ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ናቸው ሲባል በእድገታቸው ውስጥ በርካታ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ መዘንጋት የለበትም። ምክንያቱም ህፃናት በእድገታቸው ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ የሂወት መስመራቸውም መሰረት ስለሚጥሉ ነው።
በሀገሪቱ በችግር ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታ ያልገቡ ህፃናት እንደሚገኙ ይታወቃል። ታድያ ህፃናቱ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ለማድረግ የተለያዩ በጎ አድራጎት ማህበራት እየሰሩ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በባህርዳር ከተማ የሚገኘው ኄራን የበጎ አድራጎት ማህበር ተጠቃሽ ነው።
ለዛሬ በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ ውስጥ በችግር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን እየደገፈ ስለሚገኘው ኄራን የበጎ አድራጎት ማህበር እንቃኛለን። ከማህበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ የኔነህ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
ኄራን የበጎ አድራጎት ማህበር በተለያየ ምክንያት በችግር ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመርዳት እራሳቸውን እንዲችሉና ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጐች እንዲሆኑ ማድረግና እንዲሁም ረዳት የሌላቸውን ችግረኛ አረጋውያንን በመርዳት የሀገራችን የእርስ በርስ መረዳዳት እሴትን በማጎልበት ሰብዓዊ ግዴታችንን መወጣት በሚል አላማ ከባህርዳር ከተማ የበጎ አድራጎት ማህበራት ምዝገባ ክትትልና ድጋፍ መስጫ በመጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና አግኝቷል።
በአሁኑ ሰዓት በባህርዳር ከተማ የሚገኙ 56 ችግረኛ ህፃናትን በየወሩ 350 ብር እንዲሁም በአመቱ መጀመሪያ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እና የደንብ ልብስ ለሌላቸው ተማሪዎች የደንብ ልብስ በማሟላት በቋሚነት ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ግርማ ይናገራሉ።
የማህበሩ ዋና የገቢ ምንጭ ከማህበሩ ቋሚ እና ተባባሪ አባላት የሚሰበሰብ ወርሃዊ መዋጮ ሲሆን ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ የአልባሳት እና ቁሳቁስ እርዳታዎች እንደሚገኝ ያመለክታል።
ማህበሩ በተለያየ ምክንያት በችግር ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመርዳት እራሳቸውን እንዲችሉና ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጐች እንዲሆኑ በማድረግ የሀገራችን የእርስ በርስ መረዳዳት እሴትን በማጎልበት ሰብዓዊ ግዴታችንን መወጣት እንደ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ነው።
ማህበሩ ከበጎ አድራጊዎች ድጋፍ በተጨማሪ የራሱ የሆነ የገቢ ማስገኛ ኖሮት ችግረኛ ህጻናት የሚኖሩበት መንደር በመገንባት እና ራሳቸውን በማስቻል በ2020 ዓ.ም. በክልሉ ቀዳሚ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበር የመሆን ራዕይም አለው።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በዋናነት የተሰሩት ስራዎች የተቸገሩ ህፃናትን በባህርዳር ከተማ በሚገኙ ክፍለ ከተማዎችና ቀበሌዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በየአካባቢው የድሀ ድሃ ተብለው የተመዘገቡ አሉ። እነዚህ ሰዎች ልጆቻቸውን የሚያግዝላቸውና የሚያስተምርላቸው ሰው ይፈልጋሉ። እናም ከቀበሌዎች በሚገኝ መረጃ መሰረት በማህበሩ ምልመላ ኮሚቴ እንዲታይ እንደሚደረግ አቶ ግርማ ይናገራሉ። የተመለመሉ ሰዎችን በየቤታቸው በመሄድ በማየትና በመጠየቅ በየወሩ በቋሚነት 350 ብር እንዲሰጣቸው እንደሚደረግ ይገልፃል።
ሌላው ደግሞ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ይሰጧቸዋል። ደብተር፣ እስኪርቢቶ፣ ዩኒፎርም፣ የስፖርት ትጥቅ፣ ቦርሳና በዓመት አንድ ጊዜ የዳቦ ዱቄት እንደሚሰጣቸው ያመለክታል። ቁሳቁሶቹን ከስፖንሰር በሚገኝ ድጋፍ የሚገዛ ሲሆን አልባሳትና የተለያዩ ነገሮችን ከማህበሩ አባላት ውስጥ ድጋፍ የሚያደርጉ እንዳሉ ይናገራል።
ከየሰዉ የሚሰበሰቡ ልብሶችን ለተማሪዎቹ በየልካቸው እንዲሰጣቸው እንደሚደርግ ይጠቅሳል። አሁን ባለው ሁኔታ በማህበር ውስጥ ታቅፈው ድጋፍ እያገኙ ያሉት 56 ልጆች ናቸው። አራት ልጆች ከየክፍለ ከተማው ለመቀበል ለምልመላ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይናገራል። በተያዘው ወር አራት ልጆችን በመጨመር ድጋፍ የሚደረግላቸው ስልሳ ይደርሳሉ።
ማህበሩ ልጆችን ከመደገፍ በዘለለ ሌሎች ነገሮች ላይ ተሳትፎ የማያደርግ ሲሆን ወጣ ተብሎ ለማህበረሰቡ የተደረጉ ነገሮች እንደሌሉ አቶ ግርማ ይናገራል። ማህበሩ ካለው አቅም አንፃርና የሚያገኘው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ በልጆች ላይ ብቻ አተኩሮ ይሰራል። እንዲሁም ማህበሩ በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ስለማህበሩ ገለጻ ያደረገ ሲሆን በራሪ ጽሁፎችንም በትኗል።
በዚህም በአማራ መንገድ እና ህንጻ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት፣ በባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በላሊበላ ጥናት ዲዛይን እና ቁጥጥር ስራዎች፣ በጢስሳት ውሃ ስራዎች፣ በመቅደላ ኮንስትራክሽን፣ በጋፋት ኢንዶውመንት፣ በጣና ፍሎራ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በሌሎችም ድርጅቶች በየወሩ የአባልነት ክፍያ የሚከፍሉ ቋሚ አባላትን ማፍራት መቻሉን ያስረዳል።
ማህበሩ ህጋዊ ሆኖ ከተቋቋመ ጀምሮ ተረጅ ህጻናቱን የሚከታተልበት ወርሃዊ የክትትል ቅጽ በማዘጋጀት እና የክትትል ባለሙያ በመመደብ የህጻናቱን እና ወላጆችን ሁኔታ መከታተልና ጥሩ እና መሻሻል የሚገባቸውን ሁኔታዎች በመለየት ጥሩ የሆኑትን በማጎልበት እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸውን ደግሞ እንዲሻሻሉ ጥረት አድርጓል። በማህበሩ እየተረዱ ያሉ ሁሉንም ህጻናት በወር አንድ ጊዜ በየቤታቸው በመጎብኘት የህጻናቱን ሁኔታ እና ጤንነት በመከታተል አስፈላጊ ድጋፎችን አድርጓል።
በማህበሩ ከሚረዱ ህጻናት ሶስት ወንድ ህጻናትን በጋራዥ ሙያ ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመነጋገር ልምድ እንዲቀስሙ የተደረገ ሲሆን ይህም ጥሩ ጅማሮ ሆኖ ይታያል።
በማህበሩ ለሶስት ተከታታይ አመታት ሲታገዙ ከነበሩ ህጻናት መካከል የሁለቱ ህጻናት ቤተሰቦች ጥሩ ለውጥ በማምጣት ራሳቸውን በሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናቸውን በማረጋገጥ ከማህበሩ ተረጅነት የተሰናበቱ ሲሆን ማህበሩን በሚችሉት ሁሉ ለማገዝ የክብር አባል ሆነው እንዲቀጥሉም ማድረጉን አቶ ግርማ ይገልፃሉ።
የማህበሩ ዋና የገቢ ምንጭ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ከቋሚ አባላቱ ከሚሰበሰብ ወርሃዊ መዋጮ እና ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚገኙ ድጋፎች ሲሆን፤ በአማካኝ 80 በመቶ የሚሆነውን ወርሃዊ ገቢ ለተረጅዎች በቀጥታ በወርሃዊ ክፍያ መልክ እየሰጠ ያሉበትንም ሁኔታ ይከታተላል።
በተጨማሪም ለሰራተኛ ደመወዝ እና ለቢሮ ኪራይ ክፍያም ይከፍላል:: ቀሪውን 20 በመቶ ገንዘብ ደግሞ በማህበሩ ስም በተከፈተ የሂሳብ ደብተር ተቀማጭ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ።
የህብረተሰቡ አቀባበል
በባህርዳር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ለማህበሩ ጥሩ አቀባበል አላቸው። ነዋሪውም ወደ ማህበሩ እየተቀላቀለ ይገኛል። እስካሁን 480 ቋሚ አባላት እንዳሉ አቶ ግርማ ይገልፃሉ። 480 አባላቱ በቋሚነት መቶ ብር በየወሩ ያዋጣሉ።
ህብረተሰቡ ድጋፍ የሚፈልጉ ህፃናትን በመፈለግ በኩል እገዛ የሚያደርጉ ሲሆን አብዛኛው አባል በመሆኑ የተለያዩ አልባሳትን ይሰጣሉ። በሌላ በኩል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለማህበሩ የሚወገዱ የቢሮ እቃዎችን ይሰጣሉ። በገንዘብ ድጋፍና ስፖንሰር እንደሚሆኑ ይገልፃል።
በ2012 ዓ.ም. በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከሚገኙ አባላት ማለትም በአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት 110 ሺህ 710 ብር፣ በላሊበላ ጥናት፣ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት 67 ሺህ 900 ብር ተሰብስቧል።
በተጨማሪም በባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት 28 ሺህ 600 ብር የተገኘ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት ደግሞ 19 ሺህ 200 ብር ሊሰበሰብ ችሏል።
በተመሳሳይ በጢስሳት ውሃ ስራዎች ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት 16 ሺህ 400 ብር፣ በመቅደላ ኮንስትራክሽን ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት ስምንት ሺህ 100 ብር፣ በአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት ሰባት ሺህ 860 ብር የሚሆን ገቢም ተገኝቷል።
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ መሰረት በወጋገን ባንክ ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት ስድስት ሺህ 100 ብር፣ በዳሽን ባንክ ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት ሁለት ሺህ 200 ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት አንድ ሺህ 800 ብር እንዲሁም በተለያዩ የግል እና የመንግስት ስራ ዘርፎች ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት እና ከባንክ ወለድ የተሰበሰበ 33 ሺህ 445ከ 52 ብር ገቢ መሆን ችሏል። በድምሩ በ2012 ዓ.ም. በጀት አመት 305 ሺህ 615 ከ52 ብር ገቢ መሰብሰቡን አቶ ግርማ ያስረዳሉ።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ እንቅፋት እየፈጠረ ያለው በመንግስት መገናኛ ብዙሀን በኩል ስለ ማህበሩ ስራዎች ለመስራት ታስቦ እገዛ አለማድረጋቸው መሆኑን አቶ ግርማ ያመለክታሉ። ሌላው ማህበሩን እየገጠመው ያለው የገንዘብ እጥረት ነው። ለልጆቹ የሚሰጠው 350 ብር በአሁን ወቅት በቂ የሆነ ነገር የሚያከናውን አለመሆኑን ይጠቅሳል።
ከከተማው አስተዳደር በኩል የተጠየቁ የቦታ ጥያቄዎችን አቅርቦ እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ማህበሩ ከተመሰረተ አምስት ዓመት የሆነው ሲሆን በተሻለ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ችግሮች እየገጠሙ መሆኑን ይናገራል።
ማህበሩ ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች ቢሰራም አሁን ከሚሰራው በተሻለ መልኩ በመስራት ራዕዩን ማሳካት እንዲችል የሚከተሉትን ችግሮች ለመፍታት ከማህበሩ እና ከባለድርሻ አካላት በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በማህበሩ የሚረዱ ህጻናት እና የህጻናት ወላጆችን በዘላቂነት ራስን ማስቻል አለመቻል፣ በማህበሩ ለሚረዱ ህጻናት ማሳደጊያ ቦታ እና ህጻናቱን በዘላቂነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ በመርዳት ብቁ እና ጤናማ የአገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ እንዲሁም የተቸገሩ አረጋውያንን በተገቢ ሁኔታ ለመርዳት የሚያስችል የንግድ ሀሳብ እና ቦታ አለማግኘት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ማህበሩን በተለያዩ ነገሮች የሚደግፉ ቋሚ እና ተባባሪ አባላት ብዛት በተፈለገው ፍጥነት አለማድረግ፣ ማህበሩ ካለበት የገንዘብ እጥረት የተነሳ የህጻናቱን መሰረታዊ ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ መሸፈን የሚያስችል ወርሃዊ ክፍያ አለማግኘት ሌላው መሰረታዊ ችግር ነበር።
በተጨማሪም በማህበሩ እየተረዱ ከሚገኙ ህጻናት መካከል ባሳለፍነው በጀት አመት የሶስት ህጻናት አባቶች በተለያዩ ምክንያቶች መሞት እና የአንዲት ህጻን ብቸኛ አሳዳጊ አያቷ በማረፋቸው ምክንያት ያለ አሳዳጊ መቅረት ባሳለፍነው አመት ከገጠሙ ችግሮች ዋነኞቹ እንደነበሩ አቶ ግርማ ያብራራሉ።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
በቀጣይ ማህበሩ ትልቅ የህፃናት ማዕከል ለመክፈት እቅድ ያለው ሲሆን ማህበሩ በገቢ እራሱን ችሎ ተማሪዎቹ ለወላጆች፣ ለአገርና ወገን የሚበቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እቅድ አለው።
ድጋፍ የሚደረግላቸው ህፃናት ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ሳይሆን ለራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲኖር ለማድረግ ማህበሩ የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ግርማ ያብራራሉ። የሚደረግላቸው ልጆች እራሳቸውን ችለው ለሀገር እንዲበቁ ለማድረግ ማህበሩ ጠንክሮ ይሰራል።
በተጨማሪም ለሙያ ትምህርት የደረሱ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ልጆችን ለማስተማር ጥረት እንደሚደረግ ያስረዳል። ወላጅ የሌላቸውን ተማሪዎች በሚገነባው ማዕከል ውስጥ ለማሳደግ እቅድ እንዳለ ይጠቅሳል።
የአባላቱን ቁጥር በየጊዜው መጨመር እና ከአጋር አካላት ጋር በመስራት የማህበሩን የመርዳት አቅም ማሳደግ፣ የሚረዱ ህፃናትን ቁጥር መጨመር እና ወላጆቻቸው ወይንም አሳዳጊዎቻቸው እራሳቸውን የሚችሉበትን አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል።
ማህበሩ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ያጡ ህፃናትን በዘላቂነት ለመርዳት ይረዳው ዘንድ የህጻናት ማሳደጊያ ቦታ ከመንግስት ማግኘት እና የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የማህበሩን አቅም ማጎልበት፣ የማህበረሰቡን የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህል የሚያንፀባርቁ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት በጎ ፈቃደኞችን እና ችግረኛ ወገኖችን የሚያገናኝ መድረክ ማመቻቸት ላይም እየሰራ ይገኛል።
የማህበሩን በጎ ስራዎች በተለያዩ የመገናኛ መድረኮች እና የማህበራዊ ሚዲያዎች በማስተዋወቅ ማህበሩን በተለያዩ ነገሮች ሊደግፉ የሚችሉ አዳዲስ አባላት ማፍራት እና ማህበሩን እየረዱ ለሚገኙ አባላት አስፈላጊውን መረጃ በማድረስ በማህበሩ ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከፍ እንዲያደርጉ ለማስቻል እንደሚሰራ አቶ ግርማ ይገልፃሉ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም