ፅፈናል።)
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን “የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም እያሳወቅን እንገኛለን።” የሚለውን፤ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሀነመስቀል ጠናን “ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በከተሞች እድገት፣ መሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ለዓለም እያስረዳን ነው። አስፈላጊውን እገዛም እያደረግን ነው።” አስከትለን ወደ ዝርዝሩ ስንሄድ የምናገኘው እውነት የአገራችን አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ለአገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ነው።
ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስንሄድ እንደ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲነቱ፣ ከሌሎቹ አኳያ ማለት ነው፣ የበርካታ ምሁራን ማፍሪያና መገኛ ሲሆን በጥናትና መርምር ዘርፉም ተሳታፊ ነው። በመሆኑም በቅርቡ “ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሀብት አኳያ ግድቦችን የመገንባት መብት አላት። […] ያላት የውሀ ሀብት ሰፊ ሆኖ እያለ ለምግብ ፍጆታ እየተጠቀመች ያለችው ገና 3 በመቶ ሲሆን 97 በመቶው በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ ነው።” የሚለውን በምሁራኑ አማካኝነት ለአደባባይ አብቅቷል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነትና ቀዳሚ ተሳታፊነት “የገናለኬ ዳዋ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ኦሞ ጊቤና የዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶችን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት 12 ተፋሰሶችን ለማልማት ጥናትን መሰረት ያደረገ ስትራተጂክ እቅድ እያሰናዳ” መሆኑን ከመስማታችን ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ወንዞች አካባቢ በአርሶ አደሮች መካከል አልፎ አልፎ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ እንደሆነም ተሰምቷልና ይበል ያሰኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም “ኢትዮጵያ ከውሃ ፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ የምትወጣው ሀብቱን አልምታ ብልፅግናዋን ስታረጋግጥ ነው” የሚለው አስተያየት (ሪኮመንዴሽን) የተገኘው በዩነቨርሲቲዎቻችን ከተጠኑ ጥናቶች ሲሆን ውጤቱም ብዙዎችን ያስማማ ሆኖ ተገኝቷል።
ዩኒቨርሲቲዎቻችን በዚህ ከቀጠሉ፣ የህዝብን ግንዛቤ ከመዳበር ባለፈ፣ ችግሮቻችን ወደ ዜሮ የመውረዳቸው፤ እንደ ጨው እየሟሙም የመትነናቸው ጉዳይ አጠራጣሪ አይሆንምና ተግባሩ የሚያበረታታ ነው። እንቀጥል …
“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል ተመሰረተ” የሚለው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜናን ስንፈትሽ ጎንደር ዩኒቨርሲቲንም በዜናው አካቶት እናገኛለን።
ወደ ስራ እንደ ገቡ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙት አንዱ የሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፣ (ከፊስቱላ ጀምሮ ሌሎችንም ያከናውናል) ስራዎችን በርካታ አገራዊና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን የቅርቡና ከወቅቱ ጋር የሚሄደውን እንኳን ብንገልፅ “በህዳሴው ግድብ ድርድር የግብፅና ሱዳን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም በተቻኮለ ውል ማሰር ነው” በሚል የዜና ርእስ የተገለፀውን ስራ እናገኛለን።
ከዚሁ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ርእሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሌላ ጥናት የምናገኘው ከእዛው አካባቢ ሲሆን እሱም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ “በህዳሴው ግድብ የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለመግታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር” እንደሚገባ ያሳሰበበት ጥናት ሲሆን ሌሎችም በዚሁ ላይ የየራሳቸውን ጥናት ያቀረቡ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ችለናል። (ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ፣ የኪነጥበብ (በተለይም ስነጽሑፍን በተመለከተ – ሀዲስ አለማየሁን ይዞ- በርካታ ስራዎችን እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን፤ ጥናትና ምርምሮች እንዴት ወደ መሬት መውረድ (ተግባር መለወጥ) እንዳለባቸውም በማጥናት ላይ መሆኑን ማስታወቁም አይዘነጋም። ምን ላይ እንደደረሰ ባናውቅም ጉዳዩ ግን ለአገራችን እጅግ ወሳኝ መሆኑን መግለፅ ተገቢ ነው።)
“የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎ ዘርፍ በተያዘው ዓመት ለመስራት ባቀዳቸው ስራዎች ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አደረገ፡፡” የሚለውን ቆየት ያለ የተቋሙ ድረ-ገጽ ዜናንም ሆነ፤ የመቱ ዩኒቨርሲቲ “የማህበረሰብና ማማከር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ውይይት መድረክ ያካሄደው የሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት የተጠናና የማህበረሰቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረ እንዲሆን ነው፡፡” የሚለውን ከተቋሙ የተገኘ መረጃን በማስታወስ በተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካኝነት በርካታና ወደ ለውጥ የሚያመሩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲም በአንድ ወቅት ከምርጥ የስንዴ ዘር ጋር በተያያዘ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ውጤታማ ማድረጉን ሰምተን አጨብጭበንለት እንደነበር እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
“በሰላም ጉዳይ ላይ የዜጎችን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ እየሰራሁ ነኝ” ከሚለው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ እስከ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እቅድ አውጥቶ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በጋራ እየሰራ ካለው አምቦ ዩኒቨርሲቲ፤ “በደረሰው ሰብአዊ ቀውስና የንብረት መውደም ምክንያት ከአጣዬና አካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እንደገና እንዲጠናከሩ የማድረግ ስራን እየሰራሁ እገኛለሁ” ከሚለው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እስከ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሳካ በምርምር በመደገፍ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው” እሚለው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ስንዘልቅ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ለውጥ መኖሩንና በለውጡም በርካታ አገራዊና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እንመለከታለን እንዲህ አይነቱ ተግባር ሲከናወንም ማመስገኑ ተገቢ በመሆኑ እናመሰግናለን። (አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን የሰራ ከመሆኑ አንፃር እራሱን ችሎ በሌላ ጽሑፍ ሊቃኝ የሚገባው መሆኑን መግለፅ ተገቢ ነው።)
እዚህ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያተኮርን ይመሰል እንጂ ሌሎች ፖሊ ቴክኒክን የመሳሰሉ ተቋማት፣ የግብርና ኮሌጆችና ሌሎችም በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለይ ሆለታን የመሳሰሉ የግብርና ኮሌጆች ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም።
ይህ እየተነጋገርንበት ያለው መሰረታዊ ጉዳይ ለአገራችን እንግዳ አይደለም። ቀድሞ በተፈጠረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር አማካኝነት ችግሮችን ለመፍታት መሞከር የሁልጊዜ ተግባር የነበረ ሲሆን እንደውም የጥናትና ምርምሮቹ ትኩረት ከአገራዊም አልፎ አህጉራዊ የነበረ ሲሆን ለዚህም የዓለምን አጠቃላይ ሁኔታና ይዞታ የፈተሸ፣ ያገናዘበም ነበር። ይህን ለማረጋገጥ በወቅቱ ከተቋሙ ሲወጡ ከነበሩት ህትመቶች አንዱ የሆነውን “ውይይት/Dialogue” መጽሔትን መመልከት ይቻላል። (ምን ያደርጋል ብዙዎች እንደሚስማሙበትና በቁጭትም እንደሚናገሩት በ1985 42ቱን ቁንጮዎች ካጣ በኋላ ቀልቡ ተገፈፈ እንጂ ዩኒቨርሲቲውስ ዩኒቨርሲቲ ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው።)
ወደ ማጠቃለያው ከመሄዳችን በፊት፤ በተለይ ከ2010 (ለውጡ) በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኩል እየታየ ያለው ተነሳሽነት ሲታይ ከዛ በፊት የነበረው አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ወዘተርፈ ድባብ ጥሩ እንዳልነበረ በራሱ የሚናገረው ነገር አለና ያንን ትተን የተጀመረውን ማስቀጠሉ ተገቢ ነውና በተሻለ ሁኔታ (ተጠናክሮ!!!) ይቀጥል እንላለን። በተለይ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ተጠንቶ በዩኒቨርሲቲዎች ፀድቆ ወደ ስራ በመግባት ላይ ያለው አዲስ የዩኒቨርሲቲዎች አደረጃጀት (ልየታ / Differentiation) ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ከዚህ የበለጡ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚመጡ ይጠበቃልና ህዳሴያችን በቅርብ እውን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።
አንድ አገር ያለ እውቀት፣ በተለይም ያለ ሳይንሳዊ እውቀት የትም ልትደርስ እንደማትችል ይታወቃል። ይህ ደግሞ በተለይ ለእንደኛ አይነቶቹ አገራት የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ ግዴታ ነው። ይህ ችግሮችን በጥናትና ምርምር የመፍታት አሰራር ወደ ባህል ከተለወጠ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ፈለግነው ደረጃ እንደምንደርስ፤ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ/ጫና እንደፈጠረው (በሌሎችም)፣ እንደ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሀንቲንግተን አይነት ሰዎችና ስራዎችን፤ እንደ እኛው አክሊሉ ለማ፣ ገብረህይወት ባይከዳኝ አይነቶችን እንደምናፈራ ከ50 በላይና ከ100 በመቶ በታች ሆኖ መናገር ይቻላል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013