ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ ያላት እና ነፃነቷንም ለማንም አሳልፋ ሳትሰጥ የኖረች አገር ስለመሆኗ በተደጋጋሚ የሚነገር እውነታ ነው። ለዚህም እስካሁን ድረስ አሻራቸው በጉልህ የሚታዩ የቀደምት ስልጣኔ ምልክቶች ህያው ምስክሮች ናቸው። ከአንድ ሚሊኒየም የዘለለው የአክሱም የስልጣኔ አሻራ ዛሬም ድረስ ያልተደረሰባቸው ረቂቅ የስልጣኔ ምልክቶች ያሉት ሲሆን ከዚያ በኋላም በርካታ የታሪክ ምስክሮች እንዳሉ አይዘነጋም።
ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በቅኝ ግዛት የሰከሩ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት አፍሪካን ለመቀራመት ወረራ በፈፀሙበት የቅኝ ግዛት ዘመን ይህንን የወረራ ታሪክ በመቀልበስ ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት አርአያ መሆን መቻሏ የዓለም ህዝብ የሚመሰከረው ሃቅ ነው። በአድዋው ጦርነት እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የወራሪ ኃይል ረጅም ቀናት በእግራቸው በመጓዝ ፊት ለፊት የገጠሙት የቀደሙት ጀግኖቻችን ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ለነፃነታቸው ቀናኢ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው።
በዘመኑ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከት በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የእርስ በርስ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወሳል። በተለይ በዘመኑ የፖለቲካ አካሄድ መሰረት አፄ ምኒልክ ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አንድ ለማድረግ በሚያደርጉት ትግል ከአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ እምቢተኝነት የነበረ ቢሆንም ከግብርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞም የራሳቸው ቅሬታ የነበራቸው አንዳንድ የውስጥ ኃይሎች ነበሩ።
ነገር ግን የውጭ ወራሪ ኃይል በመጣበት ወቅት ስለሀገራቸው ለመፋለም ለቀረበው የመንግስት ጥሪ አንድም ያወላወለ አልነበረም። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ሁሉም በጋራ ሀገራቸውን ከጠላት ለመመከት ለቀረበው ጥያቄ ጊዜ ሳይሰጡ በአንድ ልብ የተነሱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ጉዳይ ከማንም ጋር መደራደርን አያውቁም። ሀገርን አሳልፎ መስጠት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ነውር ብቻ ሳይሆን ተገቢ ያልሆነና ከማህበራዊ ህይወትም የሚያስወጣ ተግባር ነው። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ድህነትና ኋላቀርነት የተንሰራፋበት ቢሆንም ያለፈውን ገናና ታሪክ ለመፋቅ የሚሞክሩ የውጭ ኃይሎች በርካታ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተነስተው በአጭር ጊዜ ወደስልጣኔ ማማ የደረሱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ የቀደመውን ገናና ታሪኳን ዳግም እንዳታድስና ወደከፍታ እንዳትወጣ በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ሲያሳድሩ ይስተዋላል። ከዚህም አልፎ የቀደመውን የስልጣኔ አሻራ ለመፋቅ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያውያን ከሚሰሯቸው መልካም ሥራዎች በርካታ ጠንካራ ጎኖች ይልቅ በችግሮችና በደካማ ጎኖች ላይ ብቻ የሚያነጣጥሩት የነዚህ ኃይሎች ተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማሳያ ነው።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን ለመፋለም ካደረገችው ሥራ ይልቅ በድርቅ ምክንያት የደረሱ ችግሮች ቀልባቸውን ይስባል። ከጠንካራ እሴቶቻችንና መልካም ባህሎቻችን ይልቅ ጥቂት ደካማ ጎኖችን መዝዞ የማጉላት ሥራ በሚዲዎቻቸው አማካኝነት ሲያራግቡ ይውላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ እንቅስቃሴና የብልጽግና ጎዳና ለማደናቀፍ አንዳንድ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ጀምረዋል።
በተለይ በቅርቡ ኢትዮጵያ በትግራይ ያደረገችውን የህግ ማስከበር ዘመቻ መነሻ በማድረግ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች የሞተውን ህወሓት ከመቃብር አስነስቶ ነፍስ ለመዝራትና ዳግም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። አንዴ መንግሥት የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀመ ነው፤ ሌላ ጊዜ በትግራይ ከፍተኛ ረሃብ እየተከሰተ ነው። ሌላ ጊዜም ተደራደሩ በሚሉ ተለዋዋጭ ሃሳቦችን በማንሳት የመንግሥትን እጅ ለመጠምዘዝና በኢትዮጵያ ጉዳይ ገብተው ለመፈትፈት ከፍተኛ ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህንን ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ አንዳንድ የህወሓት ወዳጆችና የነሱ ጉዳይ አስፈፃሚዎች ተቀብለው ለዓለም ማህበረሰብ በተሳሳተ መንገድ ለማቅረብና ዓለምን ለማሳሳት ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አገርን የማተራመስ አጀንዳ ነው። ይህንን ሴራ ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን አምርረው እየተቃወሙት ይገኛሉ። በትላንትናው እለትም ‹‹ብሔራዊ ክብር በህብር›› በሚል መሪ ሃሳብ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሀገር አቀፍ ዘመቻ ተካሂዷል። በዚህ ዘመቻም የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቃወም የኢትዮጵያውያንን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ማስተላለፍ ተችሏል።
ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚጥሩ እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማዳከምና ወደእርስ በእርስ ግጭት ለማስገባት ብሎም አገርን ለማፍረስ በሚሰሩ ሃይሎች ጫና የሚደረግ ሴራ ሁሉ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያወግዝ ይገባል። ኢትዮጵያ ትላንትም ሉዓላዊ ሀገር ነበረች፤ ነገም ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ትቀጥላለች። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሩን ክብር ለማስቀጠል ዘብ ይቆማል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013