ሉአላዊነት የአንድ ሀገር ነፃነት ነው። አንድ ሀገር በሌላው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል ዓለም አቀፍ መርህም ነው። ይህ መርህ ዓለም አቀፍ ከመሆኑ አንጻር የትኛውም ሀገር ለዚህ መርህ ይገዛል፤ ለተፈጻሚነቱም የመንቀሳቀስ ግዴታ ይኖርበታል።
ትንሹም ፣ትልቁም ፤ ሀብታሙም ፣ ድሀውም ሁሉም ሀገር ለዚህ ዓለም አቀፍ መርህ የመገዛት የህግና የሞራል ኃላፊነት ፤ ከዛም በላይ ግዴታ አለበት። እንደ ሀገር የመቆሙና የመጽናት ህልውና መሰረት ያደረገው በዚሁ መርህ ላይ ነው። ለዚህም ነው ህዝቦች ለሉአላዊነት ከፍ ያለ መስዋዕትነት እየከፈሉ የመጡትና ሁሌም ለመክፈል ዝግጁ የሚሆኑት ።
ይህ ዓለም አቀፍ መርህ በታሪክ ሂደት ውስጥ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እንዳለፈ የዓለም ታሪክ በስፋት የሚተርከው እውነታ ነው። በተለይም የዓለም ፖሊስ አድርገው ራሳቸውን የሚያዩት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት መሪዎች ከሚታይ ምክንያት ጀምሮ በፈጠራ ትርክቶች የሀገራትን ሉአላዊነት ሲጋፉ ማየት የዕለት ተዕለት የሚዲያ ትርክት ከሆነ ቆይቷል።
በአንድ በኩል የዓለምን የመረጃ ፍሰት በሞኖፖል የያዙት የነዚሁ ሀገራት የመገናኛ ብዙሃኖች የሀገራትን ሉአላዊነት ለሚገዳደሩት የሀገራቱ መሪዎች የሴራ ተግባራት መንገድ ጠራጊ በመሆን ከስነ ምግባር ውጪ የሆኑ ዘገባዎችን በማሰራጨት ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ በተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳተ እይታ እንዲኖረው በማ ድረግ ሥራ ተጠምደዋል።
በእነዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የተሳሳቱ ትርክቶች ጭንብል ሉአላዊነታቸው አደጋ ውስጥ የወደቀ ፤ በዚህም የሀገራቱ ህዝቦች ለከፋ እልቂትና ስደት የተዳረጉበት እውነታ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አዲስ አይደለም።
ከምዕራቡ ዓለም ያፈነገጠን አንድ መሪ ከስልጣን ለማውረድ የተገመደው ሴራ የሀገሪቱን ህዝቦች የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህቺው አገር ተመልሳ ሀገር እንዳትሆን ሀገርና ህዝብ ጉዳያቸው ያልሆኑ ቡድኖች የእልህ መፈንጫ ሆናለች ።
የነዚህ ሀገራት ህዝቦች የከፈሉት እና አሁንም እየከፈሉት ያለው ዋጋ የህዝቦቹ የእጅ ሥራ ውጤት ሳይሆን ፣ አለሙ የተገዛበት ልክ ያጣ የተጠቃሚነት መሻትና ከዚህ የመነጨው ሴራ ውጤት እንደሆነ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
ይህ ከዓለም አቀፍ መርሆዎች በላይ ገኖ የሚታየው የሀገራት የተጠቃሚነት ልክ ያጣ መሻትና ይህንን ለማሳካት እየተሄደበት ያለው የሴራ መንገድ ሰብዓዊ እሴቶችን የቱን ያህል እየሸረሸረና ዓለም አቀፍ አደጋ እየሆነ ስለመምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ችግሩን ከሁሉም በላይ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ የሴራ ትብታቦች ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ — ወዘተ የሚባሉ ትላልቅ ሰብዓዊ እሴቶችን ታከውና ጥላ አድርገው የመተግበራቸው ጉዳይ ነው። እነዚህ ሰብአዊ እሴቶች በየወቅቱ የተለያዩ ትርጓሜዎች እየተሰጣቸው በተለይ ለሶስተኛው ዓለም ሀገራት ህዝቦች አዲስ የቅኝ አገዛዝ መሳሪያ መሆናቸው እየታየ ነው።
በተለይም ራሳቸውን ብዙ ዋጋ ከፍለው ያገኙና የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን የሚጥሩ ህዝቦችን መነሳሳት ለመቅበር ፣ ህዝቦቹ ከጀመሩት ታሪካዊ የመነሳሳት ጎዞ ለማስቀረት እነዚህን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ አሴቶች እየጠቀሱ በተናበበ መልኩ የሚያደርጉት የመድፈቅ ተግባር ማብቂያ ሊኖረው ይገባል ።
እስካሁን ባለው የዓለማችን ታሪክ ራሳቸውን የዓለም ፖሊስ አድርገው በሚያዩ የምእራቡ ዓለም መሪዎች በጎ ፈቃድና ይሁንታ ከአሮጌው ታሪካቸው ወጥተው የራሳቸውን እጣ ፈንታ መወሰን የቻሉ ህዝቦች የሉም። ያሉ የሚመስሉትም ቢሆኑ እውነታው ከመምሰል ያለፈ አይደለም ።
ዛሬ በኛም ሀገር እየሆነ ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሕዝባችን የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ ለመወሰኝ በሚያስችለው ታሪካዊ ምእራፍ ውስጥ ይገኛል ። እዚህ ታሪካዊ ምእራፍ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍሏል ። ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ እንደቀደሙት ዘመናት ባክኖ እንዳይቀር በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።
እንደቀደሙት ዘመናት ቀኝ እና ግራ ፤ ምዕራብ እና ምስራቅ ሳይል ማህበረሰባዊ እሴቶቹን መሰረት ባደረገ መልኩ በአዲስ የለውጥ መንገድ ላይ ይገኛል። ይህንን የለውጥ መንገድ ለመቀልበስ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በግልጽም ይሁን በስውር የሚካሄዱ የሴራ ተግባራት መልካቸውን እየቀያየሩ የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ተስፋ እየተፈታተኑ ይገኛሉ።
በተለይም አንዳንድ የምዕራቡ ሀገራት መሪዎችና የሀገራቱ የመገናኛ ብዙኃን በሰብአዊ እና በዴሞክራሲያዊ መብቶች ስም እየሄዱበት ያለው የተዛባና የተሳሳተ መንገድ ፤ ለፍትህና ለእውነተኛ የህሊና ዳኝነት ጆሯቸውን የዘጉበት እውነታ በቀደመው ዘመን በነዛ ክፉ ቀናት እንደ ሀገር በሊግ ኦፍ ኔሽን ያጋጠመንን እውነታ እንድናስታውስ ያደርገናል።
እነዚህ ሀገራት ባለፉት 27 ዓመታት ትህነግ በሀገሪቱ ስላካሄደው ከፍ ያለ የሰብአዊም ሆነ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት የዛሬውን ያህል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያላሰሙት ለምንድን ነው? በሀገሪቱ የነበረውን እውነታ ስላልሰሙና ስላላዩ ነውን? አሁን በትህነግ መቃብር ላይ ቆመው ስለትህነግ ትንሳኤ መጮህስ ለምን አስፈለጋቸው?
የትህነግ አገዛዝ በብዙ ወስዋዕትነት እንዳይመለስ ሆኖ በተሰናበተበት ሀገራዊ ምህዳር ውስጥ ሀገሪቱንና ቀጠናውን ሲያሸብር ለቆየው ቡድን ለሞቱ ትንሳኤ ለመስጠት እያደረጉት ያለው ጥረት የሀገራቱ የፖለቲካ አሴቶች የቱን ያህል ሰው ሰው መሽተት እንዳቃታቸው በተጨባጭ የሚያሳይነው ።
በተለይም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት እየሆነ ያለው እውነታ የአደባባይ ሚስጥር በሆኑበት ሁኔታ የውሸት መረጃዎችን እየፈጠሩና ትክክለኛ መረጃዎችን እያጣመሙ በሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙሀን ዘገባዎችና በተከፋይ ሎቢስቶች በሚቀነቀኑ የበላተኞች ጩኸት ላይ መሰረት አድርጎ የሚሄድበት መንገድ በሀገራቱ ግንኙነት ውስጥ ተጨማሪ ታሪካዊ ስህተት ሊፈጥር የሚችል ነው። ይህ አካሄድ በሀገራቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ዘመናት የተሻገረ ግንኙነት አደጋ ውስጥ ሊከተውም ይችላል። በአጠቃላይ ሞቶ ለተቀበረ ስርአት ትንሳኤ ከማፈላለግ ይልቅ ሕያው የሆነውን የሀገሪቱን ህዝቦች ተስፋ በመደገፍ የመነሳታቸው ታሪክ አካል መሆን ከተጠቃሚነት ስሌት በላይ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም