አዲስ አበባ፡- ሱዳን በቅርቡ የቤኒሻንጉል መሬት የኔ ነው የሚል ያልተገባ ትርክት ይዛ መምጣቷ ኢትዮጵያ ትኩረቷን ከግድቡ እንድታነሳ ለማድረግ የተቀየሰ ሴራ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ አስታወቁ፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ሱዳን በቅርቡ የቤኒሻንጉል መሬት የኔ ነው የሚል ያልተገባ ትርክት ይዛ መጥታለች። ትርክቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን የድንበር ችግር የበለጠ በማወሳሰብ ኢትዮጵያ ትኩረቷን ከግድቡ እንድታነሳ ያለመ የሱዳንና የግብጽ ምኞት ነው።
የአንድን ሉዓላዊ አገር መሬት የእኛ ነው በማለት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስተጓጎል መጣር ከንቱ ምኞት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፣ ኢትዮጵያ ባቀደችው መሰረት ግድቧን ሰርታ ትጨርሳለች፤ ለዚህም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወንበት ጊዜም እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለጻ፤ ቀደም ሲልም ግብጽና ሱዳን የግድቡን ግንባታ ሊከለክሉትና ሊያስጓጉሉት የሚችሉበት ምንም መንገድ አልነበረም:: አቅምም አልነበራቸውም:: በዚህ የተነሳ ከኢትዮጵያ ጋር ስለግድቡ አሞላል እና ስለግድቡ የውሃ አያያዝ ውይይት ሲያደርጉ ነው የቆዩት:: እነርሱ የሚሰሩት ሥራ ሁሉ ኢትዮጵያ ግድቧን ጨርሳ፣ ውሃ ሞልታ፣ መብራት የምታገኝበትን መንገድ ሊያደናቅፍ የሚችል አይደለም ::
ሱዳን በትንሹም ሆነ በትልቁ የኢትዮጵያን መሬት የእኔ ነው ማለቷ አንደኛ የጉርብትንና መልካም ጎን እጅግ በጣም የሚያበላሽ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ ህግንም የሚጻረርና የሚጥስም ነው:: ለወደፊትም ቢሆን ኢትዮጵያና ሱዳን በጉርብትናቸውና በመልካም ግንኙነታቸው ህዝቦቻቸውን በሰላምና በልማት የሚያስተዳድሩበትን መንገድ የሚያስተጓጉል እንደሆነ አመልክተዋል::
ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵያ ጉዳዪዋን ከመፈጸም እና ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ዝንፍ አትልም:: ሱዳን በምትከተለው የተሳሳተ መንገድ ለዘለቄታው ተጎጂ ሀገር ልትሆን እንደምትችል አሳስበዋል :: ይንንም የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ የተገነዘበው ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል ::
በቀጣይም የሱዳን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጉርብትናው አብሮ የሚቀጥል እንደሆነ ያመለከቱት ፕሮፌሰር ያዕቆብ ፣ የሱዳን ህዝብ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲመለከተው ፣ ለወደፊት የሚጎዳቸውን ነገር መንግሥታቸው በድፍረት እና በግዴለሽነት እንዳይፈጽም ጫና ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል ::
ሱዳን ቤኒሻንጉል የእርሷ ስለመሆኑ በማናቸውም ዓለም አቀፍ ሰነድ ልታስረዳ የምትችልበት ነገር የላትም፤ መሬቱ ይገባኛል ማለቷ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነቷን እንዲሁም የትብብር መንፈሷን ከማበላሸት ያለፈ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡
ይህም መልሶ የሚጎዳት ሱዳንን መሆኑን አመልክተው፣ ከምንም በላይ ጥያቄው መሰረት የሌለው፤ በጣም በግዴለሽነትና በማንአለብኝነት የሚደረግ በመሆኑ ችግሩ መልሶ የሚጎዳትና ዋጋ የሚያስከፍላት ሱዳንን መሆኑን አስታውቀዋል ::
ሱዳን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚካሄድበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላይ የባለቤትነት ጥያቄ አለኝ ማለቷ፣ ቅጥ ያጣ ድፍረት መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013