አንድ ሀገር በምርጫ አሸነፈች/አሸነፈ የሚባለው ምርጫው ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ያችን/ያንን ሀገር ማሻገር የሚያስችል አቅም ሲፈጥርና በተጨባጭም ማሻገር ሲችል ነው ። ለዚህ ደግሞ መላው ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ አዋላጅ አስተዋጽኦቸው የጎላና የማይተካ ነው።
በተለይም የተሻለ እና አሻጋሪ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምጥ ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን በማዋለድ ሂደት ውስጥ የምርጫ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ለዜጎች ቀኖች ክፉ ፤ሁሉ ነገር የተዘጋጋ መውጪያ የሌለ በሚመስላቸው የፈተና ጊዜያት የምርጫ ጉዳይ አማራጭ የሌለው መሻገሪያ መንገድ ነው ።
በተለይም እንደኛ ባሉ በዘመናት መካከል የመሆን ምጥ ምኞታቸውን በሰላም መገላገል ያልቻሉ ፤ በየዘመኑ ለመውለድ ባማጡ ቁጥር አዋላጅ አጥተው ተስፋቸው የሚጨነፍግባቸው ሕዝቦች ከምንም በላይ ተሻግሮ ለመገኘት ለምርጫ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
በእኛ ሀገርም ቢሆን ከቀደሙት ትውልዶች ጀምሮ ሀገር አሸናፊ የምትሆንበትን ፤ በዚህም ዜጎች እንደዜጋ ሁሉም አሸንፈው የሚወጡበትን ምርጫ ለማካሄድ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ። በየዘመኑ የከፈልነው ዋጋ ፍሬ ሳያፈራ ትውልዶች ሀገር አሸናፊ ባልሆነበችበት አስገዳጅ እውነታ ውስጥ ኖረው ለማለፍ ተገደዋል።
ከእያንዳንዱ ምጥ ጭንገፋ ማግስት የሚፈጠሩ አምባገነን ቡድኖችም አገራቱንና ሕዝቦቻቸውን ተነግሮ የማያልቅ ዋጋ አስከፍለዋል ። እነዚህ ቡድኖች ከተፈጠሩበት የሴራ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከወለደው ክፋትና አመጽ የተነሳም ዛሬ አገሪቱ የህልውና ስጋት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋታል።
እነዚህ ቡድኖች በስልጣን ላይ ለመቆየት የሄዱበት መንገድ በሕዝቦቿ መካከል የነበረውን የመከባበር፣ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ በከፋ መንገድ እንዲሸረሸር አድርጓል ። ቁስል አካኪ የሆኑ ትርክቶችን በመፍጠር በሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠርም አድርገዋል ።
ያለንበት ድህነት ፣ ከዚህ የሚመነጨው ጉስቁልናችን፤ ይህም በብሔራዊ ክብራችን ላይ የፈጠረው ጭጋግ ፣ ጭጋጉ የፈጠረብን አንገት መድፋት፣ አንገት መድፋታችን ለጠላቶቻችን የፈጠረላቸው ጉልበት ከዚሁ እውነታ የምናጭደው መኸር ነው።
ሀገርን አሸናፊ ሊያደርጉ የመጡ የለውጥ ምዕራፎችን ለሀገራዊ ልዕልና እና ለሕዝቦች ተስፋ ብስራት ከማድረግ ይልቅ ባደቡ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ደንታ በሌላቸው ቡድኖች እየተጠለፉ የሕዝባችን መስዋዕትነት አምባገነኖችን አምጦ የመውለድ የመከነ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ቀርቷል።
ስለሆነም መላው ሕዝባችን ከዛም በላይ ሀገራዊ ተስፋን ለማዋለድ አቅምና ትግስት ያጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠያቂ ከሚሆኑበት የሀገር ተሸናፊነት የታሪክ አዙሪት ልንወጣም ይገባል። ሀገር አሸናፊ ባልሆነችበት እውነታ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ከቀደሙት ታሪኮቻችን ለመማር ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል።
ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የቱንም ያህል በተሸነፈ ሀገር ውስጥ የአሸናፊነት መንፈስ ተጎናጽፈው አሸናፊዎች ቢመስሉም የተሸናፊነታቸው እውነታ ከሳቱበት መንገድ ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት እየጎላና እየዋጣቸው መምጣቱ የማይቀር ፍጥረታዊ ክስተት ነው።
የዚህ ክስተት አደገኛነት ደግሞ በተሸነፈ ሀገር ውስጥ የአሸናፊነት ስሜት የሚሰማቸውና በዚህ ስሜት የሳቱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የተሸናፊነታቸውን እውነታ ላለመቀበል የሚሄዱበት መንገድና የመንገዱ ጥግ ሀገርን እንደ ሀገር የከፋ ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑ ነው ። ይህ እውነታ በእኛም ሀገር ባለፉት ስድስት አስርቶች በተጨባጭ የታየና ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለና አሁነኛ በሆነው ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሰፊውን ስፍራ ያያዘ ነው ።
በብዙ የሴራ ትብታብ እውነተኛ የሆነውን የአሸናፊነት መንፈስ መጎናጸፍ አይቻልም ። የሚመነጨውን ሀገራዊ ልዕልና ማምጣትና ለሕዝባችንም የዘመናት የትውልዶች ጥያቄ መልስ መስጠት አይታሰብም። በዚህ መንገድ መፍጠር የሚቻለው በችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች ብቻ ነው ። ለዚህ ደግሞ በቂና ከበቂ በላይ አጉባጭ ችግሮች አሉን ።
አሁን ሁላችንም ወደ ህሊናችን ልንመለስ የሚገባበት ወቅት ነው ። የተጀመረው የለውጥ መንገድ ሀገር የማሻገር አቅም እንዲኖረው በምርጫው ሀገር የምታሸንፍበት መንገድ ላይ ቆመን መራመድ መጀመር ይጠበቅብናል ። ለኛ ለኢትዮጵያውያን የምርጫ ጉዳይ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ከመምረጥ ያለፈ ዋጋና ትርጉም ያለ ው ነው።
ምርጫው በፊታችንና በእጃችን ያለ የመሻገሪያ ተስፋችን ነው፤ ከዘመናት የታሪክ አዙሪት ወጥተን በአዲስ ተስፋና ተስፋው በሚወልደው ብርቱ መነቃቃት ወዳሰብነው ብልጽግና የምንሸጋገርበት ነው ። የአባቶቻችንን የተጋድሎ ታሪክ ሙሉ አድርገን አንገታችንን አቅንተን መጓዝ የምንችልበትን እድል የምናጸናበትም ነው።
ካለንበት ታሪካዊ ምዕራፍ አንጻር ሁላችንም ከመጣንበት ራስ ወዳድነት ወጥተን በምርጫው ሀገር የምታሸንፍበትን እውነታ ልንቀበለው ይገባል። ለዚህ የሚሆን ሀገራዊ ዝግጁነት መፍጠርም ይኖርብናል። በተለይም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ ሀገር አሸናፊ እንድትሆን ስልጡን አዋላጅ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አገር ተሸናፊ በሆነችባቸው የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ አሸናፊ የሆኑ የመሰላቸው ቡድኖች በሳተ የአሸናፊነት መንፈስ ተገርተውና ስተው እራሳቸውና መላውን ሕዝባችንን የቱን ያህል የከፋ ዋጋ እንዳስከፈሉ ለማስተዋል ጊዜው አሁን ነው።
አገር ስታሸንፍ ተሸናፊ አይኖርም ። ተሸናፊ በሌለበት ደግሞ ቁዘማ ፤ ከዚህ የሚመነጭ ሴራ ፣ ከሴራ የሚወለድ ሁከትና ብጥብጥ የሰላም መደፍረስ አይኖርም ። ይህ ደግሞ ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ጉዞ ትልቁ አቅማችን ነው ። ለዚህ ሁሉንም አሸናፊ ለሚያደርግ የሕይወት ጉዞ ሁላችንም ራሳችንን በጠንካራ ዲሲፕሊን እናዘጋጅና በምርጫው ኢትዮጵያ አሸናፊ ትሁን፤ የዘመናት እንቆቅልሻችን መፍቻው ቁልፍ ይሄው ብቻ ነው፤ ቁልፉም አሁን በጃችን ነው!አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013