በኢትዮጵያ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑ ህመምተኞች ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱት ለትናንሽ የጤና ችግሮች መሆኑን በዚህ ዘርፍ የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ።የህክምና አገልግሎቶችም በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ባለመሆናቸው ተቋማቱ በህመምተኞች ሲጨናነቁ ይስተዋላል።የህክምና ባለሞያዎችም በተደራራቢ የሥራ ጫና ሲፈተኑ ይታያል።
የዛኑ ያህል ደግሞ አዳዲስ የህክምና ባለሙያዎች ስራ ባለማግኘታቸው ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ ሳይወጡ ይቀራሉ።ከዚህ በመነሳትም የሀገሪቱን የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትና የህክምና ባለሙያዎችን የስራ አጥነት ችግር ይቀርፋል የተባለ አዲስ ጥናት ፕሪሳይስ ኮንሰልቲንግ ኢንተርናሽናል በተባለ ድርጅት ተሰርቶ በቅርቡ ይፋ ሆኗል።
በፕሪሳይስ ኮንሰልቲንግ ኢንተርናሽናል የጤና ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ሄኖክ ባያብል እንደሚገልፁት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አዳዲስ ወይም ልምድ ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች በራሳቸው ቢሮ ገብተው የህክምናና ከጤና ጋር የተያያዙ የምክር አገልግሎቶች መስጠት አይችሉም።ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን የግድ በግል ወይም በመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ገብተው መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡
የጥናቱ መነሻዎችም በቅድሚያ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በፖሊሲ፣ በጤና ተደራሽነትና የጤና ባለሙያዎች ስራ አጥነት ችግሮች ዙሪያ የተደረጉ ውይይቶች ናቸው።በዚሁ ውይይትም እንደ አንድ የመፍትሄ አማራጭ ሆኖ የተጠቆመው ሀኪሞች በቢሯቸው ሆነው የህክምና አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ነው።ይህም የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግና የስራ አጥ ሃኪሞች ቁጥርን ለመቀነስ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
ከዚህ በመነሳትም ድርጅቱ ሀኪሞች በትንሽ አቅም፣ ገንዘብና ሀብት አገልግሎቱን በአነስተኛ ቢሮ ሆነው ለመስጠት የሚያስችላቸውን አሰራር ለመፍጠርና ይህንኑ አሰራር በማስተዋወቅ ሂደት ውስጥ ያሉ የፖሊሲ ማእቀፎችን፣ እድሎችንና ተግዳሮቶችን የሚፈትሽ ጥልቅ ጥናት እ.ኤ.አ ከመስከረም 2020 አስከ ጥር 2021 ድረስ በአዲስ አበባ ሲያካሂድ ቆይቶ አጠናቋል።
የዚህ ጥናት ዋነኛ አላማም አንድ አዲስ ወይም ልምድ ያለው የህክምና ባለሙያ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ሳይጠበቅበት የራሱን አነስተኛ ቢሮ ከፍቶ ወደራሱ ለሚመጣ የአገልግሎቱ ፈላጊ የህክምና ምክር መስጠት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው።ህመምተኛው ላብራቶሪን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን ከፈለገ ደግሞ አገልግሎቱ ወዳለባቸው ሌሎች ቦታዎች መምራት የሚያስችለውና የላብራቶሪ ውጤቱን ይዙ ወደ ሀኪሙ ከመጣም በኋላ ተገቢውን ህክምና ለመስጠት፣ መድሃኒት ለማዘዝና ክትትልም ለመስጠት ያስችለዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ጥናቱ ለአእምሮ ሀኪሞች፣ ስነ ምግብ ባለሙያዎች፣ አዋላጅ ነርሶችም ጭምር የህክምና ምክር ለአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመስጠትና ስራውን ለማስጀመር ያስችላል።በተለይ ደግሞ በርካታ ቁጥር ላላቸው ሰዎች በህክምና ምክር አገልግሎት ተደራሽ ለመሆን ይረዳል።ታካሚዎችም አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው ለማግኘት ያስችላቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጥናቱ የተፈተሸው የህክምና አሰራር ጤና ጣቢያዎች በአብዛኛው ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ፣ በእረፍት ቀናትና በዓመት በአላት ነፃ በመሆናቸው ሃኪሞች ተደራጅተው የጤና ጣቢያውን መሰረተ ልማት በመጠቀም የህክምና ምክር አገልግሎት እየሰጡ ገቢ የሚጋሩበትን ሁኔታ ይፈጥራል። እወቀታቸውን ኢንቨስት ለማድረግም ያስችላቸዋል።
የህክምና አሰራሩ ለበርካታ የህክምና ባለሙያዎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከመጨመር አኳያም ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አመላክቷል።ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ይህን አሰራር ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ከአንዳንድ አካላት የሚነሱ ችግሮች እንደሚኖሩም ጥናቱ ጠቁሟል።ለአብነትም ጀማሪ ሀኪሞች በራሳቸው አገልግሎቱን በዚህ አሰራር ቢሰጡ ሊቸገሩ እንደሚችሉ ጥናቱ አሳይቷል።
ይሁንና ጀማሪ ሀኪሙ የሲ ኦ ሲ መመዘኛ አስካሟላና በተማረበት የህክምና ሙያ በዲግሪ ተመርቆ በህክምና ልምምድ ውስጥ አስካለ ድረስ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም በጥናቱ ተጠቁሟል።ጥርጣሬውን በተሻለ መንገድ ለማስወገድ ደግሞ ጀማሪ ሃኪሞች ልምድ ካላቸው ጋር የሚጣመሩበት ሁኔታም እንዳለ በጥናቱ ተገልጿል።
ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት ጥናቱን ለማካሄድ ሁለት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች በአማካሪነት የተቀጠሩ ሲሆን ቃለመጠይቆችንና የቡድን ውይይቶች በዘዴነት ጥቅም ላይ አውሏል። የመጀመሪያና ሁለተኛ ዳታዎችም በጥናቱ ተካተዋል።በግሉ የጤናው ዘርፍ የተሰማሩና ከጤና ሚኒስቴር የሚመለከታቸው አካላትም ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።የሌሎች ሀገራት ጥናታዊ ፅሁፎችም ተቃኝተዋል።የሀገራት መልካም ተሞክሮዎችም ተቀድተዋል።
በዚሁ መሰረት በከተማዋ በርካታ ስራ አጥ የህክምና ባለሙያዎችና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ችግሮች ከመኖራቸው አኳያ የህክምና ምክር አገልግሎትን በአነስተኛ ቢሮ መስጠት /medical office practice/ ቢጀመር የህክምና ባለሙያዎች በትንሽ ሃብት ስራውን በቀላሉ ለመጀመር እንደሚያስችላቸው የጥናቱ ውጤት አሳይቷል።በከተማ ብቻ ሳይሆን በርካታ የህክምና ባለሙያዎች ወደቀያቸው ሲመለሱ ይህንኑ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችላቸውም ጥናቱ አሳይቷል።
አገልግሎቱ የሀኪምና ህመምተኛ ግንኙነትን ከማጠናከር በዘለለ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ የህክምና ተቋማትን ጫናም እንደሚቀንስ በጥናቱ ተመላክቷል።
በአሁኑ ግዜ ጥናቱ በጤና ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊነቱ ታምኖበት ተቀባይነት አግኝቷል።በጤና ሚኒስቴር የፖሊስ ማዕቀፍ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በጤና ሚኒስቴር በኩል የአፈፃፀም መምሪያና የፖሊሲ ማእቀፍ እየወጣለትም ይገኛል፡፡በጥናቱ ዙሪያም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተጨማሪ ውይይቶችና ትችቶች እየተደረጉበት ይገኛል።በቀጣይም ጥናቱ ወደ ፖሊሲ ማርቀቅ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።ድርጅቱ በጥናቱ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በቀጣይ ፖሊሲ አውጪዎችና ህብረተሰቡም አገልግሎቱ እንዳለ እንዲያውቅ በተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች ይሰራሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013