
የምርጫ ቦርድ 11 ሚሊዮን መመዝገቢያ ካርድ አሳተመ
47 ሰዎች ለምርጫ አፈጻጸም በመሠልጠን ላይ ናቸው
በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ መሠረት፤ለሦስተኛ ጊዜ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል የሚሆኑ የሕዝብ እንደራሴዎች ለመምረጥ የሚደረገው ዝግጅት ከአሁኑ እንደቀጠለ ነው።
በአገር ግዛት ሚኒስቴር የምርጫ ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሥዩም እጅጉ እንደገለጹት፤በአሁኑ ጊዜ ለምርጫው አፈጻጸም የሚያገለግሉ ፲፩ የመመዝገቢያ ካርዶች ታትመዋል።ሕዝቡ እንደራሴን ለመምረጥ የሚያስችለው ምዝገባ የሚጀምረው ከ፱ ወር በኋላ ማለት ፤በ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም ጥር ፩ቀን ሲሆን፤ የአመራረጡ ሥነ ሥርዓትም የሚፈጸምባቸው ፩ሺ፪፻፹ የምርጫ ጣቢያዎች ተመድበዋል።
ዋናው ዳይሬክተር አቶ ሥዩም እጅጉ እንዳስረዱት ፤የታተሙት ካርዶች ወደ የምርጫ ጣቢያው በመላክ ላይ እንደመሆናቸው መጠን ፤እሰከአሁን ፮፻ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ተልከዋል።
ከዚህም በስተቀር የምርጫ ቦርድ የእንደራሴዎቹን ሕጋዊ የአመራረጥ ሥነ ሥርዓት የሚቆጣጠሩና የሚያስፈጽሙ ፵፯ ሰዎች በማሰልጠን ላይ መሆኑ ታውቋል።
ሚያዚያ 8 ቀን 1956 አም
ለሰኔ ወር ትራፊክ ተጨማሪ ዳኞች ያስፈልጉታል
በአዲሱ የትራንስፖርት ሕግ መሠረት በሰኔ ወር ተሽከርካሪዎች በግራ በኩል በሚነዱበት ጊዜ ለሚደርሰው የትራፊክ ጥፋት የፍርዱን ቅጣት የሚሰጡ ለአዲስ አበባ ከተማ ከአሥር የማያንሱ ዳኞች በተጨማሪ እንደሚያስፈልጉ ታውቋል።
የአነዳድ አቅጣጫ ሲለወጥ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ሲባል የፖሊስ ሠራዊት ተጨማሪ ፖሊሶችን ከሌላ ሥራቸው አንሥቶ በትራፊክ ቁጥጥር ተግባር ለተወሰነ ጊዜ ለማሠማራት ማሰቡን፤በማስተማር ላይ መገኘቱን በቅርቡ ለመረዳት ችለናል።
በዚህም ጊዜ የተከሰሱ ባለ ተሸከርካሪዎች ፖሊስ አብሯቸው ፍርድ ቤት መገኘት ሳያስፈልግና ተከሳሹም ለሌላ የሚያውለውን ጊዜ እግረመንገዱን ወደ ሚገኘው ዳኛ ቀርቦ ወዲያው ውሳኔ የሚያገኝበት ዘዴ ለሰኔ ወር ብቻ በማሰብ አማካይ በሆኑ አሥር ስፍራዎች ላይ ዳኞች እንዲሰየሙ የፖሊስ ሠራዊት የፍርድ ቤትን እንደጠየቀ ተገልጿል።
ሚያዚያ 21 ቀን 1956
የአንበሳ አውቶቡሶችን በር ለማዛወር $ 168,700
ወጪ ይሆናል
የበሩ አቀያየር ሥራ ትናንት በግርማዊ ጃንሆይ ተጎብኝቷል።
የአንበሳ አውቶቡስ ማኅበር ከአዲስ አበባ ናይሮቢ የሕዝብ ማመላለስ ተግባር ለመጀመር ፈቃድ የጠየቀ መሆኑን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ኦራን አስታውቀዋል።
ከሚመጣው ሰኔ ወር ፶፮ ዓ.ም ጀምሮ ተሽከርካ ሪዎች የቀኙን መንገድ ይዘው እንዲሔዱ በመደረጉ፤ በግራ የነበረው የአንበሳ አውቶቡሶችን በር ለማስለወጥ $ 168,700 የሚጠይቅ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ በተጨማሪ ገልጸዋል። የአውቶቡሶች በር አቀያየር ሥራ፤መጋቢት ፫ ቀን ትናንት በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ተጎብኝቷል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ከበደ ፤የማኅበሩ ቦርድ አባሎች ፤ዋናው ሥራ አስኪያጅና የክፍሉ ሹማምንቶች ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አቀባበል አድርገዋል። የማኅበሩን አውቶቡሶች በር የመቀየር ሥራው የተጀመረ መሆኑን በማስረዳት ዋናው ሥራ አስኪያጅ ባደረጉት ገለፃ ፤በሮቻቸው በቀኝ በኩል የሆኑ ፳፪ አውቶቡሶች በግንቦት ወር የሚገቡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በማኅበሩ አውቶቡሶች በ፲፱፻፶፬ ዓ.ም 12,000,000 መንገደኞች በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም 17,000,000 መንገደኞች፤ እንደ መጓዛቸው መጠን ፤የዚህ ዓመት ተሳፋሪዎች መጠን 21,000,000 እንደሚደርስ የተገመተ መሆኑን ዋናው ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። የተሳፋሪዎች መጠን እየጨመረ እንደ መሄዱ መጠን በሚመጡት አምስት ዓመታት የአውቶቡሶቹ ጠቅላላ ቁጥር 240 የሚደርስ መሆኑ ታውቋል።
የማኅበሩ አውቶቡሶች ባለፈው ዓመት 4, 701, 320 ኪሎ ሜትር ተጉዘው $ 3,723,000 ገቢ አስገኝተዋል።ከዚህ ውስጥ $ 237,906 የተጣራ ትርፍ ነው።
ሚያዚያ 1956
ግልጽ ደብዳቤ
የሙዚቀኞች ይዞታ
ናይት ክለብ የሚሄደው ሁሉ ለመስከር አይደለም ። ሁሉም ለመጨፈር አይሄድም። የማይጠጣ ይኖራል። የማይጨፍርም ሞልቷል። ሙዚቃ ለማዳመጥ የሚሔድ አለ። ውዝዋዜንም እንደ አርት ለማድነቅ የሚገኝ አለ።
ስለ ሙዚቃ ካወሳን ዘንድ በሀገራችን አሉ ከሚባሉት የሙዚቃ ጓዶች አንዱ የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ጓድ አንዱ መሆኑ አይካድም። የሙዚቃ ተጫዋቾች የሚጠብቁት ክብር አላቸው። ናይት ክለቦችም የሚጠብቁት ሥርዓት ሊኖር ይገባል።
የካቲት ፲፪ ቀን በፓትሪስ ሉሙምባ የማታ ክበብ እንደተመለከትነው ከሆነ ይኽ የሙዚቃ ጓድ ክብሩን የጠበቀ አይመስልም ፤ክለቡም የክለብ ሥርዓት አልያዘም።
ከሙዚቃው ድምፅ የሰካራሙ ፉጨት አይሎ ይሰማል። ግማሹ በወለሉ ላይ ይበጠብጣል። ግድ ካልደነሳችሁ ብለው የሚሳደቡ ፤የሚገላምጡ ሞልተዋል። በፀጥታ ሙዚቃ ለማዳመጥ በፀጥታ ውዝዋዜ ለመመልከት ገብተው ቅር እየተሰኙ የወጡ ብዙ ናቸው። ሙዚቀኞቹ የሚከፈላቸውን ገንዘብ ብቻ መመልከት የለባቸውም። ክለቡም ገቢውን ብቻ ሳይሆን የክለብ ሥርዓት የሚሆንበትን ሁናቴ ማሰብ ነበረበት። ካለበለዚያ ግን ሙዚቀኞቹ ለክብራቸው ተስማሚ ሥፍራ ቢፈልጉ ይሻላል።
ጸዳል ገበየሁ
መጋቢት 12 ቀን 1956
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013