እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጣራ (Ethiopia is the roof of Africa.) ነች። ይህን ስንል ሌላውን ሁሉ ትተን አንዱን ብቻ ለመግለፅ ያህል እንጂ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሁሉንም ነች ማለት ይቻላል። ሁሉንም ትሁን እንጂ ምላሹ ግን ሁሉንም እንደመሆኗ አይደለም። ጎንታይዋ ብዙ ነው፤ ጠላትም አጥታ አታውቅም።
መቼም “ኢትዮጵያ በጠላት የተከበበች አገር ነች” የሚለውን ያልሰማ የለም። ባይሰማ እንኳን አንብቧል። በመሆኑም አባባሉም ሆነ አሁን ከእነ ግብፅና አጃቢዎቿ እየተደረገ ያለው ኢትዮጵያን የማተራመስ አካሄድ አዲስ አይደለም።
ቅኝ ገዥዎች በኢትዮጵያ ላይ ማተኮር የጀመሩት ገና ካፒታሊዝም በምዕራብ አውሮፓ ማቆጥቆጥ ከጀመረበት ከ16ኛው ምዕተ ዓመት አንስቶ ነው። በጊዜው በአውሮፓ ኃያል የነበረችው ፖርቹጋልና በመካከለኛው ምሥራቅ በየብስ ንግድ የበላይነትን የያዘችው ኦቶማን ቱርክ የቀይ ባህር አካባቢን ለመቆጣር ያደረጉት በነበረው ፉክክር ኢትዮጵያን ለመያዝ ሙከራ አድርገዋል። ለፉክክራቸውም የሀይማኖት ሽፋን በመስጠት ፖርቹጋል ነገሥታቱን፣ ቱርክ ደግሞ አሚሮችንና ሱልጣኖችን በመደገፍ በየበኩላቸው መላ ኢትዮጵያን ለመያዝ ታግለዋል። ይሁን እንጂ አንዱም አልተሳካላቸውም።
በ19ኛው ክ/ዘመን ካፒታሊስት አገራት ዓለምን ለመቀራመት ባሰፈሰፉበት ወቅትም ቀዳሚ ትኩረታቸው “ለሟ ኢትዮጵያ ነበረች።” በዘመነ መሣፍንትም በእርስ በርስ ሽኩቻ (ልክ እንደ አሁኑ) በመታመሷና ውስጣዊ አንድነቷ በመዳከሙ ለኢምፔሪያሊስቶች ጥቃት ተጋልጣ ነበር። ዝርዝሩ ብዙ ነው። (የአገራችን የአገራትን ቀልብ የመሳቧን ጉዳይ ከአሁኑ ወቅት ፀሐፍት አገራትን፣ በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋምና ያላቸውን አተያይ ዘርዘር ባለ መልኩ፤ ራሳቸውን አስችሎ ያየው የፍቅረሥላሴ “እኛና አብዮቱ” ሲሆን፤እሱን መመልከት ጠቃሚ ነው።) የውጪ ጠላት፣ ወራሪ ሀይል ወዘተ ስንል “እነዚህ ሀይሎች እነማን ናቸው?” የሚል ጠያቂ ወጣት ቢኖር ትክክል ነው። ለትክክለኛነቱ ደግም ምክንያት ያለው ሲሆን፤ ምክንያቱም እነዚህ ሀይላት እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝረው የሚያልቁ ባለመሆናቸው ግርታን መፍጠራቸው የማይቀር መሆኑ ነው። እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን … እያልን ብንጀምር መቆሚያችን እሩቅ ነው፤ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ … እያልን ወደ ራሳችን አህጉር – አፍሪካ ብንመጣም እየተመላለሱ የሞከሩንን ዙር መቁጠሩ በራሱ አድካሚ ነው። ባጭሩ “ኢትዮጵያ በጠላት የተከበበች አገር ነች” የሚለውን ይዘን መዝለቁ የተሻለ ነው።
ከላይ ኢምፔሪያሊስት አገራት እንበል እንጂ ጉዳዩ በእነሱ ብቻ አያበቃም፤ የራሳችን ወንድሞች፤ ለኢምፔሪያለዝም አጎብዳጅ በሆኑ አንዳንድ አፍሪካዊያን አገራትም በተደጋጋሚ የመውረር፣ መውጋትና ከዓላማ የማደናቀፍ ተግባራት ተፈፅመውብናል። ከእነዚህ ቀዳሚና ፊት መሪዎቹ ግብፅና ሱዳን ሲሆኑ፤ እስካሁን በተደጋጋሚ ትንኮሳ የሚደርስባቸው አልተገኘም። ጉዳዩም ከግብፅ ጀምረን እንመልከተው።
በፈረንጆቹ በ1927 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ግብፅና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸው በግልፅ መደፍረስ የጀመረው ከዚሁ ግንኙነታቸው አስቀድሞ በአልባንያዊው መሐመድ አሊ ፓሻ ዘመን (ከ1805 እስከ 1848 ግብፅን የመራ) ሲሆን፤ “ግብጽን ለማዘመን” በሚል መነሻ አባይን ለመቆጣጠር ማቀዱ፤ የልጅ ልጁ ከዲቭ እስማኤል ፓሻ የአያቱን “ሌጋሲ” ለማስቀጠል መፈለጉና በመሐመድ ፈለግ ለመሄድ መሞከሩ ነው። ናሥር፣ ሣዳት፣ ሙባረክ … እያልን ከአሁኑ አልሲስ ድረስ ብንመጣ ያላቸው አቋም ያውና ያው ሆኖ ነው የምናገኘው ከመሆኑም በላይ፤ በአሉላ (የጉራው አንበሣ)ና ሠራዊታቸው ከሚገባው በላይ ተገርፋ በ”አይለመደኝም” የተመለሰችበትን የጉንደትና ጉራ ጦርነት ለመክፈት ምክንያት የሆናት “እነዚህ ሰዎች ከተማሩ አባይን ልገድብ ይላሉ” ስለዚህ … ፤ ያ ሥጋቷ ዛሬ (“የፈሩት ይደርሳል …”እንዲሉ) ላይ እውን ሆኖ ማየቷ የፈጠረባት ንዴትና ቁጭት እንደ ጦስ ዶሮ እያሯሯጣት አበው በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንዳሉት በገዛ ውሀችን እንዴት ሆኖ ግድብ ይታሰባል በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ እንዳለች እነሆ ግድቡ ለጠናቀቅ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል።
በተለይ የ”ኢትዮጵያ–ግብፅ ጦርነት” በመባል የሚታወቀው ጦርነት (ከ1874 እስከ 1876) በሁለቱ መካከል ከተካሄዱ ግጭቶች ጎልቶ ይታይ እንጂ ግብፅ ሁሌም ከኢትዮጵያ ላይ አርፋም ሆነ ተኝታ አታውቅም፤ እንደባነነች ነው። ዓላማና እቅዷ ደግሞ አባይን ሙሉ ለሙሉ ከመጠቅለል ጣናንና አካባቢው ሁሉ ኢትዮጵያን ማስወጣት ድረስ ይዘልቃል። (ለበለጠ ግንዛቤ በገብረ-ፃድቅ ደገፉ ተጽፉ በወርቁ ሻረው ወደ አማርኛ የተመለሰውንና “ናይል፤ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ልማታዊ ገፅታዎች፤ ለ21ኛው ክፍለ-ዘመን ማስጠንቀቂያ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውንና በመረጃ የታጨቀውን መጽሐፍ መመልከት ይቻላል።)
ይህ “እነዚህ ሰዎች ከተማሩ አባይን ልገድብ ይላሉ” ዓይነት የግብፅ ፉከራና ከዲፕሎማሲ ፍልስፍና ጋር አምርሮ የተጣላ ኢትዮጵያንና አባይን የተመለከተ ስድ አስተያየት የአንድ መሪ ብቻ አይደለም፤ ከፈርኦን ጀምሮ ሁሉም በሚባል ደረጃ ተመሳሳይ አንደበት ነው ያላቸው – እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ። “ኢትዮጵያን በቦንብ መደብደብ …”፣ “ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ የሚያስገባን ውሀ ብቻ ነው…” እስከ ቅርቦቹ በአንድ በተን /የኮምፒውተር ቁልፍ/ ነው የምናጠፋት” ድረስ አንድ ናቸው። የፑትሮስ ፑትሮስ ጋሊም ሴራ የእነሱው የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታ እንጂ ሌላ አይደለም። ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ግብፅ ሕገመንግስቷ ውስጥ “አባይን የነካ …” የሚል አንቀፅ (“አንቀፅ 44”ን ይመለከቷል) ማካተቷም የዚሁ ከውሃ ዲፕሎማሲ መራቋን እንጂ ሌላ አያሳይምና ዛሬም እዚያው ነች ማለት ነው።
የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተቃራኒ ጎራ መቆሙን ለመገንዘብ ከኋላ ጀምሮ መመልከት የሚቻል ሲሆን፤ አፄ ዮሐንስ ለውይይትና የጋራ መፍትሄ ፍለጋ የላኳቸውን አምባሳደር እስከማሰር ድረስ የሄደ ፀረ-ዲፕሎማሲ አቋሟን ማንሳት ይቻላል። በጥቅሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የአፍሪካዊ ወንድማማችነትና አብሮነት ሲሆን፤ በተቃራኒው የግብፅ ደግሞ የጠላትነትና ኢትዮጵያን የእስልምና ሀይማኖትና የአረቡ አለም ጠላት አድርጎ የማቅረብ እኩይ ተግባር ሆኖ ነው እዚህ ድረስ የዘለቀው። ኢትዮጵያ ከመደበኛውም አልፋ እስከ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ድረስ ብትሄድም በግብፅ በኩል ያለው ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት እንጂ ወደ ወንድማማችነት የመምጣት ሁኔታ አልታየም። (ሌላውና ኢትዮጵያን እያስመሰገናት ያለው መሠረታዊ ጉዳይ “ለአፍሪከ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ አጥብቃ መያዟ ሲሆን፤ በእነ ግብፅ በኩል ግን ወደ እነዚያ፣ ቅኝ ሲገዟቸው ወደነበሩት ማቅናታቸው ለከፋ ትዝብት ያጋለጣቸው መሆኑ ነው።) ወደ ሱዳን እንምጣ። ከዚያ በፊት ግን የግብፅ አጠቃላይ ግብ ምንድን ነው? የሚለውን እንመልከት።
ጂ.ዶኢን (ከላይ በገለፅነው የወርቁ ትርጉም ላይ እንደሰፈረው) እንደሚሉት “…የከቪድ [በወቅቱ በግብፅ የቱርክ እንደራሴ] የቅኝ አገዛዝ ሥራን አንድ ሀረግ ሊያጠቃልለው ይችላል። እሱ ናይልን የግብፅ ወንዝ ማድረግ፣ የተፋሰሱን ጂኦግራፊአዊ አካባቢዎችንም ወደ አገሩ ለመቀላቀል፤ … ታላቅ ንድፍ፣ ከፍተኛ ብልህነት የሚታይበት ምልክት።” (በወቅቱ ግብፅ የኦቶማን ቱርክ ጠቅላይ ግዛት ነበረች።) ሱዳን፤ የሱዳንና የኢትዮጵያን ግንኙነት በተመለከተ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ የሚሉት አለ። እንደ እሳቸው አስተያየት የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት እንዲህ በቀላሉ የማይታይ ሳይሆን “የአሜሪካንንና የካናዳን ግንኙነት መምሰል አለበት። ለዚህም በቂ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ የሥጋ ዘመዳሞች ነን። መርዌዎችን በመልክ ከኢትዮጵያውያን መለየት አይቻልም። […] ሁለቱ ሕዝቦች የሠላም መልክተኞችን ይለዋወጡ ነበር።
“መርዌዎች ጳጳስ ከግብጽ እንድናስመጣላቸው እርዳታ ለመጠየቅ ጊዮርጊስ የሚባለው ንጉሣቸው መልዕክተኛ ልኮ የነበረው ወዳጆች ስለሆንን ነው። “ሱዳን” በዐረቢኛ፥ “ኢትዮጵያ” በግሪክኛ ይሁን እንጂ ትርጉሙ አንድ ነው። “ጥቍሮች”፥ “ጠይሞች”፥ “ኩሻውያን” ማለት ነው።” የሚሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ያኼንን ወዳጅነት ተንከባክበን መያዝ አለብን።” ሲሉም ለዘላቂ ሠላም ሲባል አሁን ላይ ያለውን የሱዳን ጥፋት መታገስ እንደሚገባና በጥበብ የተሞላ ዲፕሎማሲን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። ቀጥለውም፤
“በቅርቡ እንደሚሰማው ኢትዮጵያም ሱዳንም ምድሬ ነው የሚሉትን በኢትዮጵያዊያን እጅ ያለውን መሬት ሱዳን ወርራለች። ይኼ ድርጊት መልካም ጉርብትናን ከማጉደፍ አልፎ ጦርነት የሚያስነሣ ድፍረት ነው። ከሕዳሴ ግድባችን ጋር የተያያዘ አደፋፋሪ እንዳለ ግልጽ ነው። ሆኖም ድፍረቱ ሕይወቷ የኢትዮጵያ ውሀ የሆነውን ሱዳንን አርቆ አስተዋይ የሌለባት ሀገር አድርጓታል። ምክንያቱም፥ ማንም መንግሥት ለማስተዳደር የተሾመበትን ወይም ራሱን የሾመበትን ሀገር ሌላ ሀገር ሲዳፈር ምን እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። ያለአንዳች ጥያቄ ጦርነት ያስነሣል።” በማለት የአሁኑን የሱዳንን ያላዋቂ ጠብ አጫሪነት ይገልፃሉ፤ ሆኖም ግን መቻልና በገለልተኛ አካል ለችግሩ መፍትሄ ማፈላለግ ተገቢ እንደሆነም ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያንና የሱዳንን ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ የሱዳንን ያልበሰለ አስተሳሰብና የኢትዮጵያን ስክነት በተመለከተም “መሬቱ ለበልግ በሚዘጋጅበት ጊዜ ወርራለች፤ ይህ ድርጊት ከድፍረት አልፎ ሰውን ለረሀብ የሚዳርግ ወንጀልም ነው። ወረራው ወንጀልም ሠይፍ የሚያማዝዝም ሆኖ ሳለ፥ ኢትዮጵያ ያለፈውን ታሪክ በማስታወስ፥ የወደፊቱን የጋራ ጥቅም በማሰብ ትዕግሥት ማሳየቷ የሚያስመሰግናት ነው።” ብለዋል። ይህ የአሁኑ የሱዳን አካኪ ዘራፍና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አንዳንዶች እንደሚሉት የኢትዮጵያ አቅም ማጣት ሳይሆን ስክነቱ የሚያስገኘውን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ነው ከጌታቸው የምንረዳው። ሆኖም ግን መቻልና ለችግሩ መፍትሄ ማፈላለግ ተገቢ እንደሆነም ነው ያሳሰቡት – ፕሮፌሰሩ።
እንደዚህ ፀሀፊ እምነት የሱዳንን ታሪካዊ ባህርይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በተመለከተ ባጭሩ ግልፅ አድርጎ ያሳየ ሥራ ቢኖር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” ሲሆን፤ ሱዳን “ሁሌም ጥርስ ብቻ ነች”። ኢትዮጵያ ለሱዳን እንጂ ሱዳን ለኢትዮጵያ ምን ጊዜም የልብ ወዳጅ ሆና አታውቅም ማለቱ ነው። ይህንንም ይኼው እየተመለከትነው ነውና የሱዳን ሥራ የባህርይ ነውና አይደንቅም።
የወቅቱን የሁለቱን አገራት ሁኔታና በኢትዮጵያ ላይ እያሴሩ ያሉትን ሸር በተመለከተም መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉትና የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት አብዱራህማን ሰኢድ አቡሃሽም ከቢቢሲ አማርኛው ጋር ባደረጉት ቆይታ “አንዱ የጡዘቱ ምክንያት [በአሁኑ ወቅት በሁለት መንግሥት – ጦር ሀይሉ ለብቻ፤ ራፒድ ፎርስ የሚባለው ደግሞ ለብቻ አገሪቱን እየመሩ ይገኛሉ] ሱዳን አቋም መቀየር ነው” በማለት መግለፃቸው “አባይን በተመለከተ የሱዳንና የኢትዮጵያ አቋም አንድ ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ሱዳን ያሳየችው የአቋም ለውጥ በፊት ከነበረው በጣም የተለየና ያልተጠበቀም ነው” ሲሉም ምክንያታቸውን መናገራቸው የፍቅረሥላሴን “ሱዳን ሁሌም ጥርስ ብቻ” የሚያፀድቅ ነው።
በራሷ የውስጥ መረጋጋት የሌላትና ከግብፅ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት ላይ የምትገኘው “ሱዳንና ግብፅ የደረሱበት ስምምነት ሰፊ ነው። የዲፕሎማሲ ግንኙነትም አለው፤ ሌሎች ሌሎች ስምምነቶችም አሉ። እንግዲህ ኢትዮጵያ ግፊት ደርሶባት በአባይ ላይ ያላትን አቋም ብታቀዘቅዝ ግብፅም ትጠቀማለች፤ ሱዳንም ትጠቀማለች። ስለዚህ ጥቅሙ የሁለቱም ነው” የሚሉት (ቢቢሲ) ደግሞ ኔዘርላንድስ የሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር አደም ካሴ ናቸው። እንደ ዶክተር አደም አስተያየት ሱዳን ከእንዲህ ዓይነቱ ኢትዮጵያን ከሚጎዳ ተግባር ብትቆጠብ ይመረጣል። ምክንያቱ ደግሞ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚፈሩት ወደለየለት ጦርነት የሚያመራ ከሆነ ሱዳን ከምታተርፈው በላይ ልትጎዳ” ስለምትችል ነው።
ፕሮፌሰር ያዕቆብም (በአንድ ጥናታቸው) እንደሚሉት አባይን የመገንባት ጉዳይ አሁን የተጀመረ ሳይሆን የኢትዮጵያ የቆየ ሕልም እንጂ ዛሬ የተወጠነና የተጀመረ አይደለም። ኢትዮጵያ በ1894 ዓ.ም የአባይ ተፋሰስንም ሆነ ገባሪ ወንዞችን ፍሰት ላለመግታት በይፋ ቃል ገብታ የነበረ መሆኑም ለዚሁ ማረጋገጫ ነው።
በ1994 ዓ.ም ግብፅና ሱዳን ተፋሰሱን በብቸኝነት ለመጠቀም በድብቅ ሲደራደሩ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ተቃውማ መግለጫ አውጥታ የነበረ ሲሆን፤ የመግለጫው ይዘትም የሁለቱ ሚስጥራዊ ድርድርና ውሣኔ ፍፁም ስህተት መሆኑን፤ ክፍፍሉም ኢፍትሀዊ መሆኑን፤ ኢትዮጵያ ወደፊት ተፋሰሱን በወቅቱ ለነበረውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲባል ጥቅም ላይ ልታውለው እንደምትችል የሚያመላክት ነበር። (ይህ የግብፅና ሱዳን መደጋገፍ በኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት ወቅትም ምን ያህል የተጠናከረና ለኢምፔሪያሊስቶች በማደር ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚችሉት በላይ እስከ መሄድ እንደደረሱ በወቅቱ ከነበሩት ሰነዶች መረዳት ይቻላል፤ ከዚህ ቀደምም በዚሁ ጋዜጣ ስለ ጉዳዩ ጽፈናል።)
በተለያዩ ጊዜያት እንዳመለከትነው ተቆጥረው የማያልቁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያና ግብፅ ውዝግብ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በሂደቱም ሱዳንም ከግብፅ ልጣፍ ሥር ጠፍታ አታውቅም። አገራቱ ምድር ያፈራችውን የተፈጥሮ ፀጋ ‘የኔ የኔ’ ሳይባባሉ በጋራ መጠቀም ያለባቸው መሆኑንና ወዳልተፈለገ ውሀ አመጣሽ ጦርነት መግባት እንደሌለባቸው፤ ለውኃ ዲፕሎማሲ መርሆችም ሊገዙና ሊመሩ እንደሚገባ፤ መፍትሄውም የጋራ ውይይት፣ ፍትሀዊነት፣ እኩልና የጋራ ተጠቃሚነት መሆኑን ያስገነዝባሉ። “‘Oil Then,’ ‘Water Now’: Another Reason for War in the 21st Century?”ም ይህንኑ የሚያስረግጥ ጥናት ነው።
በእነዚህም ሆነ ሌሎች በርካታ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተውም ሆነ የተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት በሦስቱ አገራት መካከል ያለው የቆየ የግንኙነት ታሪክና ዳራው ሲፈተሽ ኢትዮጵያ የምትከተለው የግንኙነት መሠረት በመርህ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ የውኃ ዲፕሎማሲ፤ ፍትሀዊ አጠቃቀም መርህን በተመለከተ ግብፅና ሱዳን ከሚያራምዱት ጋር ሲነፃፀር ፍፁም ዘመናዊ ሆኖ ነው የሚገኘው፤ በጋራና እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑም እንደዚያው።
በመጨረሻም አስታራቂ፣ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች በየወቅቱ ብቅ ጥልቅ ሲሉ የመስተዋላቸው ጉዳይ ነው። ለበጎ ከሆነ እሰየው፤ ካልሆነና እኛን ከግድባችን ለማላቀቅ ከሆነ ግን አፄ ምኒልክ ፌብሯሪ 27 ቀን 1893 ለአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት የላኩት ደብዳቤ መግቢያን ዛሬም እዚህ እንድንደግመው እንገደዳለን።
“ኢትዮጵያ ማንንም አትፈልግም፤ እጇን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።”
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም