ኢትዮጵያ ካላት ረጅም ዘመን የስልጣኔ አሻራና ታሪክ አንጻር በሚገባት የዕድገት ደረጃ ላይ ሳትደርስ ኖራለች፡፡ በተፈጥሮ ያላትን ሰፊ የማደግ ዕድልም በአግባቡ ሳትጠቀም ሩቅ ዓላሚ፤ ቅርብ አዳሪ ሆና ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ የማሻር ረጅም ራዕይ ሰንቀው የተነሱ ጥቂት መሪዎቿና ተራማጅ ዜጎቿም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተጠልፈው ቀርተዋል፡፡ እነሆ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን እነዚህን የመከኑ እድሎች ከወደቁበት በማንሳት የኢትዮጵያን ዳግም ትንሳኤ እውን ለማድረግ ዘርፈብዙ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡
ነገር ግን ይህንን የብልፅግና ጎዳና ለማደናቀፍና ከዚያም አልፎ ህዝቦቿን በመከፋፈል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጠላቶቿ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሩጫ ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመረጡት መንገድ ፊት ለፊት መግጠም ሳይሆን እርስ በርስ ማጋጨትን ነው፡፡ በዚህ መሰረት ለበርካታ ዘመናት አብረው የኖሩትን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መለያየትና ከዚያም አልፎ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት ማድረግ፤ ከዚያም ከፍ ሲል ርስ በርሱ ማጋጨት አንዱ የማፍረሻ ስልት አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሰረት ባለፉት ሶስት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት እንዲገደሉ፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ፤ ቤት ንብረታቸው እንዲቃጠል ተደርጓል፡፡
በተለይ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አጋጣሚዎች ለዘመናት ተዋልዶና በጉርብትና አብሮ የኖሩትን የአማራና የኦሮሞ ብሄረሰቦች በማጋጨት ዜጎች እርስ በርሳቸው እንዲጠፋፉና ወደማያባራ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ ያልተሞከረ ሙከራ አልነበረም፡፡ መሰረታቸውን ውጭ አገር ባደረጉ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት አንዱ ብሄር በሌላው ላይ ጦር መዞ እንዲነሳ ለማድረግም በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡
ከዚህም አልፎ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሰላም እንዳይሰማቸው ለማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎች በማንነታቸው ብቻ እንዲገደሉ በማድረግ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንዲጠፋና እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን እንዲከላከል በሚል ሽፋን ወደለየለት የእርስ በርስ ግጭት እንዲገባ ለማድረግ በርካታ የጥፋት ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ይህ እንዲሳካም በህገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በገፍ እንዲገባና እንዲሰራጭ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንዱ ሃይማኖት በሌላው ላይ እንዲነሳና እንዲተላለቅ ያልተሞከረ ሰይጣናዊ ሴራ አልነበረም፡፡ በዚህ የተነሳ በአንድ በኩል የሃይማኖት ተቋማትን በማቃጠልና የሃይማኖት አባቶችንም በመግደል ዜጎች ከእምነታቸው ውጭ ያለውን ሰው እንዲጠራጠሩና አልፎም ወደግጭት እንዲገቡ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ለዚህም በጅማ፣ በሃረር፣ በሞጣና በሌሎች ስፍራዎች የተደረጉ የሃይማኖት ተቋማት ጥቃቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ የግጭት አጀንዳዎች ታዲያ ላለፉት ሶስት ዓመታት ያለመታከት በተለያዩ ስልቶች ሲከናወኑ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በነዚህ የለውጥ አመታት በትግራይ እስከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ድረስ ብቻ 113 ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡ የእነዚህ ግጭቶች ዓላማ ደግሞ የብሄር ወይም የሃይማኖት ግጭት በማስነሳትና በአገሪቱ ውስጥ የማያባራ ጦርነት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡
እነዚህ ግጭቶች ታዲያ ከዋነኛው የአገር ውስጥ አፍራሽ ቡድን ህወሃት መመታት በኋላ በአንጻሩ የቀነሱ ቢሆንም የዚህ ቡድን ተላላኪ የሆነው ሸኔና እዚህም እዚያም ተሰግስገው የቀሩት የኦነግ ጋሻጃግሬዎቹ ዓላማውን ለማስቀጠል በተቻለ መጠን የአልሞት ባይ ተጋዳይ ስልት ቀይሰው መንቀሳቀሳቸውን ቀጥለውበታል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እቅዶች ስኬታማ እየሆኑ መምጣታቸው የነሱን እውነተኛ ሞት የሚያፋጥንባቸው በመሆኑ ጥፋትን የሙጥኝ ብለው ሌት ተቀን የጥፋት እጃቸውን መዘርጋታቸውን ቀጥለውበታል፡፡
በቅርቡ በተቀናጀ መልኩ የተካሄደውና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገው የጦርነትና የጥፋት ጥንስሳቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ድግስ በተለይ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ መንገዷን አጠንክራ መቀጠሏ ያመጣባቸው ፍርሃት የወለደው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የውስጥ እግር እሳት የሆነባቸው ግብጽና አጋሮቿ ድጋፍ ያጀበው ትልቅ ሴራ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ለዘመናት እንዲህ አይነት ልዩነት አስተናግደው የማያውቁትን የእስልምናና የክርትስና እምነት ተከታዮች ለማጋጨት የተሄደበት መንገድ አንድ ሴራ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልን ለመፍጠርና በዚያው ልክም የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎችን ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች በመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም በህዝበ ሙስሊሙ የነቃ አእምሮና ንቃት ሊከሽፍ ችሏል፡፡
1442ኛውን የኢድ አልፈጥር በአል የጦር አውድማ ለማድረግ የተደገሰውን ድግስ የተገነዘበው ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ሴራው ምን ያህል የተቀነባበረ እንደነበር በማስተማር ጭምር አልፎታል፡፡ ለዚህም በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር መከበሩ አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል በበዓሉ ላይ ለውጭ ሃይሎችም ጭምር ኢትዮጵያውያን የአንድነትና የሰላም ሰዎች መሆናቸውን እነዲሁም በአገራቸው ጥቅም እንደማይደራደሩ በተግባር የሚያስመሰክሩ መፈክሮችና ሰላማዊ መዝሙሮችን በማሰማት ኢትዮጵያውያን ውድቀቷን በሚፈልጉ ሃይሎች ሴራ እንደማይንበረከኩ በተግባር አስመስከረዋል፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት የአብሮነትና የአንድነት መልዕክቶችና ሰላማዊ ሁነቶች ኢትዮጵያን ለማሻገር ወሳኝ ናቸውና ወደፊትም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም