በኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት እያበቡ የመጡ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በማስተናገድ በኩል የትምህርት ተቋማትን ያህል የላቀ ሚና የተጫወተ የለም ቢባል አልተጋነነም። ስለ ዓለም የፖለቲካ ሁኔታና በአገሪቱ ስለሚኖረው አንደምታ እንዲሁም ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየርና ለውጥ ለማምጣት ከሌሎች የአገሪቱ ዜጎች በተለየ ሁኔታ ዘመናዊ ትምህርትን ለመቋደስ የበቁት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ታሪክ ይመሰክራል። በተለይም በ1960ዎቹ በተካሄዱት አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ተቋማቱ ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተራማጅ ተማሪዎች በወቅቱ የነበረውን የዘውዳዊ አገዛዝ በግልጽና በጽኑ በመቃወም በአገሪቱ አብዮት እንዲነሳና በመላ አገሪቱ እንዲቀጣጠል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን ያህል እንደነበር ጸሓፍት በከተቡት ብዕራቸው ይገልጹታል። ይህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መነሻ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፤ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት ፓኬጅም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በዘመናዊ አኳኋን እንዲመነደጉ ከማድረግ፤ በተጨማሪም ተቋማቱ የአንድን ሀገር ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማዘመን ጥያቄዎችን ወደ ለውጥ በማንደርደር ረገድ ያላቸውን ሚናን ያመላክታል።
በተቋማቱ እነዚህና መሰል ውጤቶች ማየት የሚቻለው ተቋማቱ በአግባቡ ከተደራጁ፣ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማቋቋም ጥራትን መሰረት አድርገው የሚያስተምሩ ከሆነ ብቻና ብቻ መሆኑን በርካታ ምሁራን ይሞግታሉ። ይህም ዜጎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመቅረጽ ለራሳቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሀገራቸው ጠቃሚ ዜጋ የሚያፈሩበት ግዙፍ የእውቀት ማዕከል መሆን እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የከፍተኛ ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት ጉዳይ ለተቋማቱ ትልቅ ጉልበት እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። የመስማሚያ ሀሳባቸውንም ስንመለከት ደግሞ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተራማጅ ሀሳቦች ጎልተው ከመሰማት ባሻገር ለውጥ እስከማምጣት የመድረሳቸው እንቆቅልሽ የተፈታው በወቅቱ በዩኒቨርሲቲዎች የነበረው የአካዳሚክ ነጻነት የተከበረበት ጊዜ በመሆኑን ነው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን።
በእርግጥም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተቋማቱ አመራሮች የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎችን በተቋማቸው በነጻነት ማንሳት የሚችሉበት መደላድል ስለመኖሩም ይነገራል። ይህም በተቋማቱ አብዮተኝነት ከፍ ከማለቱ ጀርባ በወቅቱ የነበረውን የአካዳሚክ ነጻነት ይጠቁመናል።
በሀገራችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ነጻነት መከበሩን ተከትሎ በታሪክ የተመዘገቡ ለውጦች ዳግም እንዳይመዘገቡ የተቋማቱ የለውጥ መሰረት የመሆኑን ታሪክ አምባገነኑ የደርግ መንግስት ጀምሮት፤ ኢህአዴግ ከክብሩ አውርዶ ገድሎ የቀበረው መሆኑን ከበቂ በላይ አስተያየቶች ሲሰጡበት ኖረዋል። ይህም ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃ አለመሆናቸው፣ የአመራሮች ቁመና እና ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተደማምረው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ለሀገር አለኝታ መሆናቸው ቀርቶ ወደ ስጋትነት ዝቅ ብለው እንዲጓዙ ያደረጋቸው ስለመሆኑም እንደዛው።
በዚህ ረገድ ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሰፊ ችግር የተፈጠረ መሆኑን ከሚገልፁ በርካታ ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ይገኙበታል። ዶ/ር ዳኛቸው በአንድ መድረክ ላይ አቅርበውት በነበረ ዲስኩር ችግሩን ሲገልጹ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች ከፖለቲካ ነፃ አይደሉም። በተቋማቱ የአካዳሚክ ነጻነት አለመኖሩን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎቹ የግጭትና የጦርነት ቀጣና ሆነው ዘመናትን እንዲጓዙ አስገድዷቸዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው በሀገራችን ወታደራዊ መንግስት ከሆነው ከደርግ ዘመን ጀምሮ ተቋማቱ ፖለቲካዊ ገጽታን መላበሳቸውን “በደርግ ዘመን በርካታ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችና መምህራን ወደ ፖለቲካው ሲገቡ “ወዶ ገቦች” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ዘመን ተሻግሮ ቢመጣም ባለፉት ሰላሳ አመታት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተቋማዊ ነጻነታቸውን መላበስ አልቻሉም ነበር። ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ የተሻሻለ አይደለም። በመሆኑም ተቋማዊ ነጻነቱን ማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።” በማለት ችግሩን ከነመፍትሄው ይገልፁታል።
የአካዳሚክ ነጻነት መዋጥ፣ በፖለቲካው ሥርዓት መጣስ የኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት መሰረታዊ መለዮ የመሆኑ ታሪክ ሊያበቃ እንደሚገባ የብዙዎች እምነትና ፍላጎት ነው። በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሲቀርቡ ከነበሩ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መካከል የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አካዳሚክ ነጻነታቸው ተከብሮ የእውቀት ማዕከል ቅርጽን እንዲላበሱ ማስቻል ይገባል የሚል ነበር። ከሰሞኑ የተሰማው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነትን የማስከበር ጉዳይ ላይ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረው እንቅስቃሴ ይሄንኑ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለሚያዘጋጀው አገር አቀፍ ሰነድ እንዲረዳው የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ያዘጋጀ ሲሆን፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካዳሚክ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚዘጋጀውን ሀገር አቀፍ ሰነድ በተመለከተ ሲናገሩ፤ በሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነታቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ በዘርፉ እየተካሄደ ያለው መሻሻያ (ወይም መለወጥ) አካል ነው።
የተቋማቱ በነጻነት መስራት ለአገራዊ ችግሮች ሳይንሳዊ መፍትሔ በማበጀት የሃሳብ ልዕልና እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም የተባለው። በኢትዮጵያነት በሃሳብ ከማሸነፍ ይልቅ ሃሳባዊያንን የመግደልና የማስፈራራት አዝማሚያዎች በሥፋት የሚታዩ መሆናቸውን ያመላከቱት ደግሞ ዶክተር ሳሙኤል ናቸው።
«ይሄን ችግር ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚኖረው ሲሆን፤ በውጤቱም ተቋማዊ ነጻነቱ ብቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመፍጠር ያስችላል» ያሉት ዶክተሩ ሀገር አቀፍ ሰነዱ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተሸብበው ከኖሩበት አውድ በመውጣት ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሜዳ የሚፈጠርላቸው ሥለመሆኑም ተናገረዋል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የከፍተኛ ትምህርት ከተጀመረ 70 ዓመት ማስቆጠሩን ያስታወሱት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደተናገሩት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቋቋሚያ ሰነዳቸው ተቋማዊ ነጻነታቸውን ማረጋገጥ ትኩረት ከሰጧቸው ዋንኛ ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ተቋማዊ ነጻነት እየተተገበረ የሚገኘው በተሸራረፈ መልኩ ነው። ስለዚህ ተቋማዊ ነጻነቱ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ሰነድ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ሰነዱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 የተቀመጠውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻነት አስመልክቶ ያሉ ጉዳዮችን በዝርዝር ያብራራል።
የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ከማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀብታሙ ካሳ በበኩላቸው ሰነዱ ለመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደር፣ የአካዳሚ፣ የሰው ሃብት አስተዳደርና የፋይናነስ ነጻነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ያስገነዘቡ ሲሆን፤ በአስተዳደራዊ ነጻነት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን ከፍተኛ አመራር የመምረጥ፣ የራሳቸውን መዋቅርና ቅርጽ በነጻነት የመወሰን መብት እንዲኖራቸውም የሚያደር መሆኑንም አመላክተዋል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራረሪያ ከሆነ ተቋማቱም “የተማሪ ቅበላን፣ የትምህርት ይዘትን፣ የጥራት ማረጋገጫ አሰራሮችን፣ የትምህርት መርሃ ግብሮች የመቅረጽና ተያያዥ ጉዳዮችን በራሳቸው የመወሰን የአካዳሚ ነጻነት ያገኛሉ። የፋይናንስ አስተዳደርን በተመለከተም በራሳቸው በጀት የማስተዳደር፣ የተለያዩ የውስጥ ገቢዎችን የማመንጨትና የተማሪዎችን ክፍያ የመወሰን መብት ይኖራቸዋል።” የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአመታት የተነፈጉትን የአካዳሚክ ነጻነት በሚዘጋጀው ሰነድ አማካኝነት በሚገባ ለመመለስ የሚያስችል ቁመና እንዲኖራቸው ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
በአጠቃላይ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተሸብበው ከኖሩበት ድባብና እውነታ እንደሚያወጣቸው የሚታለመው ይህ አገር አቀፍ ሰነድ በሀገራችን፤ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮና ራዕይ ለማሳካት ተቋማዊ የአካዳሚክ ነጻነት ስርዓትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ ስለመሆኑ ተነግሯል።
የትምህርት ጥራትን፣ አግባብነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ውጤታማነትን፣ ተወዳዳሪነትንና ቅልጥፍናን በማሳደግ ተቋማቱ ለውጥ እንዲያመጡ የማድረግ አላማ ያነገበ ስለመሆኑ ተብራርቷል። በመሆኑም በሰነዱ ላይ ግብአት የማሰባሰቡ ሂደት በቀጣይ በሚዘጋጁ ተከታታይ መድረኮችም ይኖራሉ። ከመድረኮቹ የሚሰበሰበውን ግብዓት መሰረት በማድረግም ሰነዱን የማጎልበት ሥራ የሚሰራ ከመሆኑም በተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎች የሚዘጋጁ ይሆናል። አገር አቀፍ ሰነዱንና የሕግ ማዕቀፉን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት እቅድ መያዙን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013