የዲፕሎማሲ አንዱ ሥራ ከአገራት ጋር ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን መገንባት ነው። ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይም በሌሎች አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና ማዳበር ነው። የሻከሩ ነገሮችም ካሉ ማለስለስን ያካትታል። ሌላው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑት መካከል አንዱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ነው። ማለትም ወደ አገሪቱ ኢንቨስትመትን መሳብ፣ በአገራት መካከል ያለውን ንግድ ማጠናከር፣ የሌሎች አገር ጎብኝዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ማድረግና መሳለጥ፣ ማግባባትና ማደፋፈር ያካትታል። እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ ለሌሎች አገሮች ማስተዋወቅንም ይጨምራል። እንዲሁም የኢትዮጵያን ገፅታ መገንባት፤ በጎ መልኳን፣ ተስፋዎቿንና ራዕይዎቿን ሌላው ዓለም በትክክል እንዲያውቅና እንዲገነዘብ ማድረግ ነው።
ከዚህ አኳያ ከአምባሳደር ዋነኛ ተግባራት አንዱ በሚሰማራበት አገር የአገሩን ጥቅምና ፍላጎት ማንፀባረቅ ብሎም አግባብ ባለው መንገድ መፈፀም ነው። የአገርን ጥቅም በሙሉ ልብ፣ በፍላጎት፣ በታማኝነትና ትዕግስት ባለው መንገድ ማከናወን ነው። አምባሳደር ማለት የአገር መገለጫ፣ ገፅታና ፊት ነው። እንዲሁም የአገር ቁም ነገርም መታያና መመዘኛ ነው። ስለሆነም ይህን ኃላፊነት የተሰጠው ሰው በዚህ ልኬት የአገሩን ፍላጎትና ጥቅም ማራመድ እንደሚኖርበት ዲፕሎማቶች ይገልጻሉ፡፡
የአገር አምባሳደር መንግሥት የሚመድበው አምባሳደር ብቻ ሳይሆን ዲያስፖራውም በብዙ መልኩ የአገር አምባሳደር መሆኑን እነዚህ ዲፕሎማቶች
ይናገራሉ፡፡ በተለይ በመልካም ይሁን በአስቸጋሪ ጊዜ በሚኖርበት አገርና ኢትዮጵያ መካከል ትብብር ለማጠናከርም ሆነ ምን አልባት የማይግባቡባቸውን ጉዳዮች ካሉ ደግሞ ግንኙነታቸውን ለማለስለስ ዲያስፖራው የሚጫወተው ሚና ከፍ ያለ ነው።
አንድ ዲያስፖራ በአገሩ ኢንቨስት ከማድረግ፣ ኢንቨስትመንትን ከመሳብና በውጭ ያገኘውን የሥራ ባህልና እውቀት ከማሸጋገር ባለፈ በውጭ አገር ሲኖር የሚወክለው የሚሰራበት ድርጅትን ወይም ራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩንና ሕዝቡን ስለሆነ አገራዊ ኃላፊነቱ ከፍ ያለ ነው። ዲያስፖራው በሚኖርበት አገር ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚነሱ ጉዳዮችን የማስገንዘብ፣ የመከላከል፣ የማስረዳትና ለመልካም ገፅታ ግንባታ የማመቻቸት አገራዊ ኃላፊነት ጭምር አለበት።
ዲያስፖራው በሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ በተለያዩ መድረኮችና በአደባባዮች ጭምር አገርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ለመወያየት ወይም ለማስረዳት እነዚህን ምቹ መድረኮች መጠቀም ይኖርበታል። በአጭሩ ከዲያስፖራው የሚጠበቀው በአስቸጋሪ ጊዜም ቢሆን የአገርን ጥቅም ለማስከበር መልካም ገፅታዋን ለመገንባት በታማኝነት፣ በፅናት፣ በብቃት ማስረዳት እንዲሁም አገርን ከሚጎዱና ከሚያጠለሹት ለመከላከል መጣር ነው። ይኽን የማይፈፀም ዲያስፖራ ለአገርና ለሕዝብ ፍቅርና አክብሮት እንደሌለው ይቆጠራል።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገር ጋር ኢትዮጵያ ያላት ግንኙነት መልካም ፍሬ ያለው እንዲሆን የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ «የዳቦው መጣፈጥ የሚለካው በዕይታ ሳይሆን ሲበላ ነው» እንደሚባለው ሁሉ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር መኖራቸው ጥቅሙ የሚለካው ራሳቸውን ከመለወጥ ባሻገር ለአገራቸው በሚያደርጉት ሁለተናዊ ተሳትፎም ጭምር ነው።
ሰሞኑን በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎች በትግራይ ክልል ሕግ ማስከበር ዘመቻና በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ በውጭ አገራት በተለይ አሜሪካ በውስጥ ጉዳያችን የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት አደባባይ በመውጣት ጭምር ተቃውመውታል፡፡ ይህ ደግሞ ዲያስፖራው በሚኖርበት አገር የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ እየሰራ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለዘመዶቻቸው ገንዘብ በመላክ፣ ኢንቨስት በማድረግና በውጭ አገር የቀሰሙትን እውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ በአገራቸው እንዲስፋፋ ከማድረግ ባሻገር የሚኖሩበት አገርና በኢትዮጵያ መካከል ያሉ መልካም ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና ውጥረቶች እንዲረግቡ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተወጡ ናቸው፡፡
በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ህብረትና አንድነታቸው ያን ያህል ቢሆንም፤ የባንዳነት ተግባር የሚፈጸሙ ዲያስፖራዎች ቢኖሩም፤ አገር ወዳድ ዲያስፖራዎች የውጭ ጣልቃ ገብነትም ሆነ ያልተገባ ውሳኔ ለመቃወም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት ለማስረዳት የሚያሳዩት መነሳሳት የሚደነቅና የሚበረታታ ነው፡፡
አሜሪካ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት የምትፈጥረውን ጫና በመቃወም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታችን አንደራደርም፣›› ‹‹የውስጥ ጉዳያችን ራሳችን እንነፈታዋለን፤›› ‹‹በሀሰት መረጃዎች ኢትዮጵያ ላይ ጫና አትፍጠሩ፣›› ‹‹እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ›› የሚሉ መልዕከቶችን በማስተላለፍ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው አቋም የተሳሳተ መሆኑን አደባባይ በመውጣት ገልጸዋል፡፡፡
እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቴሌግራም፣ ኒውስ ዊክ፣ አልጀዚራ፣ አሶሼትድ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሚያሰራጩት ሚዛናዊነት የጎደለውና የሀሰት ዘገባዎች እንዲቆጠቡም ጭምር የሚያሳስቡ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡ ዲያስፖራው አገሩን በሚመለከት የሚፈጠሩ ውጫዊ ጫናዎችን መቃወም ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛል፡፡
አባቶቻችን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ነፃነቷን አስጠብቀው ያቆዩአትን አገር ውስጥም ውጭም የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሁሉ የውጭ ጣልቃ ገብነትምና ጫናን በአንድነትና በትብብር ተናበን መመከት ይኖርብናል፡፡
ይህን የምናደርገው ዋናው በኢኮኖሚ ልማት ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦች እና ምርቶች ለዓለም በማስተዋወቅ…ወዘተ መስኮች መሳተፍ አለባቸው። እየተሳተፉ የሚገኙም ዲያስፖራዎች
አሉ፡፡ እነዚህን ተግባሮች ዲያስፖራው በሚፈለገው መጠንና ዓይነት መፈጸም ከቻለ፣ ኢኮኖሚያዊ እመርታን ለሚወዳት አገሩ በማስመዝገብ ታሪካዊ አሻራውን ሊያሳርፍ መቻሉ አያጠራጥርም። እዚህ አገር ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርገው ገንዘብ ደግሞ ከራሱ ባለፈ አገሩንና ወገኑን የሚጠቅም ነው። ስለሆነም በሁሉም የኢንቨስትመንት መስኮች በመሳተፍ የሚወዳትን አገሩን መደገፍ ይኖርበታል።
ስለዚህ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዕውቀት፣ የሙያ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለኢትዮጵያ እንዲያበረክቱ እንዲሁም አገር ውስጥ ገብተው መስራት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትን ጨምሮ ልዩ ልዩ አሳታፊ ተግባራትን በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የዲያስፖራው ሚና የማይናቅ ነው፡፡ መንግሥትም የዲያስፖራው መብት እና ጥቅሙ እንዲከበር ከመታገል ጎን ለጎን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የዲያስፖራ ፖሊሲ በማውጣት ኢትዮጵያውያን በአገሩ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርግ የአገሪቱ አለኝታና አጋዥ በማድረግ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ነገርግን እንደ የዘመኑ ግለትና መብረድ የዲያስፖራው ተሳትፎም አንዳንዴ ሞቅ አንዳንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ ይላል። እናም የዲያስፖራ እንቅስቃሴ ግለቱን ጠብቆ ያለመቀጠል ካልሆነ በስተቀር ሥራዎች አልተሰሩም ማለት አይቻልም። ሆኖም የሚፈለገውን ያህል ግን እንዳልሆነ መናገር ይቻላል። በዓለም ዙሪያ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገራት እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ የእነዚህ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በአገር ላይ የሚያመጣው ለውጥ ከፍተኛ ነውና ዲያስፖራው አሁንም ጠንክሮ ለአገሩ ጥቅም መቆም አለበት፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013