መቼም የአመት በዓል ሰሞን በሃገራችን ሃብታሙም ደሃውም፣ ሴት ወንዱ ሁሉም እንደየአቅሙ በዓሉን በደስታ እና በሰላም ከቤተሰቦቹ፣ ከዘመዶቹ፣ ከጎረቤቶቹ ጋር እየተጠራሩ ለማሳለፍ ከገበያ የሚገዙ ነገሮችን ለመግዛት ሸማቹ ከላይ ታች፤ ከዚያ ከዚህ ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ ከበዓል በፊት ያለ በዓሉን በዓል ከሚያሸቱ ሁነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሻጭም ጥሩ ትርፍ ለማግኘት በማድለብ ሲደክምበት የከረመውን በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ ወዘተ… ወደ ገበያ ያወጣል፡፡ አትራፊ ነጋዴዎችም ከሩቅ አገር የገዙትን በሬ፣ በግ ፣ ፍየል፣ ዶሮ ወዘተ…ወደ ከተሞች ወስዶ በመሸጥ የድካማቸውን ዋጋ ለማግኘት ሲጣጣሩ የሚታየው በዚሁ በበዓል ገበያ ነው፡፡
የአመት በዓል ገበያ ጥሩ ነገር ለመሸጥ የወጣ ነጋዴ እንዳለ ሁሉ ያለ አግባብ በማጭበርበር ትርፍ ለማግኘት በማሰብ መጥፎ ነገር ከምግብ ጋር ቀላቅሎ በመሸጥ እና የጤና መታወክ ያለባቸው በሬ፣ ዶሮ ወዘተ…ወደ ገበያ በማምጣት ለመሸጥ የሚመጣውም ነጋዴ ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የአመት በዓል ገበያዎች ያየነው እውነታ ነው፡፡
ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ነጋዴዎች የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ እነኚህ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ገበያ ያልተገባ ነገር ይዘው በመምጣት ለህዝቡ እንዳይሸጡ ለማድረግ ያለው ቁጥጥር ምን ይመስላል? ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን አድርሰዋል፡፡ ዝግጅት ክፍሉም የነዋሪዎቹን ጥያቄ በመያዝ ጉዳዩ የሚመለከተውን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንን አነጋግሮ ያገኘውን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አበራ ደነቀ እንደገለጹት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዓልም ቢደርስም ባይደርስም ጥራቱን ያልተጠበቀ ምግብ በህዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ስለሚታወቅ ሁሌም ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ ከምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ጋር ተያይዞ በፌዴራል እና በክልል ተቆጣጣሪዎች የሚሰራው ስራ የተለያየ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ምግብን ከባእድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ሰዎችን የሚቆጣጠሩት የክልል ተቆጣጣሪዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል ተቆጣጣሪዎች ይህን ቁጥጥር አያደርጉም ማለት አይደለም፡፡
ከትንሳዔ በዓል ጋር ተያይዞ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በመያዝ እና ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ ከፌዴራል እስከ ታች ድረስ ባሉ የቁጥጥር ባለሙያዎች እና በየአካባቢው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጎበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሰው ልጅ ለመኖር መሰረታዊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ጥራቱ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ነው የሚሉት አቶ አበራ፤ ይሁን እንጂ ለመኖር መሰረታዊና አስፈላጊ የሆነው ምግብ በተገቢው መንገድ ተመርቶ፣ በማከማቸት፣ በመያዝ እና በማጓጓዝ ወይም ለተጠቃሚው የምግቡ ደህንነት በተጠበቀ መልኩ በማቅረብ ሂደት ምግቡ ሊበላሽና ጎጂ ሊሆን ይችላል። ምግብ ለጤና ተስማሚ ሆኖ ለህብረተሰቡ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ማቅረብ እና በተገቢው የንግድ ስርዓት አልፈው ለተፈላጊው አላማ ካልዋሉ እንዲሁም ሕገወጥ የምግብ ዝውውር ካልተከላከልን እና ቁጥጥር ካላደረግን ከጠቀሜታቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘነ ነው።
