ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ነው። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ የደረጃ አራት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከትምህርታቸው ጎን ለጎንም በግላቸው የልብስ ስፌት ሙያን ከፋሽን ዲዛይን ጋር አዋደው ሰልጥነዋል። ከትምህርት በኋላም በልብስ ስፌት ሙያቸው ተቀጥረው ሰርተዋል። ተቀጥረው በሰሩበት አጋጣሚም ሙያውን ይበልጥ አዳብረዋል። ይህ ሙያም ለዛሬ እንጀራቸው ሰፊ በር ከፍቶላቸዋል- የጂ ኤስ ኤች ጋርመንት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ገነት ሰውነቴ።
የልብስ ስፌት ሙያውን ጠበቅ አድርገው የያዙት ወይዘሮ ገነት በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ከፍተኛ አሰልጣኝ በመሆን ተቀጥረው ስልጠና ሰጥተዋል። ሙያውን ፈልገው ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተማሪዎችም ሥልጠና እየሰጡ የወር ደመወዝተኛ በመሆን ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል። ያኔ ከእርሳቸው ጋ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ዕውቅ ዲዛይነር ለመሆን በቅተዋል። በወቅቱ በዓመት አንድ ጊዜ ይካሄድ በነበረው ሀገራዊ የፋሽን ትርኢት ውድድርም ተሳታፊ በመሆን ያስተማሯቸውን ተማሪዎች በማገዝ ለውድድር አብቅተዋል።
በወቅቱ በፋሽን ዲዛይን ዘርፍ የሰለጠኑና የመመረቂያ ፅሁፋቸውን የሚሰሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገር ውስጥ በመምጣት ከፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ጋር በጋራ ይሰሩ ነበር። ወይዘሮ ገነትም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚመጡ ባለሙያዎችን የማግኘት ዕድሉ ገጥሟቸው ብዙ ዕውቀት አግኝተዋል። ይህም ሙያቸውን ይበልጥ ለማሻሻልና ለማሳደግ አስችሏቸዋል። ከዚህም በላይ በሀገሪቱ የዲዛይንና ፋሽን ሙያ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ወይዘሮ ገነት ከውጭ የሚመጡት ባለሙያዎች በሀገሪቷ በሚገኙ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ዲዛይነሮችንና አሰልጣኞችን በሚያሰለጥኑበት ጊዜ ከዕውቀት ሽግግር በተጨማሪ የተለያዩ የዲዛይን መጽሀፍትን የማግኘት እድል ገጥሟቸቸዋል። በዚህ ጊዜ ያገኙት ዕውቀትና የቀመሩት ልምድም ዛሬ ላይ ለደረሱበት ውጤት ትልቅ መሰረት ጥሏል። እርሳቸው ያሰለጠኗቸው ተማሪዎችም በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጅ ሀገራዊ የፋሽን ዲዛይን ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነው ዕውቅናን አትርፈዋል።
ውድድሩን ከመሳተፍ ባለፈም ውጤታማ እየሆኑ የራሳቸውን የልብስ ስፌትና የዲዛይን ሥራ መሥራት የቻሉ በርካቶች ናቸው። በወቅቱ የእርሳቸው ተማሪዎች የነበሩ ወጣቶች በግላቸው የራሳቸውን ልብስ ስፌት ድርጅት ከፍተው መስራት መቻላቸው እርካታ የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ለራሳቸውም ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል። የልብስ ስፌት ስራን በግላቸው ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ ተረድተው ጉዟቸውን አንድ ብለው ጀመሩ።
ዛሬም ድረስ በተለያየ መንገድ የሚያግዟቸው ቤተሰባቸው የግል ሥራ ለመጀመር ‹‹ሀ›› ብለው ሲነሱ ለስራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲቆጥቡ ረዳቸው። የቅጥር ሥራቸውን ሳያቋርጡ በሁለት ሰራተኞችና በ60 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ገነትና ህብስት ልብስ ስፌት ህብረት ሽርክና ማህበር በሚል ንግድ ፈቃድ አወጡ። ከመደበኛ ሥራቸው በኋላ ምሽት ላይ የልብስ ስፌት ሥራቸውን መስራት ቀጠሉ። ቀደም ሲል ተቀጥረው ይሰሩበት የነበረው መስሪያ ቤት እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰራተኞችን ሲፈልጋቸው እንደሚጠራቸው በመግለፅ ከስራ አሰናበቷቸው። በዚህ ጊዜ ታድያ ወይዘሮ ገነት ያለስጋት ባዘጋጁት የራሳቸው ልብስ ስፌት ሥራ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው መስራት ጀመሩ።
በቀና ከተነሱ ሁሉም ነገር የተቃና እና የተሳካ እንደሚሆን የሚያምኑት ወይዘሮ ገነት፤ ከሥራ መቀነሳቸው ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ተቀብለው ወደ ራሳቸው ስራ ገቡ። ስራው ቢሳካም ባይሳካም የራሱ ጉዳይ በማለት ሁለትና ሶስት መቶ ማሽኖች ካላቸው ድርጅቶች ጋር በድፍረት ጨረታ በመጫረትና የቫት ሥርዓት ውስጥ በመግባት ተገቢውን ክፍያ እየከፈሉ ሙሉ በሙሉ በልብስ ስፌት ስራ ውስጥ ገቡ።
አዲስ ሥራ ሲጀመር ገበያ እስኪያገኝ ድረስ ፈተናዎች ያሉት በመሆኑና ለሥራው ካላቸው ጉጉት የተነሳ ወይዘሮ ገነት አንዳንዴ ሥራ ፍለጋ ይወጡ ነበር። መሰል ሰራተኞችን በማግኘት ሥራ ካላቸው ማገዝ እንደሚፈልጉ እየገለፁም ሥራ ያገኙ ነበር። በዚህ ጊዜ ቬሎ ቤት ከፍታ ያገኟት የቀድሞ ልብስ ስፌት ተማሪያቸው በርካታ ቬሎዎችንና የሚዜ አልባሳትን ለመስፋት የወሰደችውን ሥራ አግዘው እንዲሰሩ ባደረገችላቸው ግብዣ የግል ልብስ ስፌት ስራ መንገዳቸው ተከፈተ።
በባህሪያቸው ሥራ መምረጥ የማይወዱት ወይዘሮ ገነት ሥራ የሚገኝበትን ቦታ ሁሉ በማሰስ ስራ መስራት የዘወትር ተግባራቸው ሆነ። በሄዱበት መንገድ ሁሉ ሥራ ታዘው የበዛባቸውንም ሆነ አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ሥራቸውን በጥራት መስራት ቀጠሉ። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንደሚባለውም በሂደት ደንበኛ እያፈሩ እውቅና እያገኙ ወደ ገበያ ውስጥ በስፋት ገቡ። በወቅቱ ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ይሰሩ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በዋናነት ለተለያዩ የህክምና ተቋማት በተለይም ለጤና ባለሙያዎች፣ ለጥበቃ ሰራተኞችና ለፅዳት ሰራተኞች የሚያገለግሉ አልባሳትን በጨረታ እየተወዳደሩ ያቀርባሉ። በዚህም በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል።
ምንም እንኳን በጥረታቸው ወደ ሥራው ገብተው ደንበኞችን ማፍራት የቻሉ ቢሆንም ገበያው ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ሞራል የሚነኩና ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ስለመሆናቸው ወይዘሮ ገነት ይናገራሉ። በተለይ ጨረታ ውስጥ ገብተው ውድድሩን ሰብረው የሚገቡ በጥራት የማይሰሩ ድርጅቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ። በተጨማሪም በመንግስት ተቋማት ውስጥ ሆነው የጨረታ ውድድሩን በትውውቅና በሙስና የሚያበላሹ በርካታ አሰራሮች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። እነዚህ አሰራሮችም ዘርፉን ከመጉዳቱ ባለፈ ኢኮኖሚውንም እንደሚጎዱ፤ በትክክለኛው መንገድ የሚሰሩ ሰራተኞችን ሞራል የሚነካ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
ወይዘሮ ገነት እነዚህን እና መሰል ችግሮችን እየተጋፈጡ ከቪሎ ሥራ ወጥተው በቀጥታ ወደ ሆስፒታል የደንብ ልብስ ስፌት ስራ ውስጥ ገቡ። በአሁኑ ግዜም ጥራት ባለው ግብዓት ሆስፒታሎች የመረጡትና የሚወዱትን የደንብ ልብሶች ያመርታሉ። በተለይ የነርሶች አልባሳትን ፣ የህክምና ባለሙያዎች ጋወኖችን፣ ለጥበቃና ለጽዳት ሰራተኞች የሚውሉ አልባሳትን ያመርታሉ። ምርቶቹንም ለመንግስት ተቋማት በጨረታ ተወዳድረው፤ ለግል ሆስፒታሎች ደግሞ ከጨረታ ውጪ በስምምነት አምርተው ያቀርባሉ።
ያለምንም ጨረታ የሚፈልጉትን አይነት አልባሳት በስምምነት ብቻ ካሰሯቸውና እያሰሯቸውም ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥም ተክለሃይማኖት፣ሀሌሉያ፣ አሜንና የረር ይገኙበታል። እነዚህ ሆስፒታሎች ለወይዘሮ ገነት የረጅም ጊዜ ደንበኞች በመሆናቸው በፈለጓቸው ጊዜ ሁሉ ቀድመው በመገኘት ጥራት ያለውን ምርት በፍጥነት በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ዛሬ ላይ ለደረሱበት ውጤትም አስተዋጿቸው የጎላ ነው።
አዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኘው ጂ ኤስ ኤች ጋርመንት በተጨማሪም ገነት የልብስ ዲዛይን ማሰልጠኛ የሚል ተቋም እዛው ከፍተው ስልጠና በመስጠት ጭምር የተሰማሩት ወይዘሮ ገነት፤ መሰረታዊ የሆኑትን የፓተርንና የዲዛይን ስልጠናን በተግባር ይሰጣሉ። ስልጠናውን ፈልጎ የሚመጣ ምንም የማይችል ሰው ሰልጥኖ ሲ ኦ ሲ በማስመዘን አብዛኞቹን እዛው በመቅጠር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑም ይደረጋል።
ማእከሉ በትምህርት ቢሮም ዕውቅና ያገኘ ሲሆን በአብዛኛው ሰልጣኞቹ ዘንድም ውዴታን አትርፏል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ተዘግቶ ዳግም የተከፈተ ቢሆንም የሰልጣኞች ቁጥርም ግን እንደበፊቱ ሊሆን አልቻለም። ነገር ግን የጋርመንት ሥራው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ወይዘሮ ገነት ጨረታ አሸንፈው ሥራው ሲገኝ በአማካኝ 25 ሰራተኞችን ይዘው የሚሰሩ ሲሆን፤ ሥራው ቀዝቃዛ ከሆነ እስከ 16 ለሚደርሱ ሰራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ይሰራሉ። ሥራው በመጣ ጊዜ ሁሉ በኮንትራት ከሚያሰሯቸው 30 ከሚደርሱ ሰራተኞች በተጨማሪ በቀጥታ ሙያ ውስጥ ገብተው የሚሰሩ ስምንት ቋሚ ሰራተኞችም አሏቸው።
እስፔሻል ማሽኖችን ጨምሮ ለሥራው የሚያገለግሉ 20 የሚደርሱ የልብስ ስፌት ማሽኖችን ይዘው የሚሰሩት ወይዘሮ ገነት፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ በሚመጣበት ጊዜ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ጭምር እንደሚሰሩ ይናገራሉ። የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው በቤታቸው የሚሰሩበት 10 ተጨማሪ ማሽኖችም አሏቸው። በቤታቸው ሆነው ስራቸውን ሲከውኑም ቤተሰቦቻቸውንም ያሳትፋሉ።
