አዲሱ ገረመው
ነጠላውና ቀሚሱ እንዲመሳሰል የነጠላው ጥለት ላይ እንደ ቀሚሱ ዓይነት መሰል ነገር ይለጠፍበታል። ልክ እንደ ሐበሻ ልብስ በዓላት ሲቃረቡና በሠርግ ወቅት ገበያው ይደራል። በእርግጥ እንደ ባህል አልባሳት በዓላትን ብቻ ጠብቆ አይለበስም። በወቅታዊ የአልባሳት ገበያ የሐበሻ ልብስ ውድና ቶሎ የሚቆሽሽ በመሆኑም ወጣቱ ይህን ልብስ ተመራጭ አድርጉታል። በተለምዶ አጠራር የቻይናው የባህል ቀሚስ “ሽፎን”።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ላይ በተለምዶ የሐበሻ ልብስ ተብሎ የሚጠራውን የሚመስል ሽፎን የሚባል ልብስ በብዛት በተጠቃሚዎች ዘንድ እየተለበሰ ይገኛል። ይህ ጽሁፍ እስከተሰናዳበት ጊዜ ድረስም የዚህ ባህል ልብስ መሳይ (ሽፎን) ከነ ነጠላው እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር እየተሸጠ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ለመሆኑ ሽፎን ለፋሽን ኢንዱስትሪው ምን አበርክቶ አለው?
ኢትዮጵያውያንና ፋሽን
በአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፋሽን ዲዛይን አሰልጣኝ አቶ ሚኪያስ ታደለ ጊዜውን እያማከለ የመጣው የፋሽን ልምድ (ፋድ) በኢትዮጵያዊያን ዘንድ እየተተገበረ ይገኛል በማለት ሽፎንም የዚህ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሁኔታዎችን ጠብቆ የሚመጣው የትኛውም ነገር ፋሽን ነው የሚሉት አቶ ሚኪያስ፤ ፋሽን ጊዜና ሁኔታን እንዲሁም ደግሞ ቦታን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችንም አገናዝቦ እንደሚዘወተር ይናገራሉ። “ፋሽን በአንድ ጊዜ አይመጣም፤ በአንዴም አይጠፋም። እንቅስቃሴዎችን ተክትሎ የሚመጣ ነው። አንድን ፋሽን ፋሽን ነው ብሎ ለመግለጽ የማህበረሰቡ ቅቡልነት ያስፈልገዋል። ማህበረሰቡ እንዲቀበለው ደግሞ ዝግጅትና አውድ ያስፈልገዋል” ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ማህበረሰቡ ፋሽንን ቶሎ የማይቀበልበት ሁኔታዎች ይኖራሉ። የኛ ማህበረሰብ ወጣ ያለ ልብስ አይለብስም። ይህ የሆነበት ምክንያት ከሀይማኖትም ሆነ ከባህል አኳያ ትክክል አይደለም ብሎ ስለሚፈርጅ ነው። እንዲህ አይነት አልባሳትን የመግዛት አቅሙም አንዱ ተጽእኖ ፈጣሪ ጉዳይ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ሁሉም ባይባልም ኢትዮጵያዊያን ከባህል ጋር ተዛማችነት ላላቸው አልባሳት ትኩረት ይሰጣሉ።
አቶ ሚኪያስ እንደሚገልጹት፤ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ የፋሽን ማዘውተሪያ መንገድ አለ። ይህ ሲባል ታዋቂ ሰዎች አሊያም ባለሀብቱ ሲለብሰው ተራው የማህበረሰብ ክፍል ደግሞ ይከተለዋል። በሌላ በኩል ከታች ወደ ላይ የሚወጣ የፋሽን አተገባበርም አለ። ይህም ተራው ሰው ከለበሰው በኋላ ሌሎች ታዋቂ ሰዎች የሚለብሱበት ሂደት ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው አይነት የፋሽን መንገድ በብዛት ይዘወተራል። ለምሳሌ ትልትል ጅንስ ሱሪና ጃኬት በዚህ መንገድ ነው በብዛት የሚለበሱት።
ከሌሎች የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ በየጊዜው ከሚገቡ አዳዲስ ፈሽኖችም በብዛት በእንዲህ አይነት ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ናቸው። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ሽፎን አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት የሐገራችን ሽፎን ቀሚሶች ከማንኛውም ጊዜ እስከ ትላልቅ ፕሮግራሞች የሚለበሱ ሆነዋል።
ሽፎን በኢትዮጵያ
አቶ ሚኪያስ፤ በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት የሌሎች አገራትን አልባሳት ለመልበስ የምንገደድበት አጋጣሚ መኖሩን ይጠቅሳሉ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ከቻይናና ሕንድ ከመሳሰሉ አገራት የሚመጡትን አልባሳት እንደሚያዘወትሩ ይገልጻሉ። እነዚህ አገራት ደግሞ በተለይ ባህላዊ አልባሳት ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሌሎች አገራት አልባሳትን ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ስለማይችል ብቻ አይደለም። ነገር ግን ቢሰራ በዚያ ደረጃ ላይሆን ይችላል። በመጠን ደረጃም ለሁሉም ተደራሽ አይሆንም። በዚህ ምክንያት የግድ የሌሎችን አቅርቦት እንፈልጋለን። ስለዚህ ካለን አቅም አንጻር ተቀባይ ሆነናል። ለዚህም ነው ሽፎን የሚባለው የቻይናው የሐበሻ ቀሚስ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በብዛት የሚለበሰው።
ልብሱ ከኢትዮጵያውያን የአገር ባህል አልባሳት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ከውጭ የሚመጣው ጨርቁ ብቻ ሲሆን፤ ፋሽን ዲዛይን ተደርጎ የሚሰራው ደግሞ አገር ቤት ውስጥ ነው። በዚህም ዘርፉን ማነቃቃት ችሏል። ሽፎን በአዳዲስ ፋሽን ለገበያው ሲቀርብ አንቀላፍቶ የነበረው የባህል አልባሳት ዲዛይንም በአዲስ መልክ ተነቃቅቷል።
“የባህል አልባሳት ሁልጊዜ በበዓላትና የሠርግ ሰሞን የሚለበሱ ሲሆን፤ ሽፎን ግን በማንኛውም ፕሮግራም ወቅት እንዲለበስ ተደርጎ ነው የሚሰራው። ለዚህ ነው ፋሽን ሆኖ የባህል አልባሳት ገበያውን እያነቃቃ የሚገኘው። ምንም እንኳን የሽፎን ጨርቅ እኛ አገር ባይመረትም ፋሽንነቱ የሚሰራው የኛን ባህላዊ አለባባስ አካታች አድርጎ ነው” ሲሉ አቶ ሚኪያስ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የባህል ልብስ ፈልጎ ወደ ገበያው የሄደ ሰው ከሚያገኛቸው አልባሳት ዝርዝር ውስጥ አንዱ ሽፎን እንደሆነ አቶ ሚኪያስ ይጠቅሳሉ። ደንበኛን መሳብ የሚችሉ ውብ እሴቶች ተጨምረውበት ዲዛይን እንደሚደረጉም ያመላክታሉ። በዋጋ ደረጃም ቢሆን ከአገር ባህል አልባሳት አንጻር ቅናሽ ስለሆነ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያማከለ ነው ይላሉ። የሽፎን አልባሳት ለየትኛውም ፕሮግራም የሚለበሱ መሆናቸውም ተመራጭ መሆኑንና ውስን የሆነ አውድን ብቻ የሚጠይቅ አለመሆኑ በብዙኃን ዘንድ እንዲዘወተር መቻሉን ይናገራሉ።
ፋሽኑ መነቃቃትን እንዳሳየው ሁሉ የባህል አልባሳት ገበያውን በመጋራት ነባር አልባሳት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም አቶ ሚኪያስ ይገልጻሉ። የባህላዊ ጨርቅ ፍላጎትንም ሊቀንስ እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁንና የአገር ባህል አልባሳት ተጠቃሚ እንዳይቀንስ በተለይ የባህል አልባሳት ፋሽን ዲዛይነሮች ተጨማሪ እሴት ተጠቅመው ሌሎችንም እኩል ተወዳዳሪ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራሉ። የፋሽን ዲዛይነሮች የሽፎንን የፋሽን ገባያ ተወዳዳሪነት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባልም ይላሉ።
ምንም እንኳን ሽፎን ገበያ ላይ በዋለበት ወቅት በንግድ ሽያጩ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ የሽፎን ተጠቃሚን እንዲበዛ ያደረገው ግን የባህል ልብስ ያለው የዋጋ መጋነን ነው። ይህ ደግሞ የባህል አልባሳት ያላቸውን የዋጋ ውድነትም ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ነው አቶ ሚኪያስ የሚገልጹት።
ሽፎን እየተለመደ ሲመጣ በገበያው ላይ ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለመፍጠሩንና እንዲያውም ዲዛይን ተደርጎ የሚሠራው ውድ ለሆነባቸው ተጠቃሚዎች መልካም አጋጣሚ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህም ባለፈ የአገር ልብስ መልበስ እየፈለጉ ላልቻሉ ጥሩ መፍትሔ እንደሆነም አቶ ሚኪያስ አክለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013