በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ሥርጭት እለት በእለት እየጨመረ መጥቷል። ይህንንም ተከትሎ በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል። በቫይረሱ ተይዘው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ያሉ ዜጎች ቁጥርም አሻቅቧል። ይህም ሀገሪቱን ከአፍሪካ ቀዳሚ አድርጓታል።
ቫይረሱ በዜጎች ጤና ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና አስቀድሞ ለመቀነስ በመንግስት በኩል አዳዲስ የኮቪድ-19 የህክምናና ማገገሚያ ማዕከላት ተገንብተዋል። አንዳንድ ነባር ሆስፒታሎችንም ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማእከል የመለወጥ ስራ ተሰርቷል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱና በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥርም በማሻቀቡ በሚፈለገው ልክ የህክምና አገልግሎት መስጠት አልተቻለም።
የፅኑ ህሙማን ክፍሎችም በታማሚዎች በመጨናነቃቸውና አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎችም ከህሙማን ቁጥር በታች እየሆኑ በመምጣታቸው በየእለቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በመንግስትም ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
ይህን ጫና ከመቀነስ አኳያ የግሉ ጤና ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ያኔት›› የተሰኘ የኮቪድ 19 የህክምና ማእከል ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የሊያና ሄልዝ ኬር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚና የህክምና ማእከሉ ባለቤት ዶክተር ግርማ አባቢ እንደሚገልፁት እንደ ግል የጤና ተቋም ኮቪድን በሚመለከት ኩባንያው ላለፉት አስራ አምስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች ለመሳተፍ ሙከራ አድርጓል። የኮቪድ ምላሽን በሚመለከትም በአማካሪ ግብረሃይሉ ውስጥ በመሳተፍ በሀዋሳ ከተማ 80 አልጋዎች ያሉትና ስድስት የፅኑ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የኮቪድ-19 ህክምና ማእከል ወደ ስራ በማስገባት ላለፉት ሶስት ወራት ሲሰራ ቆይቷል።
በተመሳሳይ በኮቪድ ምክንያት ያለውን ንክኪ ለመቀነስና ሰዎች በቤታቸው ሆነው የህክምናና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ አዲስ አበባ ላይ ከአራት ወራት በፊት የዲጂታል ጤና እንክብካቤ ማእከል ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ከኮቪድ ህክምና ጋር በተያያዘ የአልጋ ውስንነቶች በመኖራቸው፣ ለፅኑ ህሙማን በቂ አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ባለመሟላታቸውና ከሚታየው የኦክስጂን እጥረት በመነሳት ኩባንያው በከተማዋ ሀያት አደባባይ አካባቢ ለህሙማን የሆስፒታል ሳይሆን የሆቴል ስሜት የሚሰጥ የኮቪድ ህክምና ማእከል ከፍቷል።
እንደዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ ማእከሉ ስምንት የፅኑ ህሙማን፣ ሃያ ሰባት የሃይ ዲፔንደንሲ ዩኒትና በመጠነኛ ሁኔታ የታመሙና በኮቪድ ምክንያት ራሳቸውን አግለው ለሚቆዩባቸው አገልግሎት የሚሰጡ አልጋዎችን አካቷል። የሚታየውን የኦክስጅን እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባትም ማእከሉ በእህት ኩባንያው በኩል በሀዋሳ ከተማ የሚያመርተውን ኦክስጂን ለማቅረብ አመቻችቷል፤ አምቡላንስም አዘጋጅቷል። የዲያሊሲስ ማሽኖችንም አሟልቷል። ለማእከሉ የህክምና መሳሪያዎችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ማሟያም 25 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂው በኩል ታካሚዎች በማዕከሉ ሆነው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቅርበት መስራት የሚችሉበትን አሰራርም ዘርግቷል። የህክምና አገልግሎት ክፍያውም በተቻለ መጠን በጥናት ላይ የተመሰረተና የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ተደርጓል። አገልግሎቱን ለመስጠትም በማዕከሉ 60 የቴክኒክና 29 የአስተዳደር ሰራተኞች ተመድበዋል።
የዚህ ማእከል ወደ ስራ መግባትም ሀላፊነት በተሞላበት መንገድ ለማህበረሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ የኮቪድ-19 ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። በዋናነት ደግሞ የኮቪድ ህክምና አገልግሎት በመንግስት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ የመንግስትን ጫና ከማቃለል አኳያ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ለህክምና ወደውጪ ሀገር የሚወጡ ሰዎችንም ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ይሞላል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደሚሉት ኮቪድ-19 የጤናው ሴከተርም ሆነ መንግስት ለብቻቸው የሚቋቋሙት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር ይጠይቃል። ከዚህ አኳያም መንግስት ወረርሽኙ በሀገር ውስጥ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግና በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን አከናውኗል። ከላብራቶሪ ግንባታ እስከ የህክምና መስጫ ተቋማትና ባለሞያዎችን የማዘጋጀት፣ የቅኝት ስራውን የማጠናከር እንዲሁም የማህበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራም ተሰርቷል።
የመንግስት አቅም ውስን ከመሆኑ አንፃርም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተለይ የግሉ ዘርፍ በኮቪድ-19 ምላሽ አሰጣጥ ላይ ወሳኝ በመሆኑ ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ በርካታ የግል ጤና ተቋማት በኮቪድ ህክምና፣ ላብራቶሪ ምርመራና በሌሎች ስራዎች ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ ተደርጓል። የዚህ ማዕከል ስራ መጀመርም ከዚሁ ጋር የሚያያዝና በተለይ የግሉ ዘርፍ የኮቪድ-19ን ከመከላከል አንፃር ያለውን ሚና የሚያጎለብት ነው።
በዋናነት ደግሞ ማእከሉ በኮቪድ-19 ተይዘው መለስተኛ ምልክት ያሳዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተንቀሳቃሽ ባለሞያዎችና በቴክሎጂ በታገዘ መልኩ የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ ያስችላል። ይህም ለጤናው ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚሆንና በመንግስት በኩል ያለውን የህክምና አገልግሎት ጫና የሚቀንስ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በበኩላቸው በመንግስት አቅም እየተሰጠ ያለው የህክምና አገልግሎት እንዳለ ሆኖ እንደ ‹‹ሊያና›› ዓይነት ለከተማዋም ሆነ ለሀገር ትልቅ አቅም የሚሆኑ የግል የኮቪድ ህክምና ማእከላት ስራ ሲጀምሩ ሊበረታቱና ሊደገፉ ይገባል። የኮቪድ ወረርሽኝ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣበት ወቅት በመሆኑ እንደዚህ አይነት የግል የኮቪድ ህክምና ማእከላት መምጣት በተለይ በመንግስት ጤና ተቋማት የሚታየውን የፅኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ጫናን ከማገዝና የአጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረትን ከመቅረፍ አንጻር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።
የኮቪድ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ የሚቆም ባለመሆኑና ለተወሰኑ ጊዚያቶች አብሮ የሚቆይ እንደመሆኑ የዚህ ህክምና ማእከል ወደ ስራ መግባት ለመንግስት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርና ሌሎችም በዚህ ዘርፍ ገብተው እንዲሰሩ ይገፋፋል። በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ አቅም ላላቸውና ከፍለው መታከም ለሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ኮቪድ ካለፈም በኋላ ማእከሉ ሌላ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት እድልም ይኖራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም