የማይፈርስና ሊፈርስ የማይችልን ግዙፍ የነሳ አካል ለማፍረስ የሚመክሩ አይጠፉም። ጉብታዎችን ንደውና ደልድለው መንገድ ስለሰሩ ወይም ህንጻ ስላቆሙ ተራራን ያህል ግዙፍ ነገር ንደው ፍላጎታቸውን ሊያሳኩ የሚፈልጉ አይታጡም፤ አሉ። እነዚህ ወገኖች ተራራው በራሱ እንደሚያስፈልግ፣ ባለቤት እንዳለው ሁሉ ይዘነጉታል። ባለቤት ቢኖረውስ ምን ያመጣልም ብለው ይደፍራሉ፤ በእንዲህ አይነቱ ዘመን ላይ ነን።
ይህን ለማስፈጸም ከህዝብና ሀገር የዘረፉትን ሀብት ይረጫሉ፤ ሴራ ይጠነስሳሉ፤ ያሰለጥናሉ፤ መሳሪያ ያስታጥቃሉ፤ ያሰማራሉ። ለሚተባበሯቸው ሁሉ የማይገቡት ቃል የለም፤ ረጃጅም እጅ አላቸው። ወንድምን በወንድምና እህት፣ በአባትና በእናት ላይ ያስነሳሉ።
የአንድን አካባቢ ማህበረሰብ አብሮት ከኖረው ሌላ ማህበረሰብ ጋር ያጋጫሉ። አንዱ በሌላው ለዘመናት የተጎዳ አርገው በማቅረብ ለደሀነትህ ለሁዋላ ቀርነትህ ምክንያቱ ይህ ማህበረሰብ ነው፤ ታገለው፤ በለው ከጎንህ ነን ብለው ያነሳሳሉ፤ አላማህን ለማሳካት ከዚህ ወቅት ሌላ አይኖርህም ይላሉ። አላማቸው እስከሚሳካ ድረስም ከሩቅ ሆነው በለው ይላሉ።
እነዚህ ሀይሎች አላማቸው መበጥበጥ፣ አለመረጋጋት መፍጠር ሊሆን ይችላል፤ የአንድን ሀገርና ህዝብ መብት ጭምር መንፈግም ሊሆን ይችላል። ለእዚህ አላማ የሚያሰልፏቸውን ተላላኪዎች የሚጠቀሙትም ለተላላኪዎቹ አስበው አይደለም። የአላማ መመሳሰል ኖሯቸውም ላይሆን ይችላል። ለይስሙላ አብረው የሆኑ ይመስላሉ እንጂ አብረው አይደሉም። ወንድም እህት ሲሉ ቢገልጸቸውም አላማቸውን ያሳኩ በመሰላቸው ጊዜ ወይም ሲከሽፍባቸው ግን ዞር ብለው አያዩዋቸውም።
ያበቃለት የጋሪ ፈረስ አለ አይደል፤ እንደዚያ ይቆጥሯቸዋል። በሊቢያ ያየነው ይህንን ነው። የጋዳፊን ተቃዋሚዎች ሲረዱ ቆዩ፤ ጋዳፊን አስወገዱ፤ ሀገሪቱን በታተኑ፤ ጨዋታው አበቃ። ያ የእነሱ መጠቀሚያ የሆነ ቡድን የት እንዳለ አይታወቅም፤ ሀገሪቱ ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖች የሚራገጡባት ሆና ቀረች። የሌሎች መሳሪያ መሆንን የመሰለ ክፉ ነገር የለም። ከራስም ከሀገርና ከህዝብም አለመሆንን ያስከትላል። በየተራ መብላትም ሊከተል ይችላል።
እንደ ጅቡና በሬዎቹ ነው ነገሩ። አንድ በማህበረሰባችን ዘንድ የሚታወቅ ታሪክ አለ፤ ሶስት በሬዎች ነበሩ፤ ቀለማቸው ነጭ፣ ጥቁር እና ግንባሩ ቦቃ ነው። ኑሯቸውን ጫካ ውስጥ ነበር፤ ልብ በሉ እንግዲህ፤ አሉ ነው ነገሩ። በሮቹ አንበሳን ጨምሮ የትኛውም ክፉ አውሬ ቢመጣ ክብ በመሥራት እየተዋጉ ባለማስጠጋት ይታወቃሉ፤ ይፈራሉ፤ ይከበራሉ።
አንድ ቀን ግን አያ ጅቦ ይመጣል። በሬዎቹ በሙሉ ባሉበት ምንም ማድረግ እንደማይችል ይረዳል። መላ መፈለግ ውስጥ ይገባል። ነጩ በሬ በሌለበት ከሁለቱ በሮች ጋር ውይይት ያደርጋል። “ይሔ ነጭ በሬ ያስጨርሳችኋል፤ እሱ ከሌለ በጨለማ አትታዩም” የሚል መጥፎ ሀሳብ በውስጣቸው እንዲፈጠር አደረ። ሁለቱ በሬዎችም በሀሳቡ ተስማምተው ተባብረው ነጩን በሬ አባረሩት። ጅቡም ነጩን በሬ ለብቻው አገኘው፤ በላው።
ጅቡ ሌላም ጊዜ ተመለሰ። ለጥቁሩ በሬ “ግንባረ ቦቃው ካለ አሁንም ለአደጋ የተጋለጥህ ነህ” አለው። በዚህም ሁለቱን በሬዎች እንዲለያዩ አደረገ። ጅቡም ግንባረ ቦቃውን በላው። በሌላ ቀን ጅቡ ጥቁሩ በሬ ጋ ሄደ። በሬውም “ዛሬ ምን ፈልገህ መጣህ? ልትበላኝ ነው?” ሲል ጠየቀው። ጅቡም “አንተ እኮ የተበላኸው መጀመሪያ ጓደኛህን አሳልፈህ የሰጠኸው ጊዜ ነው” ብሎ ጥቁሩን በሬም በላው ይባላል። አየህ ወዳጄ በየትኛውም ጊዜ ተባብሮ (አንድ ሆኖ) ያተረፈ እንጂ የከሰረ የለም፤ የከሰረው የተለያየ ነው።
አሁንም አገራችን እየገጠማት ያለው ችግር ከዚህ የተለየ አይደለም፤ በውጭ ሀይሎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ሀገራችንን ለማጥፋት ያለ የሌለ ሀይላቸውን የሚጠቀሙ ሀገር ከሀዲ ቡድኖች አሉ። በዚህ ላይ የውጭ ሀይሎችም አሉ።
የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዲኖር አይፈልጉም፤ ለእዚህም በዚህ ወሳኝ የምርጫ ወቅት የተጠና አድማ በሚመስል መልኩ በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱት። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዲፈጸም አይፈልጉም። ኢትዮጵያ ሁሌም የእነሱን እጅ እንድታይ ነው ፍላጎታቸው ። ኢትዮጵያ ላይ የተጀመረው ዘመቻ መልኩ ምንም ይሁን ምን ማጠናጠኛዎቹ እነዚህ ናቸው።
እነዚህ ሀይሎች ይህን ለማሳካት ሀገሪቱን ሽባ ለማድረግ፣ ለማጥፋት የተለያዩ ፕላኖችን ይዘዋል። አንዱ በጎጥ እና በእምነት መከፋፈል ነው። ይህ ያዋጣል ብለው እየሰሩ ናቸው። ወንድም በወንድሙ ላይ እያዘመቱ ያሉት ደግሞ ሀገሪቱ ጠንካራ ከሆነች እንቸገራለን ብለው ነው። ለአንዱ መሳሪያ እየሰጡ ሌላውን ያስወጋሉ። በእነዚህ ተላላኪዎች የንጹኃን ደም በከንቱ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ጠፍቷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ይህ እንዲቀጥል የተፈለገም ይመስላል። አንድ መንግስት ለአሸባሪው ትህነግ እውቅና መስጠትን የሚያመክት እርምጃ ውስጥ ከገባ ሌላ ምን ማለት ይቻላል።
በዚህች አለም ከመንግስት ይልቅ አሸባሪ እየተመረጠ ነው። የውጭ ጠላቶቻችን ለያዙት አጀንዳ ማስፈጸሚያ ትህነግን መርጠዋል። ትህነግ ሀገር የካደና በአሸባሪነትም የተፈረጀ ቡድን ነው። የባይደን አስተዳደር ግን ኢትዮጵያን ገፍቶ ከትህነግ ጋር መቆሙን አረጋግጦልናል። ለአሸባሪ እውቅና ሰጥቷል።
የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚባል ነገር አለ። ያም ቢሆን ግን የፈለገውን ያህል የአንድን ሀገር መንግስት መጥላት ውስጥ ቢገባ እንዴት ተደርጎ ለእዚያውም ሰይጣንን ወዳጅ ማድረግ ውስጥ ይገባል። ሲገባ ግን እየተመለከትን ነው።
ከእዚህ መረዳት ያለብን ቀጣዩ ጊዜ ፈተኛ መሆኑን ነው። እነዚህን ሀይሎች በጥንቃቄ መመከት እንዲሁም ማሳፈር አለብን። የእነሱ አንዱና ዋናው መሳሪያ በሀገር ውስጥ ያለውን ክፍፍል አነፍንፈው በማግኘት በዚያ ቀዳዳ መጠቀም ነው። ይህ መርዝ መጥፎ መርዝ ነው። ይህን መርዝ ማርከስ የሚቻለው አንድነትን በማጠናከር ብቻ ነው። ከአባቶቻችን ከራሳችንም ስኬቶች በመማር አንድ መሆናችንን ማሳየት ነው።
በአለማችን እንዳልነበሩ ከተደረጉ ሀገሮች ታሪክ መማር ይኖርብናል። በየመን፣ በሶሪያና በሊቢያ ይህ ሁሉ ውድመት የደረሰው እርስ በርሳቸው እንዲጫረሱ በመደረጉ ነው። ሁሉም ጠንካራ መንግስታት ነበሩ። ዛሬ እንደ ሀገር መቆም ተቸግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ግን በዚህ አይነቱ ሴራ አይሸነፉም። ያለፉት ሶስት አመታት የግጭት ድግስ የቱንም ያህል ችግር ቢኖር ኢትዮጵያውያን በአንድነታቸው በሀገራቸው ላይ የተቃጣን ጥቃት በጋራ እንደሚመክቱ አሳይቶናል። የግጭትን አስከፊነት በእነዚህ አመታት በሚገባ ተመልክተናል። ተጎድተናል፤ ነገር ግን ጠላቶቻችን በደገሱት ልክ አልተፈታንም።
ጠላቶቻችንም ይህን በሚገባ ያውቃሉ። ሲያደርጉ የነበረው ዙሩን ማክረር ነው። የጭፍጨፋው አሰቃቂነት ይህን ያመለክታል። በዚህ ግን የተፈታ አልተገኘም። አሁንም ይበልጥ ዙሩን ሊያከሩ ይችሉ ይሆናል። እኛ ግን የእስከ አሁኑን ጥንካሬ ይበልጥ በማጎልበት ፈተናውን ለማለፍ መስራት ይኖርብናል። ተለያይተን ራሳችንን ከማስበላት በአንድነት አባቶች የሰጡንን አገር ከእነሙሉ ክብሯ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል። በአንድነት ሆነን መታገል እንጂ “እንዲያና እንዲህ” ሁነን ነበር እያሉ ማውራቱ አይጠቅምም።
መላ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው የሚቆሙበት ጊዜው አሁን ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ ፅንፈኛ ኃይሎችና የስልጣን ርሀብተኞች አሁንም ልዩነታችንን አጥብቀው ይፈልጋሉ። መግቢያ ቀዳዳ የሚሆናቸው እሱ ነዋ። ይህን ቀዳዳ መድፈን ይገባናል።
ወቅቱ እጅ ለእጅ የምንያያዝበት ወቅት ነው፤ ከሚያለያዩን ጥቂት ምክንያቶች የሚያቀራርቡን አንድ የሚያደርጉን በርካታ ናቸው፤ አንድነት ብርቱ ኃይላችን ነው። ጠላቶቻችን የሚረጩትን መርዝ ማርከስ የሚችለው አንድነታችን ብቻ ነው። ቀደምት አባቶችና እናቶችም ይህንኑ መዳህኒት ተጠቅመው ነው ታሪክ እየሰሩ ያቆዩን። አንድ ሆነን እንቀጥል።
የልቤ ደርሶ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013