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፤ ሕገወጥ ምግብ ማለት ከሚመለከተው ተቆጣጣሪ ድርጅት እውቅና ሳያገኝ፣ መስፈርቱን ሳያሟሉ ወይም የማምረት የብቃት ማረጋገጫ ሳያገኙ እና ደረጃውን ባልጠበቅ ሁኔታ ተመርተው የሚከፋፈሉ፣ የሚቸረቸሩ እና ለገበያ የሚያቀርቡ ምግቦች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ህገወጥ ምግብ በተለያዩ በህገወጥ መንገዶች በመጠቀም ይጓጓዛሉ፡፡ ለምሳሌ በመኪና፣ በሰዎች እና በእንስሳት ከውጭ ሀገር ተገቢውን የጉምሩክ እና ሌሎች የቁጥጥር ሥርዓት ሳያሞሉ ወደ ሀገር በኮንትሮባንድ መልክ የሚገቡ እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተቆጣጣሪውን መስፈርት እና እውቅና ሳይኖራቸው የሚመረቱ ምግቦች ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅለው ደረጃቸውን ሳይጠብቁ የሚጓጓዙ በህገወጥ መንገድ እና ከሌላ ባዕድ ነገሮች ጋር የሚከማቹ ህጋዊ ያልሆኑ ወይም ምንጫቸው ያልታወቁ የምግብ መጨመሪያ፤ ማቅለሚያ፤ ማጣፈጫ፤ ማድረቂያ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም የምግቡን የመጠቀሚያ ጊዜ ለማራዘም እና በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚደረጉ እና ለገበያ የሚቀርቡ ናቸው።
ሕገወጥ ምግብን ለመከላከል መንግሥት የተለያዩ ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣት እና ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶችን በአዋጅ ጭምር በማቋቋም ከፌዴራል መንግሥት እስከ ወረዳ የቁጥጥር ሥርዓት ቢዘረጋ እና ቁጥጥር ቢያደርግም የሚፈለገውን ያህል ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። ለቁጥጥሩ አስፈላጊ የሆነ ግብዓቶች እና የሰው ኃይል የተጠናከረ ባለመሆኑ እና አዳዲስ ህገወጥ አሠራሮች በየጊዜው እየተቀያየሩ ስለሚፈጠሩ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት አስቸጋሪ መሆኑን አመላክተዋል።
በዋንኛነት የቁጥጥሩ አካል መሆን የነበረበት ህብረተሰቡ የግንዛቤ ችግር በመታየቱ ቁጥጥሩን አዳጋች አድርጎታል የሚሉት አቶ አበራ፤ ሆኖም ግን ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጥና ሕገወጦችን እንዲያጋልጥ ለማስቻል ተቆጣጣሪው ከህዝብ ክንፍ፣ ከሚዲያዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በህገወጥ ምግቦች ምክንያት የሚከሰቱትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመግታት ተቆጣጣሪ ድርጅቶች ታላቅ ኃላፊነት ስላለባቸው በተቀናጀና በመረጃ የተደገፉ የድህረ ገበያ ጥናት እና ከህብረተሰቡ የሚመጡትን ማንኛውንም ጥቆማ ዋጋ በመስጠት ህብረተሰቡ ላይ የከፋ ችግር ሳይከሰት ቁጥጥሩን አሁን ካለው በላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማጣማር እና የሌሎች አገሮችን ልምድ በመቅሰም ጥናቶችን በማድረግ አሁን ካለው የበለጠ የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰዋል። ህገወጥ የምግቦች ዝውውርን በጋራ በመከላከል የህብረተሰባችንን ጤና በመጠበቅ ነገ የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር መደረግ ይኖርበታል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፤ ሕገወጥ ምግቦች ሲያጋጥሙን ወደ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም ወደ አዲስ አበባ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በነፃ የስልክ መስመር 8864 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባ እና ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በአቅራቢያ ወደሚገኙ የጤና ተቆጣጣሪ አካላት በመሄድ ማሳወቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013