በአለርት ሆሰፒታል የውስጥ ደዌ እስፔሻሊሰት የሆኑት ዶከተር ሀይሌ ጫኔን ያገኘናቸው በሆስፒታሉ የኮቪድ 19 ክትባት በሚሰጥበት ማዕከል ውስጥ ነው። የኮቪድ 19 ክትባት ምንነት፤ ጥቅሙ፤ ጉዳቱ፣ ማን መውሰድ አለበት? ማንስ ክትባቱን መከተብ አይችልም የሚሉ ሐሳቦችን በእርጋታ ለተከታቢው ካብራሩ በኋላ ከእያንዳንዱ ሰው የሚነሳውን ጥያቄ ያለመሰልቸት ይመልሳሉ። ክትባቱ ለማህበረሰቡ ከመሰጠቱ በፊትና ከተሰጠም በኋላ መደረግ ስለሚኖርባቸው ጥንቃቄዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አነጋግረናቸው የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!!
እንደሚታወቀው የእንግሊዝ ምርት የሆነው ‹‹አስትራዜኒካ››ና የቻይና ምርት የሆነው ‹‹ሲኖፋርም›› ክትባቶች ጥናቱን ባያጠናቅቁም ለህብረተሰቡ መሰጠት ይችላሉ በሚል ፍቃድ ሀገራችን ገብቷል። ‹‹አስትራዜኒካ›› የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ እድሜያቸው ከ60 በላይና ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እንዲወስዱት ተደርጓል።
አሁን ደግሞ ‹‹ሲኖፋርም›› በይበልጥ በሥራ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ ከ18 እስከ 60 ዓመት ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የሚሰጥ ክትባት ነው። የሲኖፋርም ክትባት የተሰራው ከሞተ ቫይረስ ሲሆን፤ የሰውነትን የመከላከል አቅም ያሳድጋል፤ ከተከተብን በሽታው ቢይዘንም እንኳን ከከፋ ደረጃ ሣያደርስ እንደ ጉንፋን በቀላሉ ማገገም እንድንችል፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ደረጃ እንዳንደርስ ያስችላል።
ክትባቱ የበሽታውን ሥርጭት ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ነው። ሥርጭቱን በተገቢው መንገድ ለማስቆም
ክትባት የወሰድን ቢሆኑም እንኳን፤ የፊት ጭንብል ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን ቶሎ ማፅዳት እና ህመም ሲሰማ ቤት መቆየት አስፈላጊ ነው።
ክትባት ከተወሰደ በኋላ፣ የተወሰነ የሚታዩ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ልክ ህፃናት የተለያዩ በሽታ ክትባቶችን ሲከተቡ ትኩሳት ህመም የመሳሰሉት የሚገጥማቸውን ያህል ክትባቱን የወሰዱ ሰዎችም የተለያየ ዓይነት ቀላል ህመሞችን ያስተናግዳሉ። ይህ ማለት ግን ይታመማሉ ማለት ሳይሆን ክትባቱ መስራት ሲጀምር የሚከሰት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የተወጉበት ቦታ ህመም፣ ትኩሣት፣ ብርድ፣ የሰውነት ቁርጥማት፣ ራስ ምታት፤ ጉሮሮን የመከርከር ስሜት እና ድካም ሊስተዋል ይችላል።
የሲኖፋርም የክትባት ዓይነት ሁለት ጊዜ የሚወሰድ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ክትባት ለመውሰድ የመጀመሪያው ክትባት ከተወሰደ ከሃያ አንደኛው እስከ ሃያ ስምንተኛው ቀን ውስጥ ሊወሰድ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው ቫይረሱ አዲስ እንደመሆኑ በርከታ ጥናቶች እየተደረጉ በሂደት ባህሪውን የሚለውጥ ቢሆንም አሁን ላይ ቫይረሱ ኖሮባቸው የዳኑ ሰዎች ድጋሚ በሽታው ሊይዛቸው ስለሚችል ክትባቱን ማግኘት አለባቸው።
እድሜያቸው ከአስራ 18 ዓመት በታች የሆኑና ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው ክትባቱን እንዲወስዱ አይመከርም፡፡ ምክንያቱም ክትባቱን ለመስራት በተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ያልተካተቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እርግዝና ላይ ያሉ እናቶች ወይም የሚያጠቡ ሴቶች ለልጆቹ ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ምን እንደሚያመጣ ባለመታወቁ ክትባቱ አይሰጣቸውም።
የሚያጠቡ እናቶች በተለይም ተጋላጭ የሆኑ ከሆኑ ጡት ማጥባት አቁመው ክትባቱን መውሰድ አለባቸው። አዲስ የኮሮና ቫይረስ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ክትባቱን መውሰድ የለባቸውም። ምክንያቱም ቫይረሱ እያለባቸው ክትባቱን ሲወስዱ በሽታውን ሊያባብስባቸው ስለሚችል ነው።
ክትባቱ ወረርሽኙን ለማጥፋት ዘላቂ መፍትሄ ሲሆን፤ የኮሮና ክትባትም ለዚህ ወረርሽኝ መጥፋት ዋና መሳሪያ ነው። ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ይኼንን ለመቀበል ከብዶታል። አሁን ብዙ ሰው እየወሰደ እንኳን ቢሆንም ጥርጣሬው ያለቀቃቸው ሰዎች አሉ። ለዚህም ምክንያት ተብሎ የሚታሰበው ክትባቱ በፍጥነት በመሰራጨቱ፤ ምርምሮች አለመጠናቀቃቸው እና ማህበረሰቡ ላይ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አለመሰራቱ ነው።
እንደማህበረሰብ አዲሰ ነገር ለመቀበል መዘግየት እንዳለ ሆኖ ህብረተሰቡ ውስጥ የተስፋፋው የሰው ወሬ ጥረጣሬውን አብዝቶታል። ከሁሉ የሚገርመው ክትባቱ መሃን ያደርጋል የሚለው ወሬ ነው። መሀንነትን ለማወቅ በምርመራው ሁለት ዓመታትን የሚፈጅ ሲሆን፤ ኮቪድ 19 ክትባት ከመጣ ስድስት ወር እንኳን ሳይሆነው መሀን ያደርገል ብሎ ማስወራት ተገቢ አይደለም።
ክትባቱ ጅን ላይ፤ ሆርሞን ላይ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት የማያመጣ በመሆኑ የተነሳ “ይህ መሀን ያደርጋል፤ ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ያመጣል” ተብሎ በማህበረሰቡ ውስጥ የተነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው።
ሀገራችን አቅም ኖራት ለሁሉም ህብረተሰብ ክትባቱን ማዳረስ ቢቻልና ሰው በነፃነት ቢኖር እጅግ መልካም ነበር። ይህ ግን ሊሆን አይችልም። አሁን የገቡት ክትባቶች በሌሎች እርዳታ በርካታ ገንዘብ ወጥቶበት ባልተገባ አሉባልታ የተወሰነ ሰው ብቻ ተከትቦ የተቀረው ወደ ኋላ ሲል መመልከት እጅግ በጣም የሚገርም ነው።
አሁን ላይ ከሁሉ በፊት ራስን በመጠበቀ ከበሽታው ነፃ ለመሆን መጣር ነው። ክትባቱንም ለመውሰድ እድሉን ያገኘ ሰውም እድሉን ሲያገኝ ማሳለፍ የለበትም። በዚህ ወቅት ስንት ልጆች ያለ ወላጆች ቀርተዋል። ስንት ትላልቅ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎችን አጥተናል። እስከ ዛሬ ድረስ የተከፈለው ዋጋ ይበቃል፤ ሰው በራሱ በእጁ ሊከላከለው የሚገባውን ነገር በመከወን ጤና ማግኘት ይኖርበታል።
ዶክተር ሀይሌ ይህንን ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ፤ የወገኖቻቸንን ህይወት በየቀኑ ከሚነጥቀው ወረርሽኝ የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም መዳን ይኖርብናል። በተቻለ መጠን ራስን በመጠበቅ ከሚደርስብን ድርብርብ ጉዳት እንዳን – የእለቱ መልክታችን ነው። በጤና ያሠንብተን።