የተቋቋመው ከአራት ዓመት በፊት በ14 ሠዓሊዎች ነው። ሁሉም በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ የተለያየ የትምህርት ዘመን ተመራቂዎች ናቸው። ቡድኑ ከመመሥረቱ በፊት የተወሰኑት ጓደኛሞች ነበሩ። ልምዳቸውን በሚካፈሉበት ጊዜ በቡድን የመደራጀት ሃሳብ ብልጭ ይልላቸዋል። ቡድን አዋቅረው ቢሠሩ ልምዳቸውን እንደሚያጎለብቱ ተማመኑ። የህብር የስነጥበብ ቡድን አባላት።
የቡድኑ ጸሀፊ ወጣት አብዱልቃድር መሐመድ እንደሚለው፤ የቅርብ ጓደኛሞች ስለሆኑ ብዙ ጊዜ ይገናኛሉ፤ ታዳጊ ሳሉ የነበራቸውን ሠዓሊ የመሆን ፍላጎት ይበልጥ ለማጎልበት የተሰባሰቡም ናቸው። ማኅበር መሥርተው የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አርቲስቶችን ይመለከታሉ። እነሱም እንደ ሠዓሊ አንድ ነገር ማበርከት አለብን በሚል ተነሳስተው ኅብርን መሠረቱ ። ከቡድኑ ስብስቦች 90 በመቶው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለፈለገ የሥነጥበብ ት/ቤት የተመረቁ ናቸው። ሁለት ተማሪዎች ደግሞ ከእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት አርት ዲፓርትመንት በስዕል ተመራቂ ናቸው።
መደራጀታችን ለእኛም ለኅብረተሰቡም ጠቅሟል የሚለው ወጣት አብዱልቃድር፤ በግል የምንሠራቸውን በቡድን ሆነን ስንሠራ ሥዕሉን ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ይላል። ስንደራጅ ተሰሚነትና አቅም እናገኛለን ሲልም ገልጾ፣ ያንን ጉልበት ከፍ እያደረግን መጥተናል፤ በመደራጀታችን አባሎቻችን፣ ወጣቶች እንዲሁም ሀገሪቱ ትጠቀማለች ሲል ያብራራል።
አብዱልቃድር እንደሚለው፤ አርት ልምድ ነው፤ ልምድ መለዋወጥን ያስፈልጋል ፤ሥዕል በሠሩበት ቁጥር እየዳበረ ሲሄድ ልምድ መጋራትም ይኖራል። አባላቱ በራሳቸው ስቱዲዮ በየራሳቸው ልምድ ላይ ተመርኩዘው ሥዕል ይሠራሉ፤በአሁኑ ወቅት በማኅበር ለመደራጀት እየተንቀሳቀሱ ናቸው።
ህብሮች አድዋን ለሦስት ዓመታት በመዘከር በየካቲት ወር በተከታታይ ዐውደ ርዕይ አሳይተዋል። ዝክረ አድዋ ቁጥር አንድና ሁለት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል፣ የዘንድሮው (ሦስተኛው) ደግሞ የአንድነት መሠረት በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚያም ለተመልካች አቅርበዋል። በያዝነው ዓመትም ቦሌ ጋኪ ጋለሪ ውብ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በመስከረም 14 ቀን፣ በአርበኞች የድል ቀንም የኦሮሚያ ሠዓሊያን ማህበር በአዲስ አበባ ሙዚየም ባዘጋጀው የሥዕል ዐውደ ርዕይ ተሳትፈዋል።
አድዋ የሀሳብ ለውጥ ያመጣ የጥቁሮች ድል በመሆኑ ነው፤ በርሱ ላይ ተመርኩዘን ሥዕሎች ለማሳየት የወደድነው የሚለው ወጣቱ ሠዐሊ አብዱልቃድር ፤አንጋፋ ሠዓሊያን ልዑል ሰገድ ረታ፣ ባርባራ ጎሹ፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ወርቁ ጎሹ እና እሸቱ ጥሩነህ በወቅቱ እኛ መሥራት ያለብንን ነው የሠራችሁት ብለው ማመስገናቸውን ፤ህፃናቶቹም ሥዕል በማቅረባቸው መደሰታቸውን ይጠቅሳል። ታዳጊዎች በኢግዚቢሽኑ ላይ ሥዕል እንዲያቀርቡ መደረጋቸው ፍላጎታቸውን ያበረታታል ነው ያለው ።
“አንጋፋ ሠዓሊያንን ጨምሮ ወደ 10 ህፃናት የተካተቱበት 15 ተጨማሪ አርቲስቶችን ጨምረን ስዕሎቹ በብሔራዊ ሙዚየም እንዲታዩ ተደርጓል። አድዋ የተሠራው በቲያትር በግጥሞች ስለነበር ሥዕሉ በብዛት እንዲሠራ እኛ በር ከፍተናል። ለቀጣይ አድዋ የዓለም የጥቁሮች ድል እንደመሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አርቲስቶችንም ለማሳተፍ ሀሳቡ አለን “ሲል አብዱልቃድር ይገልጻል።
የተቋቋምነው ለጥቅም ሳይሆን ጥበባችን ለማሳየት ለሀገር አስተዋፅኦ ለማበርከት ነው የሚለው ሰአሊው፣ ሥዕሎቹን የውጪ ሰዎች እንደሚፈልጓቸው፣ ጥበብ ከሀገር እንዳይሸሽ የኛም ባለሀብቶች ቢገዟቸው ሲል ያመለክታል። ስእሎቹ በቤትም በሆቴልም የተወሰነ ቦታ ቢሰቀሉ ውበት እንደሚሆኑ የሚገልጸው።
ወጣት አብዱልቃድር እንደሚለው፤ ሠዓሊያኑ በኅብር መደራጀታቸው ሀሳቦችን በጋራ አንስተው ሥዕሉን በቀለምና በሸራ ከይነው (ኪን) ለሰዎች እንዲያቀርቡ ረድቷቸዋል። ህብሮች የስነጥበብ ቡድኑን በመሠረቱ በሁለት ወር ውስጥ ነው በአዲስ አበባ ሙዚየም የመጀመሪያውን አድዋ ማሳየት የቻሉት። አድዋን በሥዕል ዐውደ ርዕይ እናሳይ በሚል ነበር ስራውንም የጀመሩት።
ዐውደ ርዕዩን በጣም የተሳካ ብዙ ተመልካች ያገኘም ሲል ገልጾታል፤ እነ አብዱልቃድር እስከ ዛሬ አለመሠራቱንም የሚያስቆጭ ሆኖ አግኝተውታል። ስለ አድዋ ግንዛቤ የሌላቸው ተመልካቾችም አግኝተዋል፤ በዚህም ተገርመዋል።
ኢግዚቢሽኑ እንዴት ዋጋና መስዋዕትነት እንደተከፈለበት ብዙ ያልተረዱ ሰዎች እንደነበሩም ጠቅሶ ፤‹‹ሥዕሎቹ ግን ስሜት የሚያጭሩና የሚቀሰቅሱ ሆነው ተገኝተዋል።” ይላል። መስዋዕትነት ተከፍሎበታል ብለው እንዲያስቡ ያደረገ የ15 ቀናት ዐውደ ርዕይ እንደነበረ አስታውሶ፣ ብሔራዊ ሙዚየሙም በወቅቱ ተመልካቹ ብዙ መሆኑን ተመልክቶ ወደ አንድ ወር እንዳራዘመላቸው ገልጾል።
ህብሮች ሦስቱንም ተከታታይ ዐውደ ርዕዮች ያዘጋጁት በራሳቸው ወጪ ነው። የትኛውም ድርጅት ሊያግዛቸው ፈቃደኛ አልነበረም፤ዐውድ ርዕይ የሚያሳዩበትን ቦታ ያገኙትም በብዙ ድካም ነው። ሥዕሎቻችንን የሚያንቀሳቅሱበት ስፖንሰር ያስፈልጋቸው ነበር፤ በክልሎች ለማሳየት ቢፈልጉም ባለሀብቶች ትልልቅና ድርጅቶች ለሥዕል ስፖንሰር የማድረግ ልምድ የላቸውም፤ከሥዕሉ ይልቅ ለሙዚቃው ለድራማው ያደላሉ።
ባለሀብቶችና ትላልቅ ድርጅቶች የሥዕል ኤግዚቢሽኖችን ስፖንሰር ቢያደርጉ ሥዕሉን ጥበብ ያዳብራሉ ሲል ያስገነዝባል። ሠዓሊያንን ስፖንሰር በማደረግ የሥዕል ጥበብ ከሸገር ወደ ክልል እንዲሸጋገርና በዐውደ ርዕይ እንዲታይ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ያቀርባል።
የቡድኑ ጸሀፊ እንደሚለው፤ ህብሮች ታዳሚው ሊሰጣቸው የሚችለውን ሀሳብ አስቀድመው ተረድተዋል። በመሆኑም በአዲስ አበባ ብቻ የሥዕል አውደ ርዕይ ማሳየት አይፈልጉም፤ ወደ ክልሎች መውጣት ይፈልጋሉ። የሚያግዟቸው አካላት ቢያገኙ ህብረተሰቡ ይበልጥ ለሥዕል ጥበብ ግንዛቤ እንዲኖረው እነሱም እንዲበረቱ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
“የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስነጥበብ ዲፓርትመንት ኃላፊ የትብብር ደብዳቤ በመጻፍ አግዘውናል። ለሥዕል ሙያችን በመተባበር አነቃቅተውናል።” ሲሉ ስነጥበብ ቡድን ጸሐፊው አብዱልቃድር ለቢሮው ምስጋና አቅርበዋል።
ወጣት አብዱልቃድር እንደሚለው፤ ኅብር የስነጥበብ ቡድን የሥዕልን ልምድ ለታዳጊዎችና ለጥበቡ አፍቃሪዎች እያሳየ ይሠራል። የስዕል ጥበቡን ለህዝብ በማቅረብ ፤ስነጥበብ ለሚወዱ ሰዎች ሥዕል በማስተማር፤ ለልጆች ስለ ሥዕል አሳሳል ስለ አርቱ ሃሳብን በማካፈል የተወሰነ ኮርሶችንም ይሰጣል። ለታዳጊዎች ሥዕሎች እንዴት መሠራት እንዳለባቸው፤ ታሪኩን ይነግሯቸዋል። ለትልልቆች ግን የሚሰሩትን ሥዕል እንዲያዩ ያደርጋሉ።
ትልቁ ችግር ሥዕል የምናሳይበት ቋሚ ቦታ አለመኖሩ ነው የሚለው አብዱልቃድር ፣ በቋሚ ቦታ በተደጋጋሚ ሰዎች ሥዕል ማየት ቢችሉ ጥሩ መሆኑን ይገልጻል። ሥዕል ከልጆች ጋር ቶሎ የመግባባት እና ስሜት የመስጠትና የማማለል፣ የማማር ባህሪ ስላለው ህፃናት ይወዱታል፤ ይደሰቱበታል ሲል ጠቁሞ፣ ወደ ስነጥበቡም ሊሳቡበት እንደሚችሉ ነው የጠቆመው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013