የአንድ ሀገር ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወድቀው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲካሄድ ነው። ከዚህም የተነሳ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ በሚፈልጉትና ተስፋ ባደረጉበት መንገድ ለህዝብ ያቀርባሉ፤ ደጋፊም ለማፍራት ይንቀሳቀሳሉ። በሰላማዊ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ የሚዋጣላቸው እንዳሉ ሁሉ ውጤቱን ባለመቀበል ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱም አይጠፉም።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል። ነገር ግን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ያለመሆናቸውን ጉዳይ ለቀባሪ ማርዳት ነው። ዘንድሮ የሚካሄደውን 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ልዩ የሚያደርገው ወደፊት ለምናደርጋቸው ምርጫዎች የተለየና ፈር ቀዳጅ መሆኑ ነው። ይህ ምርጫ የሀገሪቱን የወደፊት መሰረት የሚጥል፥ ህዝባዊ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል እንዲሁም ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚያሻግር እንዲሚሆን የታመነበት ነው። ምርጫው እንከን የለሽ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡበት የሚገባ አሻጋሪ ምርጫ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።
እንደ አገር እንከን የለሽ መሆን ያለበትና ውዝግብ የማያመጣ ፍፁምነትን የተላበሰ ምርጫ ማካሄድ እንዳለብን ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በዳበረ ዴሞክራሲ መንፈስ ውስጥ ሆነው ህዝቦቻቸውን በተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ስር መምራት የቻሉ ሀገራት እና መንግሥታት ሕዝባቸውን ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላ የከፍታ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር ችለዋል። ቀጣይነት ባለው የዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ በማለፍ ቀጣይነት ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ማስመዝገብም ችለዋል። ከዚህም በላይ የተረጋጋ ሀገርና ማህበረሰብም መፍጠር ችለዋል።
ከዚህ በተጻረረ መልኩ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ የህዝብን ስልጣን ለመንጠቅ የሚጥሩ ሀገራትና የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ የከፉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ሲገቡ እያየን ነው። እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ያዙም አልያዙም የምንጊዜም ዓላማቸው ያልተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር ነው። በዚህ ባልተረጋጋ አዙሪት በመሽከርከር የስልጣን ጥማቸውን ማርካት ላይ አተኩረው ይሠራሉ፤ ይህ በአንዳንድ ዴሞክራሲን ባልገነቡ ሀገራት የሚታይና የሚስተዋል ጉዳይ ነው።
በእኛም ሀገር ከተካሄዱት ምርጫዎች የምንገነዘበው እውነታ ከዚህ የተለየ ነው ለማለት የሚከብድ አይደለም። የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለማጨንገፍ ስልጣንን በአቋራጭ መንገድ ለመውሰድ የሚያደርጉት ያልተገባ ጥረት አደጋው በግልጽ እየታየ ነው። ይህ እውነታ ከወዲሁ መታረም ካልቻለ እንደሀገር ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችልም የታመነ ነው።
በቀደመው ታሪካችን ጀግኖች አባቶቻችን ጠላትን ለመከላከል በአንድነትና በህብረት ከአደባባይ እስከ በረሃዎች ድረስ የሕይወት ዋጋ የከፈሉ ስለመሆናቸው የሚታወቅ ነው። ለሕዝቦች መብት በመታገልና ለዛሬው ትውልድ የተከበረች ሃገር አውርሰውን ያለፉበት ደማቅ ታሪክ አስቀምጠዋል። የዚህ ትውልድም የቤት ሥራ የሚሆነው ለቀጣዩ ትውልድ ዴሞክራሲን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ቀርጾ ማለፍ ይሆናል። ይህም የሚሆነው የዛሬው ትውልድ የራሱ ነገዎች እንዳሉት ከማሰብ ባለፈ ለነገው ትውልድ ተስፋ የሚሰንቅ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ሲችል ነው። ለዚህም ዓላማ መሳካት ሁሉም የምርጫው ተሳታፊ ወገኖች ለህግ ተገዢ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ሁሉም ሰው ከህግ በታች እስከሆነ ድረስ ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቪስት፤ መራጭም ሆነ አስመራጭ፣ ተወዳዳሪም ሆነ ታዛቢ ሁሉም ከህግ በታች ነው።
ከሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የታመኑና ትልቅ ሰብዕና ያላቸው ግለሰቦች የምርጫ ቦርድን እንዲመሩ ተደርጓል። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለሙ የምርጫ ህጎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡም ተደርጓል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተለያዩ መድረኮች፣ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ ጣቢያዎችና በጋዜጦች የምርጫ ማኒፌስቷቸውን በነፃነት እያቀረቡ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ ሁነቶች ምርጫው በፍትሐዊነትና በተአማኒነት እንዲከናወን የሚያስችሉ ፈር ቀዳጅ የሆኑ መሰረታዊ ነጥቦች መሆናቸው የሚያጠራጥር አይደለም።
በአጠቃላይ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ምርጫውን ከሚታዘቡ ሲቪክ ማህበራት፣ ከመራጮችና ምርጫ አስፈፃሚዎች በላቀ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ረገድ የመንግሥት ከልብ የመነጨ በጎ ፍቃደኝነት እጅጉን አስፈላጊና ወሳኝ ነጥብ ነው። ስለሆነም የምርጫውን ወሳኝነት በመረዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለስኬቱ ማማር በሙሉ ተስፋ ሊሳተፉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013