የአረንጓዴና የልምላሜ ምሳሌዎች ናቸው ከሚባሉት የአገሪቷ አካባቢዎች አንዱ በሆነው በኦሮሚያ ክልል አርሲ በቆጂ አካባቢ ተወልደው አድገዋል።እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውንም እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸውና ድሃ ከሚባሉት አርሶአደር ቤተሰቦቻቸው ጉያ ሆነው ተከታትለዋል።ከስምንተኛ ክፍል ትምህርት በኋላ ወደ ወትድርና ገብተው አገልግለዋል።ውትድርና ውስጥ በቆዩበት ወቅት ግራ እግራቸው ላይ በደረሰ የጦር ጉዳት ለህክምና ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።አዲስ አበባ ገብቶ የሚወጣ ሰው የለም የሚሉት ባለታሪካችንም በህክምና ምክንያት አዲስ አበባ ገብተው ሰምጠው እንደቀሩ አጫውተውናል።
ከወታደር ቤት 1272 ብር ብቻ ይዘው የተሰናበቱት የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ በዳዳ ገመቹ ይባላሉ።ከወታደር ቤት ባገኙት ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ቤተሰብ መስርተው ኑሮን ማሸነፍ እንደማይቻላቸው በመረዳት በ70 ብር የወር ደመወዝ የጥበቃ ሥራም ተቀጥረው ሰርተዋል።በጥበቃ ሥራ የሚገኘውስ 70 ብር እንዴት ነበር የሚብቃቃው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም በወቅቱ በልቶ ለማደር በቂ እንደነበርና አንድ ነገር በቂ ነው አይደለም ለማለት ደግሞ የግለሰቡ ዕቅድና ፍላጎቶችን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ያላቸውን ዕምነት አጫውተውናል።
አቶ በዳዳ፤ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት መኪና ማጠብና ሊስትሮ መጥረግ የመሳሰሉትን ሥራም ሰርተዋል።በወቅቱ የተለያዩ አስከፊና አሳዛኝ የሕይወት ገጠመኞችን አሳለፈው ዛሬ ላይ የደረሱት የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ያለፉበት መንገድ ምንም እንኳን አባጣ ጎርባጣ የበዛበት ቢሆንም አሁን ላይ የደረሱበት ደረጃ የስኬት ተምሳሌት ስለመሆናቸው ምስክር ነው።አቶ በዳዳ፤ በአሁኑ ወቅት በግል ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን በዋናነት አዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች ያሉትን የሪል ስቴት ሥራዎች ያማክራሉ።ከዚህ በተጨማሪም እርሳቸውን ጨምሮ ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር በጋራ በመሆን ሪልስቴቶችን ገንብተው ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ ተሳታፊ በመሆናቸው የሪልስቴት አልሚም ሆነዋል።
‹‹የሰው ልጅ ያለምግብ ሰባት ቀን ያለ ውሃ ሦስት ቀን ይኖራል፤ ነገር ግን ያለ ተስፋ ሦስት ደቂቃ መኖር አይችልም›› የሚለውን አባባል ያነሱት አቶ በዳዳ፤ የጦር ጉዳት የደረሰባቸውን እግር ይዘው ተስፋ ባለመቁረጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል።በአንድ ወቅት በድለላ ሥራ ላይ ስልጠና የሚሰጡ ድርጅቶች መኖራቸውን ሰምተው የሦስት ወራት ስልጠና ወስደው ሰልጥነዋል።ከስልጠናው በኋላም ወደ ሥራው በመግባት የተለያዩ የሚደለሉ ነገሮችን በመደለል ገቢ ያገኛሉ።
በአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ የድለላ ሥራ ምንም እንኳን የጠለሸ ስም ቢኖረውም ሥራው ሕጋዊና መደበኛ የሆነ የንግድ ሥራ እንደሆነ ያምናሉ።ለዚህም ከ25 ዓመት በላይ በሰሩበት በዚሁ የድለላ ሥራ አንድም ቀን ስማቸው በክፉ ተነስቶ የማያውቅና በፍትሀ ብሔርም ሆነ በወንጀል ተከሰው አያውቁም።ለዚህም ሥራውን የሚሰሩት አብዛኛው ሰው እንደሚያምነው የማጭበርበርና የውሸት ሥራ ሳይሆን ዕውነትን በዕውነትና ሕጋዊ የሆነ መንገድን ተከትለው በመሆኑ ነው።‹‹ለሕገ ወጥ ሥራ ጊዜ የለንም›› የሚለውን መርህ አስቀድመው የሚሰሩ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን ችለዋል።
አቶ በዳዳ የድለላ ሥራውን በመደበኛነት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው መስራት ከመጀመራቸው አስቀድሞ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።በአንድ ወቅት ቤት ለማሻሻጥ ከአራት ኪሎ የቀድሞው መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ኮተቤ በገዥዎቹ መኪና አቅንተዋል።ገዥዎቹ ወደሌላ መስመር ሲሄዱ አቶ በዳዳ ደግሞ ወደ አራት ኪሎ መመለስ ነበረባቸው።ኪሳቸው ውስጥ ያለችው አስር ሳንቲም ብቻ ናት።በወቅቱ በከተማ አውቶቡስ አስራ አምስት ሳንቲም ተከፍሎ ከኮተቤ አራት ኪሎ መጓዝ ይቻላል። ነገር ግን ዜሮ አምስት ሳንቲም ስለጎደላቸው አቶ በዳዳ ልመናን አብዝተው የሚጠሉ ናቸውና አልጠይቅም ብለው ጉዳት የደረሰበትን እግራቸውን እየጎተቱ ከኮተቤ የአራት ኪሎ መንገድን ይዘው ተጓዙ።
በጉዟቸውም ውትድርና ቤት የተመታው ግራ እግራቸው በደረሰበት ከፍተኛ ጫና አራራት ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ መራመድ አቅቷቸው ወድቀዋል።በወደቁበት ቦታም በምሬት ሲያለቅሱ የተመለከታቸው ሰው ሊያግዛቸው ተጠግቶ ቢያናግራቸውም እርሳቸው ግን ልመናን እጅግ አድርገው የሚጸየፉ ናቸውና ምንም እንዳልተፈጠረ ተናግረው ጉዟቸውን ቀጥለዋል።ይህ ካሳለፉት ውጣ ውረዶች እጅግ አሳዛኝና ፈታኝ ከሆነባቸው ገጠመኞቻቸው መካከል አንዱ ሲሆን ስለ ሁኔታው ሲያስቡ ዛሬም ድረስ እንባቸው ይቀድማቸዋል።
በተፈጥሯቸው እርዳታ መጠየቅና የሌሎችን እገዛ የማይፈልጉት ተስፋን ሰንቀው ነገን የሚናፍቁት አቶ በዳዳ፤ ክፉኛ ባዘኑበትና ማጣት መቸገር ለምን ይህን ያህል ተፈታተነኝ ብለው እራሳቸውን መጠየቅና መውቀስ በጀመሩበት በዚህ ወቅት ዛሬ የደረሱበት የሕይወት መስመር ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ።በዚያው ሰሞን ታድያ ሻጭና ገዥን ያገናኙበትና በብዙ ድካምና ህመም ከኮተቤ ወደ አራት ኪሎ በእግራቸው የተመለሱበት ሥራ ዕውን ሆኖ ያገናኙት ቤት አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር ተሸጠ።በወቅቱ ብሩ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የእርሳቸውም ድርሻ ከፍተኛ ሆኖ ህልማቸውን ዕውን የማድረግና ሥራቸውን መስመር አስይዞ የመስራት ትልቁ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡
በወቅቱ ከአንድ ወገን 30 ሺ የሚከፈል በመሆኑ ከሁለቱም ወገን ማለትም ከሻጭና ከገዥ በድምሩ 60 ሺ ብር አግኝተዋል።በመሆኑም ያገኙትን ትልቅ ገንዘብ ይዘው ይመኙት የነበረውን የድለላ ሥራ ሕጋዊ መንገድ በማስያዝ ለመስራት ንግድ ፈቃድ አውጥተው ቢሮ ከፍተዋል።ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሥራው ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መሰረት ያዘ።በወቅቱ ሥራው በስፋት የሚታወቅ ባለመሆኑ ንግድ ቢሮ ድለላ እንዴት ፈቃድ ይወጣበታል በሚል ተቸግረውም ነበር።ይሁንና ያኔ የተጀመረውና ሕጋዊ መስመር የያዘው የድለላ ሥራ እየተስፋፋ መጥቷል።በሥራው የተገኘውን ዕውቀትና ልምድ በማዳበርም የተለያዩ ትላልቅ ካምፓኒዎችን የማማከር ሥራን እየሰሩ ያገኛሉ።
በተለያየ ወቅት ከ20 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ ቀጥረው ከሚያሰሯቸው ሠራተኞች በተጨማሪም በመላው የአገሪቱ አካባቢዎች በሚባል ደረጃ በኮሚሽን ሥራ ያሰማሯቸው በርካታ ሰዎችም አሉ።እነዚህ ወኪሎችም ባሉበት ሆነው የተለያዩ ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች እንዲያፈላልጉ በማድረግ የተለያዩ ነገሮችን ከፈላጊዎች ጋር የማገናኘት ሥራ ይሰራሉ።በሥራውም ወኪሎቹ ባሉበት ሆነው ተገቢውን ክፍያ ያገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በማማከር እና በድለላ ሥራ ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ‹‹ታይኮ ሪልስቴት›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር በማቋቋም ሪልስቴቶችን እየገነቡ ይገኛሉ።ወደ ዘርፉ ለመቀላቀልም ያነሳሳቸው ነገር በድለላ ሥራቸው በአገሪቱ የሚከናወኑ በርካታ ሁኔታዎችን ማስተዋል በመቻላቸው ነው።በመሆኑም በከተማዋ ያለው የቤት ፈላጊ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ሥራውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሰርቶ መቅረብ ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በማመን ከአጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ወደ ሥራው ገብተዋል።ሕግን መሠረት ሳያደርጉ የሚሰሩ የሪልስቴት አልሚዎች በመኖራቸው በገዥዎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበትን አወቃቀር ለመከላከል እነርሱ ደግሞ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመስራት ዘርፉን ተቀላቅለዋል።
ይህም ተሳክቶልናል የሚሉት አቶ በዳዳ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አምስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ አስራ አንድ ፎቆች ያሏቸውን የመኖሪያና የንግድ ሕንፃዎች እየገነቡ የሚገኙ ሲሆን፤ እስካሁን በአማካኝ የንግድ ሱቆችን ሳይጨምር ለመኖሪያ ብቻ ከ20 እስከ 24 አባዎራዎችን መያዝ የሚችሉ ሕንፃዎችን ገንብተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።አገልግሎቱን እያገኙ ያሉና የተረከቡ ባለቤቶችም እጅግ ደስተኛ በመሆን አመስግነዋል።ቦታዎቹም ቦስተን ስፓ አጠገብ፣ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ፣ አትላስ ሆቴል ፊት ለፊት ሳይ ኬክ ቤት ጀርባና አምስት ኪሎ የምስራች የመነጽር ማዕከል አጠገብ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ራማዳ ጀርባ እና አምስት ኪሎ የሚገኘው የሁለት ሕንፃዎች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሦስት ቦታዎች ግን ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ከሪልስቴት በተጨማሪም በሎጅ ተሳትፎ ያላቸው አቶ በዳዳ፤ ቀደም ሲል ተቋቁሞ ሲሰራ የነበረና 600 አባላት ያሉት አስበሬራ ሎጅ ላይም የማማከር ሥራ በመስራት የተወሰነ ጥቅም ያገኛሉ።እዚህ ለምጃለሁ የሚል ትርጓሜ ያለውና ደብረዘይት የሚገኘው አስበሬራ ሎጅ ለአባላቱ በዓመት እስከ 12 ሺ ብር የሚከፍል ነው።በአሁኑ ወቅት የሎጁ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለሕዝቡ ክፍት በመሆኑ ሰርግን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
በንግድ ሕግ ደላሎች ነጋዴዎች ተብለው የሚጠሩና ከንግድ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ድለላ ዓለምአቀፍ ከመሆኑም ባለፈ የዓለምን ገበያ እየመሩ የሚገኙ ደላሎች ናቸው የሚሉት አቶ በዳዳ፤ ይሁንና በአገሪቱ ያለው የድለላ ሥራ ፈረ የያዘ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በብዙዎች ዘንድ ለድለላ ሥራ እየተሰጠው ያለው ሥም ያስቆጫቸዋል።በተለይም የመንግሥት ባለስልጣናት ሳይቀሩ አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ በጅምላ ደላሎች ናቸው እያሉ መውቀሳቸው ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።በቀጣይም ከንግድ ዘርፎች አንዱ የሆነውን የድለላ ሥራ ይበልጥ ዘመናዊና ሕጋዊ ማድረግ እንዲቻል ብሎም ዘርፉ ፈር እንዲይዝ በድለላ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች ሥልጠና ለመስጠት የተለያዩ ቅደመ ዝግጅቶችን አድርገው ፈቃድ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ማንኛውም ሥራ በዕውቀት መሰራት አለበት ብለው የሚያምኑት አቶ በዳዳ፤ ደላልነት ያገኙትን ነገር ሁሉ መሸጥ አለመሆኑንም ያምናሉ።በተለይም የአገሪቷን ሕግ መሠረት አድርገው የተከለከሉ በርካታ ነገሮች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ እርሳቸው ሁሉንም ነገር ልሽጥ ልለውጥ ብለው አይነሱም።ስለዚህ ሌሎች በድለላ ሥራ የተሰማሩ ሰዎችም ይህን ጠንቅቀው ማወቅና መተግበር አለባቸው።ስለዚህ ለሥራው ተገቢ የሆነውን ዕውቀት በመያዝ ሕግና ሕግን ብቻ መሠረት አድርጎ በሀቅ መስራት ይገባል።ለዚህም እርሳቸው ለሦስት ወራት የወሰዱት የድለላ ሥራን መሠረት ያደረገው ሥልጠና ለዛሬ ስኬታቸው ትልቅ መሠረት እንደሆናቸው አጫውተውናል፡፡
አንድ ሰው ሊሆን ከሚችለው በላይ ለመሆን መጣር የለበትም።መሆን የሚችለውን ብቻ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑት አቶ በዳዳ፤ ሰዎች መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ ላይ ለመድረስ ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ መስራት ከቻሉ ሕልማቸውን ዕውን ማድረግ ይችላሉ።ስኬታማ ለመሆንም ሰዎች የሚወዱትንና የፈለጉትን ሥራ በትጋት መስራት አለባቸው፤ ይህ የስኬት ቁልፍ ነው።በመጨረሻም ሰዎች ለራሳቸው፣ ለደንበኞቻቸውና ለሥራቸው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ሲመክሩ ትርጉሙም ሥራን ሳይሰሩ እንደሰሩ አድርጎ ሥራን ማታለል፤ ደንበኛንም እንዲሁ ሳይሰሩለት ሰራሁልህ ብሎ ማታለል እና ሥራውን ሳንሰራ ሰርተናል ብለን እራሳችንን ማታለል የሌለብን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል።እኛም የአቶ በዳዳን መርህ ተውሰን ሰዎች ለራሳቸው፣ ለሥራቸውና ለደንበኞቻቸው ታማኝ በመሆን የሚገኘውን ውጤት በማጣጣም ተጠቃሚ እንሁን በማለት አበቃን፡፡
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013