የጤና ዘርፍ ላይ በግል ስራ ምን ያህል ወጤታማ ነው? ወጤታማ ላለመሆኑስ ምን ችግር አለና የመሳሰሉትን ጥናቶች ከተደረጉ በኋላ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራን ለመስራት ያሰበ ስልጠና ሰሞኑን ተዘጋጀቶ ነበር።
ፕሪሳይዝ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል የተባለ በግል ድርጀቶች አከባቢ ጥናት የሚያደርግ፤ በዋናናት በቢዝነስና ግብርና ላይ ሲሰራ በቆየ ድርጅት ሲሆን ጥናት ባካሄደባቸው ጉዳዮች ላይ በጤና ዙሪያ ለሚሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን እንዴት ከህክምናው ጋር አስተሳስሮ መሄድ ይቻላል በሚል ስልጠና ሰጥቶ ነበር። በቅርቡ በሀገራችን ስለተሰማው የህክምና ባለሙያዎች የስራ አጥነት ችግር ጋር በተያያዘ ምን መደረግ አለበት የሚል ሀሳብም ተነሰቶ ነበር።
በቅዱስ ፓውሎሰ ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ መምህርነት የሚያገለግሉት ዶክተር ትግስቱ ስለ ጉዳዩ ጥናቱን ያካሄዱ ሲሆን ይህንኑ ለጋዜጠኞች በዚህ መልኩ አስገንዝበዋል። የህክምና ስራን በተሻለ መንገድ ለማስኬድ፤ አገልግሎቱን ቀልጣፋና የጠራ ለማድረግ ያለው መፍትሄ አንድ ጤና ድርጅት ውስጥ ማስተማሩንም ህክምና መስጠቱንም እንክብካቤ ማድረጉንም የምርመራ ስራውንም የህክምና ስራዎች በአጠቃላይ አንድ ቦታ እጭቅ ማድረጉን አቁሞ በተበተነና በቀላሉ ሊመራ በሚችል መልኩ መሰራት ይኖርበታል።
በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ሀገሮች ሀኪሞች ቁጥር በጣም ጥቂቶች ቢኖሩንም እንኳን በሀገር በጀት የተማሩ ሰዎች ስራ አጥተው ቁጭ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ስራ ባጡበት በቂ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ባልተቻለበት የህክምና ተቋማቱ መሰረተ ልማቶች በበቂ መልኩ ባልተማላበት የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ምን መሰራት ይኖርበታል የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ዶክተሩ ለሁሉም መፈትሄ እራስን ወደ ዘመናዊ አስተሳሰብ ማስገባት ነው ይላሉ።
መንግስት የጤና ተቋማትን በየወረዳው ያቋቋመው ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆነ፣ ኪስ የማይጎዳና ጥራት ባለው መልኩ እንዲደርስ ነው። ይህን ለማድረግ መንግስት የራሱ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት፤ የጤና ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
መንግስት ሀገሪቱ ውስጥ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ለማሳደግ የጤና ተቋማትን ማስፋፋት፤ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን፤ ግብአቶችን ማሟላትና ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት እንዲኖር በየጊዜው ጥራትና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል የሚሉት ዶክተር ትዕግስቱ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ የህክምና ሳይንሱን በአግባቡ መተግበር ይኖርባቸዋል። ከህብረተሰቡም ጋር ባላቸው መስተጋብር ደግሞ የሚፈለገውን ስራ ሰርተው ትክክለኛ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ህብረተሰቡም ደግሞ አንድም ህመም በጣም ባልፀናበት ሁኔታ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህመም ሳይጠና መታከምና በጤና ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ይጠበቅበታል። ሁሉም የራሱን ሀላፊነት ቢወጣ የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ የሚሆነው የባለሙያ ወይም የግብዓት አጥረት መኖር፣ ለስራው ምቹ ሁኔታ ያለመመቻቸት፣ ህብረተሰቡ ጤናን እንዴት ማግኘት እንዳለበት ያለው እውቀት አናሳ መሆኑ እና በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት የመምጣት ልምድ ያለመኖር ችግሮች ይጠቀሳሉ። የእነዚህ ችግሮች አለመፈታት የጤና ስርዓቱ የተማላ እንዳይሆን አድርጎታል የሚሉት ዶክተር ትዕግስቱ ባለፉት አስርና አስራ አምስት አመታት የጤና ስርዕቱን መንግስት ለማሻሻል ግብዓቶችን ማሟላት የመሳሰሉ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
ሆኖም ግን የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን በተፈለገው መልኩ ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሉ በሀገራችን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ስራ አጥተው ይገኛሉ። ታዲያ ይህ እስከ ዛሬ የተሄደበትን አካሄድ በትኩረት መመልከትና መፈተሽ የሚጠይቅ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ትእግስቱ አንድ የጤና ባለሙያ በጤና ተቋም ውስጥ ሆኖ ታካሚውን ከሚጠብቅ ወደ ህብረተሰቡ ቀረብ በማለት አገልግሎት መስጠት የሚችልበት አካሄድ መታየት የሚኖርበት መሆኑን ነው የተናገሩት።
ባለሙያው ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ማገልገል ሲኖርበት ሀገር በርካታ ወጪ አውጥታ ያስተማረቻቸው እነዚህ ሰዎች ቁጭ ብለው ስራ ከሚጠብቁ ህብረተሰቡ ባለበት አከባቢ ተጠግተው የራሳቸውን ስራ በቀላሉ መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት አለበት ይላሉ። ወደ ማህበረሰቡ የቀረቡ ባለሙያዎች የተሻለ ህብረተሰቡን የማዳመጥ የተሻለ የመማከርና አገልግሎት የመስጠት ስራ ላይ ቢሰማሩ የስራ እድል በመፍጠር ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት አሰራር ይፈጠራል።
የህክምና ባለሙያዎች አዲስ ምሩቅ ሲሆኑ የክህሎት ክፍተት አይኖርም ወይ ለሚለው ሀኪሞች ከመመረቃቸው በፊት ለአንድ አመት ከሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ጋር ስራ ላይ መሰማራታቸው ተረጋግጦ፣ ብቁ መሆናቸው ከታወቀ በኋላ ነው የሚመረቁት።
በአብዛኛው ህብረተሰቡን ወደ ጤና ተቋም የሚያመጣቸው ህመሞች በአቅራቢያው በፍጥነት በቀላል ህክምና ሊፈታ የሚችል ችግር መሆኑን ተናግረው በቀላሉ የሚሰሩትን ሰርተው ያልቻሉትን ሪፈር ማድረግ የሚያስችል የአሰራር ሂደት መከተል የሚያስችል ጥናት መጠናቱን ነው ዶክተር ትእግስቱ የተናገሩት።
ዶክተር ትእግስቱ አዲስ ምሩቆችስ በምን መልኩ ነው ስራ መፍጠር የሚችሉት የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ እንደተናገሩት አዲስ ምርቆችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥሪት ማካባት አይጠበቅም። መንግስት የጤና ባለሙያዎች ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ መሆኑን ከተረዳ፣ ጤና ጥበቃ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር መነሻ ገንዘብ ማመቻቸት ይችላሉ ብለዋል።
ባጠቃላይ በቀላሉ ለህብረተሰቡ ጤናን ተደራሻ ለማድረግ መስራትና የስራ ፈጠራ መታየት አለበት። ይህም ለሀኪሞች ስራ ለመፍጠር ብቻ የታቀደ ጉዳይ ሳይሆን ለቀጣይ አመታት የጤና ስርዓትን ለማዘመን የሚሰራ ስራ ነው። የጤና ስርዓቱን ለማዘመን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መለማመድ፣ ጥራትንና ተደራሽነትን ባረጋገጠ መልኩ መሰራት ይኖርበታል ሲሉ ማብራሪያቸውን አጠናቀዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013