በዛሬው የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን በ1960ዎቹ ከወጡ ዘገባዎች ጥቂቶቹን ይዘን ቀርበናል። በአገራችን ዋጋ አለአግባብ በመጨመርና ከምርት ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ እየተባባሰ መምጣቱ ይታወቃል። ይህ አይነት ችግር በተጠቀሱት ዓመታትም ይከሰት እንደነበርና መንግሥት ተከታትሎ እርምጃ ይወስድ የነበረ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች ይወጡ ነበር። እነዚህና ሌሎች ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
በስንዴና ጤፍ ላይ አፈርና ሟጨራ የጨመሩ 2 ሰዎች 100 ብር ተቀጡ
ናዝሬት፡- /ኢዜአ/ ለሸማቾች ባቀረቡት ስንዴና ጤፍ አፈርና ሟጨራ የጨመሩት ፪ ሰዎች ፻ ብር እንዲቀጡ የሸንኮራ ወረዳ ፍ/ቤት ባለፈው ሳምንት ውስጥ በዋለው ችሎት ፈረደ።
ጽጌ ጉሽሜና ተሾመ ዝቄ የተባሉት እነዚሁ ሰዎች ይህንኑ የማታለል አድራጎት የፈፀሙት በሸንኮራ ወረዳ ውስጥ በባልጪ ከተማ ሕዝብ በተሰበሰበበት የገበያ ወቅት መሆኑ ተገልጧል።
ከሁለቱም ተከሳሾች መካከል አንደኛው ተሾመ ዝቄ ጤፍ የአልሆነውን ሟጨራ ጤፍ ነው ብሎ ሲሸጥ በፖሊስ ተከታታይነት ሲያዝ ፪ኛው ተከሳሽ ጽጌ ጎሽሜ ደግሞ በዚሁ በባልጪ ከተማ በስንዴ ውስጥ በርከት ያለ አፈር ጨምሮ ሲሸጥ ወዲያውኑ እጅ ከፍንጅ ለመያዙ በማስረጃና በሕግ ምስክሮች በመረጋገጡ እያንዳንዳቸው ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል።
እንዲሁም በዚሁ በሸንኮራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተፈሪ ኪዳኔ፣ አቶ በጋሻው መስቀሌ፣ አቶ ነጋሽ ጁማ አቶ ተሰማ ወጋየሁና አቶ ጥንድ ጌታ አየለ የተባሉት ዘይት ነጋዴዎች በአባይ መስፈሪያ እየለኩ ዘይት ሲሸጡ በመገኘታቸው ተከሰው ከነዚሁ ውስጥ አራቱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው ፲፭ ብር ሲቀጡ፣ በጋሻው መስቀሌ ፲ ብር የተቀጣ መሆኑን አንድ የፍ/ቤቱ ቃል አቀባይ አስታውቋል።
ዋጋ አስበልጠው እቃ የሸጡ 7 ሰዎች 570 ብር ተቀጡ
ሐረር:- /ኢዜአ/ ከታሪፍ በላይ ፭ ሳንቲም አስበልጠው ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ የተያዙት ፯ ነጋዴዎች ፭፻፸ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የባቢሌና የወበራ ፍርድ ቤቶች በዋለው ችሎት ፈረደ
እነዚሁ ተከሳሾች አብደላ ዳውድና ሚዋን ዘርፉ የተባሉት ፭ ሳንቲም መሸጥ የሚገባውን ክብሪት በ፲ ሳንቲም ሲሸጡ በመያዛቸው፣ ሀሰን መሀመድና ንጋቱ ኢላላ የተባሉት ነጋዴዎች ፳ ሳንቲም መሸጥ የሚገባውን ሮል ሳሙና ፳፭ ሳንቲም ሲሸጡ በመገኘታቸው፤ ፬ቱ ነጋዴዎች በቀረበባቸው ክስ በማስረጃ ስለተረጋጠባቸው እያንዳንዳቸው ፻ ብር በጠቅላላው ፬፻ ብር መቀጣታቸውን የመ/አ አሰፋ አበበ የባቢሌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ገልጠዋል።
እንዲሁም የሐረርጌ ጠ/ግዛት ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል እንዳስረዳው ከተወሰነው ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙት ፫ ነጋዴዎች ወበራ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ፻፳ ብር መቀጫ መቀጣቸው ታውቋል።
ከነዚሁ ውስጥ አቶ ሰይድ ሼክ አብዱላሂ ፳ ብር፣ አቶ ሁመር አክሌ ፵ ብር፣ እንዲሁም አቶ አሊ አብዱ ፴ ብር መቀጣታቸውን የማስታወቂያ ክፍሉ በተጨማሪ ገልጧል።
ወወክማ አጥፊ ወጣቶችን ግብርና ሥራ ላይ ለማዋል አቀደ
ወወክማ በከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ የሚገኙትንና ወደ መጥፎ ድርጊት በማዘንበል የጥፋት ተግባር የሚፈፅሙትን አንዳንድ ወጣቶች በእርሻ ሥራ ላይ ለማሰማራት ማቀዱ ተገለፀ።
ይህም የዕቅድ ፕሮግራም በሥራ ላይ የሚውለው ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎች የገንዘብ ዕርዳታ በሚገኝበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።
ወወክማ ካሉት ፕሮግራሞች በተጨማሪ ይህን ዕቅድ በሥራ ላይ ለማዋል ያሰበበት ዋና አላማ ወጣቶችን ከመጥፎ ጠባይ ለመጠበቅ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው ለመርዳት የሚችሉበትን መንገድ ለመሻትና ጥሩ ዜጋ ለማፍራት ነው።
በዚሁ መሰረት ወወክማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመዘዋወር የሚታዩትን ልጆች ከአጥፊነት ለመመለስ የሚያስችል ከአራት ዓመታት በፊት አንድ ፕሮግራም ጀምሯል።
ፕሮግራሙ ‹‹ኦፕሬሽን ቤተር ቮይስ›› የተሰኘ ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮግራም አማካይነት በየመንገዱ የሚባዝኑትን ወጣቶች በማነጋገርና በመቅረብ ከመጥፎ ድርጊት እንዲጠበቁ ማድረጉን የወወክማ ማስታወቂያ ክፍል አስታወቀ።
ከዚህም በቀር በእሁድ ቀን የተባሉትን ልጆች በወወክማ ቅፅር ግቢ በመሰብሰብ ጊዜያዊ ህክምና በመስጠትና ልዩ ልዩ አገልግሎትን በማበርከት ወጣቶችን ከመጥፎ ተግባር ለመጠበቅ መቻሉን የማስታወቂያ ክፍሉ በተጨማሪ አስርድቷል።
ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ካሉት ፕሮግራሞች አንዱ የእርሻ ልማት ሥራዎችን ማከናነወን ነው፡፤ በዚሁ መሰረት በጅማና ነቀምቴ የእርሻ ፕሮግራም አቋቁሞ ለአነስተኛ ገበሬዎች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመስጠት በመርዳት ላይ ይገኛል። በቅርቡም በናዝሬት ወወክማ ይህንኑ መሰል ፕሮግራም የሚያቋቁም መሆኑን በዜናው ለመረዳት ተችሏል።
በዝንጀሮ ጉበት ሴትዬዋ ዳነች
ቦን፡- በምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን ውስጥ በሚገኘው የቦን ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ ውስጥ የሚሠሩ ሐኪሞች ለአንዲት በራሷ ጉበት ፈንታ የዝንጀሮ ጉበት ተክተው ከሞት ያተረፏት መሆኑን የክሊኒኩ ቃል አቀባይ ገለፀ። ከሞት ያመለጠችው ሴት በቅርቡ ድና እንደምትነሳ በተጨማሪ ተገልጧል።
፳፪ ዓመት እድሜ ያላት የኤክስ ሬይ ምርመራ ረዳት ሠራተኛ የሆነችው ጀርመናዊት ከሦስት ሳምንት በፊት በሄፓታይተስ በሽታ መክንያት ሐኪም ቤት ገብታ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጉበቷ ሥራውን አቁሞ ህይወቷን ከመሳት ደረጃ ደረሰች። ሆኖም ህይወቷ ከማለፉ በፊት ሐኪሞች አንድ ሙከራ ማድረግ መረጡ። ምርጫውም ሥራ ባቆመው ጉበት ፈንታ በቅርብ ይገኝ ከነበረ ዝንጀሮ የተወሰደ ጉበት ለሴትዬዋ መተካት ነበር።
፲፪ ሰዓት የፈጀ የጉበት ማዛወር ሥራ ከተከናወነ በኋላ ሴትዬዋ ነፍስ ገዛች። ሆኖም ዶክተሮች ባደረጉት ጥረት የራሷ ጉበት እንደገና መደበኛ ሥራውን ለመጀመር በመቻሉ በዝንጀሮው ጉበት ፈንታ እንደገና የራሷ ጉበት ተተክቶላት ከሐኪም ቤቱ ለመውጣት የምትችል መሆኗን የዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ ሐኪም ገለፀዋል።
ሮይተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013