ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1940ዎቹ ያቀርባቸው ከነበሩ ዘገባዎች መካከል የከተማ ወሬ በሚል የሚያቀርባቸው ይገኙበታል፡፡ ይህም በቂ የሕግ ባለሙያ ስላልነበር ነው። በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችንም በ1945 እና 46 ከታተሙ የዚሁ ጋዜጣ የከተማ ወሬ ዘገባዎች ጥቂቶቹን ይዘን ቀርበናል፡፡
በፍል ውሃ ውስጥ ሞቶ የተገኘ ሰው
ሐምሌ ፲፪ ቀን ከምሽቱ ፫ ሰዓት ስሙና አድራሻው ለጊዜው ያልታወቀ ሰው ፍልውሃ ለመታጠብ ገብቶ ሳለ በዚያው ሞቶ መገኘቱን የ ፮ኛው ፖሊስ ጣቢያ አመልክቷል፡፡
ማንኛውም ይጠቅማል የሚባል ነገር ሁሉ መጠንና አኳኋን ስላለው የሚያስፈልገውን በመጠን ማድረግ እንጂ እንዲያው ይጠቅማል ብሎ ከመጠን አሳልፈው ቢሠሩት፤ አደገኛ ነገር ያመጣል፡፡
እንዲሁም ለጤነኛው የሚስማማው ነገር ለበሽተኞች ስለማይስማማና ለበሽተኞች የሚስማማው ነገር ለደኅነኞች ስለማይስማማ፤ ማንኛውም ሰው ቢሆን ተስማሚውንና ጠቃሚውን ነገር ማመዛዘን አለበት፡፡
ፍል ውሀ ለንጽሕናና ለፅዳት የሚጠቅመውን ያህል ለበሽተኛ ሰዎች ከፍ ያለ ጉዳት የሚያመጣ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
ስለዚህ ጉዳይ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየጊዜው በሚሰጠው ምክር ላይ ጉዳት አምጪነቱን ከመግለጹ በላይ ለደኅነኞችም ቢሆን ያለጥንቃቄ እንዳይደረግ ማሳሰቡ አልቀረም፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ምክሩን ያልሰሙ ወይም ያልተገነዘቡ ሰዎች በየጊዜው በፍል ውሀ የሕይወት ማጣት ከባድ አደጋ ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ ይህም አብዛኛውን ጊዜ በጤነኞች ላይ ሳይሆን በበሽተኞች ላይ መሆኑ በግምት የሚታወቅ ነው፡፡
ለምሳሌ ሕመም ያልደረሰበት ሰው፤ ይልቁንም የልብ በሽታ ያለበት ሰው በፍል ውሀ ውስጥ በሚታጠብበት ጊዜ በአጭር ጊዜ እጥበትን መፈጸም እንጂ እንደ ደኅነኞቹ ብዙ ጊዜ መቆየት አይገባውም፡፡ ይህን ያላደረገ እንደሆነ ግን የውሀው ሙቀትነትና እንፋሎት በዙሪያው ያለ አየር ማነስም ከፍ ያለ ድካም እንደሚያመጣበትና ወደ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያደርሰው ተደጋግሞ የታየ ነገር ስለሆነ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡
ስለዚህ ይህን የመሳሰለ አደጋ እንዳይደርስ ማንኛውም ሰው እንዲያስብበት የሚያስፈልግ ከመሆኑም በላይ ይልቁንም የልብ ድካም ያለባቸው በጣም ቢጠነቀቁበት መልካም ነው፡፡
ሀምሌ 18 ቀን 1945
የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በሐረር ጠቅላይ ግዛት የፈጸሙት የሥራ ፍሬ
የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች
፩ኛ አቶወልደገብርኤል አምባው ዳኛ
፪ኛ አቶ መኩሪያ ዳመና ዳኛ
፫ኛ አቶ በቀለ ወልደኪዳን ዳኛ
፬ኛ አቶ ሣህሉ ወልደ ኪዳን ዐቃቤ ሕግ
የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚጠባበቁትን ነገሮች በፍርድ ለመወሰን ሐምሌ ፳፬ ቀን ፵፭ ዓ.ም በኢትዮጵያና የፈረንሳይ ምድር ባቡር ወደ ሐረር ጠቅላይ ግዛት ሄደው በሐረር ዋና ከተማ ላይ አስችለው በወንጀልና በፍትሐብሔር ከቀረቡት 164 ፋይሎች 136 ነገሮች በፍርድ ሲወሰኑ 28ቱን ነገሮች በቀጠሮ አስተላልፈው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡
ጥቅምት 14 ቀን 1946
የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በሰሜንና በበጌምድር ጠቅላይ ግዛትና በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ላይ ለማስቻል ስለመሄዳቸው
፩ኛ ፊታውራሪ ተፈራ መስፍን ዳኛ
፪ኛ አቶ መንገሻ ወልደአማኑኤል ዳኛ
፫ኛ ፊታ. ደስታ ወልደሚካኤል
፬ኛ አቶ ሺፈራው ከበደ ዐቃቤ ሕግ በሰሜንና በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በጎንደር ፤ እንዲሁም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በደብረ ማርቆስ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚጠባበቁትን ነገሮች አይተው በፍርድ ለመወሰን ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደር ሔደዋል፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታ ግጥሚያ
ቢሾፍቱ ሐረር ሜዳ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአየር ኃይል ትምህር ቤት የስፖርት ክፍል ወጣቶች ባደረጉት ጥሪ መሠረት ጥቅምት ፰ ቀን ፲፱፻፵፮ ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫዋቾች ቢሾፍቱ ተገኝተው ከአየር ኃይል ወጣቶች ጋር የእግር ኳስ ጨዋታ ግጥሚያ አድርገዋል፡፡
በመጀመሪያው ጨዋታ ከ፱ ሰዓት እስከ ፲ ሰዓት ተሩብ የቅዱስ ጊዮርጊስና የአየር ኃይል ሁለተኛ ክፍል ተጨዋቾች ተጋጥመው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛ ክፍል ተጨዋቾች ፩ ለዜሮ አሸንፈዋል፡፡
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስና የአየር ኃይል የ፩ኛ ክፍል ተጨዋቾች ግጥሚያ አድርገው የቅዱስ ጊዮርጊስ የ፩ኛ ክፍል ተጨዋቾች አራት ለአንድ አሸንፈዋል፡፡ የጨዋታው መልክ ሥነ ስርዓት የያዘ ከመሆኑም በላይ በአየር ኃይልና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድኖች መካከል የተደረገው መቀራረብ በጠቅላላው የእስፖርትን መስፋፋትና መሻሻል የሚያስገነዝብ ነበር፡፡
(ጥምቀት 14 ቀን 1946 ከወጣው አዲስ ዘመን )
የካቲት ፮ ቀን ፵፮ ዓ.ም ከቀኑ ፭ ሰዓት ላይ፤ የካቲት ፲፪ አደባባይ አጠገብ ፪ የቀን ሠራተኞች የሚፈርስ የቤት ግድግዳ ሲቆፍሩ ሣለ ድንገት ግድግዳው ፈርሶባቸው በሠራተኞቹ ላይ ጉዳት አድርሶባቸዋል፡፡
ይህም አደጋ እንደተሰማ የ፩ኛ እሳት አደጋ ጣቢያ ሠራተኞች በፍጥነት አደጋው ወደሆነበት ሥፍራ ሔደው ስለነበረ አድራሻውና ስሙ ያልታወቀ አንድ ሠራተኛ ሞቶ ሲገኝ እንዲሁም መሐመድ ሙሳ የተባለ ሰው በጣም ቆስሎ አግኝተውታል፡፡ ከዚህ በኋላ እነዚህን አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ወስደዋቸው ተመልሰዋል፡፡
ስለዚህ ማንኛቸውም ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ ከጥንቃቄ ጋር ሆኖ መሥራት፤ ለሥራው አፈጻጸም መልካም ከመሆኑ በላይ፤ ሕይወትን ይህን ከመሳሰለው አደጋ ለመጠበቅ ያስችላል፡፡
(የካቲት 9 ቀን 19 46 ከወጣው አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013