ኢትዮጵያን ከብዙ አገራት በተለየ በተፈጥሮ የታደለች ሃገር ከሚያስብሏት የተፈጥሮ ገፀበረከቶች ውስጥ አንዱ ምቹ የአየር ፀባይ ነው፡፡ 13 ወራት የተመጣጠነ ፀሃይና በቂ ዝናብ በማግኘት በዓለም ዘንድ ከሚታወቁ ሃገራት ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡ ይህ ደግሞ ለአረንጓዴ ልማት ምቹ ያደርጋታል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ ነው፡፡ ከ80 ከመቶ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ አርሶ እና አርብቶ አደር መሆኑ ደግሞ ምቹ የአየር ፀባይ የመኖርን አስፈላጊነት የግድ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአረንጓዴ አሻራ ውጤት የሆነው ዛፍ ለሃገራችን ማህበረሰብ የህይወቱ አንድ አካል ነው፡፡
በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ ለሚካሄደው የሃገራችን የግብርና ስራ ደን የሚጫወተው ሚና ተኪ የሌለው ነው፡፡ ሞፈር እና ቀንበር ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ለዘመናት የባህላዊ አኗኗራችን አንድ አካል ሆኖ የኖረው የእርቅ እና ሌሎች የሽምግልና ስርዓቶች የሚከናወኑት በአብዛኛው በዛፎች ጥላ ስር ነው፡፡
ከዚህም አልፎ ከቤት ቁሳቁስ ጀምሮ እስከቤት ውስጥ መገልገያ መሳሪያዎቻችን ድረስም ዛፍ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው፡፡ በገጠሪቱ የሃገራችን ክፍሎችም ሆነ በትናንሽና መካከለኛ ከተሞች አብዛኞቹ መኖርያ ቤቶች የሚገነቡት ከእንጨት ነው፡፡ እነዚህና መሰል የኢኮኖሚ መሰረቶች ሁሉ የዛፎችን አስፈላጊነት መሰረታዊ ያደርጉታል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በመጠቀምና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከማዋል አንጻር በአግባቡ ባለመሰራቱ የባከነ ሃብት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ከዚህም አልፎ በተለይ ካለፉት አምስት አስርት አመታት ወዲህ ያለንን አረንጓዴ ልማት ከማሳደግ ይልቅ ወደማጥፋቱ በመሄዳችን እና የበለፀጉ ሃገራት የሚለቁትን የተበከለ ጋዝ ጨምሮ ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ሄዷል፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ እስከመመታት የደረሰችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተአመት በፊት የነበራት የደን ሽፋን ከ35 ከመቶ የዘለለ ሲሆን ካለፉት አምሳ አመታት ወዲህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረጉ የደን ውድመቶች ይህ ሃብት በአጭር ጊዜ ወደ ሶስት ከመቶ ድረስ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ደግሞ በሃገራችን በተደጋጋሚ ለተከሰቱ የድርቅ ወቅቶችና የጎርፍ አደጋዎች አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይገለፃል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን የአረንጓዴ ልማት ስራ ለማሻሻልና ከራሳችንም አልፎ በጎረቤት ሃገራት ተሞክሮውን ለማስፋት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ በጀመረቻቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ውስጥ አረንጓዴ አሻራን አንዱ የልማቷ አካል በማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ስራዎች አከናውናለች፡፡
በዚህም መሰረት በ2011 ዓ/ም የክረምት ወቅት ኢትዮጵያ በአንድ ክረምት ብቻ አራት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከልና አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ ባለፈው አመትም 23 ሚሊየን ዜጎችን በማሳተፍ አምስት ቢሊየን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ ከተጀመረ ባለፉት ሁለት ዓመታትም መላውን ህዝብ በማነቃነቅ ከዘጠኝ ቢሊየን ችግኞች በላይ መተከላቸውንና የፅድቀት መጠናቸውም 88 ከመቶ መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በመጪው ክረምትም 7 ነጥብ 7 ቢለየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ ችግኝ የማዘጋጀት ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥም 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞች ለሃገር ውስጥ፣ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ደግሞ ለጎረቤት ሃገራት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ለጎረቤት አገራት የሚሰጡ ችግኞች ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ኬንያ የሚገኙ ተፋሰሶችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡
መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለፀው ኢትዮጵያ የምትከተለው የብልፅግና ጉዞ ብቻዋን ሮጣ ብቻዋን የማሸነፍ ሳይሆን አብሮ የማደግ ስትራቴጂን የተከተለ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ጎረቤት ሃገራትን ታሳቢ ያደረገው የልማት እንቅስቃሴ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ታላቁ የህዳሴ ግድብን እውን ስታደርግም አብሮ የመልማት ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
አሁን በምንገኝበት ዘመን ዓለምን እየተፈታተኑ ከሚገኙ የተፈጥሮ መዛባቶች ውስጥ አንዱ የአየር ፀባይ ለውጥ ነው፡፡ የዚህ ዋነኛው ችግር ደግሞ በአንድ በኩል ከሰለጠኑ ሃገራት የሚወጣ ጋዝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የደን ውድመት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን አረንጓዴ አሻራ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከራስም አልፎ ጎረቤት ሃገራትና ዓለምንም ጭምር ከተፈጥሮ አደጋ የማዳን አካል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠሉ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ሂደቱ አካል በመሆን የራሱን አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013