ለጋርመንት ሥራቸው ከሚጠቀሙበት የልብስ ስፌት ማሽኖች ውጭ ለማስተማሪያነት የሚጠቀሙባቸው 15 የልብስ ስፌት ማሽኖችም ያሏቸው ሲሆን፤ የልብ ስፌት ትምህርቱን ታታሪ እህታቸው ያስተምሩላቸዋል። ከእህታቸው በተጨማሪም እንደልጅ ያሳደጓቸው በሙያው ላይ ሰፊ ዕውቀት ያላቸው ሌሎች የቤተሰቡ አባላት በስልጠናው ላይ ተሳታፊ ከመሆናቸው ባለፈ ትምህርቱንም ያስተምራሉ። መደበኛ የስፌት ሥልጠና ከሶስት ወር እስከ አራት ወር የሚፈጅ ሲሆን፤ መሰረታዊ ፓተርን ስልጠና ከተጨመረ ደግሞ ከስድስት ወር እስከ ስምንት ወር ይቆያል።
ወይዘሮ ገነት ስልጠናውን ከሚወስዱ ሰልጣኞች መካከል በልብስ ስፌት ድርጅታቸው ውስጥ ቅጥር እንዲፈፅሙ በማድረግም በልብስ ስፌት ስራው የሚገጥማቸውን የሰው ሀይል እጥረት እንደሚቀርፉ ያስረዳሉ። የስልጠና ማዕከሉን ለመክፈት ሲነሱም አላማቸው በልብስ ስፌት ዘርፍ የሚያጋጥመውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማሟላት እንደነበርም ያስታውሳሉ። ከእርሳቸው አልፎ ለሌሎች ልብስ ስፌት ድርጅቶች የሚተርፍ የሰው ሀይል ለማቅረብ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ማእከሉን እንደከፈቱም ይጠቅሳሉ። ለዚህም አብዛኛውን ጊዜ በዘርፉ ስልጠና ሲሰጡ መቆየታቸው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ይናገራሉ።
ለልብስ ስፌት ስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከመርካቶ ነጋዴዎች ይረከባሉ። ይሁን እንጂ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዋጋ መለዋወጥ ምክንያት ጥሬ እቃዎቹ እንደለብ አያገኟቸውም። የዋጋው መወደድና የዕቃው እንደልብ አለመገኘት ደግሞ ደንበኞቻቸውን እንዳሸሸባቸውና በተለይ ጥራት ያላቸውን ጨርቆች ገዝቶ ለመስራት ፈተና እንደሆነባቸው ይጠቁማሉ። ከጨርቅ በተጨማሪም የተለያዩ አይነት ክሮችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን እንደሚጠቀሙም ይናገራሉ።
ጂ ኤስ ኤች ጋርመንት ከተለያዩ ሆስፒታሎች ለሚቀርብለት ትዕዛዝ በቀን ከ200 እስከ 500 ልብሶችን የማምረት አቅም አለው። በተለይም አዲስ የሚመሰረቱ ሆስፒታሎች ለየዘርፉ ቅያሪን ጨምረው የሚያዘጋጁ በመሆኑ ከ2000 እስከ 3000 የሚደርሱ አልባሳትን ይፈልጋሉ።
ከተማሪነት ተነስተው በልብስ ስፌትና ዲዛይን የሰለጠኑት፤ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ ከፍተኛ አሰልጣኝ ሆነው በቅጥር ያገለገሉት ወይዘሮ ገነት፤ በአሰልጣኝነት ሲሰሩ ያካበቱትን ሙያ ይዘው በዘርፉ የበለጠ ለመስራትና ለመለወጥ ብዙ ወጥተዋል ወርደዋል። በመውጣትና በመውረዳቸውም በልብስ ስፌት ዘርፉ በርካታ ተሞክሮዎችንና ዕውቀቶችን አግኝተዋል። የቀመሩትን ዕውቀትና ያገኙትን ተሞክሮም ለሌሎች ለማሻገር በሚል በ60 ሺ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት ጋርመንትና የልብስ ስፌት ማሰልጠኛ ተቋማቸው ዛሬ ላይ አጠቃላይ ካፒታሉ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ደርሷል። ወይዘሮ ገነትም በልብስ ስፌት ሙያ ብዙዎችን ለፍሬ በማብቃት ስኬታማ ሴት ለመሆን በቅተዋል።
በቀጣይም ግዙፍ ፋብሪካ በማቋቋም ከውጭ ሀገር የሚገቡ አልባሳትን በሀገር ውስጥ የመተካትና ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር ራዕይ አላቸው። ራዕያቸውን ለማሳካትም በቻሉት አቅም ሁሉ እየተጉ ይገኛሉ። እኛም ዕቅዳቸው እንዲሳካ ምኞታችንን እንገልፃለን። ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013