ትናንት የተጠናቀቀው ታላቁ የሮሞዳን የፆም ወር ሰፊ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ፣ የመተዛዘንና የአብሮነት መልካም እሴቶች የሚገለፁበት፤ ይሄው ሆኖም ያለፈበት ነበር። ምክንያቱም እንደ እምነቱ አስተምህሮም ይህ የሮመዳን ወር ወንድም ከወንድሙ የሚጠያየቅበት፣ የሚተሳሰብበት፣ ዘካ የሚያወጣበት፣ በጥቅሉ ለሰው ልጅ ርህራሄ የሚደረግበት፣ የሰው ልጆች ችግሮቻቸውን ተጋግዘው በጋራ የሚሻገሩበት፣ በጋራ የሚሰግዱበት፣ በጋራ የሚያፈጥሩበት፣ የሰው ልጆች ህብረትና አንድነት በፍቅር የሚገለጽበት ወር ነው።
ለ1442ኛ ጊዜ በተከበረው የሮመዳን የፁም ወርም ይሄው እውነት በግልጽ ተስተውሏል። ኢትዮጵያውያን ሙስሊም እህትና ወንድሞች ህብረታቸው እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን፤ ከእምነቱ ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ያሳዩበት ነበር። ፆሙ ከጀመረበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚታዩ መረዳዳቶች፤ ሚስኪኖችን የማስፈጠር ተግባራት፤ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሃ ግብሮች፣ እና ሌሎችም ሰናይ ተግባራት የዚሁ አብይ ማሳያ ናቸው።
በዚህ የፆም ወር ሙስሉሙ ህብረተሰብ ካለው ላይ ለሌለው እያካፈለ፤ በግልም በጋራም እየሆነ የተቸገሩትን ሲረዳ፤ በጋራ ሲያፈጥር እና ፈጣሪውን ሲማጸን አሳልፏል። በኢድ ዋዜማ በአዲስ አበባ የታየው የጎዳና ላይ አፍጥር ደግሞ የሙስሊም ወንድምና እህቶች ለአንድነት፣ ለአብሮነት፣ ለመተባበርና መረዳዳት ያላቸውን ቀናኢነት ከፍ አድርጎ ያመላከተ ነበር። ትናንት በስቴዲዮም በነበረው የኢድ ሲላት ወቅት የታየው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና ጨዋነት የተመላበት መርሃ ግብርም፤ ህዝበ ሙስሊሙ ለሰላሙ፣ ለአንድነትና ህብረቱ ያለውን መልካም እሴት ያንፀባረቀበት ስለመሆኑ ምስክር ነው።
በዓመት ውስጥ ከሰተጡ 12 ወራት ውስጥ የሮመዳን ቅዱስ ወር ሆኖ በህዝበ ሙስሊሙ በፆም፣ በፀሎትና ስግደት ታስቦ ሲያልፍ፤ የቀሪዎቹ 11 ወራት መልካም ተግባራት የሚፀኑበት፣ ህጸጽና ችግሮች ደግሞ የሚታረሙበት፤ ህዝቡ ከፈጣሪው ጋር በንፁህ ልቡናና በመልካም ተግባሩ በአንድ የሚገናኝበት ስለመሆኑ እሙን ነው። ይህ ወር መልካም ነገሮች የሚሰሩበት፤ ከክፋትና ተንኮል የሚራቅበት፤ ከመለያየት ይልቅ አንድነትና አብሮነት የሚፀናበት፤ ከፀብ ይልቅ ሰላም፣ ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍ ጎልቶ የሚታይበት ነው።
ይሁን እንጂ ይህ አንድነትና መተሳሰብ እንዳይቀጥል፤ ሙስሊሙ እርስ በእርሱም ሆነ ከሌላው እምነት ተከታይ ወንድሞቹ ጋር ያለው አብሮነትና ህብረት እንዲላላና ከተቻለም እንዲበጠስ ቀን ከሌት የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን በየአጋጣሚው መመልከት ተችሏል። እነዚህ ኃይሎች ለእምነቱ ወይም ለሙስሊሙ ህዝብ ተቆርቁረው ወይም ለእምነቱና ለአማኙ የተሻለ ነገርን ተመኝተው እንዳልሆነ ደግሞ እሙን ነው።
እነዚህ ኃይሎች ትልቁ ግባቸው ህዝበ ሙስሊሙን እርስ በእርሱም ሆነ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ያለውን መተማመን በመሸርሸር በሚፈጠር አለመግባባት ውስጥ ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኘት ነው። ለዚህ ተግባራቸው ትናንት የብሔር ካባ ደርበው ሕዝቦችን ለማባላት ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህ አልሆን ቢላቸው እና የፈለጉት የሥልጣን ማማ ላይ አላደርስ ቢላቸው፤ ዛሬ ሌላ የህዝብን ስሜት ኮርኳሪ ቦታ ፈለጉ፤ ኃይማኖትን።
እናም በአንድ በኩል የክርስትናን፣ በሌላ በኩል የእስልምናን ካባ በመደረብ ኃይማኖቶች እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑና አንዳቸው ሌላኛቸውን በባላንጣነት ዓይን እንዲመለከቱ በማድረግ ተግባር ተጠምደዋል። ለዚህም ነው አንድ ጊዜ መስጂድ፣ ሌላ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በማቃጠል ለጥፋት ሥራቸው ሌላ ባለቤት በመስጠት አማኞች እርስ በእርሳቸው በጥርጣሬ፣ አለፍ ሲልም በጠላትነት እንዲተያዩ ለማድረግ ሲሰሩ የሚስተዋለው።
ይሄን መሰል የአንድነትና አብሮነት ሸርሻሪ የጥፋት ኃይሎች ደግሞ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬና ነገ ህዝቡን መፈተናቸው አይቀሬ መሆናቸውን ተገንዝቦ መሥራት፤ ለእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ጆሮ በመንሳት ለአንድነትና አብሮነት ተግቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። የየትኛውም እምነት አስተምህሮ ደግሞ ጠላትነትን ሳይሆን ፍቅርና ወንድማማችነትን፤ ፀብን ሳይሆን ሰላምና አብሮነትን፤ መጠፋፋትን ሳይሆን አንዱ ለአንዱ ጋሻና አለኝታ መሆንን ነው የሚፈቅደው።
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌላ እምነት ተከታዮች ከየትኛውም የጥፋት ኃይሎች የሴራ ወጥመድ በመራቅ በዚህ በሮመዳን ቅዱስ ወር የታዩ እነዚህ መልካም እሴቶች የሚጎለብቱበት፤ ህዝበ ሙስሊሙም ከእምነቱ ተከታዮች ጋርም ሆነ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ያለውን መልካም የሆነ ህብረትና አብሮነት የበለጠ የሚያጠናክርበት ሊሆን ይገባል።
ለዚህ ደግሞ መልካም ማድረግ ባይቻል፣ ክፋትን አለመፈፀም፤ ሌሎችን መጥቀምና መደገፍ የሚያስችል አቅም ቢያጥረን እንኳን ለመጉዳት አለመሥራት፤ ማስደሰት ባንችል እንኳን ላለማስከፋት የሚቻለንን ማድረግ ይኖርብናል። በጥቅሉ እንዳለፈው አንድ ወር ሁሉ ለመልካም ነገር በመትጋት፣ ለአብሮነት ቦታ በመስጠት፣ ሰው የማይከፋበትን፣ ፈጣሪም የማያዝንበትን ተግባር መፈፀም ከሁሉም የሚጠበቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም