ወርቅነሽ ደምሰው
ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም እትማችን ‹‹በቆሻሻ የተፈተነ የሕፃናቱ የትምህርት ጉዞ›› በሚል ርዕስ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፤ በአዲሱ ክፍለ ከተማ ለሚ ኩራ ወረዳ ሁለት ውስጥ የሚገኘውን የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ትምህርት ቤትና የአሶሳ አጸደ ሕፃናትን የመማር ማስተማር ሂደቱን አጣቢቂኝ ውስጥ የከተተ ጉዳይ የሚመለከት ዝግጅት ማቅረባችን ይታወሳል። የትምህርት ቤቱን ችግር አስመልክቶ ከወላጆች በደረሰን ጥቆማ መሠረት ቦታው ድረስ በመገኘት የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ፣ የወረዳውን ኃላፊዎች እና የችግሩ ምንጭ የሆኑትን በደረቅ ቆሻሻ ሥራ ላይ የተሠማሩ ወጣቶችን ምላሽ የሚያስቃኝ ጥንቅር ለአንባቢያን ማቅረባችን የሚታወስ ነው።
በመጋቢት እትማችን እንዳስነበብነው በወቅቱ በቦታው ላይ ያገኘናቸው የወረዳው ኃላፊዎች በትምህርት ቤቱ ህጻናት ከቆሻሻ ሽታ ጋር እየታገሉ የመማር ማስተማር ሂደት እየተከናወነ መሆኑ በእጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በመግለጽ ችግሩን ለመፍታት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አስቀምጠው እንደነበር ይታወሳል። ይህ ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ የተማሪዎቹ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዛቸውን እንዲሁ የተመለከትንበት ነበር። የዝግጅት ክፍሉም የጥቆማው ቦታ ድረስ በመገኘት በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደትን እያወከ የነበረው የቆሻሻ ሽታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር፤ ቦታው ላይ ስንደርስ ከገጠመን ተነስተን የችግሩ ስፋትና አሳሳቢነት የሚያሳይ ጽሁፍ ለአንባቢያ አቅርበን እንደነበር ይታወሳል።
ታዲያ በዚህ መልኩ ለአንባቢያን ያደረስነውን በትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ አደጋ ላይ በመጣል እንቅፋት እየሆነ ያለው የቆሻሻ ሽታ ችግር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ችግሩ ተፈትቷል ወይስ ተባብሶ ቀጥሏል ? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ነው? የሚለውን የዝግጅት ክፍሉም ቦታ ድረስ በመገኘት ባደረገው ቅኝት የትምህርት ቤቱ አካላት፣ የወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ጨምረን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ!
የዝግጅት ክፍላችን የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ወደ ስፍራ ለቅኝት ያቀናው ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር። የችግሩ መንስኤ በመጀመሪያ ደረጃው እና በአጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት መካከል ባለው አካፋይ መንገድ ላይ ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሽታ ነበር። በዚህ የቆሻሻ ሽታ የተነሳ ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት ማህበረሰብ እንዲሁም የተማሪ ወላጆች ለጤና ችግር ከመዳረጋቸው ባሻገር በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት መገደዳቸውን አስቃኝተናል።
ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ምን ያህል እልባት ተበጀለት? ስንል በድጋሚ ሰኔ 3 ቀን 2013 ቦታው ላይ በመገኘት ቅኝት አድርገናል። በሁለቱ ትምህርት ቤቶች መካከል የነበረው የችግሩ መንስኤ ቦታው ላይ ስንደርስ ቀድሞ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የነበረው ቦታ ላይ የውሃ ላስቲኮች ( ሃይላንዶች) እና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳን መመልከት ችለናል። እነዚህ ነገሮች በቦታው ላይ ይኑሩ እንጂ ቦታው የተጸዳ በመሆኑ ምንም ሽታ አልነበረውም። ያን ጊዜ በቦታው ላይ ለቆየንባቸው ትንሽ ደቂቃዎች ለራስ ምታትና ለጉንፋን ያጋለጠን የቆሻሻ ሽታ ዛሬ የለም።
ከዚያም ወደ ትምህርት ቤቱ ጎራ ሲባል የአጸደ ህጻናቱ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሂደት ቀጥሎ ተማሪዎች እንደልባቸው በጊቢ ውስጥ ሲቦርቁ ለመመልከት ችለናል። በዚያ አካባቢ ያገኘናቸውን የተማሪ ወላጆች፣ መምህራ እና የትምህርት ቤት ማህበረሰብ በማነጋገር ያገኘነው ምላሽ ያ ሁሉ አልፎ አሁን ንጹህ አየር ለመተንፈስ በቅተናል የሚል የእፎይታ አዘል የደስታ ስሜታቸውን አጋርተውናል።
በወቅቱ አቅርበን የነበረው የችግሩ አስከፊነት ምን ያህል እንደነበር ለትውስታ የሚከተለውን ማቅረብ ወደድን። የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የአሶሳ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ይስሐቅ ታምሩ እንደሚናገሩት፤ በዘንድሮ ዓመት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ 1ሺ689 ተማሪዎችንና በአጸደ ሕፃናት በሁለቱም ቋንቋዎች 584 ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሁለቱም ትምህርት ቤቶች በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች 2ሺህ 273 ተማሪዎች በመመዝገብ የመማር ማስተማር ሥራው ተጀምሯል።
ትምህርት ከተጀመረ በኋላ የመማር ማስተማሩ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ ነገር ግን የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውከው ትልቅ ነቀርሳ የሆነው ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አጸደ ሕፃናቱ በሚገኝበት ትምህርት ቤት መሀል ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሽታ ችግር ነው:: ይህም የመማር ማስተማሩን ሥራ እጅግ አስቸጋሪና በጣም ከባድ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ።
በትምህርት ቤቱ በኩል ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ከስምንት ወር በፊት ከክፍለ ከተማ እስከ ትምህርት ቢሮ በተለያየ አቅጣጫ የተለያዩ አካላት እንዲያውቁት ለማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የከተማው ምክር ቤት፤ የከተማው ምክትል ቢሮ ኃላፊ፤ የክፍለ ከተማ አመራሮች በተለያየ ጊዜ ቦታው ድረስ በመምጣት አይተውት ነበር ይላሉ። ሆኖም ግን እስካሁን ችግሩ በነበረበት ያለና መፈታት ያልቻለ በመሆኑ በመማር ማስተማሩ ሂደት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ፤ በዚህ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የተነሳ ብዙ ተማሪዎች በመታመማቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ቤታቸው እየቀሩ ሲሆን ፤ መምህራንም እንዲሁ እየታመሙ ከሥራ የሚቀሩበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ። በትምህርት ቤት ጊቢ ውስጥ በተለይ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ የቆሻሻው ሽታው መቆምም ሆነ መቀመጥ የማያስችል ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ ቆሻሻው የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በር አጠገብ እንደመገኘቱ መጠን ለሕፃናቱ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ወላጆች በየጊዜው የትምህርት ቤቱን በር እያንኳኩ እሮሮአቸውን እያሰሙ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል ከሁለት ሳምንት በፊት የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ አባላት ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመሄድ ችግሩን ለማሳወቅ ጥረት አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መምህሩ፤ በወቅቱ ወላጅ ኮሚቴ አባላት ያገኙት ምላሽ በሦስት ቀን ውስጥ ቆሻሻ እንደሚያስነሳላቸው ተነግሯቸው ነበር። ነገር ግን ቆሻሻውን የሚያነሳ አካል እንዳልተገኘ ይናገራሉ። በመቀጠልም ከሳምንት በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ኮሚቴዎች ተሰብሰበው ከተወያዩ በኋላ ግማሹ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፤ ግማሹ የካ ክፍለ ከተማ የሄዱ ሲሆን፤ ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በማስረዳት ማመልከቻ ደብዳቤ አስገብተው የተመለሱበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ችግሩ ሳይፈታ መልስ አልተሰጠውምና ምንም ዓይነት መፍትሔ ያልተገኘለት ሆኗል ይላሉ።
‹‹ይህንን ችግር በተለይ በአጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ለትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ስጋት ነው። የሚመለከታቸው አካላት ለቆሻሻ ማጠራቀሚያው ሌላ ተቀያሪ ቦታ በመፈለግ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ በማድረግ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ የሚማሩበት ለማድረግ መስራት ይኖርበታል›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ርዕሰ መምህሩ ጉዳዩን በስፋት ያነሱበትን ንግግር ለትውስታ አቀረብን እንጂ፤ የወላጅ ተማሪ መምህራን ኮሚቴ አባል፣ የአሶሳ አጸደ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አስተባባሪ ፣ ተማሪዎች ፣ ወረዳው ኃላፊዎች እና የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሽርክና ማህበር አባላት በሙሉ አነጋግረን እንደነበር የሚታወስ ነው።
የትምህርት ቤቶቹ አሁናዊ ሁኔታ
አሁናዊ ሁኔታው ምን ይመስላል? ለውጥ መጥቷል ወይስ ባለበት ቀጥሏል? ስንል የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር አቶ ይሰሐቅ ታምሩን ጠይቀናል። አቶ ይሰሐቅ እንደሚናገሩት፤ አሁን ላይ ቆሻሻው ከቦታው ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር ተደርጓል። ምንም አይነት የቆሻሻ ሽታ የሚባል ነገር የለም።
ቆሻሻው ከቦታው እንዲነሳ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ግንቦት 7 የአሶሳ አጸደ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለማስመረቅ ፕሮግራም ተይዞ ነበር። ስለዚህ ከወዲሁ ቦታው መጽዳት ስላለበት ከግንቦት 7 በፊት የወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች ቦታው ላይ በመገኘት ቆሻሻው እንዲነሳና ቦታው እንዲጸዳ ተደርጓል።
በዕለቱም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የጋምቤላ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ትምህርት ቤቱን ግንቦት 7 መርቀዋል። ሆኖም ግን የትምህርት ቤቱ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ሳይቆይ ወዲያውኑ በቦታው ላይ በደረቅ ቆሻሻ ሥራ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወጣቶች መልሰው ቆሻሻውን ቦታው ላይ መጣላቸውን ይናገራሉ።
በዚህ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገና የወረዳ ሁለት ሥራ ኃላፊዎች በቦታው ላይ ተገኝተው ነበር። የወረዳ ኃላፊዎች በደረቅ ቆሻሻ ሥራ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወጣቶች ሥራውን እንዲሰሩ ያደራጃቸው መንግሥት በመሆኑ የሚሰጣቸውን መመሪያ ተቀብለው መንቀሳቀስ አለባቸው። ስለዚህ የጣሉትን ቆሻሻ በማንሳት ወደ ሌላ ተቀያሪ ቦታ እንዲወስዱ ተደርጓል። ከዚያም የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የነበረውን ቦታውን በቆርቆሮ እንዲያጥረው በመስማማታቸው ቦታው እንዲታጠር ተደርጓል።
እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ ፤ አሁን ላይ በቦታው ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳና የተሰወኑ የውሃ ላስቲኮች (ሃይላንድ) ብቻ ቀርተዋል። እነዚህ የቀሩት ንብረቶች የማህበሩ አባላት ሲሆን፤ በቀጣይ እንዲያነሱት የሚደረግ ይሆናል። ከእንግዲህ ትምህርት ቤቱ ሲፈልግ ከውስጥ በኩል ሁለቱን ትምህርት ቤቶች አገናኝቶ በመጠቀም ፤ ካልሆነም የመናፈሻ ቦታ አድርጎ በማስዋብ ለተማሪዎች ጥሩና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ቀደም ብሎ ያለውን ሁኔታ ሲያስታውሱ እጅግ የሚንገፈገፉት ርዕሰ መምህሩ፤ ያሳለፏቸው ጊዜያት በጣም ከባድና ለተማሪዎች ሆነ ለመምህራን እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ወቅት እንደነበር ይናገራሉ። በተለይ ከቆሻሻው የሚወጣው ሽታ በትምህርት ቤት ጊቢው ውስጥ ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት በእጅጉ ያውክ እንደነበር አስታውሰዋል።
ርዕሰ መምህሩ እንደሚሉት፤ ይህ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከትምህርት ቤቱ ጋር ተነስቶ ህጻናት ምቹ በሆነ አካባቢ እንዲማሩ ለማድረግ በተለይ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጽህፈት ቤት አመራሮች የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው በፍጥነት እርምጃ በመውሰድ ችግሩ እንዲፈታ ሁሉም በመረባረብ እና በቅርበት እየተከታተሉ ችግሩ እንዲፈታ በማድረጋቸው ከልብ ምስጋና ችረዋል። አክለውም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በወቅቱ ቦታው ላይ በመገኘት ችግሩን በመመልከት ለህዝብ በማሳወቅ እና በሚመለከታቸው አካል ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ ያደረገው አስተዋጽኦ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል። እንዲሁም የአካባቢ ኮሚቴ፣ የወላጆችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ከትምህርት ቤቱ ጎን ቆመው ያደረጉት አስተዋፅኦ የራሱ ተጽፅኖ መፍጠር በመቻሉ በራሳቸውና በትምህርት ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የአሶሳ አጸደ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አስተባባሪ መምህርት ስንታየሁ ይመር በበኩላቸው ቀደም ሲል በቆሻሻ ሽታ ምክንያት የማያልፍ የሚመስለው እጅግ ፈታኝ ጊዜ ከግንቦት ሰባት ጀምሮ መታለፉን ጠቁመዋል። አካባቢው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንዳይሆንና ቆሻሻ እንዳይጣልበት ከታጠረ በኋላ ምንም አይነት ሽታ የለም ። ‹‹እኛም ደህና ሆነናል፤ ልጆቻችንም ደህና ሆነዋል። አሁን ላይ ወላጆች በዚህ ጉዳይ የሚያነሱት ችግር የለም›› ይላሉ።
ቀደም ሲል ወላጆች በትምህርት ቤቱ ላይ የሚያነሱት ቅሬታ ‹‹እኛም በየቀኑ እዚህ ስንመጣ እየታመምን ፤ ልጆቻችን በየቀኑ እየታመሙ ነው። ስለዚህ ልጆቻችን ከትምህርት ቤት እናስቀራቸው?›› የሚል ጥያቄን ይዘው ነበር ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡት የሚሉት አስተባባሪዋ፤ እኛም ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ቢያስቀሯቸው የሚጎዱት ህጻናቱ መሆናቸውን እያግባባን ልጆቹ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ እናደርግ ነበር። ነገር ግን ባለፈው የትምህርት ቤቱ ምርቃት ከተካሄደ በኋላ ቆሻሻው ከቦታው ላይ እንዲነሳ በመደረጉ ወላጆች በዚህ በኩል የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ፤ ችግራቸው ተፈትቷል ይላሉ ።
እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ፤ ቀደም ሲል ቆሻሻው በነበረበት ወቅት በአንድ ጊዜ ከአንድ ክፍል ውስጥ ከአስር እስከ አሥራ አምስት ተማሪዎች ይታመሙ ነበር። አንድ ተማሪ በጉንፋን ከታመም ሁሉም ተማሪዎች የሚያዙበት ሁኔታ ነበር። በዚህም የተነሳ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ይቀራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ህጻናቱ ከትምህርት ቤቱ በር ላይ ከወላጆች ተቀብለው ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገቡት መምህራን ስለሆኑ፤ ተማሪዎቹ ለመቀበል በር ላይ የሚቆሙ መምህራን ሁል ጊዜም እየታመሙ እንደነበር ያስታወሳሉ። አሁን ላይ ሽታ የሚባል ነገር የለም። በየጊዜው የሚታመም ተማሪ ሆነ መምህር የለም የሚሉት አስተባባሪዋ፤ እንደ በፊቱ ተማሪዎቻችን በቆሻሻ ሽታ ምክንያት ታመው የሚቀሩበት ሁኔታ የሌለ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትምህርት ቤቱን ለመመረቅ በመጡበት ጊዜ በቦታዎች ቆሻሻ እንዳይኖር ተደርጎ እንደነበር ጠቁመው ፤ ከምርቃቱ በኋላ ቆሻሻው ወዲያውኑ ወደ ቦታው በመመለስ የተደረገው በጥድፊያ መሆኑን አስታውሰዋል። በወቅቱ ሁሉም የወረዳ አመራሮች ተረባርበው ቆሻሻ ያመጡትን ሰዎች ቆሻሻው ሰብስበው ወደ ሌላ ቦታ እንዲያነሱ በማድረግ ከዚህ የቆሻሻ ሽታ እንዲገላገሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህ አጋጣሚ ይህንን ችግር እንዲፈታ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቦታው በመገኘት የችግሩን አሳሳቢነት ለህዝብና ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ ላደረገው ጥረት እና ችግሩ እንዲቀረፍ ድጋፍ ለሰጡ አካላት በእጅጉ የሚያመሰግኑ መሆኑን የተናገሩት አስተባባሪዋ፤ አሁን ላይ በትምህርት ቤቱ ህጻናቱ ደስ ብሏቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ እየተከናወነ ይገኛል ይላሉ። በቀጣይ ቆሻሻው የተነሳበትን ቦታ በሚገባ ከተጸዳ በኋላ አረንጓዴ ስፍራ በማድረግ ለማስዋብ የሚፈልግ በመሆኑ ውብና ለእይታ ማራኪ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የወረዳ ሁለት ትኩረት
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ሥራ አስፈጻሚ አቶ እዮብ እሸቱ እንደሚሉት፤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳው ቀድሞኑ በቦታው ላይ የነበረ ነው። ሆኖም ግን ችግሩ እንዲባባስ ያደረገው ትምህርት ቤቱ አዲስ በመሆኑ በቆሻሻ ገንዳ ቦታ አካባቢ ላይ የተሰራ መሆኑ ትምህርት በሚጀመርበት ጊዜ የቆሻሻ ገንዳው ባለበት ቦታ ላይ አገልግሎት መስጠቱ እንዲሁም ወረዳው በቅርቡ ከመመስረቱ ጋር ተያይዞ፤ ይህንን ችግር ለመፍታት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበር ያስረዳሉ።
በመሆኑም ወረዳው እዚህ ቦታ ላይ ያለውን የቆሻሻ ሽታ የሚያደርሰውን ችግር በመመልከት ተፅጽኖውን ለመቀነስ ተለዋጭ ቦታ በመፈለግ ወደ ሌላ ቦታ ለመቀየር እንቅስቃሴ ሲደረግ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (የኮንዶሙኒየም) ነዋሪዎች ደግሞ አሁንም የሽታው ሰለባ እንሆናለን የሚል ስጋት ሌላ ችግር መፈጠሩን ጠቁመው፤ ሌላ አማራጭ ደግሞ ፍሳሽ ካናል ቦታ በመሆኑ ተጨማሪ ችግር ሆኖ ሲጓተት መቆየቱን ጠቁመዋል።
እንደሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፤ አሁን ላይ አጠቃላይ ቦታው እና ሳይቱ ተጸድቷል። የአካባቢው ግራና ቀኝ የመኪና መተላላፊያ ጨምሮ የተጸዳ ሲሆን፤ በቆሻሻ በኩል መተላለፊያ የነበሩት የላይኛውና የታችኛው መግቢያ በር በቆርቆሮ እንዲታጠር ተደርጓል። የወረዳ አስተዳደሩ ቦታ በመለየት ራሱን የቻለ የቅብብል ጣቢያ እስከሚሰራ ድረስ አሁን ላይ ቦታው ላይ ያለው ቆሻሻ በጊዜያዊነት ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር ተደርጓል።
ወረዳው በአራት ሳይቶች ላይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ያለ ሲሆን፤ ቆሻሻ ባለበት ቦታ እንዲነሳ በማድረግ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ተችሏል። አሁን ላይ በቦታው ላይ የውሃ ላስቲኮች (ሃይላንዶች)ና እዚያ ቦታ ላይ ከመቀመጥ የዘለለ ሌላ አገልግሎት የማይሰጥ ገንዳ የቀሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በደረቅ ቆሻሻ የተደራጁት የሽርክና ማህበር አባላት በሌሎቹ ገንዳዎች ላይ ክምችት እንዲደረግ በማድረግ ጊዜያዊ ቅብብሎሽ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተመቻችቷል ይላሉ።
የተቀሩት የውሃ ላስቲኮች (ሃይላንዶች) ለማህበሩ ገንዘብ የሚስያገኙ ሲሆን፤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳው እንዲሁ ከቦታ የሚያነሳው መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህ ማህበራት የተደራጁት በወረዳው አስተዳደሩ ሆኖ የሚመሩትም በወረዳው ሥራ አስኪያጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ቦታ መስራት ግዴታቸው ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በቆሻሻው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ እነዚህ የሽርክ ማህበር አባላት ጋር ውይይት የተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም እዚህ ቦታ ላይ ያለው ቆሻሻ በዚህ ሁኔታ ማስኬድ ስለማይቻል ሌላ ተቀያሪ ቦታ በዘላቂነት እስከሚስተካከል ድረስ በሦስት ጣቢያዎች ላይ የክምችትም ሆነ የቅብብሎሽ ሥራ እንደሚሰሩ ከአባላቱ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት ፤ ከአረንጓዴ አሻራ ሥራ ጋር ተያይዞ እንደወረዳ 120 ሺህ ጉድጓድ እንዲቆፈር የታቀደ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ እስከ 41 ሺህ ጉድጓድ ተቆፍሯል። የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በዚህ በትምህርት ቤት በማስጀመር እጽዋትን ለመትከል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቆሻሻው ቦታ እንዲታጠር ሲደረግ ቆርቆሮውን ከላይና ከታች እንዲያጥር የተደረገው ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል።
ቦታው ኮብልስቶን በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላ ሁኔታ ርቀታቸውን ጠብቀው ጉደጓድ እንዲቆፈር በማድረግ አረንጓዴ አሻራ በማልበስ መርሃ ግብር ውስጥ መካተታቸውን ጠቁመዋል። በሁለቱ ትምህርት ቤቶች በአንደኛ ደረጃውም ሆነ በአጸደ ህጻናቱ በአረንጓዴ አሻራ እቅዱን ከፍ የተደረገ ሲሆን፤ በአንድ ትምህርት ቤት 20 ሺህ የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል በእቅድ ተይዟል። ይህንን ለማሳካት ከትምህርት ቤት አመራር ጋር በቅርበትና በቅንጅት በመስራት ወተመህ (የወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት) በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ። በቀጣይ አካባቢውን ማራኪ ውብ እንዲሆን ለማድረግ የትኩረት አቅጣጫ አድርገን እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
አሁንም የቆሻሻው ማጠራቀሚያው ቦታ ቢታጠርም በአጥሩ አጠገብ የተጣሉ ቆሻሻዎች የሚታዩበት ሁኔታ አለ። ይህንን በዘላቂነት ለመቅረፍ ምን ታስቧል ስንል ለአቶ እዮብ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሲሆን፤ አቶ እዮብ በሰጡት ምላሽ፤ በደረቅ ቆሻሻውን የተደራጁ የሽርክና ማህበር አባላት በቀደሞ ወረዳ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የተደራጁ ናቸው። አሁን ወረዳ ሲከፈል በአዲሱ ወረዳ ሥር ያሉት ማህበራት የህብረተሰቡ ቆሻሻ ለማስወገድ በቂ አይደሉም። ለዚህም ነው ቆሻሻን ከየቤቱ ቶሎ ቶሎ በማንሳት ላይ ክፍተት በመኖሩ ህብረተሰቡ ያለውን የቆሻሻ ክምችት ወደ አጥር ሆነ ወደ መንገድ ዳር ለማውጣት መንስኤ እየሆነ ነው ይላሉ።
በቀጣይ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ 112 አባላት ያሉት የማህበራት ቀጥሮ ለወረዳው በመላኩ አሁን ላይ ሳይት ርክክብ ተደርጓል። እንደእነዚህ አይነት የመንገድ ጥርጊያ ሽርክና ማህበራት የሚበራከቱ ከሆነ በየቀኑ የሚደረገው የቆሻሻ ቅብብል እና ተደራሽነቱ እየጨመረ በሚመጣበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ህብረተሰቡ በተቀመጠው ቀን ቆሻሻን ከቤቱ እያወጣ እንዲወገድ ይሆናል ይላሉ።
ሌላኛው የመፍትሔ ሃሳብ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ጋር ተያይዞ የሚበሰብሱና ደረቅ ቆሻሻዎች ለይቶ ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጥ ሲሆን፤ ከትምህርት ቤቱ ጠበቃዎችና ከአካባቢው ኮሚቴዎች ጋር በስፋት ምክክር በማድረግ መሆኑን ጠቁመው፤ በህገወጥ በሆነ መልኩ ቆሻሻን በሚጥሉት ላይ ህጋዊ እርምጃም የሚወሰድበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013