ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ልታካሂድ ከሦስት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቷታል፡፡ ይህ ምርጫ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምርጫዎች ለየት ያለና እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የየበኩላቸውን ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ቦርዱ ከዚህ በፊት ሲታማበት ከነበረው የመንግሥት ወገንተኝነት ወጥቶ ሕግና ሕግን ብቻ መሠረት በማድረግ እንዲሰራ መንግሥት ገለልተኛ አመራሮችን መድቦ ወደሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮም በራሱ መንገድ ሕግን መሠረት አድርጎ ሲሰራ እንደነበርም ብዙዎች ምስክርነት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ቦርዱ ስድስተኛውን አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ባለፈው ዓመት ለማካሄድ ቢወስንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ጊዜውን ማራዘሙ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ አንዳንድ ፓርቲዎች የቦርዱን ውሳኔ ባይደግፉም ቦርዱ ግን በአቋሙ በመፅናት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ወሰነ፡፡ ከዚያ በኋላ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ማስቆም ባይቻልም እየተጠነቀቁ ምርጫ ማካሄድ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው በመታመኑ ምርጫው ግንቦት 28 እና ሰኔ 5/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኖ ተግባራዊ እቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት ቦርዱ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያካሂድ ቆይቶ ከመጋቢት 16/2013 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በተሰጠው ጊዜም በርካታ ዜጎች ተመዝግበው ካርድ ቢወስዱም በአንጻሩ በተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ችግሮች የተነሳ ካርድ ያልወሰዱ ሰዎች በርካታ በመሆናቸው ቦርዱ የምርጫውን ጊዜ በማራዘም እስከ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ከዚህም አልፎ ቀደም ሲል በፀጥታ ምክንያት የምዝገባ ጣቢያ ዘግይቶ በተከፈተባቸው አካባቢዎች የምዝገባ ጊዜው እንዲራዘም በማድረግ አሁንም ምዝገባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስም ከ31 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው የምርጫውን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
በርግጥ መምረጥ መብቴ ነው የሚል ቃል በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ ስለመብት ሲወራ ግን ከቃሉ በዘለለ ምን ያህል ስለመብት እናውቃለን የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ መብቱን ለማስከበር የሚፈልግ ዜጋ ደግሞ መሪዎቹን ሕጋዊ በሆነ መልኩ መምረጥ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫ ካርድ ወስደው የምርጫው ቀን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ዜጎች በመብታቸው ለመጠቀም የቆረጡና የመብትና ግዴታን ምንነት የተረዱ ናቸው፡፡
በአንጻሩ ግን ብዙውን ጊዜያቸውን ስለመብትና ግዴታ በማውራትና በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጊዜያቸውን በዚሁ ዙሪያ ሲሰብኩ የሚውሉ ጥቂት አካላትና በአገሪቷ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ተወዳድረው ማሸነፍ እንደማይችሉ የተረዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ይህንን ምርጫ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ዋነኛ አጀንዳቸው ምርጫ መካሄድ አለመካሄዱ ሳይሆን ሁሉንም ነገር መቃወም ነው፡፡
በዚህ መሠረት ከዚህ ቀደም መንግሥት በኮቪድ 19 ምክንያት ምርጫውን ሲያራዝም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እንደፈረሰ በማድረግ ለምን የሚል ጩኸት ሲያሰሙ እንዳልነበር በአንጻሩ አሁን ወደምርጫ መገባቱ ሲረጋገጥ ደግሞ ምርጫው መራዘም አለበት በሚል ሌላ ጩኸት ያሰማሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ምርጫው እንደማይቀር ሲረጋገጥ ደግሞ ጥቂቶቹ ራሳቸውን ከምርጫው በማግለል ፍላጎታቸው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተወዳድሮ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ አለመሆኑን በተጨባጭ አረጋግጠዋል፡፡
እነዚህ ኃይሎች ዋነኛ ጩኸታቸው በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንደሌለ በማስመሰልና በዚህ ሂደት መንግሥትን በማሳጣት ራሳቸው በአቋራጭ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ መንግሥትን በማስጨነቅና ሥልጣኑን በማሳጣት ገፍቶ መጣል ዋነኛ የመታገያ ስልታቸው አድርገው ይወስዳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ ሆነው ስፖንሰር የሚያደርጓቸው አንዳንድ የኢትዮጵያ ጠላቶች በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በእጅ አዙር እነዚህን ኃይሎች ይደግፋሉ፡፡ መሣሪያ እስከማቀበልና በገንዘብ እስከመደገፍ፤ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት አገርን ማተራመስ፤ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ከሌላው ጋር ማጋጨት፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር ማጋጨት ወዘተ የየዕለት ሙከራቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች አገርን የማፍረስ ዘመቻ አካሎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን በቀላሉ ማፍረስ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ተሞክሮ ከከሸፉ ሴራዎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ለበርካታ ጊዜዎች ተሞክረው የከሸፉትና ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት የተደረጉ ሙከራዎች በአስተዋይ ዜጎች የረጋ መንፈስና በመንግሥት ጠንካራ ሥራ ሊገታ ችሏል፡፡ ሆኖም የጥፋት ኃይሎቹ አገርን የማፍረስ ጥረታቸውን እስከዕለተ ሞታቸው ድረስ አያቆሙም፡፡ ይህ ድርጊት ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜም ሆነ ከምርጫው በኋላ አዲሱ ተመራጭ መንግሥት ተረጋግቶ ሥልጣን እስከሚይዝ ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በመሆኑም የነዚህ ኃይሎች አላማ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አገርን ማፍረስ ነውና እያንዳንዱ ዜጋ የጥፋት ኃይሎችን ነቅቶ በመጠበቅ አገሩን ከጥፋት ሊታደግ ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በወሰድነው ካርድ ተጠቅመን መሪዎቻችንን መምረጥ ዋነኛው መፍትሄ መሆን አለበት!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም