ሠዓሊ ንጉሤ ታፈሰ የልብስ ሥፌት ክርን ልዩ ልዩ ቀለም እንደ ብሩሽ ተጠቅሞ፣ ሠሌዳውን ደግሞ እንደ ሸራ ተገልግሎ የጥበብ አፍቃሪዎችን እጆች በግርምት አፋቸው ላይ የሚያስጭኑ ሥዕሎችን በመስራት ይታወቃል።ይህ ድንቅ ሠዓሊ ከዚህ ዓለም ከተለየ ሁለት አሥርት ዓመት ሆኖታል።በዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ ላይ ባልተለመደ መልኩ የሥዕል ሥራዎችን የተለያየ ቀለማት ያላቸው ክሮች ተጠቅሞ የሚሰራውን ይህን ተወዳጅ አርቲስት ልናነሳ ወደናል። ሠዓሊውን በሚገባ ለመግለፅ ደግሞ ለዓመታት ሥራዎቹን ጠብቃ የቆየችውን ባለቤቱን በእንግድነት ጋብዘናል። አዲስ ዘመን በአንድ ወቅት ስለ ሠዓሊው ይዞት የወጣውን ዘገባም ተጠቅመናል፡፡
ወ/ሮ ሣባ ፀሐዬ የአርቲስቱ ባለቤት ናቸው።አርቲስት ንጉሤ መደበኛ ትምህርቱን እንደ ጨረሰ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ትምህርቱን ቢጀምርም፣ በወቅቱ ሊመረቅ ሦስት ወር እንደቀረው በአጋጠመው የአዕምሮ ሕመም ምክንያት ቤት መዋል ጀመረ ሲሉ ባለቤቱ ይናገራሉ።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው ለቤተሠቦቹ “ክርና መርፌ ግዙልኝ” ብሎ የአርት ሥራዎቹን መሥራት የጀመረው።የክር ሥዕሎቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በ1977 ዓ.ም ዐውደ ርዕይ አሣይቷል።በወቅቱ ሲሠራ ከጎኑ ሆነው የሚያስፈልገውን እየገዙ የሚያበረታቱት እናት አባቱ እህት ወንድሞቹ ነበሩ።
በኋላም ባህር ትራንስፖርት በምህንድስና ሥራ ገባ።ደርግ ወድቆ ሥራውን ሲያቆም እንደገና ቤት መዋል ጀመረ።በልዩ ልዩ ቅርጽ የተሠሩ የመስተዋት የእንጨት ፍሬሞችን እየሠራ መሸጥ ውስጥ ገባ።የአርት ሥራውን በክርና በመርፌ አድርጎ ይሠራ እንደነበር ባለቤቱ ወ/ሮ ሣባ ፀሐዬ ይናገራሉ፡፡ “በክርና መርፌ ሥዕሎችን በማቅረብ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ነበር” የሚሉት ባለቤቱ፣ አሁን ላይ አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም እስካሁን ድረስም የእርሱን ሥራዎች የመሰሉ የሉም ይላሉ።በወቅቱ ማህበረሰቡ ለሥዕል ያለው አመለካከት ዝቅተኛ እንደነበረ አስታውሰው፣ የእርሱን መሰል ሥራዎች ባለመስፋፋታቸውና የሥዕል ሥራዎቹም በስፋት ተቀባይ ባለለማግኘታቸው ምክንያት ትንሽ ተስፋ ቆረጠ ሲሉ ይናገራሉ።አውደ ርዕይ አቅርቦ አንድ አራት ዓመት እንደቆየ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ይላሉ፡፡
የክር ሥዕሎቹን ሲሠራ መርፌ በካርቶን ይገዛ እንደነበር ወላጆቹ እንደሚናገሩ ባለቤቱ ይገልጻሉ። መርፌው ጥፍሩ እና እጁ ውስጥ እየገባ ይቆስል፣ ይደማና ይመግል እንደነበርም ጠቁመዋል።ቁስሉ እስኪደርቅ ሣምንት 15 ቀን ሥራውን ያቆም እንደነበር ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ሒልተንና በኢምፔሪያል ሆቴሎች የሠዓሊው የአርት ሥራዎች በዐውደ ርዕይ ቀርበው እንደነበረም ያስታውሳሉ።ቤተሠቦቹ ሠዓሊው ሲሞት ለሥዕሉ ብቻ ቤት ሠርተው ሸፍነው ሲመቻቸውም እያናፈሱ በሥነ ሥርዓት አስቀምጠውት መቆየቱን ይናገራሉ።
በኅዳር 29 ቀን 1989 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሟቹ ሠዓሊ ተተኪ ለማፍራት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “የክር ሥዕል ሥራ ጥበቡን ለሌሎች ታዳጊ ሠዐሊያን ለማስተማርና ሌላም ፈጠራ እንዲታከልበት ለማድረግ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተነጋግሬ ነበር።የአውደ ርዕዩ ዓላማም ይኼንኑ ለማሳወቅ ያደረግሁት ነው።የወደፊት ዕቅዴ የሥዕል ችሎታና ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ ቦታ ፈልጌ በሠርቶ ማሣያ ደረጃ ከኔ ጋር እንዲሠሩና የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ነው ብለው በተጨማሪም “ሥራ የለኝም የከፋ ችግር እንኳን ቢያጋጥመኝ የክር ሥዕሎቼን አልሸጣቸውም ብለው ነበር።ሠዓሊው ሀሳባቸው ሣይሰምር በሙያቸው ተተኪ ሰው ሣያፈሩ ሞት ቀደማቸው።እዚህ ላይ “አንድ አዋቂ ሲሞት ቤተመፃህፍት ተቃጠለ” ማለት ነው የሚለው አባባል ልብ ይሏል፡፡
የአቶ ንጉሤ የክርና የቀለም የሥዕል ሥራዎች በአራት ምድብ የተከፈሉ ናቸው።“የክርና የቀለም፣ የቅርጽና የቀለም እንዲሁም የመስታወት ለየት ያለ ፍሬም ሥራ ናቸው።የሥነ ጥበብ ውጤቶቹ የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች አኗኗርና ባህልን የሚያንፀባርቁ ናቸው።
ሥዕሎቹን ከሌሎች ሠዓሊያን ለየት የሚያደርጓቸው ሁለት ነገሮች አሉ። እነሱም በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ያልተማረና የሥዕል መማሪያ መጽሐፍ እንኳን ያላነበበ ያቀረባቸው ሆነው ማራኪ መሆናቸው ነው።በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቤተመዘክር ካየኋቸው የንጉሤ ታፈሰ የክር ሥዕሎች መካከል የሐረር ጉብል፣ የአፋር፣ የጋሞና፣ የትግራይ ሰው በተናጠል ሲገኙበት፤ የገበጣ ጨዋታ፣ እረኛ ዋሽንት ሲነፋ፣ ዋሊያ የመሳሰሉትም አሉ።
በዩኒቨርስቲው ያየኋቸው የክር ሥዕል ሥራዎች እንግዳና አዲስ ናቸው።በሌላ ሠዓሊ አልተሞከረም።አንዳንድ ሰዎች በኩርንችት ሚስማር በትንንሹ ገበያ ላይ የሚያቀርቡት ሥዕል አለ።የክሩን ሥዕል ሥራ ለየት የሚያደርገው ሥዕል በክር ከሽኖ ለማቅረብ በመሞከሩ ነው።በሀገረሰብ ጥበብ የሚሠሩ የሸማኔዎችን ጥበብ ተንተርሶ የተፈጠረና ይኼንኑ ጥበብ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎ ለማውጣት የተደረገ የክር ሥዕል ጥረትም ነው።የሀገርም ቅርስ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ከክር ንድፍ ሥዕሎቹ መካከል አንዲት ሴት ባህላዊ የጥበብ ልብስ ለብሳ፤ ሙካሽ ካባ (ወርቀዘቦ አንገቱ እና ደረቱ ላይ የተጠለፈበት) ደርባ የቆመች ሴት ትታያለች።የክር ንድፍ ሥዕሉን ስታዩት ሴትየዋ በትክክል ባህላዊ ጥበብ ለብሳ በወርቀ ዘቦ የተንቆጠቆጠ ሙካሽ ካባ ደርባ የቆመች ይመስላል እንጂ ፈጽሞ ሥዕል አይመስልም።ይህን ለምሣሌ አነሳሁት እንጂ ሌሎቹም ሥዕሎቹ ተመሳሳይ ናቸው።
ባለቤቱ ወይዘሮ ሣባ እንደገለጹት የአርቲስቱ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ቤተመዘክር ይገኛሉ።ከ56 ሥራዎቹ መካከል 25ቱ የክር ንድፍ ሥዕሎች ናቸው።
የሥዕል ሥራዎቹ አሁን በዩኒቨርስቲው ቤተመዘክር ለዕይታ በሚመች መልኩ በአደራ ከተቀመጡ አንድ ዓመት ከአራት ወራት እንደሆናቸው ተናግረው፣ ለሥዕሎቹን ዋጋ ሰጥቶ ያስቀመጠውን ቤተመዘክሩን ወይዘሮ ሣባ ያመሠግናሉ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013