ከስሜታችን ከፍ የምትል ከእኛ የምትልቅ በምክንያት የተገነባች አገር አለችን። ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ለመቆም የምታደርገው ታላቅ ፍልሚያ አንዱ ክፍል ነው። ፀንታና ጠንካራ ሆና ለልጆችዋ ምቹ እና መኩሪያ የምትሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። ታዲያ በዚህ የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የእኛ የዜጎች ሚና ቀላል አይደለም። መፅናትዋ ላይ እንቅፋት ለመፍጠርም ሆነ ለማልማትና ወደፊት ለማሻገር ዋንኛ ተዋናዮች እኛው ዜጎችዋ ነን።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የአገር አንድነት የሚፃረር፤ የህዝብን ቁርኝት የሚጋፋ ድርጊትና ሁኔታ ሲታይ ግን ማመን ይከብዳል። በምክንያት የተገነባችን አገር በስሜት፣ ያለ ስሌት ለመናድ ጥረት የሚያደርግ ሲያጋጥም እጅግ ያሳዝናል፤ አልታረም የሚል ሲያጋጥም ደግሞ ያሳስባል ።
ታክሲ ውስጥ ነኝ። የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ነው። በንግግሩ በቀላሉ የሚለይ። የአምላክን ስም ደጋግሞ እየጠራ ራሱ አምላክ የፈጠራቸውን የሌሎች እምነት ተከታዮችን ለመግለፅ በሚሰቀጥጡ ቃላት ይዘልፋል፣ ያንቋሽሻል። ዘግናኝና ከአንድ ሃይማኖተኛ ሊወጡ የማይገባቸውን ቃላት ይጠቀማል። የሌላውን እምነት አዝቅጦ አማኞቹን ጭፍን በሆነ ጥላቻ ይገልፃል።
ተሳፋሪው ተቃውሞውን በጨዋ ቋንቋ በመገልጽ ቴፑን እንዲዘጉት ሹፌሩንና ረዳቱን አሳሰቡ። ሹፌርና ረዳቱ ሊደነግጡ ነው። ይብሱኑ “ከፈለጋችሁ መውረድ ትችላላችሁ፤ የእናንተ ቢጤ ነው ያስቸገረን” ሲሉ መለሱ። አሽከርካሪውና ረዳቱ መልካም ያልሆነን የተቃወመ፤ የጥላቻውን ንግግር በግድ አታሰሙን፤ ልባችንን ባልሆነ ስድብና ጥላቻ አታጥቁሩት መባላቸውን ነው የጠሉት።
ጉዞው እስኪረዝምብኝ ድረስ በሁኔታቸው አፍሬ፣ ቀጣዩ ጊዜያችን አሳስቦኝ በትወልዱ ከምክንያት ርቆ በስሜት መነዳት ተሸማቅቄ መውረጃዬ ደርሶ እፎይ አልኩ።
ስወርድ ረዳቱን “ኧረ ነውር ነው! በህዝብ መገልገያ ውስጥ አትክፈት›› አልኩት። ገላምጦኝ በሩን ዘግቶት ወደ ስድስት ኪሎ አመራ። የታክሲውን ሰሌዳ ለማየት ሞከርኩ፤ አሽከርካሪው በንዴት ያሽከርክር ስለነበር ተፈተለከብኝ።
ወዲያው ስንት ህገወጥነት በተበራከተበት፣ ሁሉም ፍቃድ የተሰጠው ያህል ስሜቱ ያዘዘውን እየተገበረ በሚያብድበት አገር ውስጥ መኖሬ ታሰበኝ። ይህን ሕገ ወጥ ተግባር በታክሲ ውስጥ እያሰማ የሚዞረውን ታክሲ ማስቀጣት ወይም ከተግባሩ እንዲቆጠብ ለማድረግ መሞከር እንዳለብኝም እያወኩ ከንፈሬን መጥጬ ወደ ሥራዬ አመራሁ።
በነገራች ላይ በህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጥ የተገልጋዮችን ምቾት የሚነሳ ተግባር መፈፀም እንደሌለበት የሚከለክል ሕግ እንዳለ እገነዘባለሁ። በተለይ ለግጭት መነሻ የሚሆኑ ቅስቀሳዎችን በአገልግሎት መስጫ ውስጥ ከፍቶ ማሰማት ተጠያቂነቱ ምን ያህል ከፍ ሊል እንደሚችልም እረዳለሁ። መብትና ግዴታችን የምንለይ የሌሎችን መብት ማክበር የእኛን መብት ለማስከበር መነሻ መሆኑ ሊገባን ያስፈልጋል።
በዚህ ምቾት የሚነሳ ገጠመኝ የተነሳ ቢሮ ገብቼ ሥራ ልጀምር ብሞክርም አቃተኝ፤ ሌላ ማሰብ ተስኖኝ ረፈደ። አገሬ ያለችበት ሁኔታ፣ የእኛ የልጆችዋን ያለ ቅጥ ማበድ፤ ከምክንያት መራቅ እያሰብኩ ብዙ ተብሰለሰልኩ።
አስቡት በሰላም አውለኝ በማለት በመልካም ንግግርና በጥሩ መንፈስ ሊጀመር የሚገባው ቀን በጥላቻ ንግግር ሲጀመር ውሎው ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት። ለዚያውም አምላኩን አስር ጊዜ እየጠራ እኔ በሱ ነው የምመካው እያለ የአምላኩን ፍጥረታት በሚያነውር የጥላቻ ንግግር በመስማት የሚጀመር ቀን ሲሆን ደግሞ የሚሆነውን ገምቱ።
እምነቶች ሌሎች እምነቶችን በመሳደብ ማነወር በፍጹም አይፈቅዱም፤? እሱ የለየራስን ክብር ለመጠበቅ ሲባል ሌላውን በማነወር አምላክን መቅረብ ይቻልስ ይሆን? በፍጹም አይቻልም። አማኝ ነኝ ባዩን አምላክ የፈጠረውን የሌላውን እምነት ተከታይ መዝለፍ ማነወር፣ መዘርጠጥ ማን ፈቀደለት ታዲያ ? እሱ በእርግጥም ያጠያይቃል። ሁለት ጥፋት ነው የተፈፀመው። በቅድሚያ ንግግሩ ተቀርፆ እየተላለፈለት ያለው አማኝ ነኝ ባይ እንድ ጥፋተኛ ሲሆን፣ ይህን ንግግር የሚዘሩት ደግሞ ሌሎች ጥፋተኞች ናቸው።
አምላክን 100 ጊዜ እየጠሩ ከእርሱ ብዙ እጥፍ የሚያርቀውን ጥላቻ መስበክ ምን የሚሉት እብደት ነው። በእዚህ አይነቱ አፍራሽ ድርጊት ውስጥ የገባችሁ እረፉ፤ ስለራሳችሁ እምነት ክብር ስትሉ የሌሎችን አክብሩ፤ ስለ አምላካችሁ ታላቅነት እና ክብር ስትሉ የሌሎችን እምነትና አምላክ አትዳፈሩ።
በሃይማኖታችን ሥር ተጠልለን በስሜት ሌላውን እየነዳን ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት እንሞክር ይሆናል፤ በእውነት የምናመልከው አምላክ ፊት ነገ ስንቆም ግን፤ እኔ ፍቅርን እንጂ ጥላቻን እንድትሰብክ አላዘዝኩህም መባላችን አይቀርም።
ስለምን እምነትና እምነቱ የሚያዘውን ከመፈፀም ይልቅ በስሜት እየተመሩ ማበድ ውስጥ ይገባል ። ወገን ትክክለኛና ለፈጣሪያችን ያደርን ከሆንን ከእኛ ውጭ ሌሎችን ማየት የማንፈልግ በሙሉ ጭፍን ጥላቻን ከልባችን መራቅ ይኖርበታል።
በጥላቻ የሞላ ልብ በአምላክ ፍጡራን ላይ ሴራን የሚወጥን ማንኛውም እምነት/ እምነቱ ላይ ችግር የለም/ ሆነ አማኝ በእርግጠኝነት ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ተግባሩ የሰው ልጅም አይቀበለውም። ለሰዎች በብዙ ጥላቻን ሰብኮ ክፋትን ዘርቶ መልካም ፍሬን የሚጠብቅ አማኝ ነኝ የሚል ካለ ያ ከእምነቱ ብዙ የራቀ ከሃይማኖቱ ያፈነገጠ ነው።
ማንም በማንም ላይ ሰልጣን የለውም። አንተ የእምነትህ ተከታይ እንድትሆን ሌላኛውም የራሱ እምነት ተከታይ እንዲሆን ያደረገው አምላክ ብቻ ነው። በየራሳችሁ እምነት በመከባበር ማደርና ያመናችሁበትን እምነት መልካምነት መልካም በሆነ ቃል ብቻ ለሌላው ማድረስ ሃላፊነታችሁ ነው። አንተ እምነቴ ብለህ በጭፍን ጥላቻ የሌሎችን እምነትና አማኞች ስትዘልፍ ስታንጓጥጥና ስታነውር ሌሎች የአንተን እምነት ሊያከብሩልህ አይችሉም። ምላሻቸው እንዳንተው ተያይዞ ገደል የሚዶል ሊሆን ይችላል።
እምነት በምልካምነት እንጂ በክፋት አይሞላም፤ ሃይማኖት መልካም ነገርን እንጂ ክፋትን በሰዎች ላይ አያዝም። እንኳን ሰዎችን ምድር ላይ ያለ ፍጥረትን ሁሉ በርህራሄ እንመለከት። መገለጫችን መልካምነት፣ ተግባራችን በጎነት፣ ሀሳባችን ፍቅር የተሞላበት እንዲሆን ለእምነታችን ስንገዛ የምንገባው ቃል ኪዳን ነው።
ወገን ከምንምና ከማንም በላይ ስለራሳችን ሃይማኖት ክብር ብልን የሌላውን ሃይማኖት ክብር እንጠብቅ፤ ለእራሳችን እምነትና አማኝ ብለን የሌሎችን አማኞች ማንነትና እምነት ከማጉደፍ እንጠበቅ።
ሁሉን ባስገኘው አምላክ ካመንን የእሱን ትዕዛዝ መተግበርና ምድር ላይ መልካም ነገሮች እንዲበረክቱ መትጋት እንጂ፣ ጥላቻን በመስበክ የሌሎችን እምነት በማነወር የሚገኝ ፅድቅ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ለመፅደቅ ፃዲቅ የሆነ ተግባር እንጂ የረከሰ ተግባር ፈፅሞ ይዞ መቅረብ አይቻልምና።
ይህቺን አገር ተከባብረን ወደፊት የምናራምዳት ተደጋግፈን የምናሻግራት፣ በየራሳችን እምነትና ባህል የምንደምቅባት፣ የሁላችን አገር መሆንዋን መቀበል ለዚህም በፅናት መሥራት ይጠበቅብናል። ለእዚህ ደግሞ ራሳችን ሊደረግ የማንፈቅደውን ሌላ ላይ አናድርግ፤ ይልቁንም አንዳችንን የሌላችንን እናክበር።
አገራችን በምክንያት የተገነባች አገር ናት። በምክንያት የተገነባችን አገር ለመጉዳት የሚደረግ አርስ በርስ የማጋጨት ሙኩራ የጤዛ ያህል ነው፤ ረፋድ ላይ ይረግፋል። ይህን ደግሞ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመልክተናል። አበቃሁ፤ አገሬ ሰላምሽ ይብዛ!
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013