
“የሎጀስቲክስ ችግር እንዳለ በብዙ ቦታ እያየን ነው። ሆን ተብሎ ምርጫውን ለማበላሸት እስካልሆነ ድረስ እንዲህ አይነት ችግሮች ይጠበቃሉ ። ዋናው ነገር ሰው ያለ ምንም እንቅፋት ምርጫውን ማድረጉ ነው ። የዚህ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲሆን ነው። ያ ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
“ለአገሪቱ መረጋጋት የሕዝብ ውክልና እና ሕጋዊነት ያለው መንግሥት ይኑር እያልን ነው። እሱ ሊሆን የሚችለው በምርጫ ነው። ስለዚህ ምርጫው ሌላ አማራጭ አለው ብዬ አላስብም። ችግሮች አሉ? አዎ አሉ። ነገር ግን የዚህ ምርጫ አንዱ ውጤት የሚሆነው እነዚህን ችግሮች ሕጋዊነት ያለው መንግሥት መጥቶ በተረጋጋ መልኩ እንዲፈታው ማድረግ ነው። ”
“እኔ ይሄ የመጀመሪያው ትርጉም ያለው ምርጫ ነው ብዬ አስባለሁ። ያለፉት አምስት ምርጫዎች ምርጫ የሚባሉ አይደሉም። ይሄኛው ምርጫ ተዓማኒ እና የሕዝብ ፍላጎት የሚገለጽበት እንዲሆን እመኛለሁ። ያ ማለት ችግር አይኖርም ማለት አይደለም። ችግር ይኖራል። ነገር ግን የምርጫውን ውጤት የማይቀይር እንደማይሆን አስባለሁ።
“አንዳንድ ቦታ ላይ ድምጽ መስጠት የሚጀመርበት ሰዓት መዘግየት ከታየበት ያ የምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ነው። ሰዓቱ በዘገየበት የምርጫ ጣቢያ ምርጫው የዘገየበትን ሰዓት ማካካስ አለበት። በተቻለ መጠን መምረጥ የሚፈልግ በሙሉ መምረጥ አለበት። ሰው በዝቶ በተባለው ሰዓት ማለቅ ካልቻለ ምርጫ ቦርድ ቢያንስ በቶሎ አልተከፈቱም በተባሉ ቦታዎች ላይ ሰዓቱን ያራዝመዋል ብዬ አስባለሁ።
“የ1997 ምርጫ የተበላሸው ድምጽ ከሚሰጥበት ቀን ጀምሮ ነው። ከዚያ በፊት መጥፎ የሚባል ነገር አልነበረም። ልክ የምርጫው ቀን ጀምሮ ገዢው ፓርቲ መሸነፉን በሚያይበት ጊዜ አይን ያወጣ ኮሮጆ ግልበጣ ተደረገ። ያ አሁን ይደረጋል ብለን አናምንም።
“ከምርጫው በፊት ችግሮች ነበሩ። ድምጽ በተሰጠበት ትናንት በተወሰኑ ቦታዎች ታዛቢዎች እንዳይገቡ የተከለከለበት ቦታ አለ። ያን ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት አርገናል። ችግሮች ይኖራሉ። ዋናው ነገር እነዚህ ችግሮች የምርጫውን ውጤት የሚቀይሩ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ላይ ነው። የተወሰኑ ችግሮች ላይ ማተኮር የለብንም። ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የምርጫውን ውጤት የሚቀይር ችግር አይፈጠርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
“የዚህ ምርጫ ተዓማኒነት የሚወሰነው የአውሮፓ ህብረት ወይም አሜሪካ ወይም ሌሎች ሀገራት በሚሉት ሳይሆን እኛ በምናደርገው ነው። ይህ ምርጫ ተዓማኒ እንዲሆን የምንፈልገው ለራሳችን ስንል ነው። በእርግጥ ቢመጡ ለምርጫው ተዓማኒነት በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ነበር። ቢሆንም ከእነሱ ውጭም ሌሎች ኃይሎች አሉ። ለምሳሌ ሲቪክ ማህበራት ፤ የፓርቲዎች ታዛቢዎች ወዘተ… ስለዚህ የዚህን ምርጫ ተአማኒነት ለማወቅ የምንችልበት መንገድ አለ”።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2013