
“የዘንድሮ ምርጫ ሂደት ሁላችንም እንደተመለከትነው ዲሞክራሲያዊ ነው፤ ሂደቱ አስደሳች ነው ፡፡ ይህም በሁሉም ምርጫ ጣቢያ ተመሳሳይ ስለመሆኑ ሪፖርቱን ሰምተናል ፡፡
“ሀገራችን ትልቅ ተስፋ ያላት ስለመሆኑ በዚህ ምርጫ ጣቢያ ላይ በደንብ ማየት ይቻላል ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝቡ በምርጫ የዲሞክራሲያዊ መንገድን በመከተል መብቱን ለመጠቀም ያለውን ጽናት መመልከት ትልቅ ደስታ ይሰጣል ፡፡
“ይሄ ትልቅ ትዕይንት ነው ፡፡ እዚህ ምርጫ ጣቢያ በጠዋት በመጀመር በኩል መዘግየት ታይቷል፡፡ ድምጽ መስጫ ወረቀት በመሳሳቱ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው፤ ወረቀቱ ተቀይሮ እስኪመጣ ድረስ ሕዝብ በፅናት ከሶስት ሰዓት በላይ ቆሞ መጠበቁን ተረድተናል፡፡ ይህም ሕዝቡ ዲሞክራሲን ለመትከል ያለውን ትልቅ ጽናት ያየንበት ነው፤ ሂደቱ በጣም ታሪካዊ እና ትልቅ ነው፡፡ ሕዝቡ ድምጹን ለመስጠት መብቱን በተግባር ለመጠቀም የወሰነውን ውሳኔ አገራችን ዲሞክራሲን እየተከለች ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
“ኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋት ምርጫ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለውጥ ነው ፡፡ ይሄ ለውጥ በሁሉም መስክ መደገም መቻል አለበት ፡፡ በአንድ እጃችን ዲሞክራሲን እየተከልን በሌላው እጃችንን ችግኝ እየተከልን አገራችንን አረንጓዴ ማልበስ አለብን፡፡
“አገራችንን ደኗ ተራቁቶባታል፤ ደኑን ወደ ነበረበት ለመመለስ ትልቅ ጥረት ተደርጓል ፣ ባለፈው ዓመት የዓለምን ክብረወሰን ሰብረናል፤ ዛሬ ደግሞ በአንድ እጃችን ዲሞክራሲን በምንተክልበት ቀን በሌላ እጃችን ችግኝ መትከላችን ከዓለም የምርጫ ሂደቶች ሁሉ ምርጫችንን ልዩ ያደርገዋል፡፡ የራሳችን የሆነ የዲሞክራሲና የሥራ ባህል እየተከልን እንደሆነ ያየንበት ነው፣ እጅግ በጣም ያስደስታል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ተካፋይ መሆን በራሱ ዕድለኝነት ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡
“በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ የተወሰኑ መዘግየቶች ሳቢያ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ያለመፍጠን ታይቶበታል፤ ሆኖም ግን ሂደቱ በጣም ዲሞክራሲያዊና ነጻ ነው፡፡ በዚህ ሂደት መካፈል ዕድለኝነት ነው፡፤ ሕዝባችን አሁን በየምርጫ ጣቢያው እንደሚታየው ሁሉ በትዕግስት ድምጽን ሰጥቶ ፤ ተግባራዊ ማድረጉ ነገ ለሚያቀርበው ጥያቄ እና ለሚመኛትም ኢትዮጵያ ዋናውንና ትልቁን መሠረታዊ ሥራ እየሰራ መሆኑን አውቆ ይህንን ሂደት በዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ብቻ መብቱን በተግባር ማዋሉ፣ በሰላማዊ ሂደት እያየን እንዳለነው መጨረሱ ለኛ አዲስና ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ በሆነ ምዕራፍ ላይ ይህንን ማየታችን ፈጣሪ ረድቶናል፤ ሕዝባችን ጽናት አሳይቷል፤ አሁንም እስከ መጨረሻ በዚሁ ጽናት ልንቀጥል ይገባል “፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2013